እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅዱስ ዮሴፍ

WhatsApp-Image-2022-06-02-at-210755

ቅዱስ ዮሴፍ

ከትንሳኤ በዓል ዑደት ሳንወጣ ዛሬ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አሳዳጊ እና የእመቤታችን ድንግል ማርያም ንጹህ ጠባቂ የቅዱስ ዮሴፍን የንግሥ በዓል እናከብራለን። ቅዱስ ዮሴፍ የቤተ ክርስትያን ባልደረባ ሆኖ ከመከበሩ ባሻገር ለእግዚአብሔር አለኝ በሚለው ነገር ሁሉ፤ ይኸውም በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አሳዳጊነት እና በእመቤታችን ድንግል ማርያም ንጹህ ጠባቂነት የታመነ ቅዱስ ነው። ዛሬ የቅዱስ ዮሴፍን በዓል ስናከብር አባትነትን እና ወንድ ሆኖ የመፈጠርን ምሥጢር እንደገና እንድናስብ እንጋበዛለን!

ቅዱስ ዮሴፍ ጌታን ያፈቀረበት የአባትነት ልብ በእኛ በእያንዳንዳችን ይሆን ዘንድ ከቅዱስ ዮሴፍ ለመማር የሕይወቱን ቁም ነገሮች በሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል። ምንም እንኳን በወንጌል ውስጥ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ የተጠቀሱት ነገሮች ጥቂት ቢሆኑም ቅዱስ ዮሴፍ ማን እንደሆነ በተለያየ ዐውድ እንድንመለከተው በበቂ መልኩ መልእክት የሚያስተላልፉ ሆነው እናገኛቸዋለን።

በመጀመርያ ቅዱስ ዮሴፍ በነበረበት ማኅበረሰብ ዘንድ ከሚያከናውነው ሥራ አንጻር በግብር “የእንጨት ባለሞያ” ተብሎ (ማቴ 13፡55) ተገልጾ እንመለከተዋለን፤ በመቀጠልም ከእመቤታችን ጋር ከነበረው ግንኙነት የተነሳ “የእመቤታችን” እጮኛ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል (ማቴ 1፡8፣ ሉቃ 1፡27)፤ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሴፍ ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ሲነገር ቅዱስ ዮሴፍ “ጻዲቅ ሰው” ነበር (ማቴ 1፡19) እያለ መንፈሳዊ ሕይወቱን ያስቃኘናል። የሉቃስ ወንጌል በበኩሉ የቅዱስ ዮሴፍ መንፈሳዊ ሕይወት ምሥጢር ምን እንደነበር ሲናገር “ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔርን ድምጽ የሚያዳምጥ እና በእምነት የሚቀበል” እንደሆነ ይናገራል (ሉቃ 2፡22፣27፣39)።

ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ አገልጋይ ሆኖ በማኅበረሱ መካከል በእጆቹ በሚሠራው በላቡ ፍሬ በሐቅ የሚኖር፣ እጮኛውን እንደ ቤተ መቅደስ ባለ ክብር የሚጠብቅ አባት ነበር። ይህ የቅዱስ ዮሴፍ አባትነት ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የወንድነቱን ክብር እና ግብር ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ቁርጥ ፈቃድ ተገልጦ የታየ አገልግሎት ነው። ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ባለ ዐደራ እና አገልጋይ ነበር ማለታችን አገልግሎቱ በትርፍ ጊዜው የሚከናወን፣ ያሉትን ዝንባሌዎች እና ተሰጦዎች ያገናዘበ ለእግዚአብሔር የሚቸር አገልግሎት ሳይሆን እርሱነቱን፣ ወንድ ሆኖ የመፈጠሩን ምሥጢር፣ ማንነቱን ጭምር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በለወጠ መሰጠት የሚፈጸም አገልግሎት ነው።

 ጌታ መስቀሉን በጎልጎታ ከፍ አድርጎ ከማሳየቱ አስቀድሞ ቅዱስ ዮሴፍ ለቤተሰቡ እና ቃል ለገባለት የእግዚአብሔር የማዳን ስራ ፍጹም በሚያስደንቅ አርምሞ መስቀሉን በመላ ማንነቱ ተሸክሞ ነበር። ስለዚህ ቅዱስ ዮሴፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ” (ፊሊ 3፡7-9) ያለውን ሐሳብ በተግባር የኖረ ስለ ጌታ የማዳን ሥራ ማንነቱን እና ለእርሱ የነበረውን የክብር ዘውድ ሁሉ መሥዋዕት ያደረገ፣ ያለውን ትርፍ ነገር ሳይሆን መሰረታዊ የሕይወት ጥያቄውን ጭምር ለእግዚአብሔር አገልግሎት መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ የአዲስ ኪዳን የመጀመርያው ሰማዕት ነው። በዚህ አይነት ለእግዚአብሔር ዓላማ መፈጸም በማኀበረሰብ ውስጥ እንደ አለመታደል እና ሲያልፍም እንደ እርግማን ተደርጎ የሚቆጠረውን ነገር እንኳን ሳይቀር ለእግዚአብሔር ልጅ ክብር እንደ በረከት አድርጎ ተቀብሎታል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ባል እና ሚስት በሚናገርበት የኤፌሶን መልእክቱ ውስጥ “ባል የሚስት ራስ” (ኤፌ 5፡23) ነው ይላል። በዚህ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግንዛቤ ውስጥ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደ ቤተ ክርስትያን ራስ በቀረበበት አገላለጽ “አካልን የሚያድን” ራስነት እንደሆነ በግልጽ መመልከት ይቻላል። ቅዱስ ዮሴፍ ባል የሚስት ራስ ነው የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሕሮ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ በተግባር የኖረ እና የቃሉን ሙሉ ትርጓሜ ያሳየን አማኝ ነው። ለቅዱስ ዮሴፍ “ራስነት” ሌላውን ወደ ታች ለመመልከት፣ ሌላውን ለመግዛት እና ሌላውን በፍርድ መንበር ፊት አሳልፎ ለመስጠት ወይም ደግሞ “ራስነት”አደብ የሌለውን የግል መሻት በሌሎች በኩል ለማርክት እና ለማሳካት አይደለም። ይልቁንም ከቅዱስ ዮሴፍ ተግባራዊ ሕይወት መመልከት እንደምንችለው “ራስነት” ራስን አሳልፎ ለመስጠት እና ለመሥዋዕትነት ነው። እንዲህ ያለው “ራስነት” ራስን ለሌላው ያለገደብ አሳልፎ በመስጠት በዚያ ሰው ላይ ያለው የእግዚአብሔር ዓላማ እንደሚገባው ይፈጸም ዘንድ የጸጋ ተባባሪ ሆኖ ለእግዚአብሔር ዓላማ መሰለፍ ነው። ለቅዱስ ዮሴፍ “ራስነት” ሌላውን በከበረ ሰረገላ ላይ አስቀምጦ የወንድነቱን ክብር በትህትናው እና በሕይወት መሥዋዕትነቱ መግለጽ መቻል ነው።

ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችንን በእጮኝነት ሲቀበላት ከወንድነቱ ባሕርያዊ ጸጋ ባሻገር ማንነቱን ሁሉ ለእርሷ እና እግዚአብሔር በእርሷ ውስጥ ላለው ዓላማ አሳልፎ ሰጥቷል፤ ጊዜውን፣ ጉልበቱን እና ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ከሁሉ አስቀድሞ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሚታዘዝ ትህትና ራሱን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ አሳልፎ ሰትቷል። ቅዱስ ዮሴፍ ከዚህ መሰረታዊ የሕይወት ፈለግ በመነሳት የሕይወት ፕሮግራሙን ሁሉ በዚህ መልክ እየቃኘ አሳዳጊነቱን እና ጠባቂነቱን በተግባር ይኖራል። በእርግጥ ይህ “የአሳዳጊነት እና የጠባቂነት” ሥልጣን እና ተልዕኮ በፍጥረት መጀመርያ ላይ ለአዳም የተሰጠ እና አዳም ተፈትኖ የወደቀበት እምነት ነበር (ዘፍ 2፡15)። የዔደንን ገነት እንዲያለማው እና እንዲንከባከበው ኃላፊነት የለበሰው አዳም ከታመነበት ገበታ የማይገባውን ቀጥፎ ስለበላ እና ለእግዚአብሔር የነበረውን ለራሱ መውሰድ ስለተመኘ ሞት በእርሱ ላይ  በእርሱም በኩል በእያንዳንዳችን ላይ እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። ነገር ግን ቅዱስ ዮሴፍ ለእርሱ የነበረውን የወንድነት ባሕርያዊ ጸጋ ለእግዚአብሔር ዓላማ አሳልፎ በመስጠት እና በኃላፊነት እንዲጠብቅ የተሰጠውን ዐደራ በመጠበቁ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በእግዚአሔር ዓላማ ለታመነበት ዐደራ የገዛ ራሱን ማንነት መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ ከአዳም ይልቅ የሚታመን ሆኗል።

ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ማንነት እና ስለ ሕይወቱ ቁም ነገሮች ስናስተነትን ቅዱስ ዮሴፍ ኑሮውን በናዝሬት ከተማ  አድርጎ እንደነበር መጽሐፍ ይናገራል። እዚህ ላይ ቅዱስ ዮሴፍ ወላጅ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንደንገነዘብ አዲስ ምልከታ ይሰጠናል። ቅዱስ ዮሴፍ በናዝሬት ይኖር ዘንድ የመረጠው ስለ ቤተሰቡ ሁልንተናዊ ደህንነት በማሰብ ነበር። የቤተሰብ ራስ መሆን አካል ሁሉ ከራስ ጋር በጤናማ ግንኙነት ተጠብቆ በደህና ይኖር ዘንድ ዋስትና ለመሆን ነው። የሔሮደስን ቁጣ ሸሽቶ በናዝሬት ኑሮውን ሲመሰርት ስለተቀበለው ኃላፊነት ሕይወት ከእርሱ የምትጠይቀውን ነገር ሁሉ እንደ እግዚአብሔር የጸጋ ሥጦታ ለመቀበል ታዛዥ ነበር። ቅዱስ ዮሴፍ በናዝሬት በነበረው ቤት ከኢየሱስ እና ከማርያም ጋር የነበረው ሕይወት በዘመናዊው ቋንቋ በቤት ሆኖ ልጅ የሚይዝ (A stay-at-home Dad) የሚለውንም ሐሳብ የሚጠቀልል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ለአንድ ቤተሰብ ጤናማ መስተጋብር የወንድ እና የሴት በተፈጠሩበት አንዱ የሌላው ምልዓት እና አክሊል የመሆን ጥሪ ውስ|ጥ በታማኝነት መኖር ያለውን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ በር የሚከፍትልን ቁም ነገር ነው። አዳም እና ሔዋን የተፈጠሩበት ዋነኛው ቁም ነገር በቅድሥት ሥላሴ መካከል ያለው ስምረት በእነርሱም መካከል እንዲሆን ነውና እግዚአብሔር ይህንን ቅድስት ሥላሴያዊ ኅብረት ታሳቢ በማድረግ  “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” (ዘፍ 2፡18) እያለ በወንድ እና በሴት መካከል ያለውን ጤናማ ምሥጢራዊ ጉራማይሌ አንድነት ይገልጻል። የሰው ልጅ በተፈጠረበት ክብር ለሌላው ጠባቂ እና ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ በመሆን እንዴት መኖር እንደምንችል ከቅዱስ ዮሴፍ ለእግዚአብሔር ዓላማ ከተሰዋ ሕይወት መማር እንችላለን!

የቅዱስ ዮሴፍን በዓል ስናከብር እነዚህን የመንፈሳዊ ሕይወት ቁም ነገሮች ሁሉ በማሰላሰል በክርስትያናዊ ሕይወት ጉዟችን እንድንበረታ በአማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን! መልካም የቅዱስ ዮሴፍ ንግሥ በዓል!

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ለምንልን!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት