እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

በእምነት የመቆም ጽናት!

በእምነት የመቆም ጽናት!

ጽናትኢየሱስ መስቀል ሥር የእሱ ሆነው ጸንተው የተገኙትን ሰዎች ቁጥር ስናስተውል አምስት አካባቢ እንደነበሩ ራሱን “ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ብሎ የገለጸው ቅ. ዮሐንስ ወንጌላዊ ይነግረናል። ያ ሁሉ ከመስቀሉ ጥቂት ቀናት በፊት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! እያለ በግለት የጮኸ ሕዝብ የት ገባ? ልብሳቸውን እያነጠፉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለቡ ጌታ፣ ጌታ… ያሉት የት ደረሱ? ካንተ በፊት እኛን ያሉ ደቀ መዛሙርቱስ? እኛ እያለን እንዴት ይሆናል ብለው ካራ የመዘዙትስ?

ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ በጭንቋ የመስቀል ሰዓት ሌሎቹ የሄዱበትን፣ የሸሹበትን ከመንገር ይልቅ በመስቀሉ ሥር የተገኙትን አምስት ሰዎች መዘርዘር ቀሎታል፤ ምክንያቱም የበለጠ የሚጠቅመን አብነታዊ ተከታዮቹን ማየት ስለሆነ ነው። በመስቀል ፊት መገኘት፣ መቆም የሁሉም ወይም የብዙዎች አይደለም፤ በጥልቅ ማየትን፣ ማሰላሰልን ይፈልጋል።

“…በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።  ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት።  ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።” (ዮሐ 19:25-27)

በሰው ልጅ ኑሮ ውስጥ ትልቅ ውርስ ብለን ልናስበው የምንችለው ነገር ምንድነው? ምናልባት ሪከርድ የያዘ ግዙፍ ውርስ የወረሱ ብለን አሰሳ ብናደርግ በብር፣ በንብረት፣ በርስት የሚገለጥ ይሆናል ...  ክርስቲያኖች ግን ክርስቶስ የመጨረሻ የመስቀል ሰዓቱ ላይ ሆኖ ልዩ አደራና ውርስ ትሆነው ዘንድ ለቅዱስ ዮሐንስ በሱም በኩል እናት ትሆነን ዘንድ ቅድስት እናቱን ሰጠን፤ እናትነቷም ልዩ የሚሆነው የራሱ የክርስቶስ እናት መሆኗ ነው!.…

እኛም በክርስቶስ የተሰጠችን እናታችን ናት ስንል ይህንን የክርስቶስን ስጦታ መቀበል መቻል ነው፤ ውርሱን ማክበር ነው! ስለዚህም ማርያምን ስናስብ ምን ዓይነት እናት ናት ብንል የእምነት፣ የጽናት፣ የፍቅር፣ የመሰጠት፣ የማዳመጥ፣ ከክርስቶስ ጋር የመኖር.... በእምነት ያለመታከትና የትእግሥት መስትዋት የሆነች እናት!

ክርስትና ከመስቀል የመሸሽ ሳይሆን መስቀልን የመሸከም እምነት እንደሆነ ክርስቶስ ራሱ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ገልጾታል። መስቀል ሥር መገኘት እንደው በድንገት እዛጋር መሆን ሳይሆን በንቃት፣ በፍቅር፣ በልብ የእግዚአብሔርን ነገር እያሰላሰሉ በትርጉም መገኘት ነው። መስቀል ለእመቤታችን ልታየው ደስ የሚላት፣ እንደማንኛውም እናት ለልጇ የምትመኝለት ነገር አይደለም፤ ሆኖም ያዙኝ ልቀቁኝ፣ ልጄን ልጄን፣ እሱ የዋህ ነው ልቀቁት… ብላ ጮኸች አይለንም ወንጌሉ፤ ነገር ግን በመሥቀሉ አጠገብ ቆማ ነበር! ሰው በአስጨናቂ፣ በዘግናኝ፣ በአስፈሪ ነገር ፊት በንቁ አእምሮ መቆም ተፈጥሯዊ አይደለም፤ አንድም ይሸሻል፣ ወይም ይዋጋል፣ መልሶ ያጠቃል አሊያም ራሱን ስቶ ይዝለፈለፋል፣ ይደነዝዛል። ነገር ግን እመቤታችንና አጠግቧ ያሉ ጥቂት የእምነት ሰዎች ቆመው ነበር።

ሕይወታችንን ስናይ ብዙ ጊዜ በመስቀል ፊት የመቆም ብርታት ላይኖረን ይችላል፣ በብዙ አጋጣሚ ከእምነታችን ርቀን፣ ሸሽተን ሊሆን ይችላል። አንዳንዴም በሃይማኖት ስም ከመስቀል ላይ ካለው ክርስቶስ ወደምንፈልገው ዓይነት ክርስቶስ መሄድ ያጋጥም ይሆናል። ግን ክርስትና በክርስቶስ ፊት መገኘትን ይፈልጋል፤ እኛ በፈለግነው ዓይነት ክርስቶስ የጎዳና፣ የሆይታ፣ የእልልታ ብቻ ሳይሆን የመስቀሉ ላይ ክርስቶስ አጠገብ መገኘትም ያስፈልጋል፤ አንዳንዴም እዚህ ግባ በማይባል ዓይነት ሰበብ እምነታችንን መተው ሊከሰት ይችላል፤ ነገር ግን ክርስትና በመስቀል ፊት መቆምን ይጠይቃል። በእንደዚህ ዓይነት የእምነት ጽናት ላይ ክርስቶስ ተናገረ፣ “እነሆ ልጅሽ፣ እነኋት እናትህ!” ።

ቅዱስ ሆሴማሪያ ኤስክሪቫ ስፔናዊ ካህን በ1965 ዓ.ም. ያረፉ በዓለም ኑሮ ውስጥ በተለይም በሥራ ሕይወታቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነትን በማሳደግ በነገሮች ሁሉ ቅድስናን መሻትን እንዲለማመዱ የሚያግዝ “የአምላክ ሥራ” የሚባል መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መሥራች፤ “ፍኖት” በተሰኘው መጽሐፋቸው “መጀመር የሁሉ ነው፤ መጨረስ ግን የቅዱሳን ነው” ይላሉ። ቅዱሳን ስለሆኑ ጨረሱ፣ ጸኑ ብለን ልናስብ እንችላለን፤ ነገር ግን ስለ ጸኑ፣ ስለ ታገሱ፣ በዓላማቸው ወይም “መንገድ” በሆነው በክርስቶስ እውነታ ስለተጓዙ ነው ቅዱሳን የሆኑት። እናም የኛም ክርስትና ለመጀመር ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የመጓዝ ነው።

የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ከሚለማመዳቸው ነገሮች ውስጥ እንደ ፈተና ሊሆኑበት ከሚችሉ ነገሮች አንዱ በጀመረው ነገር በጽናት የመቀጠል እውነታ ነው፤  በተለያዩ አጋጣሚዎችና ጊዜዎች ወይም የእድሜያችን እርከኖች ብዙ ነገር ጀምረን ግን በተለያየ ምክንያት ያለመቀጠል፤ ያለመዝለቅ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል።  

የእምነት ሕይወታችንም እንዲሁ “ሞቅ በረድ፣ ያዝ ለቀቅ” የሆነበት ሂደትም ሊኖር ይችላል። ብዙዎች ይጀምራሉ ጥቂቶች ይቀጥላሉ፣ ይዘልቃሉ። ካስተዋልን ብዙ ጊዜ ስንጀምር ብዙ ነበርን፤ ብዙ ሆነን ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ማገልገል፣ ጀምረናል፤ ዛሬ ግን ከነዚያ ውስጥ ብዙዎች በዚያ መንገድ የሉም፤ ምናልባትም የመጀመሪያ ቅ. ቁርባን ስንቀበል፣ ቅ. ሜሮን ስንቀባ ብዙዎች ነበርን ዛሬ ግን አንዱም ሌላዋም እያልን ልንገልጽ የምንችላቸው ከእምነት፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከምሥጢራት የራቁና የጠፉ ይኖራሉ። የእምነት ሕይወት የሆነ ሰሞን ግለትንና ትጋትን ሳይሆን ጽናትን ይፈልጋል፤ ምክንያቱም የዘለዓለማዊነት ጥሪ ነውና።

ክርስቶስም በዳግም ምጽአቱ ሊሆን ስላለው ነገር ሲያስተምር “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” (ማቴ 24:13) እንዲሁም በዮሐንስ ራእይ 2:10 “እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” ይላል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጽንሠቷ እስከ ፍልሠቷ ይህን እውነት በፍጹም መገለጫው የምትመሰክር እናት ናት፤ ላስተዋለው ማንነቷ ብዙ ክርስቲያናዊ እውነታን፣ ቅድስናን የሚያስተምር ሕይወት የኖረች የመጀመሪያ “ክርስቲያን” ናት፤ ክርስቲያን ክርስቶስን የሚከተል ማለት ነውና፣ የመጀመሪያ ደቀ መዝሙር ናት፣ ክርስቶስን የምትሰማ ናትና።

በክርስቶስ ፍቅር መኖራችን ሲፈተን ወደ ሌላ የመዞር ነገር አለ፤ ቅዱስ ጳውሎስም “ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” 1ቆሮ 15:58 እንዲሁም ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ።” 16:3 ይለናል።

እንደዚህች ዓይነት እናትን የጽናት ምሳሌ ሆና የምናይበት ልዩ የወንጌል ክፍል ደግሞ መግቢያችን ላይ ያነበብነው የዮሐንስ ወንጌል 19:25-27 ነው። በመስቀሉ ሥር ቆማ ነበር! ሰው በሚያስጨንቀው፣ በሚያስደነግጠው ነግር ፊት ሊሆን ከሚችላቸው ነገሮች በተቃራኒው “ቆማ” ነበር! በፈተና ውስጥ፣ በጥላቻ ውስጥ፣ በጽናት በፍቅር፣ በትእግስት የምንኖርበትን ጸጋ እመቤታችን ታማልደን፡

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት