የእምነታችን ጥጉ ሰማይ ነው፤ አምላካችን ከሁሉ ከፍ ያለ ነውና!

የእምነታችን ጥጉ ሰማይ ነው፤ አምላካችን ከሁሉ ከፍ ያለ ነውና!
Sidrach webpageየእግዚአብሔር ሀሳብ ከሀሳባችን፣ ፈቃዱ ከፈቃዳችን ሰማይ ከምድር እንዲርቅ እንዲሁ ነው /ኢሳ 55:8-9/። ይህን ካሰብን በኋላ ለምኖቻችን ሲረዝሙብንና እየሆኑ ያሉ ሁኔታዎች ባይገቡንም እንኳ የእሱ ባህርይ የማይለወጥ መሆኑ ያሳርፈናል፣ ስለዚህም ከባድ በሚመስሉ ሁኔታዎች መካከል ብንገኝም እንኳ እሱን ማፍቀራችንና ማመናችን ይቀጥላል። ስለዚህም ከቅ. ጳውሎስ ጋር "እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 8:28) እንላለን።
ፍቅር አይቆምም፣ አይገታም። የሆነ እንቅፋት ቢያጋጥመው እንኳ አይመለስም አልፎ ይሄዳል ተግባሩን ይከውናል። የፍቅር ምንጩ አምላክ ነው፣ ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ እሱ ነውና ከእሱ የሚወርደው ፍቅር ግቡ መልካም ነው፣ "ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።" (ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 55:10-11)። በጎ አድራጎት፣ ፍቅር፣ መልካምነት መንገድ ላይ አይቆሙም፣ ሙከራም አይደሉም፣ መድረሻ አድራሻ አላቸው። የተሰፈረ፣ የተተመነ ፍቅር የለም፣ በሌላ አባባል የተላከ እንጂ የተለካ ፍቅር የለም። ቅዱስ በርናርዶስ ፍቅር መገለጫው ገደብ የለሽነቱ ነው ይላል።
ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ የተገደቡ በሚመስሉ ነገሮች ሁሉ ያፈቅረናል፣ ለፍቅርም ይጠራናል።
እምነትም እንዲሁ ነው፣ ገደብን አያውቅም። በነገሮች ሁሉ ፊት ይሻገራል፣ የእምነት ሰው አምላኩ ግዙፍ ነውና እዚችጋ አይገደብም፣ አርቆ ያያል። በትንቢተ ዳንኤል ላይ ይህ እውነት ደምቆ ይታያል። /3:1-27 ሙሉውን ማንበብ ይቻላል/ የናቡከደነፆር ሀውልት፣ ዛቻና የእሳት ነበለባል ርዝመት ከእምነታቸው እንዳይበልጥ ያውቃሉና ንጉሡ ናቡከደናጾር ላሠራው ትልቅ ሃውልት ይሰግዱ ዘንደ በአውራጃው ያሉ ሰዎች ታውጆላቸው ሳለ በእምነት እምቢ ያሉ ሦስት ወጣቶች ተገኙ፤ መልሳቸውም የእምነታቸውን ጥልቀት የሚያሳይ ነው፤ እሳቱ በፊታቸው ከፍ ብሎ ቢንቦገቦግም የሚከተለውን መልስ ሰጡ፡
"ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም። ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!" አሉት /ቁ.16 እና 17/።
በርግጥም የሚያመልኩተ የሰማዩን አምላክ ነውና የእምነታቸው ጥጉ ሰማይ ነው። አንገደብም እምቢ አሉ፣ እርምህን አውጣ፣ ቁርጥህን እወቅ የሚለት ይመስል ሁሉ "ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።" (ትንቢተ ዳንኤል 3:18) በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ቢሆን፣ የእምነት አቅማችንና የመኖር አቅላችን በዚህም በዚያም ሲፈተን፣ ለምን ብለን መልሳችን ራሱ ግን ለምን ቢሆንም እንኳ፣ አዎን ሌላ አምላክ የለንም፤ የእኛም አምላክ ይኸው ነው! ነገሮችን ሁሉ ተሻግረን እናምነዋለን፣ እናፈቅረዋለን! እንመሰክርለታለን!