መላእክት ምንድን ናችው?
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Thursday, 28 December 2017 07:26
- Written by Super User
- Hits: 14710
- 28 Dec
መላእክት
መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ እና በታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና አላቸው። ብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ ስለመላእክት ይጠቅሳል። አዲስ ኪዳንም መላእክት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ያላችውን ስፍራ ይጠቁመናል። ኢየሱስም በወንጌል ውስጥ ከመላእክት ጋር ግንኙነት እንዳለው ይናገራል።
ስለዚህ መላእክት ምንድን ናችው?
በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቲያን ቁጥር 329 ውስጥ እንደተጠቀሰው ቅዱስ አውጉስጢኖስ እንዲህ ይላል “መላእክት የሚለው ቃል ተግባራችውን የሚያስረዳ ነው። ተፈጥሮአቸው ግን መንፈስ ነው። ስራችው መላእክት ያስብላቸዋል በተፈጥሮአችው ደግሞ መንፈሳውያን ናቸው። መላእክት የእግዚአብሔር አገልጋዮች እና መልክተኞች ናቸው። መላእክቶች መንፈሳውያን ፍጥረታት እንደመሆናቸው መጠን ማስተዋል (intelligence) እና ፈቃድ (will) አላቸው። መላእክት የማይሞቱ መንፈሳውያን ፍጥረታት ናቸው። እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ መላእክት እግዚአብሔርን ለማገልገል የተፈጠሩ መንፈሳውያን ፍጥረታት ናቸው። እነዚህ መላእክት በሰው መልክ ተገልጠው ከሰው ልጆች ጋር ሊገናኙ ይችላሉ።
የመላእክት ፋይዳ ምንድን ነው?
የመላእክት ተግባር እግዚአብሔርን ማገልገል፣ እርሱን ማመስገን፣ እርሱን መወደስ፣ ለክብሩ አምልኮና ስግደት ማቅረብ ነው (ኢሳ 6:3 ፤ ራዕይ 4:8) ። እግዚአብሔርን ከማገልገል ጎን ለጎን እኛን ይጠብቁናል፣ ይጸልዩልናል፣ በመንፈሳዊ ጉዟችን ይመሩናል፣ ያበረታቱናልም። በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቲያን ቁጥር 336 ላይ እንደተገለጸው " ከልደት እስከ ሞት ድረስ የሰው ሕይወት በመላእክት ጥበቃ እና አማላጅነት የታጠረ ነው። ጠባቂ መልአክ ከእያንዳንዳችን ጎን ሆኖ እንደ ብርቱ ጠባቂ እና እረኛ ወደ በጎ ነገር እና ወደ ሕይወት ይመራናል" ። እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ቸርነት ለጠባቂ መላእክት ስለተሰጠን ጠባቂ መላእክቶቻችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቁናል።
መላእክት ከጠባቂነታቸው ባሻገር በሰማያት ከሚገኙት ቅዱሳን ጋር በአንድ ድምጽ ሆነው ”ቅዱስ፤ቅዱስ፤ቅዱስ” እያሉ በእግዚአብሔር ፊት ስለእኛ ይማልዳሉ (ይጸልዩልናል) (ጦቢት 12:12 ፤ ራዕይ 5:8 እና 8:3)። ይህም ስለሆነ ኢየሱስ ‘’ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ” (ማቴ 18፤10) እያለ ስለመላእክት ተግባር በግልጽ ይናገራል።
መላእክት ልዩ ልዩ አገልግሎትና ተግባራት አሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በልዩ ልዩ ስፍራዎች የገለጠውን ተከትለው የነገረ መለኮት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩን በሰማያዊ ሥልጣናቸው ቅደም ተከተል መሰረት ዘጠኝ ነገደ መላእክት አሉ። እነዚህም ፩. ሡራፌል፤ ፪. ኪሩቤል፤ ፫. መናብርት፤ ፬. ገዢዎች ፤ ፭. ኃይላት ፤ ፮. ሥልጣናት ፯. አለቆች (ሠራዊት)፤ ፰. ሊቃነ መላእክት፤ ፱. መላእክት ናቸው።
ሡራፌል፤ ኪሩቤል፤ መናብርት እግዚአብሔርን በጥበቡ፤ በፍርዱ እና በዙፋኑ ክብር የሚወድሱት፤ የሚሰግዱለትና የሚያመልኩት ናቸው።.
ገዢዎች፤ ኃይላትና፤ ሥልጣናት ደግሞ ባጠቃላይ የተፈጥሮን ኃይላት ሁሉ የሚያስተዳድሩ ናቸው።
አለቆች (ሠራዊት) አህጉራትንና ከተሞችን የሚጠብቁ ናቸው።
ሊቃነ መላእክት የተመረጡ ሰዎች ጠባቂዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ሶስት ሊቃነ መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስማቸው ተጠቅሰው እናገኛለን፤ እነዚህም ሚካኤል፤ ገብርኤል እና ሩፋኤል ናቸው ( ጦቢት12:15፤ ዳን 12:1፤ ዳን 8፡16፤ ዳን 9፡21 )
መላእክት ደግሞ ለሁላችን የተሰጡ ጠባቂዎችና መልክተኞች ናቸው። ከዚህ በታች የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በማንበብ ስለ መላእክት ያለንን ግንዛቤ እንድናሳድግ እና በመንፈሳዊ ሕይወታችን የእነርሱን ረድኤትና ትሩፋት አግኝተን እንድንበለጽግ እግዚአብሔር ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ በሊቀ መልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት እንለምናለን!!!.
መልካም በዓል!!!
ዘፍ 19:1-17፤ መዝ 91፤ ዕብ 1:1-14፤ ዕብ13:1-2፤ ሉቃ 22:,39-43
ወጣት ሳምሶን ደቦጭ ከጀርመን