ዋጋችን ስንት ነው?

ዋጋችን ስንት ነው?

Holy Cross 2015 ecበሕይወታችን ውስጥ የምንገለገልባቸው ቁሳዊ ነገሮች አብዛኞቹ በዋጋ የሚተመኑ ናቸው፤ ምናልባትም የሁሉን ዋጋ ባናውቅም እንደየዝንባሌያችን የተወሰኑ ነገሮችን ዋጋዎች እናውቃለን፤ በተመሳሳይ መልኩም እንደየዋጋቸው ክብደት ወይም ርካሽነት ነገሮችን ጥንቃቄ እንሰጣቸዋለን ወይም እንነፍጋቸዋለን። እንዲሁም ያለ እነርሱ መኖር እንደማንችል የምናውቃቸው ነገር ግን ደግሞ የዋጋ ተመን የሌላቸው እንዲሁ በነጻ የምንጠቀምባቸው አምላክ በቸርነቱ የሰጠንም ነገሮች አሉ፤ ዋጋ እንተምንላቸው ብንል አቅመ ቢስ የሚያደርጉን እውነታዎች! ለምሳሌም አየር፣ የፀሐይ ብርሃን፣ ወንዝ፣ ባህር… ወዘተ።

ከላይ ከጠቀስናቸው ነገሮች ደግሞ እልፍ ስንል አንዳንዴ በዋጋም ማሰቡ ሞኝነት የሚያስመስል፤ በተቃራኒው ደግሞ ዋጋውንም ያለማሰቡ በተመሳሳይ ደረጃ ሞኝነት የሚያስመስል እውነታ አለ፤ ሰው። አንዳንድ ሰው ቢገዛም ባይገዛም ራሱን እስኪያዞረው የሚያስፈልጉትንም የማያስፈልጉትንም የቁሳቁሶች ዋጋ መጠየቅ ይጠናወተዋል፤ ብዙ ሰው ደግሞ ሰው የመሆኑን ዋጋ ሳይጠይቅ እድሜውን ሊኖር ይችላል፤ ዋጋውን ካላወቀ ተገቢውን ክብርና ጥንቃቄ ሊነፍገው የሚችል “ሰው” ነት እንዳለውም ሊዘነጋ ይችላል።

ታዲያ የሰው ዋጋው ስንት ነው? እስቲ ረጋ ብለን በማሰብ ዋጋችን ስንት ወይም ምን ሊሆን ይችላል ብለን እናስብ። አንዳንዴ አንዳንድ ሰው ምንም ዋጋ የሌለው፣ እንደው ዝም ብሎ የሚተነፍስ፣ የሚንቀሳቀስ፣ የሚኖር ይመስለው ይሆናል፤እናም ዋጋህን ገምት ሲባል ከግኡዛዊነት ያልዘለለ ቦታን በመያዝ ብቻ መለያቸው ከሆነ ከማዕድን (ከድንጋይ፣ ከብረት…)፣ ወይም ዝም ብሎ ባለበት የማደግና የመተንፈስ መገለጫ ከአትክልትና (ከእፅዋት) እንዲሁም በደመ ነፍስ ከወዲህ ወዲያ መንቀሳቀስ ከሚችሉት ከእንስሳትም ያነሰ ዋጋ ያለው ሊመስለው ይችላል። አንዳንዴም ሰውና ሁኔታዎች ባዶ እንደሆንን፣ ዋጋ እንደሌለን፣ የሆነ ሰው ሲከዳን፣ ዝቅ ሲያደርገን ራስችንን ባዶ አድርጎ የማሰብ ፈተና ሊገጥመን ይችላል።

በርግጥ ለሰው ለራሱ ዋጋውን መተመን ከባድ ነው፤ በትክክል የሰውን ዋጋ የሚተምነው ፈጥሮታልና ፈጣሪው ብቻ ነው፤ ሰውም የሚጠበቅበት የወጣለትን ዋጋ ማወቅና ክብሩን መጠበቅ ነው። ወደ እምነታችን ስንመጣ ይህንን የተራ ገበያ ቋንቋ ዋጋ ብለን የተጠቀምንበትን ሀሳብ “ቤዛ” በሚል ቃል መጠቀም እንችላለን። ቤዛ ስንል ሰው በኃጢአት ከጸጋ ወደ ኃጢአት ሕይወት በመውደቁ ፍጹም ሰው የሆነልን አምላክ ለእኛ በመሞት ካሣን የከፈለበት እውነታ ነው። ስለዚህም ክርስቲያን እንደመሆናችን ዋጋ ያልወጣበት ማንነት የለንም፤ ተከፍሎብናል፣ ተክፍሎልናል፤ ቅዱስ ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም” (1ቆሮ 6:20) ይለናል።  

መስቀልን ማክበር የእኛን ዋጋ ማክበር ነው፤ የተገዛንበትን ያለመዘንጋት ነው፤ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” (1ጴጥ 1:19) እንደ ሰው ከሕይወት ተራ ወጥተን ኑሮ ትርጉም ሊያጣብን የሚችለው በውስጣችን ትርጉም ስናጣ ነው፤ መኖራችን ወፍ ዘራሻዊ ሲመስለን ያለመኖራችንም አይደንቀንም። የማንነት ንጽጽራችንን፣ መርሳት የሌለብንን ስንረሳ ሕይወት ለዛ ቢስ ትሆናለች፤ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” ይለናል (ገላ 3:1)።

የአንድ ሰው ነፍስ ከዓለም ሁሉ የበለጠ ዋጋ አላት፤ የያንዳዳችን ነፍስ ዋጋዋ ከክርስቶስ ዘንድ ነው። “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማር 8:36-37)። ነፍሳችን ነፍስ ተላልፎ የተሰጠላት ናት! “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ።” (ሉቃስ 23:46)።

ስለዚህም በነገሮች መካከል፣ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነን  የክርስቶስን መስቀል ስናይ ደስታችን፣ እውነተኛ ነጻነታችን፣ ምስጋናችንና ሰላማችንን እናገኝለን፤ ሁሉ ነገራችን በመስቀል ላይ “ተፈጸመ”፤ እኛ እንከፍል ዘንድ አንበቃምና እሱ በመስቀል ላይ የእኛን ዋጋ ከፈለ፤ “ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።” (ዮሐ 19:30)። አዎን! ዋጋችን፣ ቤዛችን ክርስቶስ ነው!