ስትጾሙ ራሳችሁን ቅባት ተቀቡ፡ ፊታችሁን ታጠቡ!

ስትጾሙ ራሳችሁን ቅባት ተቀቡ፡ ፊታችሁን ታጠቡ!

fasting face

ማቴ 6:16-18..... “ስትጦሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፡ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።”

ከሰውነት አካሎቻች ውስጥ ፊት ማለት ለሰው ልጅ ብዙ ነገር ነው፡ ፊት ሁሉም የስሜት ህዋሳት የሚገኙበት ክፍል ስለሆነም ከሌሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ሂደት ውስጥ ብዙ መልእክት ማስተላለፊያ ነው። በዘልማድ ንግግራችን ውስጥ እንኳ “ፊት ነሣ’’፡ “ፊቱን አጠቆረ”፡ “ፊቱን ጣለ፡ ዘረገፈ... ስንል በክፉ ዓይን አየ፡ ምንም ቦታ አልሰጠም፡ ተቆጣ፡ አኮረፈና መሰል መልእክት ሲኖረው በአንጻሩ ደግሞ “ፊት ሰጠ” ስንል አቀረበ፡ ጥሩ ሁኔታን አሳየ ማለትን ያሰማል። ከሌላ ሌላም ብዙ አነጋገሮቻችን የፊትን መልእክት ማስተላለፊያነትና የሰውን ውስጣዊ ነገር ማንፀባረቂያነት መረዳት እንችላለን።

እንደው ከቋንቋ አንጻር በጥቂቱ ለማለት ሞከርን እንጂ በራሳችን የፊት አጠቃቀም ምን ያህል መልእክት ለማስተላለፍ እንደምንጠቀምበት ከየግል ልምዳችን እናውቀዋለን። ፊት ለሌሎች መልእክት ማስተላለፊያነቱ ብቻ ሳይሆን ለማንነታችንም የሚያረጋግጥልን ነገር አለው። ዘወትር ፊታችንን በመስትዋት በተመለከትን ቁጥር ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችን የምናይ ይመስለናል ሆኖም ግን የራሳችን ፊት መሆኑንም ሥራችን ብለን ባይሆንም እናያለን፡ ከዚያም ስለፊታችን የሚገባውን ጥንቃቄ እናደርጋለን። ምናልባት አንድ ቀን እንደተለመደው ጥቃቅን ነገሮችን ለማስተካከል ብለን መስትዋት ፊት ስንቆም ፊታችን የማናውቀው ፊት ሆኖ ብናገኘው እንዴት እንደነግጥ ይሆን? ስለዚህም ነው ፊታችን ለራሳችንም ወሳኝ የማንነት መልእክት አለው ለማለት የምንደፍረው።

በዕለታዊው ውሏችን ፈገግታ ለሚያስፈልገው ፈገግታ፡ መኮሳተር ለፈለግንበት ተኮሳትረን፡ ጥርጣሬን፡ ንቀትን፡ ፍቅርን፡ አክብሮትን...ወዘተ በፊታችን ስናድል ውለን ያንኑ ፊት ይዘን ይመሻል፡ ነግቶ ዳግም ፊታችንን አስተካክለን ይዘን እስክንወጣ ሌሊቱን እንተኛለን። በዚህ ግንዛቤ እይታ ከተመለከትነው ክርስቶስ ፊታችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን መናገሩ አይገርመንም። እርሱ በፊታችን ለሌሎች የምናስተላልፈው መልእክት ጥሩ ይዘት እንዲኖረው በማለት በተለይም በጾም ወቅት እንዴት ሊሆን እንደሚገባው ነገረን “ተቀቡ! ታጠቡ!”።

ፈሪሳውያን በጾም ወቅት በግንባራቸው፡ ጉንጮቻቸው፡ አፍንጫቸውና አገጫቸው ላይ አመድ በመነስነስ ማንም ፊታቸውን አይቶ እገሌ ብሎ መለየት እስኪያዳግተው ድረስ ይለወጡ ነበር። ይህንንም በማድረግ ራሳቸውን የደበቁ ቢመስላቸውም ቅሉ የበለጠ ራሳቸውን በሰው ዓይን እንዲገቡ በማድረግ በጾም ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩበት መንገድ ሆኖ ነበር። በዚህም ሁኔታ ከሰው ዘንድ ስለጿሚነታቸው ሙገሳን ይሸምቱ ነበር። ይህ ሁኔታ የጾምን መሠረታዊ ሃሳብ ስለሚቃወም ክርስቶስ በብርቱ አጽንዖት “እውነት እላችኋለሁ እነርሱ እንዲህ በማድረጋቸው ከሰው ዋጋቸውን ተቀብለዋል እላችኋለሁ” ይለናል /ማቴ 6፡16/።

ክርስቶስ በጾም ወቅት ብሎ የሚያጎላልን እውነተኛ ፊትን የመንከባከብ ሌላኛው መልእክትስ ምን ይሆን ብለን ማሰብ እንችላለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ማንነታችንም ሆነ ገጽታችን ክርስቶሳዊ መሆን አለበት፡ ሕይወታችን የርሱ የሆነውን የፍቅር፡ የትሕትና፡ የትዕግሥት፡ የይቅርታ፡ የመስዋእትነት... መልእክት ማስተላለፍ አለበት። እግዚአብሔር አብ የልጁን መልክ በእኛ አትሞታል። ይህ መልክ ይበላሽና ይሸፈን ዘንድ የእርሱ ፈቃድ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስም ይህ የክርስቶስ መልክ በውስጣችን በምልአት ይቀረጽ ዘንድ ያሳስበናል።ከማሳሰብም በላይ ምን ያህል በጭንቅ የሚመኝልን ነገር መሆኑን መረዳት እንችላለን “ልጆች ሆይ! ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል።” ገላ 4:19።

ምናልባት ሕይወታችን የኢክርስቲያናዊ መልእክት ማለትም የጥላቻ፡ የትእቢት፡ የቁጣ፡ የቂም፡ የቅናት...ማስተላለፊያ ከሆነ ክርስቶሳዊ ማለትም እውነተኛ ገጽታችን/ፊታችን በአመድና በጥላሸት ተሸፍኖ ክርስቶስን አይንጸባርቅም እናም እውነተኛው ክርስቲያናዊ ፊታችን ያንጸባርቅ ዘንድ ፊታችንን መታጠብ ግድ ይለናል። የእግዚአብሔር ቃልን ከልብ ሰምተን እሺ ማለትን እንድንችል፡ ጊዜያዊ የሆነውን ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለማስገዛት ዝግጁዎች እንድንሆን እምነታችንን በቅድሳት ምሥጢራት መመገብ ይኖርብናል።

በዚህ መንፈስ ሆነን የጾም ወቅትን ለመኖር ከተጋን ለቀጣዩ የክርስትና ሕይወታችን የሚጠቅሙንን ራስን የመቆጣጠርና ራስን የመግዛት ልማድ ለክርስቶስ የተመቸን እንድንሆን ያደርጉናል። እንዳሻን በመሆን ክርስቶስን ማስደሰት የማይቻል ነገር ነውና ከሥጋዊ ነገሮች ጋር የምናደርገው ቁጥባዊነት ስለ ክርስቶስ ብለን ሲሆኑ ትልቅ ትርፍ ይኖራቸዋል፡ ስለዚህም በጾም ወቅት የምናደርጋቸው የጾም ልማዳዊ አካሄዳችንን በመሣሪያነት በመጠቀም ለክርስቶስ ፈቃድ መታዘዝን እንለማመድባቸው፡ በርግጥም ክርስቲያናዊ ገጽታችን ንፁሕና ወዛም የሚሆነው የርሱን ባህርያት መኖርን ስንችል ነውና በፍቅሩ፡ በትሕትናውና በይቅርታው ፊታችን ለሌሎች እንዲያንጸባርቅ እንትጋ!

የተባረከ ዐቢይ ጾም ያድርግልን!