ባዶ!? ከባዶ ወደ ማዶ!

Written by Super User on . Posted in የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች

Easter 2012 webpageባዶ!? ከባዶ ወደ ማዶ!

"ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።"

(የዮሐንስ ወንጌል 20:1)

የክርስቶስ መቃብር ባዶ ሆኖ መታየትና መገኘት ለአማኞች የእርሱን ሕያውነት ያመለክታል። ክርስቶስ ከመቃብር በላይ ነው። በውስጣችንም ሆነ በውጫዊ ነገር ባዶነት ሲሰማን ራመድና ቀና ብለን በክብር ያለውን ክርስቶስን እንድናይ እንጋብዛለን።

"ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።" (የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24:3-5)

ምናልባት ዘንድሮ እኛ ባሰብነውና በፈቀድነው መልኩ የትንሣኤ በዓልን ሳናከብር ስንቀር ውስጣችን ባዶነት ቢሰማውም የክርስቶስን ሕያውነት በልዩ መልኩ እንድናገኝ ከመጋበዝ ውጪ ባዶነት መገለጫችን አይደለም፣ የክርስቶስ መቃብር ባዶነት ለክርስቲያኖች የእርሱ መነሣት መልእክትን ነው የሚያስተላልፈው። እንዲሁም ትንሣኤን በምናከብርበት መሰዋዕተ ቅዳሴ የምእመናን ወንበሮቻችን ባዶ ሆነው ቢታዩም በእምነት ዓይን የመገኘታችሁን መልእክት ያስተላልፋሉ፣ ክርስቶስ ሕያው ነውና ክርስቲያኖችም ሕያዋን ነን።

መቃብሩ ባዶ ሆኖ መታየቱ ለሊቀ ለካህናቱና ፈሪሳውያኑ የክርስቶስ አስክሬን ተሰረቀ ብለው ለማውራት ምክንያት ሲሆናቸው ለማርያም መግደላዊት፣ ለማርያም ሰሎሜ፣ ወደ መቃብሩ ለሮጡት ሁለቱ ደቀመዛሙርት፣ እንዲሁም በዘመናት ለነበሩትና ዛሬም ላለነው ለእኛ ባዶ መቃብር የክርስቶስን ሕያውነት ያስተጋባል።

መልካም በእምነት፣ በፍቅርና በተስፋ የተሞላ የትንሣኤ በዓል ለሁላችን!