እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

እምነት (ክፍል ፪)

እምነት (ክፍል ፪)

532200posterlእምነት ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የተነሳ የሚደረግልን ሥጦታ ነው፤ በመሆኑም እምነት በግለሰባዊ አሁናዊ ውሳኔ እና ምርጫ የሚደረስበት ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከሁሉ በላይ የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፤ እርሱም መጽሐፍ እንደሚያስተምረው ሥጦታውን ለወደደው ይሰጣልና “እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፤ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ” (ሮሜ 9፡18) ጌታ ይህንን የእምነት ሥጦታ በሚመለከት አባቱን በታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ሐሴት እያመሰገነ “አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና” (ማቴ 11፡25) እያለ የአባቱን ፈቃድ ያወድሳል። ኢየሱስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ሳለ ሐዋርያቱ በዙርያው በነበሩ ጊዜ “እናንተስ እኔ ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ?” ሲል ላቀረበው ጥያቄ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት የሰጠው መልስ ምንጩ ከየት እንደሆነ ኢየሱስ ሲናገር “በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋ እና ደም ይህንን አልገለጠልህም” (ማቴ 16፡15-17) በማለት እምነት ከእግዚአብሔር አብ፣ በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ የሚሰጥ መለኮታዊ ሥጦታ መሆኑን ያሳየናል። እግዚአብሔር ይህንን የእምነት ሥጦታ ቀስ በቀስ ለነፍሳችን እየገለጠ በመንፈስ ቅዱስ መረዳት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ራሱ ይስበናል። ይህ የፍቅር ስበት እግዚአብሔር ራሱ በሁለንተናችን እስኪገለጥ ድረስ የሚቀጥል የመንፈስ ቅዱስ ምክር ነው። ጌታ ኢየሱስ ይህንን ሲናገር “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ 16፡12-13) እያለ እምነት በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ወደ እውነት ፍጻሜ የሚደረግ የሕይወት ዘመን ጉዞ መሆኑን ያመልክተናል።

የዚህ ጉዞ የመጀመርያው ነጋዲ የእምነት አባታችን የሆነው አብርሐም ነው፤ አብርሐም እግዚአብሔር ያለውን ነገር ባመነ ጊዜ አምኖ ብቻ አልቆመም፤ ነገር ግን ካመነበት እምነት አንጻር የሕይወቱን መሰረታዊ መዋቅር እንደ አዲስ ማደራጀት ነበረበት። ይህ ከተወለደበት፣ ከአባቶቹ ርስት ለቅቆ የመውጣት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም ባመነው እምነት መሰረት እግዚአብሔር በእርሱ ውስጥ እንደ አዲስ ሊጀምር ለፈለገው ሕይወት ተገቢውን ሥፍራ ይሰጥ ዘንድ ከማንነቱ፣ እስከ እርጅናው ከተሸከመው “እኔነት” ጭምር የመውጣት የሕይወት ውሳኔ ነበር። አብርሐም ወንድ ልጅ አጥቶ ከኖረበት የዕንባ ዓመታት ይልቅ እግዚአብሔር ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ ያለበትን ዘመን በእምነት ተቀብሏል፤ በመሆኑም የሥጦታውን ባለቤት ስላወቀ የዘመናት ለቅሶው መልስ የነበረውን ልጁን ይስሃቅን ጭምር ለእግዚአብሔር ለመስጠት ታዛዥ ነበር። ይህም አብርሐም እግዚአብሔርን ያመነው ልጁን ይስሃቅን ለመሰዋት ታዛዥ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የጸሎቱን መልስ ተነጥቆ ቢሆንም ስለተቀበለው መስቀል ደስተኛ እና አመስጋኝ ሆኖ ይኖር ዘንድ የራሱን ሕይወት ጭምር ለመሥዋዕት በማቅረብ ጭምር አመነ።

“የመሥዋዕቱ በግ ወዴት አለ?” (ዘፍ 22፡7) የሚለው የይስሃቅ ጥያቄ በሌላ አነጋገር በዚህ መስቀል ፊት ለፊት ስቆም ጌታ ኢየሱስ የት አለ? የሚል የእግዚአብሔር የማዳን ምሥጢር ለመረዳት የቀረበ ጥያቄ ነበር። የዚህ ሁሉ ሕይወት ትርጉም ምንድነው? እውነተኛው “የመሥዋዕት በግ” የት አለ? የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የት ገባ? ይህ ጥያቄ በመላው ብሉይ ኪዳን ውስጥ በጉልህ የሚሰማ እውነተኛውን የመሥዋዕት በግ የማየት የናፍቆት ሲቃ ነው። አብርሃም ግና “የመሥዋዕቱ በግ ወዴት አለ?” (ዘፍ 22፡7) ከሚለው የይስሃቅ ጥያቄ አልሸሸም፤ ይልቁንም ወደዚህ በአንድ በኩል እንደ ሰው፣ በሌላ በኩል እንደ አባት ፈተና ውስጥ በሚያቆመው ጥያቄ በእምነት እየተመለከተ በሁኔታው ላይ ሥጋቱን ሳይሆን “የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” (ዘፍ 22፡8) በማለት እምነቱን ተናገረ።  የዚህ እውነተኛውን ናፍቆት ሲቃ መልስ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ታይቷል። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ሲያስተዋውቀን “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ 1፡29) እያለ ወደ ዘመናት ጥያቄ ምላሽ ይጠቁመናል።

አዲስ ኪዳን የአብርሃምን እምነት ንጽሕና እና ጽናት እያወደሰ እርሱ “በእምነት አባታችን” ነው እያለ ይጠራዋል (ገላ 3፡16)።  የአብርሃም እምነት በዙርያው ከሚከናወነው ነገር ባሻገር የሚመለከት እና የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን ምሥጢር የሚያሰላስል ነው። ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንዳረጋገጠለቻው (ገላ 3፡7) አማኝ የሆነን ሁሉ እንግዲያውስ የአብርሃም ልጆች እንሆን ዘንድ እምነትን ከእርሱ እንማራለን።

በእሥራኤል ታሪክ ውስጥ የእሥራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ሕይወት ዘወትር ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ እና እግዚአብሔርን ለመታመን የሚቸገር፣ ልቡ ራሱ በእጆቹ ወዳቆማቸው ጣኦታት የሚሸፍትበት ሕዝብ ነበር። እግዚአብሔር እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት ለማውጣት ከሄደበት ርቀት ይልቅ ግብጽን ከእሥራኤል ልብ ለማውጣት የሄደበት ርቅት ይረዝማል። ነገር ግን የብሉይ ኪዳን ዘመን አማኞች ትውልድ ወደ እመቤታችን በደረሰ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ እና ቃልኪዳን በእምነት በሚቀበል መታዘዝ በመቀበሏ የብሉይ ኪዳን አባቶች ጸሎት እና እምነት ሁሉ ፍጻሜውን አግኝቷል። ኤልሳቤጥ ይህንን የብሉይ ኪዳን አባቶች ሁሉ ናፍቆት ፍጻሜ በተመለከተች ጊዜ በታላቅ ደስታ ይህንን “በእምነት የተሞላ እሺታ” እየመሰከረች “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት” (ሉቃ 1፡45) እያለች ከመንፈስ ቅዱስ በሆነ ምሥጋና ትዘምራለች።

የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ስለ ብሉይ ኪዳን አባቶች እምነት ከመሰከረልን በኋላ የሁሉ ነገር ማሰርያ እና ፍጻሜ ስለሆነው ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በምዕራፍ 12 መክፈቻ ላይ ሲናገር “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና” (ዕብ 12፡1) እያለ የእምነታችን መልሕቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክተናል። በዚህ የዕብራውያን መጽሐፍ ግንዛቤ መሰረት እምነት ዕይታን በአሸናፊው ኢየሱስ ላይ በማድረግ በጽናት የሚኖር ሕይወት መሆኑን መመልከት እንችላለን፤ እምነት ዕይታን በአሸናፊው ኢየሱስ ላይ መትከል ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዕይታውን መሉ በሙሉ በጌታ ላይ ካደረገ በኋላ በሕይወቱ የተከናወነውን ነገር እና የደረሰበትን ውሳኔ ሲናገር “ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ 6፡14) እያለ ሁሉን ነገር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ከንቱ እንደቆጠረው ይናገራል።

መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ዙርያ በርካታ ሰዎች እንደነበሩ እና የሚለውን ነገር ለመስማት ይከተሉት እንደነበር  ይናገራል፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ጌታ ኢየሱስን በእምነት እንደተከተሉት እና በምሥጢር እንደነኩት (ማቴ 9፡20) ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። እግዚአብሔርን መዳሰስ የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት በኩል ነው። እግዚአብሔርን ስንዳስስ ከእርሱ የሚወጣው ኃይል ወደ ሕይወታችን መፍሰስ ይጀምራል፤ በአዲስ ኪዳን የተገለጠው የእምነት መንገድ እና ትርጓሜ ስለ እምነት የሚናገር ዝርዝር ሐሳብ ሳይሆን የእምነታችን ምልዓት እና ፍጻሜ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እምነታችን በእርሱ ሥጋ በለበሰው ቃል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ስለ እርሱ በሚነገረው ትርክት ብቻ አይደለም። ኢየሱስ የእምነት መምህራችን በመሆኑ በእምነት ጉዞ እንዴት መኖር እና እንዴት ማመን እንደሚገባን ያስተምረናል፤ በዚህ አግባብ ወደ እርሱ በሌሊት ለመጣው ለኒቆዲሞስ ኢየሱስ ይህንን የእምነት ምሥጢር እንደገለጠለት ማስተዋል እንችላለን። ነገር ግን ኒቆዲሞስ ስለ ዳግም ልደት የተነገረውን ባልተረዳ ጊዜ ጌታ ኒቆዲሞስን ከአእምሮአዊ ዕይታ ባሻገር ምክኒያታዊ መረዳትን ወደሚሻ እምነት ከፍ እንዲል ይጋብዘዋል። እምነት መረዳትን የሚፈልግ ምክኒያታዊ ጉዞ ነው እንጂ የተረዳሁት በመሰለኝ ነገር፣ ወይም ልረዳው እና ላስረዳው በማልችለው ነገር ተወስኜ በፍርሃት የምታጠርበት ሞኝነት አይደለም።

እምነት ኢየሱስ የሰውን ልጅ ልብ ለእግዚአብሔር ሥራ የሚከፍትበት ቁልፍ ነው፤ ስለዚህ በዕብራውያን መጽሐፍ “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” (ዕብ 11፡1) ተብሎ የተገለጸው በዚህ ምክኒያት ነው። በእምነት አማካይነት ወደ መለኮታዊ ሕይወት ምሥጢር እንቀርባለን፤ ስለዚህ በእምነት ላይ የተመሰረተ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት “እግዚአብሔር በሕይወታችን ከእኛ ጋር” ሊያከናውን የሚፈልገውን ነገር እንዲያሳካ የሚተባበር ተግባራዊ ምላሽ በመሆኑ የዘላለማዊ ሕይወት ጥሪያችንን ሁሉ የሚመለከት ወሳኝ ነጥብ ነው።

ዕብ 11 እንደሚያስረዳው እምነት በውስጣችን የሚያብብ መለኮታዊ ፍሬአማነት ነው። እምነት ከመንፈስ ቅዱስ ቸርነት በልባችን ለሚፈሰው ፍቅር የተሰናዳን ያደርገናል፤ በዚህም የእግዚአብሔርን የጸጋ ሥጦታ እየተቀበልን በመልኮታዊ ነገር ሁሉ እንበለጽጋለን። ይህንን የጸጋ ሥጦታ ለመቀበል ራስን ለመለኮታዊ ፈቃድ አሳልፎ መስጠት፣ ዕይታን በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ አስተካክሎ ማኖር እና በነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን ድምጽ መታመን ይጠይቃል። እምነት ዘወትር ከተስፋ እና ከፍቅር ጋር የተያያዘ ሕይወት ነው፤ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ” (1 ቆሮ 13፡13) እያለ ሦስቱን መለኮታዊ ሥጦታዎች በአንድነት አስተባብሮ ያቀርባቸዋል።

ይቀጥላል...

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት