እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ለክርስቶስ ልደት ዝግጅት የሚያግዙ ነጥቦች

three wise men

ለክርስቶስ ልደት ዝግጅት የሚያግዙ ነጥቦች

ለጌታችን ልደት የሚሰጥ የዝግጅት ጊዜ ምን ዓይነት ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ስናስብ ከቀን ቆጣሪ በላይ የሆነ ማንነታችንን ይፈልጋል። የገና ዝግጅት ጊዜ ማለት ሕይወት ለምትሰጠን ስጦታዎች፤ ለተስፋ፤ ለደስታ፤ ለሰላም… ክፍት መሆንና መዘጋጀት ማለት ነው። ጌታ በእውነት ይወለድ ዘንድ መፈለግ ማለት ነገሮችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ራስንም ለጌታ ፈቃድ ማዘጋጀት ነው።

የገና ዝግጅት ጌታን መቀበል እንችል ዘንድ ቦታና ጊዜን ለሰጠን ለርሱ መልሰን መሰጠት ማለት ነው፤ ስለዚህም ከራሳችን ድንበር ወጣ ብለን እርሱን ማስተናገድ ይጠበቅብናል። ይህን ሕፃን ሆኖ የመጣ ኃያል አምላክ በሕይወታችን ትርጉም ይኖረው ዘንድ ከሦስት አቅጣጫዎች መመልከቱ አጋዥ ነው።

ታላቁ ቅዱስ በርናርዶስ /ሲታዊ/ ስለክርስቶስ ሦስት አመጣጦች ይናገረናል። “በመጀመሪያው መምጣት አምላክ በምድር ላይ ታየ፤ ከሰዎችም ጋር ኖረ፤ አመጣጡም በሥጋና በደካማነት ነበር። በመጨረሻው መምጣት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያዩታል፤ አመጣጡም በክብርና በማዕረግ ይሆናል። በመካከል ያለው መምጣቱ ተደብቋል፡ የተመረጡት ብቻ በውስጣቸው ያዩታል፤ ነፍሳቸው ትድናለች፤ አመጣጡም በመንፈስና በኃይል ነው” ይለናል። ስለዚህ በነዚህ ፫ አመጣጡ ላይ ተመርኩዘን እናስተንትን።

መጀመሪያ መምጣቱ፡- ክርስቶስ ሕፃን ሆኖ ተወልዶ ሥጋችንን በመልበስ መጣ።

ይህ የመጀመሪያው መምጣቱ አሁን የምንጠባበቀው የክርስቶስ መምጣት አይደለም። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተከናውኗል፤ ይህን መምጣቱን የምናስታውሰው እርሱ ሥጋ በመልበሱ ያመጣውን እርሱ ከእኛ ጋር የመሆኑን ሕይወት እንዴት እየኖርነው መሆኑን እንድናስተውል ይጋብዘናል።

ክርስቶስ ተወለደ ስንል በሌላ አባባል እርሱ ከእኛ ጋር ነው ማለትን ያስተጋባል፡ ይህም እውነት ከተዘነጋ ሕይወታችን በሌሎች ነገሮች ትከበባለች፤ ትታወካለች፤ ለእኛ የተሻለ የሆነውን ትተን በከንቱ ነገሮች ኃይላችንና ጊዜያችን ሊባክን ይችላል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር /አምኑኤል/ ነው ስንል እርሱ ለኛ ያደረገልን ውለታ ከመጠን በላይ መሆኑንና የሰጠን ሌላ ምንም ሳይሆን ራሱን መሆኑ በነገሮች ሁሉ አመስጋኝ እንድንሆን ያስችለናል።

ምናልባት የምስጋና ሕይወት ከሌለን እግዚአብሔር አማኑኤል መሆኑን /ከኛ ጋር መሆኑን/ ዘንግተን እንዳይሆን የገና ዝግጅታችን አንደኛው መልእክት ራሱን ለሰጠን ጌታ ከማጉረምረምና የማማረር ኑሮ ማዶ የምስጋና ሕይወትን ለመኖር መወሰን ነው።

መካከለኛ መምጣቱ፤ ኢየሱስ በየቀኑ ወደ እኛ መምጣቱ።

ስለዚህኛው አመጣጥ ስናስብ አንደኛው መንገድ እግዚአብሔር በቃሉ የሚጎበኘን እውነታ ነው፤ ክርስቶስ እንዲህ ይላል “የሚወድደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ እኛ ወደ እርሱ መጥተን ከእርሱ ጋር እንኖራለን።” ዮሐ. ፲፬፤፳፫። ይህም ስለምንሰማው የእግዚአብሔር ቃልና ታዛዥነታችንን እንድናስተውል ያግዘናል። የምንወደውን ሰው ቃል እንሰማለን፤ ሰምተንም እንተገብራለን። ፍቅር ካለን ከቃልም በላይ የዚያን ሰው ፍላጎት እናደርጋለን። በየቀኑ እግዚአብሔር በቃሉ ፈቃዱን ይገልጽልናል ምናልባትም እያወቅን የራሳችንን ፈቃድ እናደርግ ይሆናል፡ በዚህም መልኩ ክርስቶስን በእለታዊ ሕይወታችን ላናስተናግደው እንችላለን። የእርሱን ቃል ማስተናገድ ባቆምን ሰዓት ሌሎች መልእክቶችን ማስተናገድ ላይ ነን ማለት ነው።

ለሰው ወሬና ለመገናኛ ብዙኀን ስርጭቶች የበለጠ ጊዜና ራሳችንን በሰጠን መጠን በውስጣችን የእግዚአብሔር ቃል ቦታ ያጣል እናም ከኛ እንዲሰደድ ምክንያት እንሆናለን፤ ክርስቶስ ከአባቱ ጋር በውስጣችን ለመኖር እየፈለገ ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ ባለማመቻቸታችን ምክንያት እሱንም አባቱንም በሕይወታችን ውስጥ እንዳይስተናገዱ እናደርጋለን። የምንወደውና የሚወድን ሰው ከሕይወታችን ሲጠፋ ምን ያህል ከባድ መሆኑን እናውቃለን፤ ይልቁን ደግሞ አብና ወልድ የማጣቱ እውነታ ከባድ ነውና ለእግዚአብሔር ቃል የምንሰጠውን ጊዜና ክብር እንዲሁም መታዘዛችንን እንመርምር።

ሌላኛው የእለታዊ የክርስቶስ መምጣት መገለጫ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን የምንቀበልበት ሁኔታ ነው። እርሱ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ” ይለናል /ማቴ. ፲፰፡፳/። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕይወት ጎዳና የሚሰጠን ሰዎች ክርስቶስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያስችሉን ስጦታዎች እንጂ አስቸጋሪዎቻችን አይደሉም ማለት ነው። እኛ የመረጥናቸውና ለኛ የሚመቹንን ብቻ ሳይሆን እርሱ ለኛ የመረጠልንና እናገኛቸው ዘንድ ያደረጋቸው ሰዎች ሁሉ እርሱ ለማግኘት የተላኩልን መሆናቸውን ማሰብ ይኖርብናል።

ክርስቶስ በየእለቱ ወላጅ፤ ዘመድ፤ ጓደኛ፤ ጎረቤት፤ የሥራ ባልደረባ፤ የኔ ቢጤ ወይም ድንገት ለአንድ ጊዜ ብቻ በሆነ ምክንያት የተገናኘውን ሰው ሆኖ ይመጣልና በእውነት፤ በጥሩነትና በበጎነት እናስተናግደው። ማቴ. ፳፬፤፴፩-፵፮ ላይም ጌታ በየጊዜው በታሰሩት፤ በታመሙት፤ በታረዙት፤ በእንግዶች፤ በተራቡትና በተጠሙትም እንደሚገናኘን ይነግረናል። ስለዚህ ለእኔና የእኔ የሆኑት ብለን ለምናስባቸው ብቻ ሳይሆን የእርሱ ፍጡር ለሆኑት ሰዎች ሁሉ የምናደርገው መልካምነትም ክርስቶስን በአካል የማስተናገጃ ዘዴ መሆኑን ዘንግተን ከሆነ የገና ጊዜ የመስተካከያ ጊዜያችን ነው።

የመጨረሻው መምጣቱ፤ በዓለም ፍጻሜ ጊዜ የሚሆነው የክርስቶስ መምጣት።

የሰው ልጅ ወደ አንድ አቅጣጫ ለዘመናት ያደረገው ጉዞ የሚደመደምበት፤ የሁልጊዜ ጥማቱና መሻቱ መልስ የሚያገኝበት እንዲሁም ሕይወቱ ሙሉ ትርጉሟን የምታገኝበት እምቅ የተስፋ ምክንያታችን የሚዘጋበት የክርስቶስ በክብርና አጀብ መገለጥ የሚከናወንበት የመጨረሻው መምጣቱ ነው።

በቀደሙት ሁለቱ መምጣቱ ላይ ያለን ግንዛቤና አናኗር ለዚህኛው የመጨረሻ መምጣቱ ያዘጋጁናል። ክርስቶስ በሥጋ ለመወለዱና በየቀኑ ለሚጎበኘን ተገቢ ምላሽን በሰጠን መጠን የመጨረሻው መምጣቱ ለእኛም የክብር ይሆንልናል። የነጻነትን፤ የፍቅርን የደስታን ሙሉነት በማንነታችን የምንቃትትበትና ምክንያትና ይህች የምንኖርባት ዓለም የመሸጋገሪያ መሆኗን ተረድተን ለወዲያኛው ዘላቂና ያልተሸራረፈ ትስስር በዓላማ መኖርን የሚያስችለን የመጨረሻው የክርስቶስ ምጽአት ነው።

አሁን ጊዜያችን፤ መኖሪያችን፤ የእኛ የምንለው ሁሉ ባለቤቱ ክርስቶስ እንደሆነና እኛም ባለአደራ ጠባቂዎች እንጂ ባለቤቶች ያለመሆናችንን እና ስስት ወይም ንፉግነት ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ በመረዳት ያለንን ነገር በፍቅርና በመተሳሰብ ተካፍለን መኖራችንን መመርመር ያስፈልጋል።

የክርስቶስ የመጨረሻ መምጣት የዛሬ ሕይወታችንን በዓላማና በትርጉም እንድንመራ ያግዘናል፡ መኖራችን ትልቅ ትርጉም ያለውና ጊዜያችንና አቅማችን በጊዜያዊ ነገር ላይ ሆኖ የተፈጠርንበት ዓላማ ደብዝዞ የተሰላቸና አቅጣጫ የሌለው ሕይወት እንዳይጠናወተን ያደርገናል። አሳቢ ወይም አማኝ ብቻ ሳንሆን አድራጊ ለመሆን የተጠራን መሆናችንን ያስታውሰናል።

ሰው በመሆናችን እውነተኛ ርካታ መጨረሻ ላይ ከሚጠብቀን ነገር ጋር የተስማማ እንጂ ለአሁንና ለቶሎ የሚባሉት ርካታ ዓይነቶች ግባችን እንዳልሆኑም እንድናስተውል የመጨረሻ ምጽአቱ ይቀሰቅሰናል።

ለነዚህ ለተመለከትናቸው የክርስቶስ ምጽአቶች መሠረት የሆነውን የኢየሱስ ሕፃን ሆኖ እንደ እኛ ሥጋ ለብሶ መወለድ ለማክበር በምንዘጋጅበት በዚህ ወቅት እርሱ የሰጠንን ፍቅርና ክብር ዘንግተን ሕይወታችንን በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳናስገባ እግዚአብሔር ዳግም እየጋበዘን ነው። ይህንን አባታዊ ጥሪውን ተቀብለን በቃሉና በምሥጢራቱ በደስታና በምስጋና ለመኖር ያብቃን። አሜን።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት