የመንጋ ወይም የገደል ማሚቱ ክርስትና!?

Written by Super User on . Posted in የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች

የመንጋ ወይም የገደል ማሚቱ ክርስትና!?

Mass Christianityየእምነት ሕይወት ከምንም በፊት ሰው መሆንን ያስቀድማል፤ ምክንያቱም ሰው መሆንን ማወቅ አምላክን ወደ መፈለግ ስለሚያመራ ነው። አምላክን የመፈለግ ሂደትም ወደ እምነት ሕይወት ቀጥሎም ከብዙዎቹ አንዱ ወደሆነውና በዚህ ጽሑፍ ልናተኮርበት የፈለግነውን ክርስትናን ያስከትላል፣ በመጨረሻም ክርስትናን የምንኖርበት ዘይቤና መገለጫ በየአስተምህሮቱ እንደመጠሪያው ይለያያል። በዚህ መሠረት ነው ሃይማኖታችንን የምንረዳው፤ ሰው መሆንን የሚዘል እምነት ብሎም ክርስትና ሊኖር አይችልም! ሥረ መሠረቱ ላይ ስንሄድም የክርስትናችን ምንንነት ሰው ሆኖ በተወለደ አምላክ በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህም ክርስትና ግለሰብን የሸፈነ፣ የግለሰብን ንጥል ልዩ ማንነትና ባለአእምሮነት የማያከብርና እንደው በስብስቡ ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያስገድድ ሊሆን አይችልም።

ከሌለ አቅጣጫም ደግሞ ክርስትና በግለ ማንነታቸው ብቻ የተጠጋጉ አንዱ ከአንዱ ጋር ቁርኝት የሌላለውና ያልተሳሰሩ ማንነቶች የተጠራቀሙበት እምነት አይደለም፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ራሱ በአካል እንዲከተሉት የጠራቸውና በዙሪያው የሰበሰባቸውን አንድ ይሆኑ ዘንድ አዟቸዋል “አባት ሆይ!...አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” /ዮሐ 17:21/ እንዲሁም ሁለትና ሦስት ሆነን በተሰበሰብንበት እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ ነግሮናል “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ”/ማቴ 18:20/።

እዚህ ላይ የምናስተውለው እውነታ የክርስትና አንድነት ራሳቸውን በሙሉነት መኖር የቻሉ ሰዎች ስብስብ እንጂ አንዱ በሌላ ውስጥ ተውጦ ወይም ራሱን የማየት ብቃቱ ተገፍፎ በሌላው ብቻ ተደግፎ ሌላው የሚለውን በራሱ አእምሮና ማንነት ሳያጣጥም የሚያስተጋባ የገደል ማሚቱ ዓይነት ክርስትና ትኩረታችንን ይሻል። የከፊል ማንነት ክርስትና ሊኖር አይችልም፤ ስለዚህም እምነታችን አእምሯችንን በሚክድ ሳይሆን በትክክለኛ መንገድ በሚመራ መልኩ የተቃኘ መሆን ይገባዋል። አንድ ሕግ አዋቂ ጌታን ሊፈትነው ሲጠይቀው የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ላድርግ አለው? “ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፤ በፍጹም ነፍስህም፤ በፍጹም አሳብህም ውደድ አለው” /ማቴ 22:37፤ ሉቃስ 10:27/ ክርስትና ነፍሳችንን፣ ልባችንንና አ’እምሯችንን አስማምተን በሙሉነት የምናመልክበት እምነት ነው።

የላየኑ ቅዱስ ኤሬኒየስ “በመላ ማንነቱ በሚገባ የኖረ ሰው የእግዚአብሔር ክብር ነው” ይለናል። ክርስትና አንድን ሰው ከስሜታዊ ማንነቱ ጡዘት አውጥቶ የማሰብ ብቃቱን እንዲጠቀም በማድረግ በማህበራዊ ሕይወቱም ተግባቦትን ማለትም የመደማመጥና መረዳዳት ብቃትን በማዳበር ከሌሎች ጋር ጥላቻንና መለያየትን ሳይሆን ፍቅርን እየኖረ ለማሳየት የሚያበቃ መገለጫ አለው።

“ጌታን ተቀብያለሁ” የሚል ክርስቲያን በምንም መልኩ ወንድምና እህቱን የማይቀበል፤ የማያዳምጥ ሊሆን አይችልም፤ በርግጥ መለየት ካለብን ክፋቶችና ከኃጢአት ምክንያቶች መለየት አለብን፤ ነገር ግን የእኛን እምነት ካልተከተልክ ጠፍተሃል አልቆልሃል...ወዘተ “ክርስቶሳዊ” ከመሆን መንፈስ ጋር ምስማማት ያለመስማማቱን ማጤን ያስፈልጋል።

እምነት ከጊዜያዊ ፍላጎት መሟላትና መርካት ባሻገር የሆነ አርቆ የሚያይ ማንነትን ይፈልጋል። እግዚአብሔርን ይበልጥ በቀረብን መጠን እግዚአብሔር የእኛን ፈቃድ እንዲያሟላ ከምንፈልገውና ከምንጥረው በላይ እኛ የእርሱን ፈቃድ ማሟላት እርካታችን ይሆናል፤ በማርቆስ 3 ላይ እንደምናነበው ክርስቶስ ብዙ ሰዎችን ሲፈውስና ከዚህም የተነሣ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገ ሰምተው ብዙ ሰዎች በዙሪያ ካሉ አገሮች እንደተሰባሰቡ እናያለን፤ ኢየሱስም “ሰዎቹም እንዳይጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ አዘዛቸው” /ማር 3:1-9/። ፍላጎቱን ብቻ የሚያስብ ሰው ይጋፋል፤ እንደውም ክርስቶስንም እስከ መግፋት ይደርሳል።

ውስጣዊ ማንነቱ ላይ ማየትና ማስተካከል የሚገባውን ነገር መጋፈጥ የማይፈልግ ሰው ከውስጡ በመሸሽ በውጭ የሚስተጋባውን ብቻ ውስጡ ሳያስገባ “አሜን” በማለትና ሌሎች የሚሆኑትን ለመምሰል በመጣር ብቻ በጅምላ ገደል ማሚታዊ ክርስቲያን ሊሆን ይዳዳዋል፤ ይህን መሰል ክርስቲያን በየትኛውም የክርስትና እምነት ውስጥ አይታጣም፤ የክርስቶስ ተከታይነት ግን እኛን በመላ ማንነታችን የሚፈልገን ነውና በሁለንተናችን ለእርሱ መገኘትን ይጠይቀናል።

ስለዚህም እምነታችንን በሙሉ ማንነታችን ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ካለብን በሙሉ ማንነታችን በምድራዊ ፈቃዶች ሳንገደብ ወደ ሰማይኛው ፈቃድ እንመልከት፤ ከማግለል አባዜ ወደ ማገልገል፤ ከምድራዊው የቤት ቁሳቁስ ማሟላት ጸሎት ወደ ዘላለማዊው ቤት ግንባታ እንበራታ፤ሆዳችንን መሙላት አግባብ ያለው ነገር ቢሆንም ከዚያም ጠለቅ ወዳለውየሕይወት እንጀራ ወደ ሆነው ቅዱስ ቁርባን እንሩጥ።