እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ክርስትያናዊ እምነት

Jesus Masterክርስትያናዊ እምነት

የክርስትያናዊ እምነት ቁም ነገር በታሪክ እና በዘመን መካከል እራሱን የገለጠው ደግሞም በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ ለብሶ በመካከላችን ያደረው እግዚአብሔር አምላክ ራሱ ነው።  ይህም ክርስትያናዊ እምነት ከሁሉ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቤተክርስትያን አስተምሕሮ፣ በእምነት መገለጫ ምልክቶች ወ.ዘ.ተ ላይ ሳይሆን ሥጋ ለብሶ በኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው። የክርስትና እምነት በሁሉ ነገር ክርስቶሳዊ ነው። የእምነታችን ጀማሪ፣ መሪ እና ፍጻሜ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ለዘላለም ተሰውሮ የኖረውን መልኩን የገለጠበት ቃል የእምነታችን ሁሉ ማዕከል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ራሱን ገለጠ ስንል ስለራሱ ወይም ስለ ሰው ልጅ መዳን ያለውን ዓላማ ተናገረ ማለታችን አይደለም። ይልቁንም እንደ ፈጣሪ፣ አዳኝ እና ፈዋሽ ሆኖ ወደ እያንዳንዳችን ቀረበ ማለታችን ነው። ይህ የእግዚአብሔር ቅርበት ስለ እርሱ ማሰብ የምንችለውን ያህል እናስበው ዘንድ ለሰው ቋንቋ እና ለሰው አእምሮ በሚመጥን ቅርበት ራሱን የገለጸበት የፍቅር ትህትና ነው። በዚህ አይነት ትህትና እና ቀረቤታ ስለ እርሱ የምንናገርበትን ቋንቋ ይሰጠናል። ይህ ስለ እግዚአብሔር የምንናገርበት ቋንቋ፣ ስለ እርሱም ለመናገር በቂ የሆነ ቋንቋ ሥጋ የለበሰው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። በእርሱ በኩል ካልሆነ በቀር ስለ አብ ወይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ለመናገር የሚችል ማንም የለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር ቁልፍ እና ምስክር ነው። የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በፊት በቅዱሳት መጽሐፍት በፊደል ተከትቦ የሚገኘው፣ በቤተ ክርስትያን የዘመናት ታሪክ ውስጥ በተገለጠው አስተምህሮ ውስጥ የታየው የእምነት መገለጫ አይደለም። ይልቁንም የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ የለበሰው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ክርስትና የመገልጥ እምነት እንጂ የመጽሐፍ ሃይማኖት አይደለም!

የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ የመዳን መገለጥ ነው። የዚህ ግልጠት ጀማሪ፣ መሪ፣ አስኳል እና ፍጻሜ እግዚአብሔር ራሱ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በሰው ልጆች ቋንቋ ራሱን ገልጦ ስለ እርሱ እንናገር ዘንድ ዕድል ሰጥቶናል ማለታችን በሰው ልጅ ቋንቋ ስለ እግዚአብሔር የተነገረው ነገር እግዚአብሔር ነው ማለት አይደለም። ስለዚህ በሰው ልጆች ቃል እና በእግዚአብሔር ቃል መካከል አስፈላጊውን መሰረታዊ ልዩነት ማድረግ ያስፈልጋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን በነብይ ቃል እና በእግዚአብሔር ቃል መካከል ልዩነት ይደረግ እንደነበረው እንዲሁ በአዲስ ኪዳንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ 1 ተሰ 2፡13 ላይ ባደረገው ስብከቱ በግልጽ እንደሚለው የስብከቱን ቃል እንደሰው ቃል ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ስለተቀበሉት የተሰሎንቄ ክርስትያኖችን ሲያመሰግናቸው እንመለከተዋለን። የእግዚአብሔር ቃል ከሰው ቃል ጋር በተቀየጠበት ሁኔታ እና ስፍራ ሁሉ በሁለቱ መካከል መሰረታዊ ልዩነት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህ መሰረታዊ ዕይታ በጎደለበት ሥፍራ በእግዚአብሔር ቦታ የሰው ስም ተተክቶ ይደመጣል። ስለ እግዚአብሔር የሚነገርበት ቃል ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም! ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር የምንናገርበትን የሰው ቋንቋ ከውሱንነቱ ባሻገር በእግዚአብሔር ቃል ወደ መናገር ከፍ ያደርገዋል። በእግዚአብሔር ቃል እንደ እግዚአብሔር ቃል መናገር የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው። “በሰው ልጅ ቋንቋ ውስጥ የሚነገረው የእግዚአብሔር ቃል እና የእግዚአብሔር ጥበብ በቋንቋ ውስጥ ያለ ምሥጢር ነው፤ ነገር ግን ምሥጢራዊ ቋንቋ አይደለም”[1]

የእምነታችን ቁምነገር እና የመጨረሻው እውነት በእምነት አባቶቻችን በኩል ከበጎ ፈቃዱ የተነሳ ራሱን የገለጠልን እና ያነጋገረን አምላክ እግዚአብሔር ራሱ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ለራሱ መስፈርያ የሌለው ነገር ግን የሁሉን ነገር ልክ የምናሰላበት ወሰን፣ ሁሉን ነገር የምንመዝንበት ሚዛንና ሁሉን ነገር የምንሰፍርበት መለኪያ ነው “Suprema Norma” / “Norma normans non normata”። የእግዚአብሔር ቃል ስንል በአንድ በኩል ስለ እግዚአብሔር የሚናገር ቃል ማለታችን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ በነገር ሁሉ ላይ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሁሉም በሁሉም ላይ የተናገረው ቃል ማለታችን ነው። እግዚአብሔር በሚናገርበት ነገር ውስጥ ሁሉ ቃሉ የፈጣሪነቱን ተግባር ያከናውናል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ መመልከት እንደምንችለው የእግዚአብሔር ቃል ከፈጣሪነቱ እና ከተግባራዊ መገለጡ ጋር የተገናኘ ነው። ስለዚህ ቃሉ ፈጣሪ ቃል፣ ያልነበረውን ወደ መኖር የሚጠራ ቃል፣ ሕያው የሚያደርግ ቃል ነው፤ ዳዊትም በመዝሙሩ “በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ” (መዝ 33፡6) እያለ የቃሉን ኃያልነት ይዘምራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ በምናገኘው የፍጥረት ታሪክ ውስጥ በተገለጠው እምነት ራሱን የገለጠው እግዚአብሔር የእውነት ሁሉ መልህቅ ነው። እርሱ የገዛ ራሱ ሕዝብ አድርጎ ለመረጠው ለእሥራኤል የሰጠው እምነት ከእሥራኤል ታሪክ እና ማንነት ጋር የተቆራኘ፣ በእሥራኤል ታሪክ ውስጥ በእውነት ተገልጦ የታየ ነው። ይህም የእሥራኤል ህዝብ ከግብጽ ባርነት አርነት የወጣበት ክስተት ነው። እሥራኤል ሕያው ሆኖ የሚኖረው ይህንን የመዳን ታሪኩን በትውልድ መካከል ሕያው አድርጎ እያስታወሰ በመኖሩ ነው (ዘጸ 15፡ 19፣ 20:2)። ልክ እንደ እሥራኤላውያን ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስትያኖች ለዘለዓለም እያስታወሰን እንኖር ዘንድ “ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” (ሉቃ 22፡19 1ቆሮ 11፡24) እያለ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ሰጥቶናል። ይህም ዘለዓለማዊው የእግዚአብሔር ቃል በመካከላችን ሊኖር የወደደበት አዲሱ የመገናኛ ድንኳን ነው። በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት ከዚሁ ዘለዓለማዊ ቃል ጋር ባለን ሕብረት አሁን ሁላችንም ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት እና ከርሱም ጋር በመዓድ መቀመጥ እንችላለን።

እግዚአብሔር አምላክ ራሱን ለሰው ልጆች ሲገልጥ ዋነኛው ዓላማው የሰው ልጆች መዳን እና መቀደስ ብቻ ሳይሆን እንደ መልካም አባት በልጆቹ መካከል መኖሩ ነው። ስለዚህ እኛ በእርሱ መኖር እንማር ዘንድ እርሱ በእኛ መካከል ከኃጢአት በስተቀር በሁሉ ነገር ፍጹም ሰው ሆነ። ብሉይ ኪዳን በእሥራኤል ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔርን መገለጥ ሲተርክልን ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ በልዩ መልኩ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለእሥራኤል የተሰጠ መሆኑን ያመላክተናል። እግዚአብሔር ከአብርሐም ጋር የገባው ቃል ኪዳን በዘመንና በትውልድ መካከል የሚቀጥል ለሚመጣው ለወደፊቱ ክፍት የሆነ ራዕይ ነው። ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ እያንዳንዱን ግለሰብ በቃል ኪዳን የራሱ አድርጎ የሚቀድስ ሲሆን የቃል ኪዳኑ መሰረታዊ ቁም ነገር እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጠው ራዕይ እና ሕዝቡ ወደዚህ ራዕይ የሚደርስበት ምሪት ነው። በዚህም የእግዚአብሔር ቃል፣ ፈቃድ እና ተግባር የእያንዳንዱን ሰው ህይወት እና ውሳኔ ጭምር የሚጠቀልል ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ዓለምን ፈጥሮ ሲያበቃ ከታሪካችን እና ከህልውናችን ውጪ ሊደረስበት በማይችል ብርኀን ውስጥ የሚኖር አምላክ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚሰራ እና የሰው ልጆችን ሁሉ ከተፈጠሩበት የልጁ መልክ ክብር የተነሳ ከዘላለም ጀምሮ ወደታየላቸው “ብዙ መኖርያ ወዳለበት” (ዮሐ 14፡2) ክብር የሚመራቸው አምላክ ሆኖ ተገልጧል። እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን በማዳኑ እና አርነት በማውጣቱ ውስጥ ሊታጠፍ በማይችል፣ ቅድመ ሁኔታ በሌለው ፈቃድ ሕዝቡን ለማዳን ያለውን ፍላጎት ይገልጣል (ዘዳ 26፡5-10፣ ኢያሱ 24፡1-13)።

የእግዚአብሔር ሥራ ምንም እንኳን ከሰው ልጆች መረዳት በላይ ቢሆንም ቅሉ፤ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውሱንነት በሚያከብር ትህትና ተገልጧል። እሥራኤል ራሱን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ተቀብሎ እንዲኖር (ዘጸ 19፡4-6)፣ በታሪክ ውስጥ ያለፈባቸውን ምዕራፎች እንደ እግዚአብሔር መገለጥ ጉዞ እንዲረዳ እና እንደ ሕዝብ ባለው የመተካካት ተፈጥሮአዊ ዑደት ሳይሆን ይልቁንም በአንድ እግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት ሕያው ሆኖ እንዲኖር ተጠርቷል (ዘሌ 18፡3)። በክርስትና እምነት የምንኖረው ምሥጢር ይህ ነው፤ በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ታሪክ ውስጥ ተገልጧል፤ እምነት በታሪካችን ለሆነው ለእግዚአብሔር መገለጥ የምንሰጠው ምላሽ ነው።

የእሥራኤልን ታሪክ ስንመለከት ዘወትር በሁለት ጽንፎች የተቃኘ ሆኖ እናገኘዋለን፤ በአንድ በኩል በግብጽ የነበረው ባርነት እና እግዚአብሔር ያደረገላቸው ነጻነት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የባቢሎን ምርኮ እና ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ አለ። እሥራኤል በምርኮ እና በግዞት በነበረነት የጨለማ ዘመን ሁሉ የማዳን እና የነጻነት ፍላጎት ዘወትር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚነሳ ቁም ነገር ነበር። ከግብጽ ለመውጣትም ሆነ ከባቢሎን ምርኮ ለመመለስ ጀማሪ፣ መሪ እና ፈጻሚው እግዚአብሔር ነበር። ልዩነቱ እሥራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን የገለጠው እንደ ድል አድራጊ (ዘጸ 15፡1-19) ሲሆን በባቢሎን ዘመን ግን የአሸናፊው የእግዚአብሔር ሕዝብ ፊቱን ከእግዚአብሔር ላይ አንስቶ በራሱ ኃይል ላይ በማድረጉ እንደ ምርኮ ገንዘብ እና እንደ ተሸናፊ ሰነፍ ከርስቱ መሰደዱ ነው። እሥራኤል በዚያ ዘመን ራሱን፣ ታሪኩን እና ማንነቱን ብቻ ሳይሆን አምላኩን ሳይቀር ያስማረከ ሕዝብ ሆኖ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንደ ሰው ከዚህ ጋር የምንመሳሰልባቸው የሕይወት አጋጣሚዎች ሩቅ አይደሉም። አምላክ የተማረከብን ሕዝብ የምንሆንበት፣ በልዩ ልዩ ሁኔታ ውስጥ አምላክ እንደሌለው ሕዝብ የምናስብበት፣ የምንናገርበትና የምንሰራበት አግባብ ይስተዋላል። እንደ ግለሰብ፣ በቤተሰብ መካከል፣ እንደ ቤተክርስትያን፣ ብሎም እንደ ሀገር የገባንበት አልቦ-እግዚአብሔርነት ወይም ደግሞ በአማኝ ሕዝብ ትርክት የምንኖርበት ኢ-አማኒነት ከእሥራኤል የምርኮ ዘመን ማንነት ብዙም የራቀ አይደለም።

እሥራኤል ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር በሙሉ ከእግዚአብሔር የፍጥረት ምሕዋር ውጪ ሆኖ መኖር አይችልም፤ ስለዚህ የሰው ልጅ በጸጋ እና በእግዚአብሔር ምሕረት የተደገፈ ፍጥረት ነው። በመሆኑም ወደ እግዚአብሔር መመልከት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና እና የፍጥረቱ ምልዓት ጥያቄ ነው። የሰው ልጅ በጥበብ እና በነጻነት ገደብ በሌለው መልዕልተ ባሕርያዊ ልህቀት ለመገለጥ የተፈጠረ በመሆኑ የፍጥረቱን ውል ይህም እግዚአብሔርን ባወቀበት መጠን ወደ ነጻነት እና ወደ ዕውቀት ሁሉ ምልዓት ያድጋል። ይህ ዕድገት ፍጹም ምሉዕ፣ ፍጹም መልካም፣ ፍጹም ፍጻሜ ወዳለው ተስፋ የሚመለከት ሲሆን፤ ይህም ተስፋ እግዚአብሔር ራሱ ነው[2]

የሰው ልጅ ከዚህ እውነታ ጋር በሰመረ ግንኙነት ሕይወቱን መምራት ይችል ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥጦታ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ በማቴዎስ 11፡25 ላይ ይህንኑ በሚመለከት እግዚአብሔር አብን “አባት ሆይ የሰማይ እና የምድር ጌታ፤ ይህንን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለህጻናት ስለገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” ይለዋል። እምነት በነፍስ ላይ ከሚዘራ ብርኀን እንጂ ከሚታይ ነገር አይነሳምና የእግዚአብሔር መንፈስ ራሱ ለአማኙ የእምነትን ብርኀን ያለብሰዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10 ላይ ሲያስተምር “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” እያለ የመገለጥና የእምነትም ሁሉ ምሥጢር ባለቤት መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይናገራል። ይህ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርኀን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፤ በጨለማ ብርኀን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነው” (2ቆሮ 4፡6)። ስለዚህ ከዚህ መንፈስ ያልተቀበለ ማንም ቢሆን ወደ እምነት ብርኀን ሊወጣ አይችልም።

በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የፈሰሰው መንፈስ ቅዱስ (ሮሜ 5፡5) በአማኞች ሁሉ ውስጥ ያለ ልዩነት ሕያው ሆኖ ይኖራልና በእርሱ ሥጦታ የተገለጠ አንድ እምነት ብቻ አለ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ እያረጋገጠ “በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉ የሚሰራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ” (ኤፌ 4፡4-6) እያለ ይመሰክራል። እምነት የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ እንደመሆኑ መጠን አማኙን በመላ ማንነቱ ይመለከተዋል። አማኙ ራሱን ለገለጠው እና ከእርሱም ጋር አብሮ ይኖር ዘንድ ሥጋ ለለበሰው አምላክ የሚሰጠው ተግባራዊ ምላሽ የክርስትና እምነት መሰረት ነው። ክርስትያናዊ ማንነት ከሁሉ አስቀድሞ “አምናለሁ!” በሚለው የነጻ ፈቃድ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ጉዞ ነው[3]

አምላኬ ሆይ! አንተ የገለጽከውን፣ ቅድስት ቤተክርስትያን የምታምነውን እና የምታስተምረውን ሁሉ አምናለሁ! አሜን!

ሴሞ

[1] G. Söhngen, Die Grundaporie der Theologie „Weisheit im Geheimnis“ und Wissen durch Vernunft, MySal I (1965), 905-980, እዚህ የተጠቀሰው ገጽ 926 ጀምሮ

[2] K. Rahner, Anonymer und expliziter Glaube, in: dieselben sämtlichen Werke, hg. V.d Karl-eahner-stiftung, Bd.22: Dogmatik nach dem Konzil, Freiburg i. Br. 2008, 338-344, እዚህ የተጠቀሰው ከገጽ 341

[3] J. Ratzinger, Einführung in das Christentum, München, 2006, ገጽ 42

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት