ደብረ ዘይት

FB IMG 1648372532212የዐቢይ ጾም ፭ኛ ሰንበት ደብረ ዘይት

ንባባት፡- 1 ተሰ 4፡13-18፣ 2ጴጥ 3፡7-14፣ ሐሥ 24፡1-21

ምስባክ፡- “እግዚአብሔርሰ ግሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፥ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፤ አምላካችን በግልጽ ይመጣል፣ ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፤ በዙርያውም ብዙ ዐውሎ አለ” (መዝ 50፡3)

መዝሙር፡- እንዘ ይነብር እግዚእነ...

ወንጌል፡- ማቴ 24፡1-35

የዐቢይ ጾም ፭ኛ ሰንበት “ደብረ ዘይት” እየተባለ ይጠራል። በዚህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ያደረገውን ስብከት እንድናስተነትን ቤተክርስትያን ትጋብዛለች። የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ ተራራ ነው። ይህ ተራራ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አምባ ክፍ ያለ በመሆኑ የጌታ በዚህ ተራራ ላይ መገለጥ የአምላክነቱን ክብር እና መለኮታዊ ግርማውን የሚያሳይ ድርጊት ነው።  

የደብረ ዘይት ተራራ በብሉይ ኪዳን ዘመን በተለያዩ አጋጣሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፤ በተለይም በ2ኛ ሳሙ 15፡30 ላይ ተጠቅሶ እንደምናገኘው ንጉሥ ዳዊት በልጁ በአቤሴሎም ክህደት ከተፈጸመበት በኋላ በዕንባ ወደዚህ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጥቶ የአቤሴሎም ጦር እንዳይደርስበት በዚያ እንደመሸገ እናነባለን። በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ ይህ የደብረ ዘይት ተራራ ኢየሱስ “ከተማይቱን አይቶ አለቀሰባት” (ሉቃስ 19፡37–41) በተባለበት ስፍራ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። ከዚህ በመነሳት በዛሬው ወንጌል እንደምናነበው (ማቴዎስ 24፡ 1-35) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ እንደሚፈርስ ከተናገረ በኋላ ወደዚህ ተራራ ወጥቶ የማትታዘዘው ከተማ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ከዳግም ምጽአቱ ጋር አያይዞ ያስተምራል። ከዚህ ጎን ለጎን ኢየሱስ ከመስቀሉ በፊት በነበረው ምሽት ለጸሎት በደብረ ዘይት ተራራ ስር ወደሚገኘው ወደ ጌቴሴማኒ እንደሄደ ወንጌል ይመሰክራል። ጌቴሴማኒ በኢየሩሳሌም ትይዩ በደብረ ዘይት ተራራ ምዕራባዊ ግርጌ አጠገብ የሚገኝ የአትክልት ሥፍራ ነው (ማቴዎስ 26፡30፣ 36)።

እንዲሁም ደግሞ በዘመን መጨረሻ እግዚአብሔር አምላክ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እንደሚገለጥ ነቢዩ ዘካርያስ ይናገራል፡- “በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ። ደብረ ዘይትም ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ለሁለት ይከፈላል፤ በመካከሉ ትልቅ ሸለቆ ያደርጋል። የተራራው እኵሌታ ወደ ሰሜን ግማሹም ወደ ደቡብ ይሄዳል። …እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ንጉሥ ይሆናል። በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ይሆናል” (ዘካርያስ 14:​4, 5, 9)።

ቅኝታችንን ከደብረ ዘይት ተራራ አንድምታ እና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ መልሰን ስለዛሬው ሰንበት ስናሰብ፣ ይህ ደብረ ዘይት እየተባለ የሚጠራው ሰንበት እኩለ ጾም እየተባለ እንደሚጠራ ይታወቃል፤ ይህም ጾማችንን እንዳጋመስን፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ተራራው ጫፍ እንደወጣን እና ከእርሱ ጋር ወደ መስቀሉ ምሥጢር እንደቀረብን የሚያስታውሰን ሰንበት ነው። ይህ ሰንበት የደቀ መዛሙርቱ የጫጉላ ጊዜ አልቆ እውነቱን የሚሰሙበት፣ ክርስትና የእሾህ አክሊል ያለበት የመስቀል መንገድ መሆኑን በግልጽ የሚያውቁበት ሰንበት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚወዱት እና ከእርሱም ጋር እስከመጨረሻው ለሚጸኑት መስቀሉን የሚያካፍልበት፤ እንደ ቀሬናዊው ስምኦን የጌታን መስቀል የምንካፈልበት እና በእሾህ አክሊል የምንሞሸርበት ሰንበት ነው። ከክብር  በፊት መስቀል ተሸከሞ መጓዝ፣ ከዘውድ በፊት የእሾህ አክሊል፣ ከጭብጨባ በፊት ጅራፍ፣ ከድል ዘንባባ በፊት ምራቅ፣ በከበረ ስፍራ ከመገኘት በፊት እንደ ባርያ ዕርቃንን በመስቀል ላይ መዋል፣ ከውድ የወይን ጠጅ በፊት ሐሞትና ኾምጣጤ፣ ከሆሳዕና ዕልልታ በላይ የሚጮህና የሚሰማ የግፍ ፍርድ መኖሩን ይናገራል።  የደብረ ዘይት ሰንበት ክርስትና ቀበቶን ጠበቅ አድርገው በጾም እና በጸሎት፤ በዕንባ እና በሥግደት የሚጓዙት መንገድ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ሰንበት ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ ከኢየሱስ መስቀል የድርሻችንን መሳተፍ የኃይል ሁሉ ምንጭ ነው፤ መስቀል የሌለበት እና መስቀል የማይሰበክበት ክርስትና የሕይወት ኃይል የለውም። ከኢየሱስ መስቀል ጋር መተባበር የጸጋ እና የኃይል ሁሉ ምንጭ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ምሥክርነቱን ሲሰጥ “ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” (2ኛ ቆሮ 12፡10) እያለ የመስቀል ምሥጢር በድካም ውስጥ የሚፈስ የእግዚአብሔር ኃይል እና ጸጋ መሆኑን ይናገራል።

በዛሬው ወንጌል እንደምናነበው ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው የሚያነሱት ጥያቄ የጌታን ክብር ለማየት የነበራቸውን ትልቅ ጉጉት የሚያመላክት ነው። ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶችን ሲጠይቁት በአንድ በኩል የክብሩን ምልዓት ለማየት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ “እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” (ማቴ 19፡28) ብሎ የሰጣቸው የተስፋ ቃል እንዲፈጸምላቸው በመፈለግ ነበር። በዚህ አይነት ደቀ መዛሙርቱ “ክብርን” ማየት እንጂ ክብር በየት በኩል እንደሚገኝ አላሰቡም ነበር! ጌታ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሲሰጥ፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” (ማቴ 24፡4) እያለ ዘወትር በንቃት እንድንጠብቅ ያስታውሰናል። በዚህም የጌታን ዳግም ምጽአት በመጠባበቅ ከመኃልየ መኃልይ ሙሽራ ጋር በአንድ ድምጽ “እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል” (መኃ 5፡2) እያልን እንድንዘምር ጌታ ይጋብዘናል። ክርስትያን ሁሉ በንቃት መኖር ይገባዋል፤ ጌታ በመጨረሻው ዘመን ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዳችን መጨረሻ ወደ እያንዳንዳችን ይመጣልና ዘወትር ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር እና እንዴት ባለ ዝግጁነት መጠበቅ እንደሚገባን ሲያስተምር “ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን” (ሉቃ 12፡35) ይላል። በሞቱ ጊዜ ሳይዘጋጅ ከጌታ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኝ አማኝ በመጨረሻው ዘመን ከጌታ ጋር ለመገናኘትም የተዘጋጀ አይሆንምና የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ከፍ ባለ ጥንቃቄ መኖር ይገባናል።

ጌታ በዛሬው ወንጌል ጠንከር ባለ መልኩ የጭንቅ ዘመን እንደሚመጣ ይናገራል፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚሆነው በየዘመኑ እንደሚነገረው እና እንደሚተነበየው ሳይሆን እነዚያን ቀናት ከአብ በስተቀር ማንም እንደማያውቃቸው ጌታ ያረጋግጥልናል። የአማኝ የቤት ሥራ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ለእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገባ መመላለስ ነው። በዚህም የጌታን መስቀል በዐይኖቹ ፊት በማኖር ሕማሙን፣ ሞቱን እና ትንሳኤውን እያሰላሰልን እንድንኖር ጌታ የሕማሙን ምልክት በመካከላችን አድርጓል። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” (ራዕ 7፡13) እያለ ይጠይቃል፤ ጌታ ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን መልስ እየሰጠ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ” (ራዕ 7፡14) እያለ ከመከራው በኋላ በበጉ ደም በኩል የሚሆነውን ነጻነት ያሳየናል። ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠላቸው ነገር ክርስትና የሚያስከፍለውን ዋጋ በግልጽ የሚያሳይ ነው፤ ተላልፎ መሰጠት፣ ስለ ስሙ በሰዎች ዘንድ የተጠሉ መሆኑ፣ የፍቅር መቀዝቀዝ ወ.ዘ.ተ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የምንሸጋገርባቸው መረማመጃ ደረጃዎች ናቸው፤ ስለዚህ ጌታ “ሥጋን አልፈው ነፍስን መግደል የማችሉትን አትፍሩ” (ማቴ 10፡28) እያለ በሚያጽናና ቃል ይናገራል።

ጌታ በዛሬው ወንጌል “ተጠበቁ” እያለ ሲናገር ከምን እንደምንጠበቅ መጠየቅ ይገባናል። ጌታ በወንጌል “ከፈሪሳውያን እና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” (ማቴ 16፡16) እያለ ከምን መጠንቀቅ እና ከምን መጠበቅ እንደሚገባን በግልጽ ያስተምራል። ይህ የፈሪሳውያን እና የሰዱቃውያን እርሾ የተሳሳተ ትምህርታቸው ነው። ይህ እርሾ ሥጋችንን የሚያበላሽ ሳይሆን ነፍሳችንን የሚበክል እና የዘላለማዊ ሕይወት ጥሪያችንን የሚያዛንፍ እርሾ ነው። ይህ አይነቱ ትምህርት ትክክል የሚመስል፣ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ መስማት የምንፈልገውን ነገር ብቻ የሚናገር ትምህርት ነው። ጌታ እንዲህ ካለው ትምህርት እንድንጠበቅ በዛሬው ወንጌል በተደጋጋሚ ያስጠነቅቀናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የጌታ ትምህርት ተከትሎ “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም” (2ኛ ጢሞ 4፡5) እያለ ለዘላለማዊ ሕይወት የሚበጅ መንገድ ያሳየናል።

ዛሬ በተለያዩ አጋጣሚዎች የምንሰማቸው የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች ጌታ እንጠነቀቃቸው ዘንድ ዐደራ ያለንን የሰዱቃውያን እና የፈሪሳውያን እርሾ ያስታውሰናል። የክርስቶስን ሕማም እና ሞት፣ ባጠቃላይ መስቀሉን ከወንጌሉ የፋቀ እና ትንሳኤውን ብቻ የሚያስተጋባ ስብከተ ወንጌል የጌታ ወንጌል አይደለም። የጌታ ወንጌል ማዕከላዊ ቁም ነገር የመስቀሉ ምሥጢር ነው። የጌታ ትንሳኤ ተካፋይ መሆን የሚፈልግ አማኝ በዕለተ ረቡዕ ከእርሱ ጋር ተላልፎ መሰጠት፣ በጸሎተ ሐሙስ ከእርሱ ጋር በደም ላብ እስከመጠመቅ በጸሎት መቃተት፣ በዕለተ ዓርብ መከራውን ተካፍሎ በመስቀል ላይ መዋል፣ በዕለተ ቅዳሜ በአዲስ መቃብር ውስጥ መቀዝቀዝ እና ወደ ጨለማ ጥግ መውረድ ይጠበቅበታል፤ ይህ ሁሉ ነገር በአንድ ቃል ተጠቃሎ ሲገለጽ “መስቀል” ይባላል። የጌታ መስቀል ከአማኝ ሕይወት በራቀ መጠን የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ ከነፍስ ላይ ይርቃል፤ ነፍስ ቀስ በቀስ እየጠወለገች በኃይልና በጸጋ መገለጥ የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ፍጻሜዋ ምርኮ ይሆናል። ከዚህ አይነቱ የነፍስ ዕርቃንነት እንጠበቅ ዘንድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የዲያብሎስን የሽንገላ ቃላት መቃወም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ ልበሱ” (ኤፌ 6፡11) እያለ የጌታን መስቀል ያስታውሰናል።

ጌታ በደብረ ዘይት ተራራ ያደረገውን ስብከት ሲያጠቃልል “በመጨረሻም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል” (ማቴ 24፡30) እያለ ምልክቱን ይናገራል። ነገር ግን ይህ የሰው ልጅ ምልክት ምንድነው? ይህ የሰው ልጅ ምልክት በነቢዩ ሕዝቄል ዘመን በእሥራኤል መካከል ስለተፈጸመው ኃጢአት በሚያዝኑና በሚያለቅሱ ተነሳሂያን ግንባር ላይ የተደረገ እና ከሞት ያመለጡበት እና  “ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ” (ሕዝ 9፡6) የተባለለት የሰው ልጅ ምልክት ነው።  ይህ ምልክት በጥምቀት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ሱታፌ ያላቸው ክርስትያኖች ለዘላለማዊ ሕይወት በክብር ያለነቀፋ ይጠበቁ ዘንድ የሚለብሱት፣ ጌታ ዓለምን ያሸነፈበት ምልክት፤ ይኸውም ቅዱስ መስቀሉ ነው። በዚህ የክርስቶስ ምልክት በምታምን እና በምትታመን ቤተ ክርስትያን ውስጥ እንደመጠራታችን የታተምንበትን ምልክት የሚመጥን ሕይወት ለመኖር ደም እስከማፍሰስ ድረስ ከኃጢአት ጋር እየተጋደልን፣ የራሳችንን መስቀል ከጌታ መስቀል ጋር አዋደን በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር ወደ ትንሳኤው እንጓዝ!

ሴሞ