ምሥጢረ ክህነት

ምሥጢረ ክህነት

R 3የዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ መሥዋዕት ለማቅረብ የተመረጠውን የድንኳን አገልጋይ በተባዕት ስም ሰዋሰዋዊ አግባብ כֹּהֵן (ኮሄን) እያለ ይጠራዋል። ይህም በላቲኑ ቩልጋታ ትርጉም “Sacerdos” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ቃሉ ከሁለት የላቲን ቃላት የተገመደ ስያሜ ነው፤ በአንድ በኩል በውስጡ “sacer” የሚል ስም የያዘ ሲሆን ይህም በትርጓሜው ቅዱስ ማለት ነው፤  ሁለተኛው እና “do” የሚለው የቃሉ ክፍል “dare” ከሚለው የላቲን ግንድ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜው “መስጠት” ማለት ነው። በውርድ ትርጉም “Sacerdos” የሚለው ስያሜ “ቅዱሳት ነገሮችን የሚሰጥ፣ የሚይዝ፣ የሚፈጽም” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የግሪኩ ሰባወክልዔቱ (Septuagint) ቅጂ ደግሞ ይህንኑ ቃል “ερως” (ሂሬውስ) ብሎ ይተረጉመዋል።

የአዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ በበኩሉ ጳጳሳትን (ἐπίσκοπος) እና ዲያቆናትን (διάκονος) በክህነት አገልግሎት ዐውድ ውስጥ አስተባብሮ ይጠቅሳቸዋል። እነዚህ ሁለቱ በአዲስ ኪዳን ዘመን የተሰጡ ክርስትያናዊ የአገልግሎት ተልዕኮዎች መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ጳጳሳት (ἐπίσκοπος)፣ ካህናት (ἱερέως) እና ዲያቆናት (διάκονος)  የሚባሉት የምሥጢረ ክህነት ደረጃዎች የብሉይ ኪዳን ሦስት የክህነት ደረጃዎች በማስተያየት የተሰጡ፣ በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን መካከል ያለውን የሰመረ መሥተጋብር የሚያመላክቱ ቁም ነገሮች ናቸው። በብሉይ ኪዳን የክህነት ጥሪ ውስጥ ሦስት ዐበይት ክፍሎችን መመልከት እንችላለን፤ እነዚህም፡- የሌዊ ዘሮች ካህናቱን በድንኳን አገልግሎት እንዲያግዙ፣ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ ካህናት (kohen – ierei – sacerdos)፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በሚያስገባ የሊቀ ካህን ማዕረግ (cohen gadol – archierei – pontifex) የሚያገለግል ሊቀ ካህን እንደነበረ መመልከት እንችላለን (ዘኁ 1፡48-53)።

በኦሪት ዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሙሴን ከ12ቱ የእስራኤል ነገድ አንዱን ማለትም የሌዊን ነገድ እንዲለይ እና የሌዊ ዘር  በእግዚአብሔር አምልኮ ካህናቱን እንዲረዳቸው ነግሮታል። ሌዋውያን ከማደሪያው ድንኳን ጋር የተያያዙትን ነገሮች እና ንዋየ ቅድሳትን ሁሉ ይጠብቁ ነበር። በመገናኛው ድንኳን ዙርያ በመስፈር የድንኳኑን ዙርያ ከብበው የእግዚአብሔርን ክብር የሚጠብቁ እንደነበሩ የዘኁልቅ መጽሐፍ ይመሰክራል። በአዲስ ኪዳን የምሥጢረ ክህነት ግንዛቤ ዲያቆናት እንደ ሌዊ ዘሮች ጥሪ፣ የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደ ድንኳኒቱ አገልጋይ ካህናት፣ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ያሉ ጳጳሳት እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ይሰየማሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች በላካት መልእክቱ ስለ ጳጳሳት እና ሰለ ዲያቆናት እያወሳ እንዲህ ይላል፡– “ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ፊል 1፡1)። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ይህ የጳውሎስ መልእክት ገና ወንጌላት ከመጻፋቸው በፊት አስቀድሞ የተጻፈ መሆኑ ቤተ ክርስትያን ከመጀመርያዎቹ ክርስትያኖች አንስቶ እንዲህ ያለ የአገልግሎት ጥሪ እና መዋቅር ያላት መሆኗን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተለያዩ መልእክቶቹ በቤተ ክርስትያን ውስጥ ይህ አገልግሎት ስለመኖሩ በግልጽ ያስቀምጣል። ለአብነት ያህል የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መመልከት እንችላለን።

ኤጲስቆጶስ፡ (ἐπίσκοπος)

 “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው” (1ጢሞ 3፡1)። “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር...” (ጢሞ 3፡2)፣ “ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና” (ቲቶ 1፡7-9)

ዲያቆናት (Διακονοι)

 “እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ” (1ጢሞ 3፡8-10)።

“ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ።በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ” (1ጢሞ 3፡ 12-13)።

እንዲሁም ደግሞ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 6 ላይ ምንም እንኳን ዲያቆናት የሚለው ቃል በቃል በስም ባይጠቀስም በአገልሎታቸው ግብር ሐዋርያትን እንዲያግዙ እጅን በመጫን ሥርዐት ማዕረግን ተቀብለዋልና አገልግሎታቸው እና የተጠሩበት ዐውድ ዲያቆናት ስለመሆናቸው ይመሰክራል፡- “በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን። ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው” (ሐሥ 6፡1-6)።

ካህናት፡

sacerdos”፣  ἱερέως (hiereus)፣  כֹּהֵן kohen፣ ካህን የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናገኝዋለን (ዘፍ 6፡13-ፍ፣ ዘጸ 20፣ ዘሌ 10፣ ዘኁ 1፡47-ፍ)። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በላይ ጉልቶ የሚወጣው የሳሌም ንጉሥ የነበረው የካህኑ የመልኬ ጸዴቅ ታሪክ ነው። አብርሐም የወንድሙን የሎጥን ምርኮ አስመልሶ በድል ከተመለሰ በኋላ ካህኑ መልኬ ጸዴቅ የምሥጋና መሥዋዕት ሲያቀርብ እንመለከተዋለን። ይህ የካህኑ የመልኬ ጸዴቅ የቊርባን መሥዋዕት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ለሚመሰርተው ዘላለማዊ የቊርባን ኪዳን ንግርት ነበር። በዘፍጥረት 14፡18 ላይ እንደምናነበው “የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። ባረከውም። አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው”። እዚህ ላይ ማስተዋል የምንችለው አንድ ተጨማሪ ነገር “ኢየሩሳሌም” የሚለው ቃል መጠቀሱን ነው፤ በግሪኩ ቅጂ ኢየሩሳሌም የሚለው ስም  Hierousalem, ወይም Hierosolyma ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም ስም በውስጡ ερες ወይም ደግሞ “ቅድስና” የሚለውን የሚያሰማ እና ለ“ካህን” የሚሰጠውን ስያሜ መያዙን ነው።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ይህንን ክህነት ለሚመጣው ክህነት ዋስትና እና ምሥክር አድርጎ በመዝሙሩ ውስጥ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም” (መዝ 110፡4) እያለ እግዚአብሔርን ያወድሳል። የዕብራውያኑ መጽሐፍ ጸሐፊ ይህንን የዳዊትን የምሥጋና ጸሎት በመንፈስ ብርኀን አስቀድሞ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተዘመረ ምሥጋና አድርጎ በመውሰድ ለጌታ ክህነት ምሥክር አድርጎ ያቀርበዋል። በዚህም ኢየሱስ በአሮን ዘሮች ሐረግ በኩል በውርስ ክህነት ሳይሆን ይልቁንም እንደ መልኬ ጸዴቅ ባለ ሥርዐት ለዘላለም ካህን ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መልኬ ጸዴቅ ባለ ሥርዐት ካህን ብቻ ሳይሆን የቀደመው የሳሌም ንጉሥ እንደነበረው እንዲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይ እና የምድር ንጉሥ ነው።

ስለ ጌታ ክህነት የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፡-

(ዕብ 5፡1-10) “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም።  እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል። እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው”።

(ዕብ 6፡20) “በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ” (ubi præcursor pro nobis introivit Jesus, secundum ordinem Melchisedech pontifex (αρχιερευς) factus in æternum.)።

(ሮሜ 15፡16) “ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ (ἱερουργοῦντα τὸ εὐαγγέλιον τοῦ Θεοῦ) ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ (λειτουργὸν) እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ”

አቤል

መልኬ ጸዴቅ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል “መካከለኛ” ሆኖ የቆመ የመጀመርያው ካህን ነው፤ ነገር ግን የመጀመርያውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር  ለማቅረብ የመጀመርያው ካህን አይደለም። በዘፍጥረት 4 ላይ እንደምናነበው “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ” (ዘፍ 4፡3-5) እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ትልቁ ቁም ነገር አቤል ያቀረበው የደም መሥዋዕት መሆኑን ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት የተቀበለው ከቅጠላ ቅጠል ይልቅ የተጠበሰ ሥጋ የተሻለ ምርጫ ስለሆነ ሳይሆን ይልቁንም አቤል ከበጎቹ መካከል “በኩር” የሆነውን መርጦ ስላቀረበ ነው። ቃየል ግን የምድርን ቁጥቋጦ እንጂ በኩሩን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ አልወደደም ነበር። ቃየል ለአዳም ቤት በኩር እንደመሆኑ መጠን ከሥራው ሁሉ በኩር የሆነውን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የበኩርነት ክብሩ ነበር፤ ነገር ግን በኩሩን ለራሱ ለማስቀረት ለእግዚአብሔር ትርፍ የነበረውን ነገር አቀረበ። አቤል ግን ለቃየል በነበረው ፈንታ ያቀረበው የበኩር ጠቦት መሥዋዕት የክህነት መሥዋዕት ነበር። አቤል በዚህ መሥዋዕት በኩል ያለወን ነገር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ልቡን እና መላ ማንነቱን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። አቤል ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡ በግፍ ተገድሎ በመሞቱ እና ደሙን በማፍሰሱ ውስጥ የበለጠ ትርጓሜ ይዞ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ ክህነት እና የመስቀል መሥዋዕት እንድንመለከት በር ይከፍትልናል።

እርሱ በግፍ በመገደሉ የሙታን ሁሉ በኩር ሆኖ ትንሳኤን ይጠባበቅ ዘንድ ክርስቶስ ኢየሱስን ተስፋ ያደርጋል። አዲስ ኪዳን ይህንን የአቤልን መሥዋዕት ከክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕት ጋር እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት ከአቤል መሥዋዕት ጋር አገናኝቶ ይገነዘበዋል። በዕብራውያን 12፡24 ስለ ኢየሱስ ደም መሥዋዕት ሲናገር የአቤልን የደም መሥዋዕት እንደ መነሻ ነጥብ በመውሰድ “ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል” እያለ ያስታውሰናል። ደግሞም የዕብራውያኑ ጸሐፊ የአቤልን መሥዋዕት በሚመለከት “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል” (ዕብ 11፡4) እያለ የአቤልን ደም ከክርስቶስ ደም ጋር እያዋደደ ይናገራል።  ከአቤል ቀጥለን በክህነት አገልግሎት የምናገኘው የአሮንን ክህነት ነው።

አሮን

በአቤል፣ በመልኬ ጸዴቅ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት መካከል የሌዋዊው የአሮን ክህነት አለ። በላቲን ቤተ ክርስትያን የዐቢይ ጾም የሰዓታት ጸሎት ውስጥ እነዚህን የክህነት ሰንሰለቶች በሚገባ ማስተዋል ይቻላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቤልን እና መልኬ ጸዴቅን ብቻ ሳይሆን የአሮንንም ክህነት ወደ አዲስ ኪዳናዊ ምልዓት ያደርሰዋል። እንደ አቤል ራስን በማቅረብ ወይም እንደ መልኬ ጸዴቅ በክህነት ባህርያዊ ሥርዐት መሥዋዕት ማቅረብ ብቻውን በቂ አልነበረም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ወደ አምልኮ ነጻነት አውጥቶ ቅዱሳንና የንጉሥ ካህናት ይሆኑ ዘንድ የዘላለም ፈቃዱ ነበር።

በሙሴ በኩል ሕዝቡ እንዴት ማምለክ እንደሚገባው ሥርዐትን በመስጠት እግዚአብሔር እሥራኤልን ከአምልኮ በሚገኝ እስትንፋስ የሚኖር እና እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሕዝብ አደረገው። እሥራኤል እውነተኛውን አምላክ በማምለክ ሕያው እና አሸናፊ ሆኖ የሚዘልቅ ሕዝብ ሆኖ ተጠርቷልና የሌዊ ነገድ በመካከሉ ይህንን የተቀደሰ አምልኮ የሚመሩ ካህናት ሆነው ለአግዚአብሔር እንደተለዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል (ዘኁ 1፡48-53)።

እሥራኤል ከእግዚአብሔር ዕቅድ አንጻር ማንነቱን የሚያስተካክል ሕዝብ ሆኖ ድንኳኑን እንዴት እንደሚተክል፣ ነዋየ ቅዱሳቱን እንዴት እንደሚሰራ እና እንደሚያከብር፣ የካህናቱ ሕይወት እና አገልግሎት ምን መምሰል እንደሚገባው ሁሉ ከእግዚአብሔር በተቀበለው ትዕዛዝ መሰረት እንደ ሰው ችሎታ እና ዕውቀት ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የአምልኮ ሕይወቱን በጥንቃቄ ያደራጃል። እግዚአብሔር አምላክ ራሱ ከዚህ ሕዝብ መካከል ለስሙ መሥዋዕት የሚያቀርቡለትን ካህናት ይለያል፤ ምርጫው ከእግዚአብሔር ከራሱ የሚመነጭ እንጂ ከግለሰቡ ማንነት እና ችሎታ አንጻር የሚደረግ አይደለም። የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ይህንን የእግዚአብሔርን ምርጫ በሚመለከት “እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም” (ዕብ 5፡4) እያለ ያረጋግጥልናል።

ይህ የእግዚአብሔር ጥሪና ምርጫ እሥራኤልን የካህናት ሕዝብ አድርጎ ከሌሎች ሕዝቦች የሚለየው እና ሕዝቡን በትክክለኛው አምልኮ የመምራት ተልዕኮ ያለው ጥሪ ነው! ይህም ተልዕኮ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆኖ በአህዛብ መካከል የስሙ ምሥክር መሆን ነው። በመሆኑም የሌዊ ነገድ እንደ ሌሎቹ ነገዶች የእኔ የሚለው ድንበር የሌለው ርስቱ እግዚአብሔር የሆነለት የካህናት ሕዝብ ሆኖ ተለይቷል። በኦሪት ዘጸአት ይህ የእግዚአብሔር ሐሳብ በጉልህ ይስተዋላል፡- “ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ” (ዘጸ 28፡41)፤ “በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም” (ዘጸ 30፡30)።

ሽማግሌዎች  (οἱ πρεσβύτεροι, ἡ γερουσία)፣ (παλαιὸς ἡμερῶν)


የግሪኩ የሰባ ወክልኤቱ ቅጂ  በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን የክህነትን አገልግሎት የሚፈጽሙትን አገልጋዮች ሽማግሌዎች οἱ πρεσβύτεροι (presbyter) እያለ ከስድሳ ጊዜያት በላይ ይጠቅሳቸዋል። በዚህ አግባብ ከኢሳያስ 9፡15 በስተቀር ሁልጊዜ በብዙ ቁጥር አመልካች ስም እየተጠሩ ተጠቅሰው ይገኛሉ፤ በአዲስ ኪዳን ለአርባ ጊዜያት ያህል በብዙ ቁጥር አመልካች ስም ሲጠቀሱ ዘወትር አይሁዳውያንን የሚመለከቱ አገባቦች እንደሆኑ ማስተዋል ይቻላል። እነዚህ ሽማግሌዎች እየተባሉ የተጠሩት በእሥራኤል መካከል ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ለመቅረብ የተለዩ ሲሆኑ (2ነገ 19፡2) በአዲስ ኪዳን አንዳንድ ጊዜ ለሐዋርያት ጭምር ጥቅም ላይ ውለው መመልከት እንችላለን (1ጢሞ 5፡17-19)። የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡- “ሙሴንም አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ” (24፡1)፤ “ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም” (ዘጸ 24፡9-11)።


የአዲስ ኪዳን ክህነት

እንደ ቤተ ክርስትያን አበው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድምታ በጳጳሳት እና በካህነት መካከል ያለውን ልዩነት ሲያብራሩ ለስብከተ ወንጌል ተልዕኮ በወጡትን አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እና ሰባ አርድእት (ሉቃ 10:1-17) መካከል ያለውን ልዩነት መሰረት አድርገው ይናገራሉ። በዚህ አግባብ ጳጳሳት እና ተከታዮቻቸው አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሲወክሉ ካህናት በስብከተ ወንጌል ሥራ የጳጳሳት ረዳቶች እንደመሆናቸው መጠን ሰባውን አርድእት ይወክላሉ፤ “ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው” (ሉቃ 10፡1)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ከሐዋርያቱ ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ሐዋርያቱ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን እንዲፈትቱ “እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና። ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” (ሉቃ 22፡19፣ 1ቆሮ 11፡24-25) በማለት የክህነትን ሥልጣን ሲሰጣቸው እንመለከታለን።

ይቀጥላል

ሴሞ