እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

ዘቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

ንባባት፡- 1ኛ ተሰ 4፡1-12፣ 1ኛ ጴጥ 1፡13-25፣ ሐዋ 10፡17-29

ስብከት፡- እግዚአብሔርሰ ሰማያት ገብረ፥ አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ። ቅድሳት ወዕበየ ስብ ውስተ መቅደሱ (መዝ 96፡5)

          እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፤ ምሥጋናና ውበት በፊቱ፣ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው (መዝ 96፡5)

ወንጌል፡- ማቴ 6፡16-24

ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት “ዘቅድስት” በመባል ይጠራል። በዚህም የሰንበትን ቅድስና የምናሰላስልበት እና ሰንበትን ለሥጋ እና ለመንፈስ እረፍት ትሆን ዘንድ፣ ሰውን ያበጀ አምላክ ያከበረውን የሥነ ፍጥረት ቀመር የምናከብርበት ሰንበት ነው። ሰንበተ ክርስትያን “ስምንተኛዋ ቀን”[1] ሆና ከጌታችን ትንሳኤ አንጻር ፍጥረት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ አዲስ ሆኖ የተፈጠረባት፤ “እነሆ እኔ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” (ራዕ 21፡3-5) ያለው እርሱ የሰጠውን ተስፋ የፈጸመባት ዕለት ናት። ስለዚህም ሰንበት ክርስትያን በአንድ በኩል ወደኋላ እየተመለከተች የጌታን ማዳን እና የተደረገልንን ቤዛነት የምናስብባት ስትሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታ በመንበረ ታቦት በመካከላችን መሆኑን የምናይባት ዕለት ናት። ሰንበተ ክርስትያን የእግዚአብሔር አምላክ የሥነ ፍጥረት ሥራ ሁሉ በልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ምልዓት እና አክሊል ያገኘባት፣ ደግሞም ይህ ምልዓት በመካከላችን ሕያው ሆኖ የሚገለጥባት ዕለት ናት።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደምናነበው የጥንት ክርስትያኖች እምነታቸው ከትንሳኤ ምሥጢር ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በሰንበት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለአምልኮ ይሰባሰቡ ነበር (ሐዋ 20፡7)። ይህም መሰባሰባቸው ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ (ሐዋ 20፡7) እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። ቅዱስ ዮሐንስ ራዕይ ስለተቀበለባት ዕለት ሲናገር “ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” (ራዕ 1፡10) እያለ ሰንበተ ክርስትያን በመንፈስ የምንሆንበት የአምልኮ፣ የመገለጥ፣ የራዕይ ዕለት[2] መሆኑን ያስገነዝበናል። በዚህች ዕለት ክርስትያኖች ከእግዚአብሔር ቃል ገበታ በጋራ ይቋደሳሉና ዮሐንስ በራዕዩ “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው” ይላል። በሰንበተ ክርስትያን የሚነበብልን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እና የዕለቱ ስብከት ዋነኛው ቁም ነገር ልባችንን ለቅዱስ ቊርባን ገበታ ማሰናዳት ነው (ሉቃ 24፡32)። ጌታ ቅዱስ ሥጋውን ለሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች ከመስጠቱ አስቀድሞ በቃሉ ልባቸውን እንዳዘጋጀ መመልከት እንችላለን። ይህንን ምሥጢር የተረዱ ክርስትያኖች ክርስትና በሥደት ላይ በነበረባቸው ዘመናት እንኳን በግብረ ሰማዕታት (Acts oft he Martyrs) ተጽፎ እንደምናነበው ሳቱርኒኑስ እና በጌታ ወንድሞቹ (Saturninus and his companions) ስለ ሰንበተ ክርስትያን እና ስለ ቅዱስ ቊርባን በንጉሥ ዲዮቅሌጥያን (Diocletian) ዘመን በ350 ዓ.ም. ሰማዕትነትን ተቀብለዋል።ንጉሡ ስለ እምነታቸው በጠየቃቸው ጊዜ የመለሱት መልስ ልባቸው በጌታ ምን ያህል እንደጸና የሚያመላክት ነው፤ “መለኮታዊ ምስጢራትን ማክበር መተው አንችልም፤ ክርስቲያን ያለ ቅዱስ ቊርባን መኖር አይችልም። ቅዱስ ቊርባን ለክርስትያኖች፣ ክርስትያኖችም ለቅዱስ ቊርባን መፈጠራቸውን አታውቅምን? በቤተ ክርስትያን ከወንድሞች ጋር የጌታን ምሥጢር አክብሬያለሁ፤  በልቤ የተጻፈው መለኮታዊ ቃል ከእኔ ጋር አለ። ቅዱስ ቊርባን የክርስቲያኖች ተስፋና መዳኛ ነው።” በማለት ሰማዕትነታቸውን ከምሥክርነት ጋር ተቀብለዋል።

ስለዚህ ሰንበተ ክርስትያን የደም ዋጋ የተከፈለበት የክርስትያኖች ቊርባናዊ ኅብረት የሚፈጸምበት ዕለት በመሆኑ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ሕገ ቀኖና ስለተቀደሰ ጊዜ በሚደነግገው አምስተኛው መጽሐፍ፣ በክፍል ሦስት፣ በአንቀጽ ሁለት፣ በቁጥር 1246 ፣ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር ስለ ሰንበተ ክርስትያን ሲናገር “በሐዋርያት ትውፊት መሰረት የፋሲካ ምሥጢር የሚከበርበት እሑድ በኲሏዊቷ ቤተክርስቲያን ከሁሉ በፊት እንዲከበር ክርስትያኖች ሁሉ ግዴታ አለባቸው። ከሰንበት ክብር ቀጥሎ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ የጥምቀት በዓል፣ ትንሳኤው፣ የዕርገቱ፣ የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚከበርባት ዕለት እና የጌታችን ዐበይት በዓላት ባጠቃላይ፣ የወላዲተ አምላክ ቅድስት ማርያም ዐቢይ በዓላት፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ፣ የሐዋርያት እና ቅዱሳን ዐቢይ በዓላት”[3][i] እንደ ክርስትያናዊ ግዴታ እንዲከበሩ ያዛል። ስለዚህ በእነዚህ ቀናት ከመሥዋዕተ ቅዳሴ መጉደል የተፈቀደ አይደለም!

ከዚህ ሰንበት ስያሜ ተመልሰን ወደ ቅዳሴው ንባባት ስንመለከት ኢየሱስ በዛሬው የወንጌል ክፍል (ማቴ 6፡16-24) ሶስቱን የጾም ቁም ነገሮች ማለትም ጾም፣ ጸሎት እና ምጽዋትን ጠቅለል አድርጎ ያቀርብልናል። በመጀመርያ ስለ ምጽዋት ያስተምራል፤ በዚህም አንድ ክርስትያን ምጽዋት ሲያደርግ ሊኖረው ስለሚገባ ትህትና እና ጭምት የሆነ ግብረገብ ካስረዳ በኋላ (ማቴ 6፡1-3) ሐሳቡን ወደ ጸሎት በመመለስ የክርስትያናዊ ጸሎት ምን መምሰል እና እንዴት ባለ የእምነት ትህትና ሊከናወን እንደሚገባው ያስረዳል (ማቴ 6፡5-8)። በመቀጠልም የጸሎት ሁሉ ትምህርት ቤት የሆነውን “አባታችን ሆይ” (ማቴ 6፡9-13) የሚለውን ጸሎት ያስተምራል፤ ከዚህ ታላቅ ጸሎት በኋላ የዛሬው ወንጌል አስኳል የሆነው ትምህርት ይከተላል። ኢየሱስ ስለ ጾም አተገባበር እና በጾም ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው ክርስትያናዊ ግብረገብ በአንክሮ እያስተማረ (ማቴ 16-18) እነዚህን ሦስት የጾም ገጽታዎች ካሳየን በኋላ፣ የእነዚህን ነገሮች ሁሉ ግብ ወደሆነው ቁም ነገር እያመለከተን በምድር የምንፈጽመው ተግባር በሙሉ በሰማያት ባለው መዝገብ በክብር የሚሰበሰብ የጸጋ ፍሬ እንጂ በዚህ በምድር ለታይታ የሚደረግ መሆን እንደሌለበት በግልጽ ያስተምራል።

ጌታ ስለ ጸሎት ካስተማረ በኋላ በቀጥታ ስለ ጾም ማስተማር መጀመሩ ጸሎት በጾም መደገፍ እንዳለበት ያሳየናል። ከጾም ጋር የሚደረግ ጸሎት ሰማያትን ይከፍታል! በመጽሐፍ ቅዱስ ታላላቅ ነገሮች በተከናወኑበት ሥፍራ ሁሉ ጾም-ጸሎት እንደነበር እናነባለን። ጌታ ሐዋርያዊ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በጾም-ጸሎት እንደነበረ ወንጌል ይመሰክራል። ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሰን የነቢዩ ዳንኤልን ሕይወት ብንመለከት ዳን 9፡3 ላይ እንደምናነበው፤ ዳንኤል ስለራሱ እና ስለ ሕዝቡ በጾም እና በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንደነበረ መመልከት እንችላለን። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነቢዩ ኢዩኤል “ጾምን ቀድሱ” (ኢዩ 2፡15) እያለ ከጾም ጋር የቅድስና ሥራ መኖሩን ያመላክታል። ነገር ግን ይህ የጾም-ጸሎት ኅብረት ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ውኃ ልክ ላይ መመስረት ይኖርበታል፤ ይህም ማለት ስንጾም እና ስንጸልይ ግንኙነታችን በሰማያት ካለው አባታችን ጋር እንጂ ምድራዊ ከሆነው የሰዎች የአድናቆት መዝገብ ጋር አይደለም ማለት ነው።

 መጽሐፈ ሲራክ የሰውን ልጅ ፍጥረታዊ ማንነት በሚመለከት ሲናገር “ሰው በመልኩ ይታወቃልና ጠቢብም በገጹ ይታወቃል” (ሲራ 19፡29) እያለ የሰው ልጅ ፊት የነፍሱን ሁሉ ነጸብራቅ የሚያሳይበት መስኮት በመሆኑ በጥበብ ሊያዝ እንደሚገባው ያስተምራል። ስለዚህ ጌታ “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ” (ማቴ 6፡16) እያለ ሊኖረን ስለሚገባው አቋም ያስተምረናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበኩሉ የጌታን ትምህርት ተከተሎ ለቆሮንጦስ ክርስትያኖች ሲያስተምር “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል።” (2ኛ ቆሮ 7፡10) ይላል። በመሆኑም ጌታ ከእንደዚ አይነቱ ዓለማዊ ኀዘን እንቆጠብ ዘንድ በዛሬው ወንጌል “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ” (ማቴ 6፡16) እያለ በጾም ውስጥ እንዴት ባለ መንፈሳዊ ጥንቃቄ መመላለስ እንዳለብን ያሳስበናል።

የጾም-ጸሎታችን ሁሉ ዋጋ ሌላ ምድራዊ ነገር ሳይሆን ለአብርሐም የተገባለት ቃልኪዳን ያውም እግዚአብሔር ራሱ ነው (ዘፍ 15፡1)። ስለዚህ በቅዳሴያችን ሁለተኛ ንባብ ላይ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ” (1ኛ ጴጥ 1፡13) እያለ ተስፋችን እና ዋጋችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ያስገነዝበናል። ከዚህም በበለጠ ትኩረታችን ሁሉ እንዴት እና በምን ላይ ሊሆን እንደሚገባ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲያስተምር ከተዋጀንበት ምሥጢር ጋር በማያያዝ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” (1ኛ ጴጥ 1፡18-19) እያለ ያበረታታናል። የተገዛንበት ዋጋችን ጠብታው ዓለምን ሁሉ የሚያድነው የጌታ ንጹህ ደም በመሆኑ ከዚያ ባነሰ ነገር ባርያ ሆኖ መገዛት ዋጋችንን አለማወቅ መሆኑን እና ለተዋጀንበት ክብርም እንደማይመጥን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ይናገራል። በመሆኑም በምድር ወይም በሰማያት ያለ ከኢየሱስ ደም ዋጋ እና ክብር ጋር የሚነጻጸር አንዳች ነገር የለምና ሕይወታችን ዛሬ የተያዘበትን ቀንበር ሁሉ በደሙ ኃይል ሰብረን በእግዚአብሔር ልጆች ነጻነት እንድንመላለስ ተጠርተናል። ለዚህም ምክኒያቱን ሲያቀርብ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” (1ኛ ጴጥ 1፡23) እያለ ዳግመኛ የተወለድንበትን ክብር ያስታውሰናል።

ለዚህ ክብር የተጠራ ሰው ሊኖረው ስለሚገባ ገጽታ መጽሐፈ መክብብ “ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ” (መክ 9፡8) እያለ ስለ መንፈሳዊ ሕይወት ግብረግብ ያስተምራል። ጾም በመንፈሳዊ ጥንቃቄ (discretion) መኖርንና ማደግን የምንማርበት እና የሕይወታችንን መንገድ ከጌታ ጋር እንዲህ ባለው ጥንቃቄ የምናስተካክልበት ጉዞ ነው። በዚህም ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ (መዝ 7፡9) ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል (ሮሜ 2፡6)። ስለዚህ ዋጋችንን ከሰው ሳይሆን የነገር ሁሉ ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንጠብቅ ዘንድ፣ ጌታ በዛሬው ወንጌል “በሥውር የምታደርገውን የሚያይ አምላክህ በግልጽ ዋጋህን ይከፍልሃል” (ማቴ 6፡6) እያለ ጾም-ጸሎታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንዳለው ይናገራል። ነገር ግን ይህ ዋጋ በምድር የምንቀበለው ምድራዊ በረከት ብቻ ሳይሆን በሰማያት ባለው መዝገብ የምንሰበስበው ኃብት መሆኑን ጌታ በዛሬው ወንጌል በግልጽ ያስተምረናል።

ጌታ “በዚህ ምድር ለእናንተ መዝገብ አትብስቡ” (ማቴ 6፡19) እያለ ሲያስተምር የትምህርቱ ትኩረት ከከንቱ ወዳሴ እና ከስግብግብነት እንድንቆጠብ የሚያመለክት ነው። በዚህ የጌታ ትምህርት ውስጥ ከሁለት ታላላቅ ኃጢአቶች እንድንቆጠብ ጥሪ ቀርቦልናል፤ እነርሱም ከንቱ ወዳሴን መፈለግ እና ስግብግብ ዐይን ናቸው፤ ከንቱ ወዳሴን መፈለግ ትዕቢትን ይወልዳል፤ ይህም የመንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ ጤናማነት ምሥክር የሆነው የትህትና ጠላት ነው። ስግብግብ ዐይን ንፉግነትን እና መጠንን አለማወቅን ይወልዳል። እነዚህም የመንፈሳዊ ሕይወት ጠላቶች ናቸውና ጾም-ጸሎታችንን ሁሉ የዜሮ ብዜት ያደርጉብናል። ምድራዊ ነገሮች ለምድር እንጂ ለሰማይ የማይጠቅሙ ከመሆናቸውም ባሻገር በምድርም ቢሆን ዘላቂነት እንደሌላቸው ጌታ ሲያስተምር “ብል፣ ዝገት እና ሌብነት” እንደሚያጠፋቸው ይናገራል።

ብል፣ ዝገት እና ሌብነት የነፍሳችንን መንፈሳዊ ጤንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች ናቸው። ነፍስ ከሚደርስባት መንፈሳዊ ጥቃት ራሷን መከላከል የምትችልበትን እና የዲያብሎስን የሽንገላ ቃላት የምታፈርስበትን “የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ”  (ኤፌ 6፡11) በሚገባ ስላለበሰች የነፍስ መለኮታዊ ኃይላት እና መንፈሳዊ ጽዋዎች በብል ተበልተው ያልቃሉ። ደግሞም ነፍስ በዚህ አይነት የብዝበዛ ቀንበር በተጠመደችበት ሁኔታ ሁሉ መንፈሳዊ ሥጦታዎቿ እየዛጉ፣ በመንፈሳዊ መክሊቶቿ ከማትረፍ እየሰነፈች ትሄዳለች። ይህም ቀስ በቀስ ሌባው ሙሉ በሙሉ እንዲዘርፋት እና ያለከልካይ እንዲያገኛት ያደርጋታል። በቅዳሴ የቃለ እግዚአብሔር ገበታ የተነበበልን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የላካት የመጀመርያይቱ መልእክቱ “ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና” (1ተሰ 4፡7) እያለ የተጠራንበት ክብር እና ነፍሳችን ሊኖራት የሚገባው ራዕይ ቅድሰና መሆኑን ያስገነዝበናል። ቅድስና የክርስትና ዐቢይ ማንነት እንጂ የምርጫ ጉዳይ ወይም ደግሞ ለጥቂቶች የተሰጠ የቤት ሥራ አይደለምና ጌታ ነፍሳችሁን በሰማያት ባለው መዝገብ ጠብቁ እያለ ለእያንዳንዳችን ያስተምራል።

ነፍሱን በሰማያት ባለው መዝገብ በጤንነት የሚጠብቅ ሰው የዳዊት መዝሙር ተውሶ “ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት። ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ” (መዝ 95፡5-6) እያለ በሁሉ ነገሩ ላይ እግዚአብሔርን ይሾማል። ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተጽፎ እንደምናገኘው ሰው እግዚአብሔርን በሁሉ ነገሩ ሲሾም የእግዚአብሔር የሆነውን ክብር ለእግዚአብሔር መስጠት ያውቅበታል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ የሮም የጦር አለቃ የነበረው ቆርኔሊዮስ  በእግሩ ሥር ተደፍቶ ሰገደለት ነገር ግን ጴጥሮስ በትህትና ተሞልቶ “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ” (ሐዋ 10፡26) እያለ የእግዚአብሔርን ክብር ለእግዚአብሔር ሲሰጥ እንመለከተዋለን። ይህ የዐቢይ ጾም ጊዜ በሕይወታችን ሁሉ በሁሉ ነገር ለእግዚአብሔር ተለይተን እንድንቀደስ እንዲሁም እግዚአብሔርን በሁሉ ነገር ላይ እንድንሾም የምንችልበትን እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር የምናተርፍበት የጸጋ ጊዜ ይሁንልን!

ሴሞ

 

[1] Ratzinger, Joseph, The Spirit oft the Liturgy, Ignatius Press, San Franscisco, (2000), 92-111 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ከገጽ 96

[2] Benedikt XVI, Die Offenbarung des Johannes, St. Bonno, Leipzig, ገጽ 13-26

[3] https://www.vatican.va/archive/cod-iuris-canonici/eng/documents/cic_lib4-cann1244-1253_en.html

 

[i] ይህ የሕገ ቀኖና ትርጉም የጽሑፉ አዘጋጅ ለዚሁ ጽሁፍ እንዲስማማ አድርጎ በግርጌ ማስታወሻው ላይ እንደተጠቀሰው ከቅድስት መንበር ድረ-ገጽ የተረጎመው መሆኑ እንዲታወቅ ይሁን!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት