ራሳቸውን ስለሚያሰማሩ እረኞች ቅ. አውጎስጢኖስ ባደረገው ስብከት ላይ የተደረገ አስተንትኖ

Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች Written by Super User Hits: 2825

ራሳቸውን ስለሚያሰማሩ እረኞች ቅ. አውጎስጢኖስ ባደረገው ስብከት ላይ የተደረገ አስተንትኖ

Sheperdsቅ. አውጎስጢኖስ ስለ ክርስቲያን እረኞች ሲናገር ክርስቲያን መሆን የራሱ ኃላፊነት እንዳለው በመግለጽ ከክርስቲያኖች ደግሞ የእረኝነት ኃላፊነትን የተቀበሉ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባል። ይህ ሁለተኛው ኃላፊነት ብዙ አደጋ እንዳለበት ሆኖም ግን በሰው ብቃት ሳይሆን በጌታ ጸጋ የሚሰጥ መሆኑንና የሚሰጥበት ዓላማም ለሌሎቹ ጥቅም ሲባል መሆኑን እንደ ሚከተለው ጽፎታል “ጌታ አምላክ በእኔ መልካም ሥራ ሳይሆን ለእርሱ ተገቢ መስሎ በታየው መንገድ ብዙ አደጋ ያለበትን ይህን ሥልጣን ሰጠኝ፤ እኔም ሁለት ግልጽ የሆኑ ባሕርያትን አሳያለሁ፡ አንደኛ ክርስቲያን ነኝ፡ ሁለተኛ ለሌሎች መጋቢ ሆኜ ተሾሜያለሁ። ክርስቲያንነቴ ጥቅሙ ለእኔ ነው፤ መጋቢነቴ ለእናንተ ነው።” በዚህም ሀሳቡ እንደ ክርስቲያንነቱም እንደ እረኝነቱም ሁለት መዝገቦች እንደተሰጡትና ሁለቱንም መዝገቦች ለአምላኩ እንደሚያቀርብ ያስረዳል።

እረኝነት ራሱ ቃሉ እንደሚያስታውሰን ለራስ ሳይሆን ለመንጋ መኖርን የሚያመለክት ሲሆን ቅ. አውጎስጢኖስ ይህን እውነታ የዘነጉ እረኞችን የሚያነቃቃበት የእግዚአብሔር ቃልና የራሱ አባባል አለው “እናንተ የመንጋው አካል፡ የእስራኤል መሪዎችና እረኞች ናችሁ። ነገር ግን እረኞች ተብለው መጠራትን ሲወዱ የእረኛን ሥራ የማይፈጽሙ አንዳንድ እረኞች እንዳሉ በነቢዩ አማካይነት ስለእነርሱ ምን እንደተባለ እናስታውስ። ‘የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም።’ (ሕዝ. 34:1-4) 

ከላይ ስለተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል ባሕርይ ቅ. አውጎስጢኖስ ሲገልጽ “ማንንም የማይደልለው የእግዚአብሔር ቃል በጎቹን ሳይሆን ራሳቸውን ለሚያሰማሩ እረኞች የሚለው” ነው ይለናል። ማንንም ለማስደሰት ወይም ለማሳዘን ያልታለመ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና ይህን መሰሉ ቃል ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እረኞች መነገሩን ያሰምርበታል። እረኛ መንጋውን የሚጠቅመውንና የሚመራውን ድምፅ ሲያሰማ መንጋው ይጠቀማል፤ አቅጣጫም ያያል፤እረኛው በየት አቅጣጫ እንዳለ ያውቃል ስለዚህም ያን ድምፅ ተከትሎ መንጋው መንገዱን ያቀናል፤ ይህ ሳይሆን ሲቀርና የእረኛው ድምፅ ከሌሎቹ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ግን መንጋውን የድምፆች ብዛት ግራ ያጋቡታል፡ መንገድንም መለየት ሊያቅተውና ሊባዝን ብሎም ሊጠፋ ይችላል። የእረኛው ድምፅ መንጋውን “በእምነቱ ሊያበረታውና ሊያጸናው አሊያም ሊያቆስለውና ሊሰብረውይችላል”  ይለናል ቅ. አውጎስጢኖስ።

እውነትን በመናገር የምታስከፍለውን ዋጋ ላለመጋፈጥ የሚጥሩ እረኞች እንዳይኖሩ ቅ. አውጎስጢኖስ ሲያሳስብ “የሚናገሯቸውን ሰዎች እንዳያስቀይሙ በመፍራት ለማይቀረው ፈተና ያለማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ለዓለም እንኳ ተስፋ ያልሰጠውን የዚህን ዓለም ደስታ ተስፋ የሚሰጡ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?” ይላል። በዚህም አባባሉ እረኛው ስለሚናገረው ነገር ለመንጋው የሚጠቅመውን እንጂ የሚያስደስት ወይ የሚያስቀይም የሚል መስፈርት መያዝ እንደሌለበት ያስረዳናል። በዚህች ዓለም የእግዚአብሔር የሆነው እውነት፡ ጥሩነትና ውበት ሁልጊዜም እንዳይደበዝዝ መጮኽ የእረኛው ድምፅ መለያ ባሕርይ ናቸው። በአንጻሩ እረኛው ሌሎች እውነት፡ ጥሩና ውብ የሚሏቸውን ነገሮች በተለያዩ አገላልጾች የሚያስተጋባ ከሆነ  ድምፁ  የመልካም እረኝነት መለያ ንጥረ ነገሮችን አጥቷል።

ክርስትና ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑንና እረኛንም በየትኛውም አቅጣጫ ከሚመጣ ተኩላ ጋር የሚያጋፍጥ መሆኑን እናውቃለን፤ እውነቱ ይህ ስለሆነም እንደ ክርስቲያንም ሆነ እንደ እረኛ ሐዋርያው ቅ. ጳውሎስ የሚለንን ንግግር ቅ. አውጎስጢኖስ እንዲህ በማለት በአፅንዖ ለእረኞች ይጠቀምበታል “ሐዋርያው ‘በክርስቶስ ጽድቅ ለመኖር የሚሹ መከራ አለባቸው’፤ ይለናል። አንተ የክርስቶስን ሳይሆን የራስህን ጥቅም የምትሻ እረኛ ይህን ቃል አድምጥ!”። ይህን ሃሳብ ተመርኩዞም “የምታደርገውን አስተውል፤ ለአንተ በኃላፊነት የተሰጠህን ሰው በምን መሠረት ላይ እንደምታቆመው ልብ አድርግ”  በማለት መንጋውን በአሸዋ ላይ ሳይሆን በዓለት ላይ የሚያቆም እረኛ በመሆን ስለክርስቶስ መክፈል የሚገባውን ዋጋ መክፈልን ያሳስበዋል።