እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

እምነት (ክፍል ፬)

532200posterl

እምነት (ክፍል ፬)

እምነት ከእግዚአብሔር መለኮታዊ በጎ ፈቃድ የተነሳ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ በኩል በምሥጢረ ጥምቀት ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በተወለድን ጊዜ የተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ መሆኑን ተመልክተናል። ይህንን መልዕልተ ባሕርያዊ እውነት መቀበል የምንችለው እግዚአብሔር አምላክ በምሥጢረ ጥምቀት ጸጋ ነፍስን በዚያ እውነት ስለሚቀድሳት ነው። ይህ የነፍስ በመለኮታዊ “እውነት” መቀደስ የእግዚአብሔርን መገለጥ እንድናምን እና በእምነት ምላሽ እንድንሰጥ የሚያስችለን ኃይል ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከእውነት ጋር ኅብረት የምናደርግበት፣ እውነት ምን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን  እውነት ማን እንደሆነ የምናውቅበት ምሥጢር ጭምር ነው።  እግዚአብሔር አምላክ ራሱን ለሰው ልጆች የገለጠበት የእምነት ምሥጢር ወደ እውነት ሁሉ የምንደርስበት መሪ ኮከብ ነው። የእምነታችን ይዘት እና የእምነታችን ምክኒያት  እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ እግዚአብሔር በበጎ ፈቃዱ ጸጋ ራሱን በአዕምሮአችን ውስጥ ስላበራ እናምን ዘንድ ነፍስ እና አእምሮ ለበለጠ እውነት ክፍት ሆነዋል፤ እምነት እግዚአብሔር አብ በዘላለማዊ የእውነት ቃል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በነፍስ ውስጥ ያበራው የመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ነው።

እምነት ከተዓምራት ላይ የሚሰበሰብ የእግዚአብሔር ሕልውና ማረጋገጫ አይደለም፤ ይልቁንም እምነት የተገለጠ እውነት ነው፤ የዚህ መገለጥ ባለቤት እግዚአብሔር ራሱ ነው። የእግዚአብሔርን እውነተኛነት እና ታማኝነት ለመመርመር ብንፈልግ እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ ሳይሆን በራሳችን መሻት ላይ እናደርጋለን፤ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11፡27-33 እና 12፡ 14-34 ላይ ኢየሱስን ሊፈትኑት የመጡ ሰዎች መኖራቸውን ማንበብ እንችላለን። እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የነበራቸውን የግል ግንዛቤ ይዘው ወደ እርሱ በመቅረብ በእርሱ ውስጥ የራሳቸውን ግንዛቤ ምልዓት የሚፈልጉ፤ ከኢየሱስ እውነተኛ ማንነት ይልቅ እነርሱ ስለ ኢየሱስ የነበራቸው ግንዛቤ የበለጠ ትርጉም ያለው እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ነበሩ። በመሆኑም ኢየሱስን የሚያዩበት ዐይን ከእርሱ አንዳች ስህተት በመፈለግ እርሱን ለማጥመድ የሚመኝ ዕይታ እንጂ በእምነት ዐይኖች አማካይነት የአምላክን ምሥጢር ለማስተዋል እና ለመረዳት በሚፈልግ ዕይታ አልነበረም።

ኢየሱስን እና በእርሱም በኩል ምሥጢረ ሥላሴን ማሰላሰል እንድንችል እምነት የሰውን ልጅ ነፍስ እና አእምሮ ወደ መጀመርያው እውነት ከፍ ያደርገዋል፤ ይህም አልፋ እና ኦሜጋ “እውነት” እግዚአብሔር ራሱ ነው። እግዚአብሔር በእምነት ምሥጢር በኩል አእምሮን እና ነፍስን በመለኮታዊ ዕውቀት ያበራል፤ ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመርያይቱ መልእክቱ “እግዚአብሔር ብርኀን ነው” (1ዮሐ 1፡5) እያለ ይናገራል። ይህ የእግዚአብሔር ብርኀን ነፍስን እና አእምሮን ሁሉ በመለኮታዊ እና በመለልዕተ ባሕርያዊ ዕውቀት የሚያበራ የመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ነው።

 ስለ እምነት ስንነጋገር ምልከታችን ከላይ ወደ ታች በመሆኑ ከእግዚአብሔር መገለጥ ወደ ሰው ልጅ ምላሽ እንመለከታለን፤ በክርስትያናዊ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑ ስነ ልቦናዊ ቁም ነገሮችን የምናጠና ቢሆን ግን ከታች ወደ ላይ፣ ማለትም ከሰው ልጅ ተጨባጭ የእምነት ልምምድ ወደ እግዚአብሔር ባሕርይ እና ማንነት እንመለከት ነበር። ነገር ግን እምነት ከሰው የሚነሳ ቁም ነገር ሳይሆን ወደ እኛ ፊቱን ከመለሰው እና ወደ እኛ ዘንበል ካለው፣ የሕይወትንም እስትንፋስ ከሰጠን ከእርሱ ከእግዚአብሔር የሚነሳ የመገለጥ ቁም ነገር ነው። የእምነታችን ምንጭ፣ ይዘት እና ፍጻሜ ስለ እግዚአብሔር የምናውቀው ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት በግልጽ የሚያስቀምጥልን የመጀመርያው የሃይማኖት አንቀጽ “በእግዚአብሔር አምናለሁ!” የሚል ነው። ስለ እግዚአብሔር በሚነገረው እና በሰው ልጅ ውሱን ቋንቋ ስለ እግዚአብሔር ማንነት በሚታሰበው መላ ምት ሳይሆን ይልቁንም በራሱ በእግዚአብሔር  አምናለሁ!

ስለዚህ በጸጋ ሥጦታው አማካይነት ከአእምሮ አቅም እና ከነፍስ ዕውቀት ባሻገር፣ ሊታሰብ ከሚችለው የሐሳብ ላይላይ ጥግ በላይ ስለሆነው፣ በቃላት ሊነገር እና ሊገለጽ፣ በሰው ተራ የቋንቋ እና የሰዋሰው መዋቅር እንዲህ ነው ተብሎ ስያሜ ሊሰጠው ስለማይቻለው፣ ስለ እርሱ እንናገር ዘንድ እርሱ ራሱ አስቀድሞ አነጋግሮናል።

በዚህም ተግባሩ ከጸጋው በጎ ፈቃድ የተነሳ የሰው ልጅ አእምሮ ያስበው ዘንድ ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ በዚህም የሰው ልጅ አእምሮ በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን እና በምክኒያታዊነት ጸጋ የእግዚአብሔርን ምሥጢር እያሰላሰለ የዕውቀትን ኃይል ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርጎ በምሥጢረ ሥላሴ ሕይወት ተካፋይ ይሆን ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት “በእውነት ጸጋ” ተቀድሷል። በዚህም መቀደስ የተነሳ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ጥበብ እና ውበት እያደነቅን በተመስጦ ሕይወት እናድግ ዘንድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” (ቆላ 3፡2) እያለ ወደ መለኮታዊው ምሥጢር እና ወደበለጠው ጥበብ ከፍ እንድንል ይጋብዘናል።

ይህ በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በነፍሳችን ላይ የሚበራው የእግዚአብሔር ዕውቀት ከፍ ወዳለው መለኮታዊ እውነት የምንመለከትበት ብርኀን በመሆኑ የእግዚአብሔር መገለጥ የሚያስተምረውን እውነት ሁሉ የምንቀበልበት ኃይል እናገኛለን፤ በመሆኑም የኢየሱስ ፍጹም አምላክ እና ፍጹም ሰውነት፣ የቤተ ክርስትያንን መገለጥ፣ የምሥጢራትን ሥጦታ ወ.ዘ.ተ. እውነት መሆናቸውን የምናምንበት የእውቀት ብርኀን እና የእምነት ኃይል ተቀብለናል። እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን የምናምነው አስቀድመን “የመጀመርያውን፣ አልፋ እና ኦሜጋ የሆነውን እውነት” ይኸውም “እግዚአብሔርን” ራሱን በማመናችን ነው። በመሆኑም እነዚህ ሁሉ የእምነት መገለጦች እውነት የሚሆኑት ከመጀመርያው፣ አልፋ እና ኦሜጋ ከሆነው እውነት ስለሚመነጩ ነው። ፍጹም እውነት ከሆነው፣ የእውነትን ትርጓሜ እና ምልዓት ከያዘው ከእግዚአብሔር ስለሚመነጩ ሐሰት ሊሆኑ አይችሉም፤ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” (1 ዮሐ 1፡5) እያለ ይህ እውነት የእግዚአብሔር ብርኀን መገለጥ እንደሆነ ይመሰክራል።

ይህ የእግዚአብሔር መገለጥ ስለ ፍጥረት እና ስለ ፈጣሪ የተደረገ ምርምር አጠቃላይ ሪፖርት ሳይሆን ይልቁንም የእግዚአብሔር መገለጥ የሚናገረን እውነት ለዘላለማዊ ሕይወት እና ለመዳን አስፈላጊ የሆነውን ቁም ነገር ብቻ ነው። በመሆኑም መሰረታዊ እና ከእርሱም በኋላ ለሚከተሉት የእምነት ቁም ነገሮች በሙሉ የመሰረት ድንጋይ የሆነው ዘላለማዊ እውነት ተገልጧል፤ ይኸውም የእምነት ምንጭ፣ ይዘት እና ምልዓት እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ ፍጥረት ሁሉ በታህታይ መዋቅር ከዚህ ከመጀመርያው እውነት ጋር ባለው ትስስር አማካይነት ከዚህ ከመጀመርያው አልፋ እና ኦሜጋ እውነት የተነሳ በእምነት ምሥጢር በኩል ያለማቋረጥ ወደ መጀመርያው ምንጭ ለመድረስ ይቃትታል።

እምነት እግዚአብሔርን የእውነት ሁሉ ላዕላይ ፍጻሜ አድርጎ የሚቀበል የነፍስ እና የአዕምሮ ሥራ ነው። እግዚአብሔር እውነት የሚናገር ሳይሆን እርሱ ራሱ የእውነትን ትርጉም እና ምልዓት በአምላክነቱ ልዕልና ጠቅልሎ የያዘ መለኮታዊ እውነት ነው። በመሆኑም እውነት ምን እንደሆነ የሚገልጥልን እርሱ ራሱ ነው፤ እርሱ ከሁሉ በላይ ስለ ራሱ እውነት ይገልጥልናል፤ በመሆኑም ጌታ ለዚህ መገለጥ ሲያዘጋጀን በወንጌላት ተጽፎ እንደምናነበው “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ 16፡12-13) እያለ ወደ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ይጠቁመናል። እግዚአብሔር የእውነት ላይላይ ማንነት እና ትርጓሜ ሆኖ ለነፍሳችን እና ለአእምሮአችን የዕውቀት ኃይል ራሱን ይገልጣል። በመሆኑም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ወደዚህ እውነት እና ብርኀን እንደርስ ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር ተሳስረናል። በዚህ በመለኮታዊ ሕይወት ውስጥ ባለን ተሳትፎ በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን እየተመራን እውነት፣ መንገድ እና ሕይወት በሆነው በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር አብ፣ አልፋ እና ኦሜጋ ወደሆነው እውነት እንደርስ ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት በተጀመረ በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን በሚመራ የእምነት ሕይወት በጉዞ ላይ ነን።

እምነት እግዚአብሔር አእምሮአችንን በመልዕልተ ባሕርያዊ ኃይል የሚያበራበት እና ወደ እርሱ እውነት የምንመለከትበትን የእምነት ዐይኖች የምንቀበልበት የጸጋ ሥጦታ ነው። ነገር ግን ይህ ማለት እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ መለኮታዊ ማንነት በአእምሮአዊ ዕውቀት መረዳት እና መግለጽ ይቻላል ማለት አይደለም። በአእምሮአችን የምንደርስበት ቁም ነገር ሁሉ ስለ እግዚአብሔር የሚናገር የእምነት ቁም ነገር እንጂ እግዚአብሔርን የሚናገር ቁም ነገር አይደለም። እግዚአብሔር በሰው አእምሮ የዕውቀት ልዕልና ሊታሰብ ከሚችለው የዕውቀት አድማስ ባሻገር ሊደረስበት በማይቻል ብርኀን ውስጥ የሚኖር እውነት ነው። የሰው ልጅ በፍጥረቱ ሰብዓዊ ኃይል ብቻ ወደዚህ ፍጽምና ለመቅረብ የሚችል አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ እኛ ዘንበል ብሎ ስላነጋገረን እና በታሪካችን ውስጥ ራሱን ስለገለጠ በእምነት ብርኀን እርዳታ ነፍስ እና አእምሮ ወደ እግዚአብሔር እውነት ከፍ እንዲሉ መንፈስ ቅዱስ ስለ እያንዳንዳችን በውስጣችን ይቃትታል (ሮሜ 8፡26)።

እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ለመግለጥ ውሱንነታችንን ባገናዘበ እና ለባሕርያችን በሚስማማ መንገድ ሊያነጋግረን ያስፈልግ ነበር። እርሱን በመለኮታዊ ግርማው ተመልክቶ በሕይወት መኖር የሚችል ማንም የለምና (ዘጸ 33፡20-23) በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናቱ ሳይቀር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ክብር ይመለከት ዘንድ በተደጋጋሚ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት አይቻለውም ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው በደረሰ ጊዜ (ገላ 4፡4) እናየው ዘንድ ለዐይኖቻችን ባሕርያዊ ግብር የሚስማማ ሆኖ ተገለጠ። ፍጥረት በሙሉ በሰማያት የሚፈልገውን እርሱን እናቱ ብቻ ደግሞም በእርሷ እቅፍ ውስጥ ሳለ እኛ ሁላችን ዝቅ ብለን እንመለከተው ዘንድ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆነ! ስለዚህ የእግዚአብሔር መልአክ የምሥራቹን ዜና ሲያበስረን “አትፍሩ”! ይላል። እምነት ወደ እግዚአብሔር የምቀርብበት የልጅነት ጸጋ ድፍረት ነው። ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ደፍረት እና መግባት በእርሱ አለን” (ኤፌ 3፡12) እያለ ወደ እግዚአብሔር ምሥጢር እንድንቀርብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተከፈተውን የእምነት በር ያመላክተናል።

 የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ራሱን ለአእምሮአችን የገለጠው የእኛ የነበረውን ሥጋ በመልበስ በትስብዕቱ ምሥጢር ውስጥ ነው። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ፣ በትስብዕቱ ምሥጢር አማካይነት የእምነት ቁም ነገር በሰው ልጅ ቋንቋ ተገልጧል። ይህም ማለት በቋንቋ ሰዋ-ሰው ስለ እግዚአብሔር የሚነገረው ነገር ማለታችን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ገልጦ አነጋግሮናል ማለታችን ነው። በምሥጢረ ጥምቀት የተቀበልነው እና በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን እያደገ የሚሔደው ስለ እግዚአብሔር ያለን ዕውቀት ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ነው፤ በጥምቀት አማካይነት እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ውስጥ ሕያው ሆኖ ይኖራልና ስለ እግዚአብሔር በምናውቀው ነገር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በእግዚአብሔር በራሱ ወደ እግዚአብሔር እናድጋለን፤ በእምነት የምንጓዘው የተስፋ ፍጻሜአችንም በዘላለማዊ ፍቅር ከእርሱ ጋር አንድ መሆን ነው።

ይቀጥላል...

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት