የምሕረት በር ተከፍቷል
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Friday, 18 December 2015 19:31
- Written by Super User
- Hits: 3314
- 18 Dec
የምሕረት በር ተከፍቷል
በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ታላቁን በር የመክፈት ልምድ አለ፡፡ ይህ ታላቁ የካቴድራሉ በር የተቀደሰ የምሕረት በር ነው፡፡ በዚህ በር የመከፈት ምሳሌነት ትልቁ የእግዚአብሔርን ምሕረት እናስታውሳለን፡፡ በተከፈተው በር ውስጥ አልፈው ወደ ካቴድራሉ መቅደስ የሚገቡ ሁሉ ከቀድሞው የኃጢአት ማንነታቸው ወደ ጸጋ ይገባሉ፤ በሩ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የሚያሻግረው የእግዚአብሄር ምሕረት ምሳሌ ነው፡፡
በሩ ትክክለኛ ትርጉሙን የሚያገኘው ምዕመናን በሩን ከክርስቶስ ማንነት ጋር አዋህደው ሲገነዘቡ ነው፡፡ በሩ ኢየሱስ ነው! ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ እንደሚያስተምሩን ከእግዚአብሔር ጋር በሕይወት ወደ መኖር የሚያደርሰን በሰፊው የተከፈተ አንድ እውነተኛ በር አለ፤ እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ አንዱ እና ፍጹም የሆነው የመዳን መንገድ ነው፡፡ የመዝሙረኛው ቃላት በፍጹም ትክክለኛነት የሚገልጡት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ኢየሱስ ክርሰቶስ ጻድቃን የሚገቡበት የእግዚአብሔር በር ነው (መዝ 118፡20)፡፡
ጌታችን ስለራሱ ሲናገር “በሩ እኔ ነኝ” (ዮሐ 10፡7) ይላል ፡፡ ስለዚህ በዚህ በር በኩል ካልሆነ በስተቀር ማንም ወደ አብ የሚደርስ የለም፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ለማዳን የተላከ የእግዚአብሔር የፍጸሜ ቃል እርሱ ነው፡፡ በሰፊው የሚከፈተው በር በመስቀል ላይ ሳለ በአይሁድ ጦር የተከፈተው የቅዱስ ልቡ ምሳሌ ነው፡፡
በዚህ ዓመት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሱን በር የከፈቱት በጽንሰተ ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ህዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ ዕለት የተከፈተው በር ለሁሉም የሰው ልጆች የተሰጠ የጸጋ ስጦታ ነው፤ በበሩ በኩል ወደ ውስጥ የሚዘልቅ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍቅር ይቀምሳል ፣ ፍቅሩ የሚያጽናና፣ ምሕረት የሚያደርግ፣ በተስፋ የሚሞላ ፍቅር ነው፡፡ በዓለም ዙርያ የሁሉም ካቴድራሎች ምሕረት በሮች በዚህ በምሕረት ዓመት ይከፈታሉ፡፡
እኛም ሁላችን በተከፈተው በር እንግባ ፤ ከኃጢአት ወደ ጸጋ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ የኋላውን ትተን የፊቱን ክብር ለመውረስ እንጓዝ፡፡ በዚህ በር በኩል ሰፊውን የእግዚአብሔር ምሕረት እንካፈል፤ በዚህ በር በኩል ስንገባ እኛ ከእግዚአብሔር ምሕረት የምንለምን ሁሉ የእኛን ምሕረት ፈልገው ይቅርታ እንድናደርግላቸው ለሚጠይቁን ሁሉ እና በድለውን ይቅርታ መጠየቅ ለከበዳቸው ሁሉ ምሕረት እናድርግ ፡፡ እግዚአብሔር አባታችን እያንዳዳችንን ይቅር እንደሚለን እናምናለን፤ ነገር ግን ይህ የበለጠ ፍጹም የሚሆነው እኛም ደግሞ ለበደሉን ሁሉ ምንም ነገር ሳንጠብቅ ከልብ ምሕረት ስናደርግ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ህይወት ምሕረትን የማወጅ፣ ምሕረትን የመቀበል እና የመስጠት ህይወት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጥሪ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት በህዝቡ መካከል መግለጥ እና መኖር ነው፡፡
ምሕረት ቤተክርስቲያን የሕልውና መሰረት ነው፡፡ ሐዋርያዊ ሥራዎቿ በሙሉ የክርስቶስን ርህራሄ የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው፡፡ ምሕረት ያልተሞላበት አገልግሎት የትኛውንም ያህል ስኬታማ ቢሆን ክርስቲያናዊ አልግሎት ነው ሊባል አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምሕረትን ለሰው ልጆች ለመግለጥ ማለቂያ የሌለው ጥማት አላት ፡፡ ለሕይወታችን ፍትህ እንዲኖር የምንታገለውን ያህል ምሕረት እንዲኖር መታገል አለብን፡፡
ምሕረት የሌለበት ሕይወት ፍሬ አልባ እና ተስፋ ቢስ ሕይወት ነው፡፡ ዓለም እርስ በእርሱ ለበቀል በተነሳበት እና የምሕረት ለዛ በጠፋበት በዚህ ወቅት እናት ቤተክርስቲያን ልጆቿን ሁሉ ትጠራለች፤ ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ሁሉ የይቅርታ እና የምሕህረት ጥሪዋን የምታሰማበት የተወደደው ሰዓት ደርሷል፡፡ አሁን ምሕረት የሚሰበክበት የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችንን ደካማ ጎኖች ከክርስቶስ መስቀል ጋር አስተባብረን የምንሸከምበት ጊዜ ነው፡፡ ምሕረት የአዲስ የሕይወት መንገድ ጀማሮ ነው፤ የወደፊቱን በታመነ ተስፋ የምንጠባበቅበት ኃይል ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ምሕረት አምባሳደር ነች፡፡ የወንጌልን የልብ ትርታ በሰው ልጆች ልብ እና አዕምሮ ውስጥ ማሰማት ጥሪዋ ነው፡፡ የክርስቶስ ሙሽራ እንደመሆኗ መጠን ሙሽራውን ተከትላ ያለልዩነት ሁሉንም የሰው ልጆች ለመቀበል መውጣት አለባት፡፡ ቤተክርስቲያን አዲሱን ስብከተ ወንጌል በጀመረችበት በዚህ ወቅት የእግዚአብሔር ምሕረት በቃል እና በተግባር ያለማቋረጥ መስበክ አለበት፡፡ መልእክቷ የታመነ ይሆን ዘንድ አስቀድማ እርሷ እራሷ ምሕረትን በተግባር በመኖር ቀዳሚ ምስክር መሆን አለባት ፡፡ ቋንቋዋ እና ድርጊቷ ሁሉ የእግዚአብሔር ምሕረት ነጸብራቅ መሆን አለበት በዚህ ዓይነት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዕቅፍ የሚመለሱበት መንገድ ያገኛሉ፡፡ የቤተክርስቲያን የመጀመሪያ እውነት የክርስቶስ ፍቅር ሕያውነት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የዚህ ፍቅር ባለ ዐደራ አገልጋይ ነች፡፡ ይህ ፍቅር ምሕረት የሚያደርግ እና ራሱን ለሌሎች አሳልፎ የሚሰጥ ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስያን ባለችበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔር አብ ምሕረት በተግባር መገለጥ አለበት፡፡ በቁምስናዎቻችን፣ በተቋሞቻችን፣ በየማህበሮቻችን እና እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ ሁሉ፣ ወይም በአንድ ሐሳብ ለመጠቅለል፣ ክርስቲያኖች ባሉበት ሥፍራ ሁሉ የምሕረት መዓዛ መኖር አለበት፡፡
ር.ሊ.ጳ ፍራንቺስኮስ
ትርጉም በወጣት ሳምሶን ደቦጭ ቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ.