እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የጌታችን  የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የእግዚአብሔር ምሕረት ሥጦታ ነው

የጌታችን  የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የእግዚአብሔር ምሕረት ሥጦታ ነው!

በሀገራችን የሥርዐተ አምልኮ ዑደት ውስጥ ፍሬ የሚታይበት፣ ምድር በአበቦች የምትንቆጠቆጥበት ጊዜ ዘመነ ጽጌ ተብሎ ይታወቃል። ዘመነ ጽጌ የመኸር ወቅት በመሆኑ ምርት ይሰበሰባል፤ ምድር ፍሬ የምትሰጥበት፣ እግዚአብሔር ሰውንም ሆነ እንስሳን የሚመግብበት እና በምድራዊ በረከት የሚያጠገብበት ወቅት ነው። ቅዱስ ዳዊት ስለዚህ የእግዚአብሔርን በረከት በማመስገን እንዲህ እያለ ይዘምራል “ተራሮችን ከላይ ያጠጣቸው ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች፤ እንጀራንም ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፤ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል” (መዝ103፡13)። እግዚአብሔር በዚህ በምድራዊ በረከት እንደባረከን (መዝ 66፡6-7) ሁሉ በሰማያዊ በረከትም ይባርከናል። ይህ የዘመነ ጽጌ ወቅት ከተገባደደ በኋላ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ በረከቷን ለመቀበል ትዘጋጃለች። ይህ የዝግጅት ጊዜ የስብከተ ገና ወራት ወይም ጾመ ነብያት በመባል ይታወቃል። የብሉይ ኪዳን ነብያት መሲሑን ለማየት በታላቅ መንፈሳዊነት ይጠበበቁ ነበር። ይህ የነብያት በተስፋ የተሞላ መጠባበቅ በዛሬው ዘመን ለምንኖር የሰው ልጆች ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት ለማክበር ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ መሰናዶ ያሳስበናል።

በመሥዋዕተ ቅዳሴ ውስጥ ተገልጦ እንደምናገኘው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከነብያት እና ከፃድቃን አልፎ ለእኛ ተሰጥቶናል። ካህናት በመሥዋዕተ ቅዳሴ ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በመድገም “ብዙዎች ነብያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ማየት ወደዱ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትን መስማት ወደዱ ነገር ግን አልሰሙም፤ የእናንተስ ያዩ ዓይኖቻችሁና የሰሙ ጆሮዎቻችሁ የታደሉ ናቸው” በማለት የተሰጠንን ዕድል ታላቅነት ይመሰክራሉ። ይህ ሥጦታ ከእርሱ ጋር በበርካታ ነገሮች የሚሞላን ሥጦታ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ በመገንዘቡ “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ” (ኤፌ 1፡3) እያለ ምሥጋናውን ያቀርባል።

የገና ጾም ይህንን መንፈሳዊ በረከት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያደረገውን ምሕረቱን እና ፍቅሩን የምናመሰግንበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ የዝግጅት ጊዜ ሕፃኑን ኢየሱስን የምንቀበልበት መንፈሳዊ ማንነት ውስጥ ለመገኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የገና በዓል›› በሚል መጠርያ የምናከብረው በዓል ብዙውን ጊዜ በቁሳዊ ዝግጅት የተዋጣለት በዓል እንዲሆን በርካታ ጥረቶችን እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ይህ ከንቱ እንዳይሆንብን መንፈሳዊውን ኃብት ለማግኘት ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ዘወትር ስለ መንፈሳዊ ትሩፋት እንድንዘጋጅ ይናገራል ‹‹ እናንተ ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ ሌላው ነገር ሁሉ ይጨመርላኌል›› (ማቴ 6፡33)፡፡  

“እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድያ ልጁን ሰጠ›” (ዮሐ3፡16) ይህ የእግዚአብሔር ሥጦታ ከሁሉ ነገር በላይ የሆነ ሁሉን ነገር የሚጠቀልል ሥጦታ ነው። አምላክ ፍቅሩን የገለጠልን ራሱን ለእኛ በመስጠት ነው። ከራሱ በላይ ምን ሊሰጠን ይችላል? የሰውን ልጅ እውነተኛ ፍላጐት የሚያረካው ሥጦታ ይህ ነው። ቅዱስ አውጉስጢኖስ  ‹‹ለአንተው ፈጥረኸናልና ልባችን አንተን ካላገኘ በስተቀር ዕረፍት የለውም›› ይላል። የሰው ልጅ በውስጣዊ ማንነቱ አምላኩን ይፈልጋል። የሰው ልጅ የነፍስ ጥያቄዎቹን የሚመልስ እና ውስጣዊ ጥማቱን የሚያረካ፣ ሰብዓዊ ጉድለቱን የሚሞላለትን ነገር ይፈልጋል።

በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መጽሐፍ ሙሽራይቱ “በአፉ መሳም ይሳመኝ ፍቅሩ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጣፋጭ ነውና” እያለች (መኃ 1፡1) ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን የመሲሁን መምጣት በመናፈቅ ይህንን መዝሙር ስትዘምር የልቧን መሻት ገልጣ ትናገራለች። ሙሴ መናገር የማይችል ኮልታፋ ነው፣ ኤርሚያስ ገና ትንሽ ብላቴና ነው፣ ኢሳያስም ከንፈሮቹ የረከሱበት ሰው ነው፣ ዮሐንስም ‹‹ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ›› እያለ በበረሃ የሚጮህ ድምፅ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነብያት ስለ እርሱ የተናገሩለት ይምጣ እያለች ትዘምራለች! የነብያት ትንቢት ስለ መሲሑ የሰጡት ምሥክርነት ሙሽራይቱ በይበልጥ ሙሽራውን እንድትናፍቅ አድርጓታል። በእርሱ ካልሆነ በስተቀር የውስጥ ፍላጐቷ እንደማይሞላ አውቃዋለችና መብራቷን ይዛ እርሱን ትጠባበቃለች።

ነገር ግን ይህ ሙሽራው የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ጥያቄአችንን ተቀብሎ መልስ ይሰጠናል፡፡ “ጊዜው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላ 4፡4) በዚህ በቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ ላይ እያሰላሰልን ሌላ ጥያቄ ወደ አዕምሮአችን ይመጣል። “ጊዜው በደረሰ ጊዜ” የትኛው ጊዜ? ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለብን። ስለዚህ ወደ ወንጌል ተመልሰን ይህ ጊዜ የትኛው እንደሆነ እንጠይቃለን።

ይህ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያረጋግጥልን “የተወደደችው የጌታ ዓመት” (ሉቃ 4፡17-19) ናት። ይህቺ የተወደደችው የጌታ ዓመት ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ የምህረት ፊት ሆኖ የተገለጠባት ዓመት ናት። ይህቺ የተወደደችው የጌታ ዓመት “ቃል ሥጋ የሆነባት እና በመካከላችን ያደረባት” (ዮሐ 1፡14) ናት። ሥጋ የለበሰው ቃል በመካከላችን ባደረበት ጊዜ ስሙ አማኑኤል ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው (ማቴ 1፡23)። እንግዲህ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነው ምሕረቱን ለመሥጠት ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንኑ እውነታ በምሥጋና መዝሙሯ ውስጥ እንዲህ እያለች ታረጋግጥልናለች፡- “ለአባቶቻችን እንደተናገረ ለአብርሐምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እሥራኤልን ብላቴናውን ረድቷል” (ሉቃ 1፡55)።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር የሚኖረንን ግንኙነት መለስ ብለን ማየቱ ጠቃሚ ነው። ሕፃኑ በመካከላችን መገኘቱ የምሕረት ሥጦታ በመሆኑ እኛም ለዚህ ሥጦታ ምላሽ ማዘጋጀት አለብን። ይህ እኛ ለሕፃኑ የምናዘጋጀው ሥጦታ ምን ሊሆን ይችላል? ከምሥራቅ የመጡት የከዋክብት ተመራማሪዎች ለሕፃኑ እጅ መንሻ እንዳቀረቡ ሁሉ እኛም ልናቀርብ ይገባናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሥጦታ በሚመለከት ሲነግረን “ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ያደረጋችሁት ነገር ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” (ማቴ 25፡40) ይላል፡፡ ይህን የኢየሱስን ምክር ተቀብለን የምናደርገው ነገር አውቀናል። ይህም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን መልካም ነገር ማድረግ እንደሆነ ተነግሮናል። ብዙውን ጊዜ ይህ ለሌሎች የምናደርገው “መልካም ነገር” ከቁሳዊ ልግሥና ጋር ብቻ ተያይዞ ይተረጎማል።

ይህ አይነቱ አተረጓጎም የተለመደ ነው፤ ድሆችን ማብላት፣ የታሰሩትን መጠየቅ፣ ሕሙማንን መጎብኘት፣ የተቸገሩትን መርዳት ወ.ዘ.ተ. መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ኢየሱስ ከዚህ በፊት መከናወን የሚገባው ዐብይ ቁምነገር እንዳለ ይነግረናል።እነዚህን ሁሉ መልካም ተግባራት ከመፈጸማችን በፊት ምን እናድርግ? ኢየሱስ ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ተገቢ የሆነውን ምላሽ ሲሰጥ “እንግዲህ መባህን በመሰዊያው ላይ ብታቀርብ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ በዚያ በመሰዊያው ፊት መባህን ትተህ ሒድ፤ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” (ማቴ 5፡23) በማለት ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እንደሚወድ ያሳስበናል። ቅዱስ ዳዊት በታላቁ የንስሐ መዝሙሩ ማገባደጃ ላይ “መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት አያሰኝህም፤ የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው” (መዝ 51፡18-19) በማለት ንስሐ ከመሥዋዕት እንደሚቀድም ይናገራል። የጌታች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በምሕረት የምንገናኝበት በዓል ይሆን ዘንድ ኢየሱስ ራሱ “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ” (ሉቃ 6፡36) በማለት ይጋብዘናል፡፡

በዚህ የልደት በዓል ዝግጅት ወቅት ለሌሎች ሰዎች ከምናደርጋቸው ነገሮች ባሻገር ሌሎች ለእኛ እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን በትህትና ለመጠየቅ እና የሚደረግልንን መልካም ነገር በአመስጋኝነት መንፈስ ለመቀበል መዘጋጀት አለብን። ይህም ማለት ወንድሞቻችንን ይቅር እንደምንለው ሁሉ እኛም የሌሎችን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብለን ምሕረት ለመስጠት በራችን ክፍት መሆን አለበት ማለት ነው። ይቅርታን መቀበልና ምሕረትን መስጠት የኢየሱስ አምባሳደር የመሆናችን ምልክት ነው። የኢየሱስ አምባሳደር መሆን ማለት ከሁሉ በላይ የምሕረት፣ የዕርቅ እና የይቅርታ አምባሳደር መሆን ማለት ነው።

የምሕረት፣ የዕርቅ፣ የይቅርታ እና የሰላም ሥራ የኢየሱስ ተልዕኮ እሴት ነው። ይህ እሴት የኢየሱስ ተልዕኮ ባሕርይ መሆኑን ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ራሱ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጣ” ( ሉቃ 19፡10) እያለ ይነግረናል። የኢየሱስ ተልዕኮ ምሕረትን መስጠት በመሆኑ የጠፋውን የሚፈልግበትና የሚያድንበት መለኮታዊ መሳሪያው ምሕረት ነው።  ኢሳይያስ በተስፋ ስለሚጠባበቀው እና እጅጉን ለማየት ስለሚናፍቀው መሲሕ ማንነት ሲናገር “ህፃን ተወልዷልና ወንድ ልጁም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል... ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም..(ኢሳ 9፤67) እያለ ኢየሱስ የሚሰጠው ሰላም ለዘላለም የሚዘልቅ እና በምንም ነገር የማይናወጥ መሆኑን ይመሰክራል።

የኢየሱስ ተልዕኮ ይህ ነው። እርሱ የሰላም አለቃ ነው፤ ሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የኢየሱስ ተከታይ የሆነ ሰው ጥሪ የዚህ ሰላም ተባባሪ መሆን ነው። ኢየሱስ እያዳንዱን ሰው በሰላም ይማርካል፤ የእርሱ የሆኑትም ሁሉ ‹‹ሰላም›› ኃብታቸው ሊሆን እንደሚገባ ይናገራል። ከሐዋርያቱ ተለይቶ ወደ አባቱ ክብር ለመግባት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የተወላቸው ኃብት ሰላም ነው፡፡ “ሰላምንም እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም አንደሚሰጠው አይነት አይደለም›› (ማቴ 14፡27) ይህ ሰላም ከምሕረት ጋር የተያያዘ ሰላም ነው፤ ምሕረትን በመቀበልና ምሕረትን በመስጠት የሚገኝ ሰላም ነው። በምሕረት ስለተከበበ ለሰላሙ ፍፃሜ የለውም። ዓለም የሚሰጠው ሰላም በፍርድና በቅጣት፤ በኃይል እና በሕግ የታጠረ ነው። የኢየሱስ ሰላም ግን እንዲህ አይደለም፤ የእርሱ ሰላም በምሕረት፣  በይቅርታ እና በዕርቅ የተሞላ ነው፤ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምሥክርነቱን ሲሰጥ “የማጥቂያም ሆነ የመከላከያ መሳርያችን ጽድቅ ነው” ይላል።

ይህ ሰላም ከኢየሱስ ጋር ከመገናኘት እና የእርሱ ደቀመዝሙር ከመሆን የሚመነጭ ነው። በመሠረቱ ሰላም ከመንፈሳዊ ጤንነት ጋር የተያያዘ ነው። የእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ጤንነት ሲጎሳቆል በየዘርፉ ሰላም መደፍረስ ይከሰታል። የሰላም አለቃ የሆነው ጌታ ባለሟሎች የሰላም መሣርያና አገልጋዮች መሆን አለባቸው፤ ነገር ግን ከአለቃው ጋር ያላቸው ጤናማ ግንኙነት መደፍረስ ሲጀምር ከእርሱ ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳቸው የነበራቸው ሰላም ይጠፋል። ስለዚህ ለእውነተኛ ሰላም መስፈን የእያንዳንዳችን ልብ መመለስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር መታረቅ ከፍተኛ አስተዋጾ አለው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ የመጀመርያ ቃላችሁ ‹ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን› የሚል ይሁን፤ በዚያ ሰላም የሚወድ ሰው ቢኖር የእናንተ ሰላም ያርፍበታል” ይላል። ሰላም የሚወድ ለሰላም የሚሰራ ነው፤ ሰላም በውጫዊ ኃይል በእኛ ላይ የሚጫን ቂም ነገር ሳይሆን የእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ጤንነት ነጸብራቅ ነው። የእያንዳንዳችን ሰላማዊ ጡብ የሰላም ድልድይ ይገነባል፤ ስለዚህም “ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑ የእኢየሩሳሌምን ቅጥር እንስራ!” (ነህ 2፡17)።

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት