ልደት በመጣንበት መንገድ የማንመለስበት ጥሪ ነው!

ልደት በመጣንበት መንገድ የማንመለስበት ጥሪ ነው!

IMG-20221223-WA00041የሰው ልጅ የተፈጠረበት የሕይወት ቁም ነገር በረከት ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር የመጣበትን የፍጥረት ሕላዌ  ገጸ በረከት አድርጎለታል። በመሆኑም የሰው ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርኳል (ኤፌ 1፡3)። በእርሱ ፊት “ቅዱሳን እና ነቀፋ የሌለብን፣ በፍቅር ሆነን” እንገኝ ዘንድ “በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ” እንዲህ ላለው የቅድስና ሕይወት እና በረከት የመሆን ጥሪ የተገባን እንሆን ዘንድ “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” ቀዳሚ እና ተከታይ በሌለው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በተፈጸመው ኪዳን “በኢየሱስ ክርስቶስ በተደረገ ቤዛነታችን” አስቀድሞ ለበረከት ወስኖናል።

በዚህ አይነት ከምድር አፈር በተወጠነ ሥጋ "አዳም" ተብሎ በተጠራው እና ሕያው በሆነው የመጀመርያው ፍጥረት በኩል ሳይሆን ይልቁንም ሕያዋን ለሚሆኑ ሁሉ ሕያው የሚያደርግ የሕልውና ምንጭ እና ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ በሆነው (1ቆሮ 15፡45) በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አዲስ ፍጥረት ሆነን ለበረከት እና ለጽድቅ ሕይወት ሙሽርነት ታጭተናል።

ኃጢአት የሰውን ልጅ ክብር ያጎሳቆለበት የሞት መውጊያው በግሪክ ፍልስፍና ሊታረቅ ወይም ደግሞ በብሉይ ኪዳን አማልክት መሥዋዕት ሊፈወስ አይቻለውም፤ የዚህ ኃጢአት የመጨረሻው ወደብ ዘላለማዊ ጥፋት ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የፍጥረቱን ዓላማ ስለሚያከብር እኛ ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ይልቁንም ስለተፈጠርንበት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ጽድቅ እና ስለ ስሙ ክብር ወደ ሕይወት ሁሉ ምንጭ ይመልሰ ዘንድ እግዚአብሔር ራሱ እንደ እኛ ሰው ሆኖ ተገለጠ፤ በእርሱ ሰው ሆኖ መገለጥ ምሥጢር ውስጥ በቅድስት ሥላሴ መካከል የተፈጠርንበት የ“ሰው”ነት ጸዳል፣ የተፈቀርንበት ልጅነት፣ የተከበርንበት ጸጋ እና ለዘላለማዊ ዓላማ የታየንበት ክብር ሁሉ ተመልሶልናል።

የጌታ መምጣት የሰው ልጆችን ከአዳም ኃጢአት በፊት ወደነበሩበት ክብር ለመመለስ ሳይሆን ይልቁንም አዳም ይደርስበት ዘንድ በእግዚአብሔር ልብ ወደታየለት የክብር ስፍራ እና የሕይወት አክሊል ሁሉ ፍጻሜ እንደርስ ዘንድ ነው። አዳም በዔደን ገነት መኖሩ የክብር ጉዞው ጅማሬ እንጂ እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ለእርሱ ያዘጋጀለት እና ለእርሱ የሚያስባት ሐሳብ ፍጻሜ አልነበረም። እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ለእያንዳንዳችን ወዳያት የክብር ተስፋ ፍጻሜ የሚያደርሰው ብቸኛ መንገድ በዚህ የክብር ሥፍራ የከበረው “ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ፣ ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ የሆነው፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል፣ እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉት፣ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ የሆነው፣ በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት የያዘ፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ የሚወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ የሆነው (ራዕ 1፡13-16)  ያለው እና የነበረው፣ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፣ አልፋ እና ኦሜጋ እኔ ነኝ እያለ የሚናገር ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

በኃጢአት ምክኒያት የጠወለገው የተፈጠርንበት የክርስቶስ መልክ፣ የሕልውናችን ቀመር የሆነው በውስጣችን ያለው የእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል ሊታደስ እና ሊፈወስ የሚችለው እግዚአብሔር ራሱ ሥጋ ለብሶ በዚህ የሰው ልጅ መልክ በመገለጡ ምሥጢር በኩል ብቻ ነው። የተፈጠርንበት በአምላክ ኅሊና ውስጥ ያለን የ"ሰው”ነት ክብር ምን እንደሆነ ማስተዋል እና ክብራችንን ማወቅ እንችል ዘንድ እርሱ ራሱ ሰው ሆኖ ተገልጧል። የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ጌታ በምን አይነት ፍጹም ሰው‘ነት እንደተገለጠ ሲናገር “ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና” (ዕብ 2፡14) እያለ የጌታን ሰው መሆን ጥልቀት ያብራራል። ይህ የዕብራውያን መጽሐፍ ጌታ "በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል የተገባው ሆነ" እያለ በአንድ በኩል ከዘላለም ጀምሮ የጌታ ወንድሞች መሆናችንን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታ በፍጹም ሰው‘ነታችን እኛን ለመምሰል እንዳልተጠየፈን እንድንመለከት ይጋብዘናል። በኃጢአት ምክኒያት የተበላሸውን ፍጥረት ከጥልቁ ለማዳን እና ከውስጡ ለመፈወስ ኢየሱስ በሁሉ ነገር እኛን መሰሏልና በሀገራችን ሥርዐተ አምልኮ በማርያም ቅዳሴ “ምግብን በመሻት እንደ ሕጻናት አለቀሰ” እያለን ድንቅ ትህትናውን እናሰላስላለን።

በዚህ ትህትናው ልክ ዝቅ ብለን በቅርበት እናየው ዘንድ ሕጻን ሆኖ በበረት ተኝቷል። በዚህ ትህትናው ልክ ዝቅ ብሎ ቀርቦ የማያየው ሰው በመስቀል ላይ ከፍ ብሎ ሲሰቀል አይቶ ለመለየት እንዳይቸገር ከመስቀል ከፍታ በፊት በግርግም ውስጥ የከፍታ መንገድ ሁሉ እናት እና አስተማሪ የሆነውን መለኮታዊ ትህትና ያስተምረናል። የጌታ ልደት የትህትና ትምህርት ቤት ነው፤ ትሑት መሆን የሚፈልግ ቢኖር ጌታ ያለበትን ስፍራ ያስተውል!

እረኞች የተነገራቸውን የምሥራች ለመመልከት እና ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት ወደ እርሱ ሲመጡ እርሱ በዚያ ነበር፤ ሰብዓ ሰገል ወደ እርሱ መጥተው የንጉሥነቱን እጅ መንሻ ሲሰጡት እርሱ በዚያ ነበር፤ የመጣ ሰው ሁሉ ያገኘው ዘንድ፣ ያገኘውም ሁሉ ቀድሞ በመጣበት መንገድ እንዳይመለስ አዲስ የሕይወት አቅጣጫ ይሰጠው ዘንድ (ማቴ 2፡12) እርሱ በበረት ውስጥ ትሑት ሆኖ ይጠብቃል። የመጣ ሰው ሁሉ ያገኘው ዘንድ፣ ያገኘውም ሁሉ ቀድሞ በመጣበት መንገድ እንዳይመለስ አዲስ የሕይወት አቅጣጫ ይሰጠው ዘንድ ዛሬም በምሥጢረ ንስሐ ይጠብቀናል! የመጣ ሰው ሁሉ ያገኘው ዘንድ፣ ያገኘውም ሁሉ ቀድሞ በመጣበት መንገድ እንዳይመለስ አዲስ የሕይወት አቅጣጫ ይሰጠው ዘንድ ዛሬም በቅዱስ ቊርባን በመንበረ ታቦት ላይ እያንዳንዳችንን ይጠብቃል!

መልካም የልደት በዓል!

ሴሞ