በእቅድ የተፈጠርን ነን!

በእቅድ የተፈጠርን ነን!
Christmas 2015የጌታችን ክርስቶስ ልደት ባጠቃላይ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ዳግም የፈጠረበት ልዩ እውነታ ነው ማለት እንችላለን። እርሱ በወሰነው ጊዜ ክርስቶስ ሕፃን ሆኖ ሰው በመሆን ሊያድነን ተወለደ። ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ክሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ።” /ገላ ፬፡፬/ ይለናል።እግዚአብሔር ልጁን በወሰነው ጊዜ እንደላከ ሁሉ የሁላችንም መወለድ እንዲሁ በእርሱ ድንቅ እቅድ የተከናወነ ነው። የጌታችን ልደት የእያንዳንዳችንን መወለድ ትርጉም ይሰጠዋል፡ በርግጠኝነት እኛም የተወለድነው በእርሱ ውሳኔ መሆኑን ማሰብ ጥሩ ነው። ማንም ያለዓላማ የተወለደ የለም፡ በርግጥ አንዳንድ ወላጆች እንደዚያ ብለው ያስቡ ይሆናል፡ ያለነርሱ እቅድ ልጅ የመጣ ይመስላቸዋል፤ የአምላክንም እቅድ ሳያውቁ የጽንሱን መወለድ ሊያደናቅፉ ይፈተኑ ይሆናል ሆኖም ግን የሁላችን መጸነስና መወለድ እግዚአብሔር በወሰነው ሰዓት ሆኗል። ስለዚህ ይህ ነጥብ የተወለድንበትን እቅድ እንድናስብ ይጋብዘናል። ትርጉም የሌለው ኑሮ ውስጥ ያለን ሲመስልን የጌታ ልደት ሕይወታችን ትርጉም እንዳለው ጮክ ብሎ ይናገረናል፡ እርሱ በወሰነው ጊዜ ተወልደናል። ለክብር፣ ለመፈቀርና ለማፍቀር፣ ለምሕረት ተፈጥረናል።
የጌታችን ሰው የመሆን ምስጢር የእያንዳንዳችንን ሕይወት ክቡርነት ያንጸባርቃል። በመወለዱ ሕይወት በየትኛውም ደረጃ ማለትም በጽንስ፣ በሕፃንነት፣ በወጣትነት እንዲሁም በአረጋዊነትም ክቡር ነው ይለናል። ሰው መሆን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ መከበር እንዳለበትም ያስተምረናል፤ ዛሬ ዛሬ በተለያዩ ምክንያቶች የሰው ልጅ ሕይወት ባለቤትነት በገዛ እጃችን የጨበጥን እስኪመስለን ድረስ ከውርጃ ጀምሮ ፍትሕን እስከማዛባት በመተግበር ሰው በሕይወት የመኖሩን ነገር ማጨናገፍ እየሰፈነ መጥቷል፤ የክርስቶስ ልደት ይህን ይቃወማል። የርሱ መልእክት ሕይወት ክቡር ናት፤ ፍቅር፣ ምሕረት፣ ይቅርታ እንጂ በነዚህ ተቃራኒ ነገሮች ልታንስ ወይም ልትጠፋ እንደማይገባ ያስተምረናል።
እንደ ክርስቲያኖች የመኖራችን ዓላማ ጌታ በልደቱ ያመጣልንን ሰማያዊ ፍቅር መኖርና ማካፈል ነው። የማያምኑ ብለን ከምናስባቸው ሰዎች መለያ የሚሆነን ሳናደራድር ወይም ቅድመ ሁኔታዎችን ሳንጠይቅ ማፍቀርና ይቅር መባባል ስንችል ነው፡ የሚወዱንን ብቻ መውደድ፣ ይቅር ሊሉ የሚችሉንን ብቻ ይቅር ማለት ክርስቲያናዊ ሊሆን እንደማይችል የክርስቶስ ልደት ያሳየናል። እርሱ ለሁላችንም ተወለደ፣ ሊጎበኘውና ሊያገኘው ለፈለገ ሁሉ ትሑት ሆነ፣ በበረት ተኛ። የደረደርናቸው ያለማፍቀር፣ ከማንፈልገው ሰው ጋር ያለመታረቅ፣ ይቅር ያለማለት ሰበቦች ካሉ የቤተልሔሙን በረት ሕፃን ክርስቶስ እናስተውል። የመኖራችን እቅድ ይህን ምሕረትና ፍቅር መቅመስና ማጣጣም ሌሎችንም ለዚሁ መጋበዝ እስከሆነ ድረስ ከዚህ በሚያርቁን ነገሮች ተከበን በመኖር ጊዜ ማሳለፍ የለብንም።
በሁላዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንድሮ የምሕረት ዓመት ተብሎ መሠየሙን ሰምተን ይሆናል፤ ይህ የመላ እድሜያችን ዓላማ የሆነ የአምላካችንን ምሕረት የመቀበልና የማቀበል ኃላፊነታችንን በተለየ መልኩ እንድንኖር የሚያግዘን ልዩ የጸጋ ጥሪ ነው። ለሌላ ጊዜ ልናራዝመው የማይገባን ግብዣም ነው። ይህን ምሕረትና ፍቅር ለመኖር ቀጠሮ መስጠት የለብንም፣ ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለን የመዳን ቀን አሁን ነው፡ አዎን የክርስቲያናዊ ፍቅር፣ የይቅርታ፣ የምሕረት፣ የንስሐ ሰዓት አሁን ነው! ቂም፣ ጥላቻ፣ በውስጣችን የሚሻክረንና የሚቆረቁረን የክርስትናችን ተቃራኒ የአኗኗር ዘይቤም ካለም ማክተሚያው አሁን መሆን አለበት፤ ክርስቶስ የተወለደው ይህን ሁሉ ለማስተካከል ነውና ልደቱን በሕይወታችን እንቀበለው።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።