እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የዐቢይ ጾም ፩ኛ ሰንበት ዘወረደ

image001 540

የዐቢይ ጾም ፩ኛ ሰንበት ዘወረደ

የሰንበት  ንባባት፦ ዕብ 13፡ 7-16፤ ያዕ 4፡ 6-17፤ ሐዋ 25፡ 13-27 ፤ ዮሐ 3፡ 10-24

እንደ ሀገራችን የሥርዐተ አምልኮ ባህል መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘወረደ በመባል ይታወቃል። በዚህ ሰንበት ቤተ ክርስትያን የምትዘምረው መዝሙር የዐቢይ ጾምን አጠቃላይ ዓላማ ግልጽ ያደርግልናል። እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሐም ተገልጦ በመገረዝ በምትሆን ቃል ኪዳን ከእኛ ጋር ለመኖር እንደፈለገ እንዲሁ ተስፋውን ከሩቅ አይተው በእምነት በተሳለሙት (ዕብ 11፡13) በነብያት በኩል ለእኛ ያለውን ዓላማ በዘመንና በትውልድ መካከል ግልጽ እያደረገ ኋላም ጊዜው በደረሰ ጊዜ (ገላ 4፡4) በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ ለብሶ ስለተገለጠ ምሥጢር ቤተ ክርስትያን ዘወረደ ተብሎ በሚጠራው በዛሬው ሰንበት “ክርስቶስኒ መጽአ በዕድሜሁ ንዑ ንሑር ውስተ ቀበላሁ ንትቀበሎ ለወልድ ዘወረደ እምሰማያት...” እያለች ትዘምራለች።

ይህ ሰንበት ጌታን ለመቀበል የምንወጣበት ሰንበት ነው፤ በዚህ ሰንበት የድኅነት ታሪካችን በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በመካከላችን መገለጥ ምሥጢር አማካኝነት ፍንትው ብሎ ይታያል። በዚህች ሰንበተ ክርስትያን በቤተ-ልሔም ከእርሱ ጋር የሰውን ልጅ እውነተኛ መልክ በእርሱ በኩል የእግዚአብሔርን ያልተነካካ የፍጥረትን ፍጹማዊ ውበት እየተመለከትን ከእግዚአብሔር ጋር በአንድ ድምጽ “እነሆ እጅግ መልካም ነው”(ዘፍ 1፡2) እንላለን፤ በዮርዳኖስ ወንዝ ከጌታ ጋር ቆመን በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው ክፍል እንዲኖረን በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን የተወለድንበትን የራሳችንን ጥምቀት እያሰብን ያለ መጋረጃ ወደ መቅደስ ገብተን ከእርሱ ጋር፣ በእርሱ ስም እና በመንፈስ ቅዱስ አንድነት ለአምልኮ የተገባን ሆነን እግዚአብሔር አብን እናዳምጥ ዘንድ ከነብይነቱ ሱታፌ ተካፍለን፣ በፍጥረት ሁሉ ላይ ባለን ጌትነት ፍጥረትን ሁሉ ለእግዚአብሔር እየቀደስን እናቀርበው ዘንድ፣ በሥራ የእግዚአብሔር የፈጣሪነት ጸጋ ተባባሪዎች ሆነን ከንጉሥነቱ ሱታፌ ተካፍለን፤ ደግሞም በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ልሣን እግዚአብሔር አብን “አባ አባት” (ሮሜ 8፡15) ብለን እየጠራን፤ ሕይወታችንን ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያስደስት መልካም መዓዛ ያለው መባ በቅድስተ ቅዱሳን ከሚቀርበው ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የቊርባን መሥዋዕት ጋር አንድ አድርገን የምናቀርብበትን ሥልጣን ከጌታ ክህነት መካፈላችንን እያሰብን በሁሉ ነገር ጌታን ለመቀበል እንወጣለን።

ዘወረደ የእግዚአብሔርን “አማኑኤላዊ” መገኘት የምናጣጥምበት እና “አሜን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው!” እያልን የምንዘምርበት ሰንበት ነው። በዚህ ሰንበት የእግዚአብሔርን በመካከላችን መውረድ ስናስብ እንደ ቀደመው የባቢሎን ዘመን ቋንቋን የሚደበላልቅ የእግዚአብሔር የፍርድ በትር መገለጥን ሳይሆን፤ ይልቁንም በበዓለ አምሳ እንደሆነው በልዩ ልዩ ቋንቋ የተነገረውን የሚያሰማ እና የሚያስማማ የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን በማሰብ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንድናስተነትን እንጋበዛለን።

ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የተኳለ የእግዚአብሔር አብ የምሕረት ፊት ሆኖ በመካከላችን ወርዷልና እኛም በሌላ ፊት ሳይሆን ምሳሌ ሆኖ በተገለጠው በዚህ የምሕረት ፊት እርስ በእርሳችን እንቀባበል ዘንድ ተጠርተናል። ይህ የጌታ ፊት የእያንዳንዳችንን ኃጢያት ተሸክሞ በኢሳያስ መጽሐፍ “መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም” (ኢሳ 53፡2) የተባለው የአዳኛችን ፊት ነው። በምሥጢረ ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በተወለድን ጊዜ እርሱ የእኛን የኃጢአት መልክ ወስዶ የራሱን ውበት እና ደም-ግባት ለእያንዳንዳችን ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ክርስትያን የሚገለጥበት ከጌታ ኢየሱስ የተቀበለው ውበት እና ደም ግባት ያለው የእግዚአብሔር የምሕረት ፊት እንጂ በወንድሙ ላይ የሚያጠቁረው የኃጢአት ፊት የለውምና፤ ዘወረደ የተባለው ይህ ሰንበት የገጽታችንን መታደስ የምናስብበት እንዲሁም በወንድሞቻችን እና በእኅቶታችን መካከል የተገለጥንበትን ፊት የምንፈትሽበት ሰንበት ነው።

የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አኮቴተ ቊርባን ስለ ጌታ በመካከላችን መውረድ ሲናገር “ፍቅር ኃያሉን ወልድ ከሰማያት ስቦ እስከ ሞት አደረሰው”[1] እያለ ከመሰከረ በኋላ “ይህን ያህል ሰው ማፍቀር እንዴት ያለ ፍቅር ነው”[2] እያለ ሲጠይቅ ከእርሱ ጋር አብረን የጌታን  ፍቅር እንድናሰላስል ይጋብዘናል። መሥዋዕተ ቅዳሴ እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመካከላችን የወረደበትና የሚወርድበት የፍቅር ምሥጢር ነው፤ በመሆኑም በሰንበተ ክርስትያን በመሥዋዕተ ቅዳሴ ከሚቀርበው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ጋር ሕይወታችንን ሁሉ ጠቅልለን ለእርሱ እያቀረብን፤ እርሱ ባወረሰን የምሕረት ፊት እርስ በእርሳችን በፍቅር እየተቀባበልን ይህንን የዐቢይ ጾም የጸጋ ጉዞ እናደርግ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ያበርታን።

አሜን!

ሴሞ

 

[1] Ethiopian Catholic Church Episcopal Committee for Liturgy, መጽሐፈ ቅዳሴ በአማርኛና በግዕዝ፣ (2016)

[2] ዝኒ ከማሁ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት