እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

“ዳግመኛ ኃጢአት አትሥራ!”

“ዳግመኛ ኃጢአት አትሥራ!” (ዮሐ 5፡14)

ክፍል ፩

sinጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከልዩ ልዩ እሥራት ነጻ ካወጣቸው እና ከፈወሳቸው በኋላ ለደህንንነታቸው መልካም ጤና እንዲጠቅም “ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ” (ዮሐ 5፡14፣ ዮሐ 8፡11) እያለ ያሳስባቸዋል። በወንጌላት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደምንመለከተው ጌታ በእያንዳንዱ ፈውስ ማሳረጊያ ላይ ይህንን መመርያ ሲናገር “ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ!”። የሰው ልጆችም በዕለት ተዕለት መስተጋብራቸው በንግግር መካከል በተለምዶ “ኃጢአት ውስጥ አታስገባኝ!” ሲባባሉ ማስተዋሉ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን ኃጢአት ምንድነው? ኃጢአት የሚደረግ እና የማይደረግ ተግባር ወይስ የሚኮን እና የማይኮን ማንነት?

ኃጢአት እግዚአብሔር ባልፈጠረው እና በማያውቀው ማንነት ውስጥ ሆነን እግዚአብሔርን ለመተዋወቅ መሞከር ነው፤ ኃጢአት ላልተፈጠርንበት ነገር የምንገዛበት ኃይል በመሆኑ ሁሉን ነገር በነፍስ ላይ እያራገፈ፣ ነፍስ እግዚአብሔር ባከበራት መልክ እና ውበት እንዳትገለጥ ይጋርዳታል። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ለዘላለማዊ ደስታ የተፈጠረ የእግዚአብሔር ፍቅር ነጸብራቅ ቢሆንም ቅሉ፣ የኃጢአት ጠባሳ እስካለበት ድረስ ይህንን የማንነቱን ክብር ትርጉም በምልዓት ለመኖር አይቻለውም። ምክኒያቱም ነጻ እና ደስተኛ የመሆን የመጀመርያው ምሥጢር እግዚአብሔር በእኔ ላይ ላለው ዓላማ መታዘዝ ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔር ለእርሱ ክብር ስለፈጠረን ለእርሱ መታዘዝ ባሕርያዊ ማንነታችን ነው። ነገር ግን በኃጢአት ጠባሳ አማካኝነት ተዓዝዞ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ስፍራ አላገኘም። የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክኒያት በእግዚአብሔር ላይ ፊቱን አዙሯል፤ የነፍሱ አቅጣጫ ኢ-መደበኛ እና ኢ-ተፈጥሮአዊ በሆነ ፈለግ መፍሰስ ጀምሮአል። በመሆኑም ለኃጢአት ሥርየት የሚከፈለው ዋጋ የሰውን ልጅ ነፍስ ወደ እግዚአብሔር አቅጣጫ የሚመልስ ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ ሁለንትና በአዲስ የመስቀል ላይ የፍጥረት ምጥ እንደገና የሚወልድ አዲስ ፍጥረት ነው።

የሰው ልጅ በገዛ ራሱ አቅም ስለ ኃጢአቱ ሊያደርግ የሚችለው አንዳች ነገር አልነበረውም፤ የብሉይ ኪዳን የእንሣት ደም መስዋዕትም ቢሆን የሰውን ልጅ በመላ ማንነቱ ወደ ነበረበት የክብር ልጅነት ሊመልሰው የሚችል ንጹህ ደም አልነበረውም። እያንዳንዳችን ስለ አዳም የውርስ ኃጢአት ቀርቶ ስለራሳችን የግል ኃጢአቶች እና መተላለፎች እንኳን በቅጡ ካሣ የምንከፍለው ነገር አልነበረንም። እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ወደ ፈጠረበት የክብር ዓላማ ለመመለስ እግዚአብሔር ራሱ ካልረዳን በስተቀር በሰው ልጅ ሁኔታ የሚሞከር አንዳች ቁም ነገር አልነበረም። ጌታ ይህንን ሁኔታ ሲገልጽልን በወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው “እውር እውርን ሊመራው ይችላልን?” በማለት ይጠይቃል።

እንዴት ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንዳለብን ለማሰብ አስቀድመን መንገዱን ማወቅ አለብን፤ ወደ የት ነው የምንመለሰው? በየት በኩል ነው የምንመለሰው? እንዴት አድርገን ነው የምንመለሰው? ለሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ ማግኘት ነበረብን። እግዚአብሔር አምላክ ለእነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች “ጊዜው በደረሰ ጊዜ” (ገላ 4፡4) የጥያቄዎቻችን ሁሉ የማያወላዳ ምላሽ፣ ከኃጢአት ባርነት አርነት እንወጣ ዘንድ የተገዛንበት ካሳ እና ወደተፈጠርንበት ክብር የምንገባበት የዋስትና ቤዛ አድርጎ አንድ ልጁን  ሰጠን። ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ክብር እንገባ ዘንድ አሁን “መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት” አግኝተናል (ዮሐ 14፡6)፤ በመሆኑም አሁን ለእግዚአብሔር ክብር ሕያው ሆነን እንኖር ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በኩል የዘላለም ልጅነት መብት አለን።

ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ወይም ደግሞ በሕይወታችን ቁም ነገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር ሆኖ መገለጥ ማለት እግዚአብሔር እንድንሆን ለፈጠረን ዓላማ ሆነን መኖር ማለት ነው። የሰው ልጅ በሙሉ ሰብዓዊነቱ ሲኖር የእግዚአብሔር ክብር እርሱ ነው። የእግዚአብሔር ክብር እንደ ሰው ለእግዚአብሔር የማደርግለት ነገር ሳይሆን፤ ይልቁንም የእግዚአብሔር ክብር የሚሆነው በእግዚአብሔር ፊት እንደ “ሰው” ፍጥረቴን አክብሬ የምኖረው፣ የልጁን ደም ዋጋ የሚያከብር ሕይወቴ ነው። የእግዚአብሔር ክብር እኔ ነኝ! የተፈጠርኩት ለደስታ ነው፤ ደስታ ስሜት እና እርካታ የሚፈራረቁበት የሕዋሳት ውዝዋዜ ጡዘት ሳይሆን፣ ደስታ እንደ እግዚአብሔር አሳብ መኖር ነው። በስብዕናችን ሙላት፣ እርሱ በሰጠን ሥጦታ፣ ፍጥረትን ሁሉ ለተፈጠረበት ዓላማ እየቀደስን፣ ነገርን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መንገድ እውነት እና ሕይወት በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ክብር አድርጎ መኖር ማለት ነው (ቆል 3፡23)። የእግዚአብሔር ክብር የሰው ልጅ በመላው ማንነቱ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅነት ክብር መገለጥ መቻሉ ነው።

ሕይወት ለእግዚአብሔር በቅንነት የምትመሰክር የእርሱ ድንቅ ሥጦታ ናት፤ በመሆኑም በውስጧ ፈጣሪዋን የምትፈልግበት የነፍስ ጥማት እና ፈጣሪዋን “አምላኬ እና መድኃኒቴ” እያለች የምታመሰግንበት ባሕርያዊ ማንነት አላት። ለእግዚአብሔር ተገቢ የሆነውን ምሥጋና አለመስጠት ወደ ስብዕና ምልዓት ያልደረሰ ሰው ምልክት ነው። “ሰው”ነት በመላ ማንነት እግዚአብሔርን ማክበር ነው። የእግዚአብሔር ክብር በእኛ ላይ አለመገለጥ ከተፈጠርንበት ዓላማ፣ ይልቁንም ከተቤዥንበት ክብር ዝቅ ብለን፣ በገበታ ከሚቀርበው የንጉሥ ልጆች ንጹህ ምግብ ሳይሆን በጠረጴዛው ሥር ሆኖ ወደ መሬት ከሚወድቀው ፍርፋሪ መሻማት እና ለአሳማዎች ከሚጣለው ለመመገብ መጎምጀት ነው (ሉቃ 15፡16)። እግዚአብሔር ለሰጠን ክብር ዋጋ አለመስጠት ከንጉሥ ገበታ ወርደን ለማያጠግብ ጥሬ ከእርያ ጋር ወደ መጋፋት ያወርደናል።

እግዚአብሔርን ማክበር ማለት ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችን በማያቋርጥ ክብር በፊቱ የሚገለጥበትን ኃይል ከእግዚአብሔር ለመቀበል ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት መሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የዚህ ዓለም መጋቢ ጭምር ነው። በመሆኑም አባትነቱን የሚቀበል መጋቢነቱን ደግሞ መቀበል አለበት። ጌታ ይህንን የአባቱን መጋቢነት ሲመሰክር እንዲህ ይላል “እንግዲህ ትንሹን እንኳን የማትችሉ ከሆናችሁ ስለምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፣ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን እንኳን በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን፣ ነገ ወደ እቶን የሚጣለውን፣ በሜዳ የሆነውን ሣር እንደዚህ የሚያለበሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?” (12፡26-28)። ስለዚህ በእግዚአብሔር ስንኖር በሕይወት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በተትረፈረፈ ሕይወት ለመኖር ተጠርተናል (ዮሐ 10፡10)። ወደዚህ በነገር ሁሉ ወደ ማበብ የማያመጣን ማንኛውም ተግባር ከተፈጠርበት ዓላማ ጋር የሚቃረን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው።

የእግዚአብሔር መጋቢነት በሕይወት እንድንቀጥል ጉልበት የሚሆነን የእግዚአብሔር አባታዊ ክብካቤ ጸጋ ነው። ከዚህ ጸጋ መለየት ማለት ሕይወትህን በገዛ እጆችህ ላይ መያዝ ማለት ነው፤ ከእግዚአብሔር ፊትህን ማዞር ማለት ከሕይወት ዛፍ መገንጠል ማለት ነው። ከእሳት መካከል ለብቻው ተገንጥሎ የወጣ ግንጥል ፍም ምንም ያህል የተቀጣጠለ ቢሆን እያደር መብረዱ እና ውሎ አድሮ መክሰሙ የማይቀር ሃቅ ነው። ኃጢአት ከተፈጠርንበት ዓላማ ዝቅ ያደርገናል። በመሆኑም ኃጢአት ይህንን ሥርዐት ማወክ፣ ይህንን ውበት ማደብዘዝ፣ በገዛ ራሳችን ራሳችንን ማቁሰል ማለት ነው። እያንዳንዱ ኃጢአት ከሁሉ አስቀድሞ ሰላም እና ደስታን ይነጥቀናል። ሰላም ነገሮች በእግዚአብሔር ፊት በተፈጠሩበት ዓላማ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥርዓት የተሰጣቸውን ተዋረድ ጠብቀው ለተፈጠሩበት ዓላማ የመዋላቸው ዑደት ሲሆን ደስታ ደግሞ ከዚህ ሥርዐተ ዑደት የሚመነጭ የነገሮች መስተካከልና ነገሮች በእግዚአብሔር ልብ ወስጥ ያላቸው ቅድም ተከተል በሕይወታችን ሲገለጥ የሚያስገኝልን በረከት ነው።

የተፈጠርንበት ዓላማ ለእግዚአብሔር ክብር ነው፤ ከእግዚአብሔር ክብር በታች ለሆነ ነገር ስንገዛ የዚያ ነገር ባርያ ወደ መሆን እንወርዳለን። ሁሉም ሥፍራውን ይዞ አንተ በሥፍራህ ላይ ካልተገኘህ ያለው ክፍት ቦታ ለባርነት ብቻ ነው። አንድ ጊዜ በኃጢአት ቀንበር ከተጠመድን ለመውጣት የምንቸገረው ኃጢአት የሆነ ነገር የማድረግ እና ያለ ማድረግ ጉዳይ ሳይሆን፣ ይልቁንም ኃጢአት ባርያ ሆኖ የመገዛት እና ያለመገዛት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በመሆኑነው። ኃጢአት “ሰው” የምንሆንበትን የጸጋ ሰብዓዊ ዐቅም ስለሚያቀጭጭ ለእግዚአብሔር እና ለእግዚአብሔር ነገር፣ ለከበረ ጥሪ እና ለሕይወት ነገር ሁሉ ልፍስፍስ ያደርገናል። የአዳም ኃጢአት ከሰውነት ተራ ያወረደን ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን መለኮት በሌለው ኃጢአተኛ ሥጋ የወለደን ክፉ ገዢ ነው።

ነገር ግን  የኃጢአት ካሣ መከፈል ያለበት ለምንድነው? እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ አልነበር? ኃጢአታችንን ያለምንም ዋጋ እንዲሁ ይቅር ቢለን ምን ችግር ነበረው? እንደውም ጨርሶ ቢረሳው አይቀልም ነበር? እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች በክፍል ሁለት ጽሑፋችን በስፋት የሚዳሰሱ ሲሆን በእነዚህ ክፍሎች ስለ ኃጢአት ምንነት፣ ኃጢአት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ስላሳደረው ጠባሳ እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በኩል ስለተደረገልን ፈውስ መሰረታዊ ግንዛቤ ለመስጠት እንሞክራለን።

ይቀጥላል...

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት