እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘምኲራብ የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሰንበት

ዘምኲራብ

 

ንባባት፡- ቆላ 2፡16-23፣ ያዕ 2፡14-26፣ ሐዋ 10፡1-8

መዝሙር፡- ቦአ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሃረ ቃለ ሃይማኖት...

ወንጌል፡- ዮሐ 2፡12-25

ስብከት፡- “እስመ ቅንአተ ቤተከ በልዓኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ

የቤትህ ቅናት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና ነፍሴን በጾም ቀጣኋት”

 

Jesus cleanses the Templeየዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሰንበት “ዘምኲራብ” ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ሰንበት ጌታ በአይሁድ ቤተ መቅደስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን ለሚገባው ዓላማ እንዳጸዳው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ይናገራል። እያንዳንዱ አይሁዳዊ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ለእግዚአብሔር ስለቱን፣ ንስሐውን እና የምሥጋናውን ቊርባን እንዲያቀርብ የኦሪት ሕግ ያዛል (ዘጸ 23፡14-17)። እነዚህም 1ኛ)፡- በዓላት የአይሁድ ፋሲካ (ዘጸ 12፡27)፡- አይሁድ የጠቦቱን ደም በበሮቻቸው  መቃን ላይ ቀብተው ከሞት የተረፉበትን የእግዚአብሔር አዳኝነት የሚያስቡበት በዓል፤ 2ኛ)፡- የስንዴ በዓል ወይም የአይሁድ በዓለ አምሳ (ዘጸ 34) ይህም እሥራኤል የምድርን በረከት የሚሰበስብበት የስንዴ መሥዋዕት የሚቀርብበት በዓል ነው። 3ኛ)፡-  የመክተቻ፣ የፍሬ በኩራት ወይም የዳስ በዓል (ዘጸ 34፡22) ይህም አይሁዳውያን ከቤታቸው ውጪ ለዚሁ በዓል ተብሎ በሚዘጋጅ ዳስ ውስጥ ለሰባት ቀናት ያህል የሚኖሩበት እና የተመረጡ ምግቦችን የሚመገቡበት፣ እግዚአብሔር አምላክ ምድረ-በዳ ያደረገላቸውን መጋቢነት እና አባታዊ ጥበቃ የሚዘክሩበት በዓል ነው። አይሁዳዊ የሆነ ተባዕት ሁሉ በዚህ የኦሪት ሕግ መሰረት በእነዚህ በዓላት ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ግዴታ አለበት (ዘጸ 13፡7)።

በዚህም አግባብ ጌታ እንደማንኛውም አይሁዳዊ የአይሁድን ፋሲካ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ በቤተ መቅደስ እንደገባ ቅዱስ ዮሐንስ በዛሬ ወንጌል “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ” (ዮሐ 2፡13) እያለ ይተርክልናል። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ትልቅ ቁም ነገር ኢየሱስ ከቃሉ አስቀድሞ በሕይወቱ ለመስበክ የሚፈልግ መምህር በመሆኑ ትህትናን እና ፍጹምነትን ሊያስተምር ከኦሪት ሕግ በታች ሆኖ ህግን ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን ነው። እርሱ ሕግ እና ነብያትን ሊፈጽም መምጣቱን በተግባር እየመሰከረ (ማቴ 5፡7)፣ ለሕግም ሁሉ ታዛዥ በመሆን እንደ አንድ አይሁዳዊ ሲመላለስ እንመለከተዋለን።  የእግዚአብሔር ልጅ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ እና ማሰርያ ሆኖ ሳለ ሕግን ለመፈጸም ታዛዥ ከሆነ እና ታላላቆቹን የእምነት ምሥጢር በዓላት በታላቅ መንፈሳዊነት ለማክበር በቤተ መቅደስ ከዋለ እኛ ደግሞ እያንዳንዳችን የቆምንበትን ስፍራ እንድንፈትሽ የኢየሱስ ትህትና ግድ ይለናል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ነበር” (ዮሐ 2፡14) እያለ ይናገራል፤ በዚህም ቅዱስ ዮሐንስ “የአይሁድ ፋሲካ” እያለ መናገሩ ይህ በዓል ስለ አይሁድ እንጂ ስለ ክርስቶስ እንዳልሆነ ያመለክተናል። አይሁድ ይህንን በዓል ለራሳቸው በመጨነቅ እንጂ ስለ እግዚአብሔር ክብር አያደርጉትም ነበርና ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ስም የራሳቸውን ነገር ለሚያመልኩ ሰዎች “የአይሁድ ፋሲካ” እያለ ይናገራል።  እንዲህ አይነቱን በእግዚአብሔር ስም ለራስ ክብርና ዝና ለመቀበል የሚፈጸም ጾም፣ ጸሎት እና ምጽዋት ሁሉ ከንቱ መሆኑን የዛሬው ወንጌል ይናገራል፤ አይሁድ እንዲህ ያለው የእግዚአብሔርን ነገር ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላለል፣ ቤተ መቅደስ ሊሰሩ በሰበሰቡት ወርቅ ጥጃ ሰርተው ማምለክ የለመዱ በመሆናቸው እግዚአብሔር አምላክ “መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፣ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ” (ኢሳ 1፡14) እያለ በነቢዩ ኢሳያስ መጽሐፍ ይናገራል። ስንጾም፣ ስጸልይ ወይም በዓል ስናደርግ ለሰው እንደሚደረግ ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደሚደረግ በእውነት እና በመንፈስ ማድረግ ካልቻልን ጌታ በመጨረሻው ቀን “በጾማችሁ እና ባለቀሳችሁ ጊዜ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝን? በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ ለራሳችሁ የምትበሉና የምትጠጡ አይደላችሁምን?” (ዘካ 7፡5-6) ማለቱ የማይቀር ነው።

በሌላ በኩል ስንመለከተው ደግሞ የዛሬው ወንጌል የእሥራኤልን ታሪክ ደግመን እንድናስተውለው ይጋብዘናል፤ አይሁድ የጠቦቱን ሥጋ በልተው፣ ደሙን በበሮቻቸው መቃኖች ላይ ቀብተው መዳናቸውን ይዘክራሉ፤ ይህም ሊመጣ ላለው ምሳሌ እና ጥላ ነበር እንጂ በራሱ ፍጻሜ እና ምልዓት አልነበረም። ስለዚህ የአይሁድ ፋሲካ ምሳሌ ነበር እንጂ ዘላለማዊ መሻገር አልነበርም፤ ነገር ግን ክርስትያኖች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምናከብረው ፋሲካ የነገር ሁሉ ፍጻሜ እና ምልአት ያለበት የዘላለዊ ሕይወት ሥጦታ የተፈጸመበት አዲስ ፋሲካ ነው። ይህ አዲስ ፋሲካ ጊዜ ቆጥረን በየዓመቱ የምንዘክረው የጌታ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ትርክት ሳይሆን ፋሲካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው! ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና” (1ቆሮ 5፡7) እያለ የፋሲካችንን ምንነት ያስረዳናል።

በመሆኑም ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ከመውጣቱ አስቀድሞ ወደ ቅፍርናሆም መውረዱ የትንሳኤውን ምሥጢር በውስጡ የያዘ ቁም ነገር እንዳለው ለመረዳት ያስችላል። ወደ ቅፍርናሆም ወርዶ የተማረኩትን ነጻ ካላወጣ፣ ሞት እና መውጊያውን ካልሰበረ ወደ ኢየሩሳሌም ለአምልኮ የሚመጣ ማንም አልነበረምና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው” (ኤፌ 4፡10) እያለ የትንሳኤውን ምሥጢር ይናገረናል። በወንጌላት ውስጥ የጌታ ተግባራት በተገለጡባቸው ሥፍራዎች ሐዋርያቱ በዚያ መኖራቸውን እናነባለን፤ ነገር ግን በዚህ በዮሐንስ ወንጌል ትረካ ውስጥ ሐዋርያቱ አልተጠቀሱም፤ በዚህ ክፍል ሐዋርያቱ ከጌታ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እንደወጡ አናነብም። የሐዋርያቱ ወደ ላይ መውጣት በጌታ ትንሳኤ በኩል የሚፈጸም በመሆኑ እነርሱ በመጠበቂያቸው ትንሳኤውን ተስፋ በማድረግ መጽናት ነበረባቸው፤ ዮሐንስ በወንጌሉ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13) እያለ በኢየሱስ በኩል ካልሆነ በስተቀር ወደ ሰማይ ሊደርስ የሚችል ማንም አለመኖሩን ያስገነዝበናል።

ጌታ በቤተ መቅደስ ገብቶ በለዋጮች እና በሻጮች መካከል በቆመ ጊዜ ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሰን የኢሳያስን ትንቢት እናስታውሳለን። ኢሳያስ በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ሁኔታ ሲናገር “እነርሱ የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉ ወደ መንገዳቸው፤ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል” (ኢሳ 56፡11) ይላል። ሰይጣን የሰው ልጆችን አስተሳሰብ፣ ማስተዋል እና ጨዋነት በመቆጣጠር በእግዚአብሔር ሥፍራ ሰው እራሱ ለራሱ ፍላጎት ባርያ ሆኖ የራሱን መልክ እያመለከ እንዲኖር አድርጎ ይበዘብዘዋል። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የተገናኘው ከተራ ነጋዴዎች ጋር አልነበረም፤ ይልቁንም የግሪኩ የአዲስ ኪዳን ቅጂ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይደረግ የነበረውን ተግባር ሲገልጥ የሚጠቀመው “ጠረጴዛ” የሚለው ቃል በዘመናዊ ቋንቋ ባንክ ብለን የምንጠራው ነው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እጅጉን ሥር ሰድዶ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሽባ ካደረገው የኢኮኖሚ ርዮተ ዓለም ጋር ሲፋጠጥ እንመለከተዋለን።

በኦሪት ሕግ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለእግዚአብሔር የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ ይገባ ስለነበር የብሉይ ኪዳን ካህናት ይህንኑ ተግባር ይፈጽሙ ዘንድ ሕዝቡን በእጅጉ ያስጠነቅቁ ነበር። ነገር ግን ካህናቱ ለእግዚአብሔር ክብር ግድ ብሏቸው ሳይሆን ነገሩን የገቢ ምንጭ አድርገው ወስደውት ስለነበር ነው። ጀርመናዊው ፈላስፋ ኒቼ (Nitsche) በክርስትያኖች መካከል እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ተግባር ከተመለከተ በኋላ “እግዚአብሔር በመካከላችን ሞቷል፤ ገዳዮቹም እኔ እና እናንተ እያንዳንዳችሁ ናችሁ” እያለ ይናገራል። በተመሳሳይ መልኩ የብሉይ ኪዳን ካህናት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ የሚመጡት ሰዎች ከዚያው ከቤተ መቅደሱ እንዲገዙ በጎችንና ርግቦችን ይሸጡ ነበር። ነገር ግን መሥዋዕት ለማቅረብ በጎችን ወይም ርግቦችን ለመግዛት ገንዘብ የሌለው አይሁዳዊ ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ እንዴት ይስተናገዳል? ይህ ጥያቄ ለካህናቱ አዲስ የሥራ ፈጠራ እና የገቢ ምንጭ ሆኖላቸው ነበርና ካህናቱ በቤተ መቅደስ ውስጥ የባንክ ሥርዐት ዘርግተው፣ የምንዛሬ፣ የብድር ወ.ዘ.ተ. አገልግሎት መስጠት መደበኛ ተግባራቸው አድርገውት በአደራ የተቀበሉትን መለኮታዊ ምሥጢርን የማስተዳደር ሥጦታ ለተለየ ዓላማ ሲጠቀሙበት መመልከት እንችላለን። ዛሬም ቢሆን በቤተ ክርስትያን የተቀደሱ ምሥጢራትን እና ለአምልኮ ተለይተው የተባረኩ እና በላያቸው ላይ የእግዚአብሔር ስም የተጠራባቸውን የቤተ ክርስትያን ነዋየ ቅድሳት ለመሸጥ የሚደረጉ መከራዎች ሰይጣን አገልጋዮችን በዘመናት እና በትውልድ መካከል እንደሚያጠምዳቸው ማሳያ ነው!

ጌታ ቤተ መቅደሱን ለያነጻ ወድዶ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” (ዮሐ 2፡16) እያለ ይናገራል። ነገር ኝ ጌታ ስለ ቤተ መቅደሱ ነጻነት ሲናገር የምናገረው ስለምንድነው? የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እኛ እያንዳንዳችን ነን። በጥምቀት አማካይነት እኛ ሁላችን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰርተናልና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “እናንተ ደግሞ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ” (1ጴጥ 2፡5) እያለ ጥሪያችንን ያስታውሰናል። ጌታ ይህንን ቤተ መቅደስ ዳግም ንጹህ አድርጎ ለመቀደስ እና በጥምቀት የተቀበልነውን ነጩን የክብር ልብስ በደሙ ለማጠብ ዛሬም ወደዚህ ቤተ መቅደስ ይመጣል። የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከእኛ ሩቅ ያለ ነገር አይደለም፤ ይልቁንም የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እኛ ራሳችን እያንዳንዳችን ነን። ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዳንረሳው እያሳሰበን “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው ያውም እናንተ ናችሁ” (1ኛ ቆሮ 3፡17) እያለ ያረጋግጥልናል። የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖ የመቀደሱ ክበር ከተፈጠረበት የእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ጋር የሚስማማ ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ ቤተ መቅደስነቱን ባላከበረበት ሁኔታ በዚያ ሊሆን የማይገባው ነገር ስፍራ ይዞ መገኘቱ የማይቀር ነገር ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ጌታ “በሬዎችን፣ በጎችን እና ርግቦችን” ከቤተ መቅደሱ ገበያ እንዳስወጣቸው ያስነብበናል። እነዚህ ሦስት እንስሳት የነፍሳችንን ሦስት መልኮች የሚመስሉ ናቸው፤ በሬ ምድርን ለማልማት የሚጠቅም እና ቀንበር የሚሸከም እንሰሳ እንደመሆኑ መጠን ወደ መሬት ብቻ የሚመለከት፣ ባሕርያዊ ከሆነው ነገር በላይ አሻግሮ ለመመልከት አንገቱን ቀና ማድረግ የማይችል እንስሳ ነው። ይህም የነፍስን በምድራዊ ነገሮች ብቻ መጠመድ እና መበዝበዝ ያመለክታል። በዚህም ነፍስ ከዕለት እንጀራ በላይ ማሰብ እንዳትችል ተደርጋ የታሰረችበትን ሰንሰለት ለመበጠስ እና ወደ አምላኳ ቀና እንዳትል ያጎበጣትን ቀንበር ለመስበር ኢየሱስ ዛሬም በደጅ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በሁለተኛ ደረጃ የሚያሳየን በጎችን ነው። በጎች በመንጋ የሚሄዱ፣ ስለሚሄዱበት ቦታ መሰረታዊ ግምት የሌላቸውና በደመ ነፍስ የሚመሩ በመሆናቸው የነፍስ መንፈሳዊ አላዋቂነት ያሳያሉ። ነፍስ ከእግዚአብሔር መንገድ በጠፋችበት የሕይወቷ ክፍል ሁሉ መቅበዝበዝ፣ አቅጣጫን አለማወቅ እና በራዕይ አለመመራት ገንዘቧ ይሆናል። ስለዚህ የራሷ ድካም እረኛዋ ስለሚሆን ድካሟ በሚያሰማራት የክፉዎች ምክር መሄድ፣ በኃጢአተኞች መንገድ መቆም እና በፌዘኞች ወንበር መቀመጥ ፍጻሜዋ ይሆናል። ጌታ ነፍስን እንዲህ ካለው ቁልቁለት ሊታደጋት በደጅ ቆሞ እያንኳኳ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣል” (ዮሐ 10፡11) እያለ ነፍስ በእርሱ እንድትታመን በፍቅር ቃል ይጠራታል። ሦስተኛው ክፍል በቤተ መቅደስ ውስጥ ርግቦች እንደነበሩ ያሳየናል። ይህም የነፍስን ባለችበት ረግቶ መቀመጥ አለመቻል፣ በምንም ነገር ደስተኛ ለመሆን መቸገር፣ ከአንድ ነገር ወደ ሌላ ነገር እየዞረች መባከንና መድከሟን የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ ለነፍስ ዕረፍትን ሊሰጣት “እናንተ ደካሞች ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ! እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ 11፡28) እያለ ያጽናናታል።

ዐቢይ ጾም ከታሰርንበት ቀንበር በላይ ከፍ ብለን ወደ እግዚአብሔር የምንመለከትበት፣ ጌታ ኢየሱስ በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው ባስገኘልን አርነት በራዕይ የምንጓዝበት እና በእርሱ እረፍት አግኝተን ለሌሎች ወደ እረፍት ስፍራ መድረስ ምክኒያት የምንሆንበት ጸጋ በነፍስ ላይ የሚፈስበት ጉዞ ነው። ዐቢይ ጾም ነፍስ ከእነዚህ ድካሞች የምታርፍበት እና ጉልምስናዋ እንደ ንስር የሚታደስበት የጸጋ ጊዜዋ ነው። በዚህ የዐቢይ ጾም ጉዞ ኢየሱስ ስለ ጾም ጸሎታችን አቅጣጫ እንደገና እንደናሰብ እና መንገዳችንን ከእርሱ ጋር እንድናስተካክል በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንዳደረገው እንዲሁ ደግሞ በእያንዳንዳቸን ሕይወት ያደርግ ዘንድ ጌታ በመካከላችን ነው። ይህ የዐቢይ ጾም ጊዜ የተከበርንበት እና ለእርሱ ተለይተን የተቀደስንበት ቤተ መቅደስነታችን ዳግም ክብሩን ተጎናጽፎ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የምሥጋና መሥዋዕት የምናቀርበበት ተሐድሶ የምናገኝበት የጸጋ ወቅት ይሁንልን! አሜን!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት