የዓለም የወንጌል ተልዕኮ ቀን

የዓለም የወንጌል ተልዕኮ ቀን

WMS19AEngCVR-774x1024በዚህ ሰንበት ቤተ ክርስትያን የዓለም የወንጌል ተልዕኮ ቀን ታከብራለች። እ.ኤ.አ. በ1926 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ የተልዕኮ ሰንበት በቤተ ክርስትያን የሥርዓተ አምልኮ ዑደት ውስጥ እንዲካተት በማድረጋቸው በዚህ ሰንበት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በልዩ መልኩ ስለ ወንጌል ተልዕኮ ትጸልያለች፤ በዚህ ቀን የሚሰበሰው መባዕ ሙሉ ለሙሉ ቅድስት መንበር ለስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ለምታከናውነው ሐዋርያዊ ተግባር እንዲውል ከዓለም ሁሉ ተሰብስቦ ወደ ቅድስት መንበር ይላካል። በዚህም መልኩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች  የወንጌል ተልዕኮን በተመለከተ ያላቸውን የጋራ ኃላፊነት ይገነዘባሉ።

የወንጌል ተልዕኮ ቤተ ክርስትያን በምሥጢረ ጥምቀት ለእያንዳንዳችን የሰጠችን ዐደራ ነው። ነገር ግን የወንጌል ተልዕኮ ምንድነው? አንድ ክርስትያን የሚሰጠው ምሥክርነት አስኳል ምንድነው? የወንጌል ተልዕኮ ቁም ነገር በምን መልኩ ሊተገበር ይችላል? ወይም ደግሞ ቤተ ክርስትያን የወንጌል ተልዕኮ ሰንበትን ስታከብር የምታከብረው ቁም ነገር ምንድነው? እነዚህ ጥያቄዎች የስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ምንነት እና ይዘትን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችን እንደ ክርስትያን የምንኖረውን ሕይወት ምንነት የሚመለከቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው። አንድ ክርስትያን የሚኖረው ሕይወት ምንድነው? ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” (ዮሐ 10፡10) ይላል። እንግዲያውስ የእያንዳንዱ ክርስትያን ጥሪ በሕይወት መኖር ብቻ ሳይሆን በተትረፈረፈ ሕይወት መኖር ነው ማለት ነው። ይህ የተትረፈረፈ ሕይወት ወይም ደግሞ በተለመደ ካቶሊካዊ ግንዛቤ ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ሕንጸት የምንለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሁሉ ማዕከላዊ ቁም ነገር ነው። ኢየሱስ ይህንን ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ሕንጸት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ማዕከላዊ ቁም ነገር እንዳደረገው ወንጌል ይመሰክራል።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ላይ “መንግሥትህ ትምጣ” የሚል ኃይለ-ቃል ይገኝበታል። ይህ “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለው ቁም ነገር የአዲስ ኪዳን ልብ እና የኢየሱስ አገልግሎት ተልዕኮ መዳረሻ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን መንግሥቱ እንድትመጣ ወደ አብ እንዲጸልዩ ማስተማሩ በጣም አይ?-አዎ! (paradoxical) ዘይቤ ያዘለ ነው። የመሲሁን መምጣት የሚጠባበቁት አይሁድ በብረት በትር የሚገዛውን ከዳዊት ቤት የሚነሳውን መሲሕ ከማየት የበለጠ ናፍቆት አልነበራቸውም (ራዕ 2፡27)፤ በመሆኑም አንተ መሲሕ ነህ (ማቴ 16፡16) ብለው አምነው ለሚከተሉት ደቀ መዛሙርት “መንግሥትህ ትምጣ” የሚል ጸሎት ማስተማሩ ግርታን የሚፈጥር ይመስላል። መሲሑ ከእኛ ጋር እያለ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምንጸልየው ስለምንድነው?

የዮሐንስ ራዕይ የቤተ ክርስትያንን ናፍቆት እያስተጋባ እንዲህ ይላል “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ ... መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ። የሚሰማም ና! ይበል ... ይህን የሚመሰክር አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና!” (ራዕ 22፡ 12፣17፣20)። ይህ በቶሎ እመጣለሁ የሚለው ክርስቶስ “ሥጋ ለብሶ በመካከላችን ያደረው ቃል” (ዮሐ 1፡14) በታሪካችን አሁናዊ ሁኔታ በጊዜ ውስጥ የተገለጠ የእግዚአብሔር መንግሥት ምልዓት ነው። ነገር ግን እርሱ ራሱ “መንግሥትህ ትምጣ” የሚል ጸሎት ያስተምረናል።

የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው ልጆች ሁሉ የቀረበ ኲሏዊ ጥሪ ነው። በመሆኑም የሰው ዘር ሁሉ በዚህ ኲሏዊ ጥሪ ወደ መዳን እንዲደርስ ቤተ ክርስትያን “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” (ማር 16፡15) የሚል ተልዕኮ ተቀብላለች። የመሲሑ የስብከተ ወንጌል ቁም ነገር የሰው ልጆች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመቀበል፣ ብሎም በእግዚአብሔር መንግሥት እውነታ ውስጥ ለመኖር  ይኖሩ ዘንድ የተጠሩበት ታላቅ ግብዣ ነው። በመሆኑም ቤተ ክርስትያን የመሲሑ የወንጌል ባለ ዐደራ እንጂ የራሷ ወንጌል ደራሲ አይደለችም፤ ስለዚህ ይህንን ተልዕኮ ክርስትያን ተብለው ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በመንፈስ ቅዱስ ልደት ለሚወለዱት ሁሉ እንደ ጥምቀት ተልዕኮ አድርጋ በመስጠት የመንግሥቱ ባለቤት ዳግም እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን እየተናገረች ትንሳኤውንም እያከበረች “መንግሥትህ ይምጣ!” በሚለው ጸሎቷ ሠርክ የአዳኟን ዳግም ምጽአት በመጠባበቅ በተልዕኮ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም የወንጌል ተልዕኮ ሰንበት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እና በዚህ መንግሥት ውስጥ በምሥጢረ ጥምቀት በተቀበልነው ቃልኪዳን መሰረት ያለንን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ውስጥ ሆነን የምናሰላስልበት የጸጋ ጊዜ ነው።

 የማርቆስ ወንጌል የመሲሑን አገልግሎት መሰረታዊ ቁም ነገር ሲያስተዋውቀን “ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” (ማር 1፡15) እያለ ያስተምር እንደነበረ ይመሰክራል። እነዚህ ቃላት የኢየሱስ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና የኢየሱስ ድርጊት መሰረታዊ ቁም ነገሮች መሆናቸውን በተቀሩት የወንጌል ክፍሎች ውስጥ መመልከት ይቻላል ((ማቴ 4፡17፣ ሉቃ 4:16)። ይህ ቁም ነገር የጌታ የመጀመርያ አገልግሎት ውስጥ ብቻ የሚስተዋል ሳይሆን፣ ይልቁንም የእግዚአብሔርን መንግሥት ማወጅ ከትንሣኤ በኋላ የጌታ አገልግሎት ዋና ፅንሰ-ሀሳብ መሆኑን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይመሰክራል (ሐዋ. 1፡3)። ስለዚህም የወንጌል ተልዕኮ አስኳል የእግዚአብሔርን መንግሥት ቁም ነገር ነው።

βασιλεία (ባዚሊያ) የሚለው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመግለጽ አዲስ ኪዳን የተጠቀመው ስማዊ ቃል ዝርው በሆነ የቃሉ ትርጉም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ዘጠኝ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል፤ ነገር ግን በቃሉ ዐውዳዊ አገባብ ፍቺ በአዲስ ኪዳን ውስጥ 151 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። የእግዚአብሔር መንግሥት ሐሳብ የኢየሱስ መልእክት እና አገልግሎት ገዢ ሐሳብ በመሆኑ ሌሎች ነገሮች ሁሉ በዚሁ ገዢ ሐሳብ ሥር በተዋረድ የሚቀመጡ ቁም ነገሮች ናቸው። “የእግዚአብሔር መንግሥት (βασιλεία τοῦ Θεοῦ) ቀርባለች” የሚለው የኢየሱስ ስብከት የቤተ ክርስትያን ተልዕኮ መሪ ኮከብ በመሆኑ በዚህ በተልዕኮ ሰንበት ቤተ ክርስትያን ወደዚህ መንግሥት የምታደርገውን ጉዞ እንድትፈትሽ ትጋበዛለች።

"βασιλεία" የሚለው የግሪክ ቃል በተለያዩ ዐውዳዊ ፍቺዎች ሊተረጎም የሚችል በመሆኑ ትርጓሜው እንደ ዐውዳዊ አገባቡ በጣም አሻሚ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ በዚህ ጽሐፍ βασιλεία ለሚለው ቃል የምንሰጠው ትርጓሜ ከነገረ መለኮታዊ ዐውዱ አንጻር ብቻ የሚታይ ይሆናል። በዚህ ነገረ መለኮታዊ አረዳድ በመጀመሪያ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር የኢየሱስ ስብከት የሚያሳስበው የእግዚአብሔር አብን βασιλεία መንግሥት ነው። ኢየሱስ ስለራሱ መንግሥት ሳይሆን አገልግሎቱ እና ሕይወቱ ሁሉ ስለ አባቱ መንግሥት መምጣት እና ስለ ሰው ልጆች በተትረፈረፈ ሕይወት የመኖር የልጅነት መብት የተሰዋ ሕይወት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር መንግሥት βασιλεία ወሰንን ወይም ድንበርን አይገልጽም፣ ይልቁንም የ እግዚአብሔር መንግሥት βασιλεία ታላቅነት የሚመጣው በእግዚአብሔር መገለጥ ምሥጢር ውስጥ ነው።

እግዚአብሔር ባለበት ሥፍራ ሁሉ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ ይታያል። ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት (βασιλεία) ታላቅነት የሥላሴ ምሥጢር በመካከላችን የመገለጡ ቁም ነገር ነው፤ ይህም ቅድስት ሥላሴያዊ መገለጥ ከሥላሴያዊ ባሕርይው የተነሳ በመላው የሰው ዘር መካከል ጤናማ ኅብረትን የሚሻ፣ የሰውን ዘር ሁሉ በሁለንተናዊ ኅንጸት የሚቀድስ ኅብረት ነው። ምክንያቱም ቅድስት ሥላሴ “ሰዎች ሁሉ ይድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ይደርሱ” (1ጢሞ 2፡4) ዘንድ መልካም ፈቃዱ ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር ማኅበራዊ ነጸብራቅ ነው፤ እኛም እያንዳንዳችን በሰመረ እና ጤናማ በሆነ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ኅብረት በጋራ ለዚህ መንግሥት መምጣት እንድንሰራ ተጠርተናል። የቤተ ክርስትያን የተልዕኮ ሰንበት ዓላማ ይህ ነው፤ የተልዕኮ ሰንበት ዓላማ ኢየሱስ ላስተማረን “መንግሥትህ ትምጣ!” ለሚለው ጸሎት የሚሰጥ ተግባራዊ ምላሽ ነው።

ይህ በቅድስት ሥላሴ መካከል የተገለጠው ኅብረት የሰው ልጅ አስቀድሞ እንደ ግለሰብ ከራሱ ጋር ላለው ጤናማ ግንኙነት ሁነኛ ሚዛን ሲሆን፤ ከዚህም በመቀጠል የሰው ልጅ ሁሉ ከባልንጀራው ጋር ላለው ግንኙነት መምሪያ እና መመዘኛ ውኃ ልክ ነው። በመሠረቱ የእግዚአብሔር መንግሥት እግዚአብሔር በግለሰቡ እና በሕዝቡ መካከል ሕያው ሆኖ የመገኘቱ ምሥጢር ነው።

የእግዚአብሔር መንግሥት እስራኤላውያን አጥብቀው እንደሚጠብቁት አይነት በሰው መስፈርት የተገነባ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መንግሥት ሳይሆን፣ ይልቁንም በእግዚአብሔር ማንነት እና እውነታ ላይ ያተኮረ መንግሥት ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት  (βασιλεία τοῦ Θεοῦ) በሰው ልጆች አስተዳደራዊ መዋቅር ተዋረድ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን በጸጋ ሥጦታ አማካኝነት በተከፈለ የደም መሰረት ላይ የጸና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ምሥጢር የሚተዳደር መንግሥት ነው። ቤተ ክርስትያን “ሞቱን እየተናገረች እና ትንሳኤውን እያከበረች” እርሱ ዳግም እስከሚመጣ ድረስ የሰው ልጆችን በሙሉ ወደዚህ መንግሥት ለመሰብሰብ በተልዕኮ ላይ ናት። በዚህ ተልዕኮ ውስጥ በምሥጢረ ጥምቀታችን ጸጋ የተነሳ ሁላችንም የክርስቶስ ወንጌል አምባሳደሮች እና ባለ ዐደራ ሆነን “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን” (2ኛ ቆሮ 10፡5)።

በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው በኩል የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን፣ የልጅነት የመጀመርያው ተግባራችን በሁሉ የፍጥረት በኩር የሆነውን ክርስቶስን መምሰል ነው። እርሱን በመሰልንበት ሕይወት ሁሉ የእርሱ መልእክት የእኛም ይሆናል! የቤተ ክርስትያን የወንጌል ተልዕኮ ከሁሉ በፊት ጌታዋን እና አዳኟን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰሏ ነው። በዚህም ቤተ ክርስትያን በወንጌል ተልዕኮዋ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያለውን ራዕይ ልትካፈል እና እርሱንም በትውልድ መካከል ልትመሰክር ተጠርታለች።

ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰው ልጅ በሁለንተናው በቀጣይነት የሚታነጽበት የሕይወት ዘመን ጉዞ አድርጎ ያቀርበዋል (ሉቃ 13፡6-9)። ኢየሱስ ወደዚህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንድንገባና በሕይወታችን ጉዞ በሙላት እንድንረዳው ጋብዞናል። በዚህ መንገድ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደፊት የሚገለጥ፣ በተስፋ ብቻ የምንመለከተው ምሥጢር ሳይሆን ይልቁንም ፍጥረት በእግዚአብሔር ፍጻሜ ላይ እስኪሆን ድረስ ያለማቋረጥ የሚገለጥ በእያንዳንዳችን ጥምቀት የሕይወታችን ክፍል ሆኖ የተዋሃደን አሁናዊ እውነታ ይሆናል። በዚህም የሰው ልጅ እንደ እግዚአብሔር አሳብ እየተመላለሰ የእግዚአብሔርን ታማኝነት፣ ፍትህ፣ ሰላም እና ፍቅር እየተለማመደ “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ይበረታ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሶ ይሞላ ዘንድ” (ኤፌ 3፡19) በሁለንተናው ይታነጻል።

ቤተ ክርስትያን በወንጌል ተልዕኮ ሰንበት በእግዚአብሔር ቃል ኃይል በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ሥጦታ ስለሚከናወነው የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕንጽት ትጸልያለች፤ በዚህ ሰንበት እርሷ ራሷ ደግሞ በትውልድ መካከል ኃይል የሚሰጣትን እና የሚቀድሳትን የእግዚአብሔር ቃል እየመሰከረች እና እየኖረች በሁሉ ነገር ራስ እና አዳኝ ወደሆነላት ወደ ተስፋዋ ፍጻሜ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ታድጋለች። በዚህ በወንጌል ተልዕኮ ሰንበት ቤተ ክርስትያን ዛሬም የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ለመሆኑ ተቀዳሚ ምሥክር ሆና በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ የሰውን ዘር በወንጌል የምሥክርነት ኃይል ሁሉ ወደ ጽድቁ መንግሥት እየሰበሰበች፣ በምሥጢራት እየቀደሰች እና የእግዚአብሔርን መንጋ በለመለመ መስክ እያሰማራች በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ በማመን እና በመታመን “ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ና!” እያለች ትዘምራለች!

ሴሞ