እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሁሉ ለበጎ ነው!

በአንድ ወቅት አንድ መንፈሳዊ አባት ከነበሩበት ቦታ ወደበረሃ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከቅዱስ መጽሐፋቸው ሌላ ሦስት ነገሮች ነበሯቸው። እነሱም፦ ቅዱስ መጽሐፉን በጨለማ ወቅት ለማንበብ የሚጠቅማቸው ቀንዲል(ኩራዝ)፣ ጎህ ከመቅደዱ በፊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሳቸው አንድ አውራ ዶሮ እና ለመጓጓዣነት የሚገለገሉበት አንድ አህያ ነበሩ።

 

መልካም እረኛአንድ ቀን ምሽት ከጉዞ የተነሣ በጣም ስለደከሙ እኚህ መንፈሳዊ አባት ወደ አንድ መንደር ቀርበው ማደሪያ ቢጠይቁም መንደርተኛው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማንም አልፈቀደላቸውም። ስለዚህም ከመንደሩ አቅራቢያ አንድ ጉድጓድ ያገኙና በዚያ ውስጥ ገብቶ ለማደር በመወሰን ገብተው አደሩ። እንደወትሮው ቅዱስ መጽሐፋቸውን ለማንበብ ቀንዲላቸውን ቢለኩሱትም የነበረው ብርቱ ነፋስ አጠፋባቸው፤ ስለዚህም ለመተኛት ጋደም እንዳሉ ተኩላ መጥቶ አውራ ዶሮዋቸውን፣ አንበሳም አህያቸውን በሉባቸው። የተደራረበ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሽማግሌው እርዳታን በመሻት ወደዚያ መንደር ቢመለሱ ዘራፊ ሽፍታዎች የመንደሩን ነዋሪዎች በሙሉ ገድለው ንብረት ዘርፈው ዓና መንደር ሆኖ አገኙት። ሽማግሌው ይህን ሁሉ ባጤኑ ጊዜ እግዚአብሔር ምን ያህል መልካም ነገርን እንዳሰበላቸው አስተዋሉ። በዚያች ምሽት በመንደርተኞቹ በአንዱ ቤት ቢያድሩ ኖሮ የዘራፊዎች ሰለባ ሆነው ሊገደሉ በቻሉ ነበር፤ ቀንዲላቸውንም ነፋስ ባያጠፋው የብርሃኑ ወጋገን እዚህ ጋር ሰው አለ በማለት ለሽፍታዎቹ ያሳብቅ ነበር። አውራ ዶሮዋቸውና አህያቸውም ባይበሉ ኖሮ ከሽፍታዎቹ ተደብቀው ማደር ባልቻሉ ነበር።


እግዚአብሔርን ለሚወዱ ሁሉ ነገሮች ዘወትር እንዲህ ውብ ናቸው። በሮሜ መልእክት ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደፈቃዱም ለተጠሩ ነገሮች ሁሉ ለበጎ እንዲደረግላቸው እናውቃለን” (8:28) ይላል። በርግጥ ከላይ ያነበብነው ታሪክ በተለያየና በግላዊ መልኩ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ተከሥቶ ይሆናል። ስንት ጊዜ በሕይወታችን “እግዚአብሔር እንዴት መልካም ነው!” ብለን ይሆን?መጀመሪያ እንዲህ ሲሆን እንዲህ ብዬ ነበር ግን ለካስ የምንልበት ጊዜም ጥቂት ላይሆን ይችላል። በሰዎች መካከል በዚህ ሁኔታ ልዩነት የሚፈጥር ነገር ካለ የተወሰኑ ሰዎች የእምነት ዓይናቸውን ተጠቅመው አስቀድመው ለበጎ ነው ሲሉ፤ አብዛኛዎቻችን ደግሞ ነገሩ ደቁሶ፣ አዳክሞንና ተስፋ አስቆርጦን ማክተሚያው ላይ ለበጎ ሲሆን ስናይ ከነበርንበት በመባነን “ለካስ!” እንላለን። ከነዚህ ከሁለቱ ዓይነት ደግሞ የከፋ ምርጫ የሚሆነው ለሚከሠቱት ነገሮች ሁሉ ውጫዊ ስሜቶቻችንን በማዳመጥ ብቻ “ክፉ” ብለን ላሰብናቸው ነገሮች ሁሉ ክፉን ለመመለስ መታጠቅ፤ አሊያም በውስጣችን ቂምና በቀልን ሰንቀን ስንቃችንን የምናራግፍበትን አጋጣሚ በመጠበቅ ውስጣችን እንደከበደ ከሸክም ጋር እንኖራለን።


ፀሐይ መኖሯን ወይም ደምናው በውሃ መልክ ዘንቦ መሬትን አረስርሶ ቡቃያ በቡቃያ እንደሚያደርጋት በመርሳት ደምናውን በማየት ብቻ በትካዜ መኖር የለብንም። እግዚአብሔር እኮ ለእኛ መልካምን ለማድረግ ወደኋላ ማለት አይሆንለትም፤ ሐዋርያው “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም” (ሮሜ 8:32)ይላል። ሳይሳሳ አንድያ ልጁን ከሰጠን በኋላ ምን ሊከለክለን ይችላል? ይህንን በመዘንጋት በሕይወት ለሚያጋጥሙን ክፉ ለምንላቸው ንገሮች ራስችንን ለክፉ ምላሾች በሌላ አባባል ለቂምና ለበቀል ራሳችንን አናዘጋጅ። ክፋትን በክፋት ለማሸነፍ መጣር ለሌላ ትልቅ ክፋት መንገድ መክፈት ነው። “ተወዳጆች ሆይ ራሳችሁ አትበቀሉ… ክፉውን በመልካም አሸንፉ” ሮሜ 12:19-21።


በሕንዳውያን መንፈሳዊ ታሪክ ውስጥቅዱስ ሰው ማነው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲሞክሩ ቅዱስ ሰው በወንዝ ይመሰላል፦ ወንዝ ወደርሱ የመጣን ሰው ሁሉ ያለምንም ልዩነት መጥፎ ነህ ጥሩ ነህ ሳይል አጠጥቶ እንደሚያረካ ቅዱስ ሰውም መልካምነቱ ለሁሉ ነው። እንዲሁም ቅዱስ ሰው በጽጌረዳ አበባ ይመሰላል፤ ጽጌረዳ መዓዛውን ለክፉም ለደጉም እኩል ያዳርሳል። በመጨረሻም ቅዱስ ሰው በዛፍ ይመሰላል ይላሉ። ዛፍ ጥላውን ሲያጠላ በሥሩ ላረፉት ሰዎች ሁሉ ያለማዳላት ያጠላል፤ ሌላው ቀርቶ ዛፉን የሚቆርጠው ሰውዬ እንኳ ከመቁረጡ በፊት ትንሽ ጥላው ሥር ማረፍ ቢፈልግም ተቆራጩ ዛፍ ንፉግ መሆን አይቻለውም፤ ምናልባትም ዛፉ መዓዛ ያለው ከሆነ ይህን መልካም መዓዛውን በቆራጩ መጥረቢያ ላይ እንኳ ይተዋል ይላሉ።


እስቲ ይህን ሃሳብ በተግባር ለዓለም ወዳሳዩ ሁለት የክፍለ ዘመናችን ታላላቅ ምሳሌዎች እንመለስ። ብፅእት እማሆ ተሬዛ የፍቅር/የበጎ ተግባራቸው እንደ አሁኑ በዓለም ሙሉ ከመናኘቱ በፊት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ድሃ ሴቶች ልጆችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበር። በዚህም ሂደት ውስጥ ዘወትር እንደሚያደርጉት ለልጆቻቸው ምግብን ከበጎ አድራጊዎች መለመን ነበረባቸውና አንድ ቀን በአንድ ሀብታም ቤት በር ላይ ሆነው ሀብታሙን ለነዚያ ድሃ ሴት ልጆች በመመጽወት ምጽዋቱ ለእግዚአብሔር ስጦታ እንዲሆንለት ሲጠይቁት ይህ ሀብታም ሰው ያለምንም ርኅራኄ በፊታቸው ላይ ይተፋባቸዋል። በዚህን ሰዓት እማሆይተሬዛ ዛሬስ ምን ዓይነቱ ጠማማ ሰው አጋጠመኝ ወይም እግዚአብሔር ይይልህ፤ የእጅህን ይስጥህ… ብለው አልሄዱም። ይልቁንም ፊታቸውን እየጠራረጉ “እሺ፤ ይህን ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ለነዚያ ምስኪን ልጆቼስ ምን ትሰጠኛለህ?” ጠየቁት። መልካም ነገርን ክፉው እስከወዲያኛው ሊያሸንፈው ከቶም አይቻለውምና ሰውየው በነዚህ የብፅእቷ ቃላት ልቡ ተሰበረ፤ ከዚያችም ቅጽበት ጀምሮ ቀሪውን እድሜ ከርሳቸው ጋር በመተባበር ድሆንችን ለማገዝ ወሰነ። “ክፉውን በመልካም አሸንፉ” ላለው የእግዚአብሔር ቃል የተሰጠ ትክክለኛ ምላሽ!


እንዲሁም የቀድሞው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1981 ዓ.ም. ተኩሶ ሊገድላቸው ሙከራ በማድረግ ያቆሰላቸውን ግለሰብ የነበረበት እስር ቤት ድረስ በመሄድ ይቅርታ እንዳደረጉለት የቅርብ ጊዜ የዓለማችን ትዝታ ነው። አይደለም ለመግደል ሙከራ ተደርጎብንና ክፉኛ ቆስለን ይቅርና ስም በማጥፋት ወንጀል ሰው ስማችንን ሊያጠፋ ሙከራ ካደረገ እንኳ ያን ሰው ልክ እስክናስገባው ድረስ ዕረፍት በማይሰማን ሰዎች በተሞላች ዓለም ተሸናፊ ሆነው ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ እባክህ ይቅርታዬን ተቀበልልኝ ማለት ለዓለም ሞንነትን ለወንጌል ግን አሸናፊነትን ያሳዩ ትልቅ አብነት ናቸው።


ክርስቶስ ሞትን ለማሸነፍ መሞት ነበረበት፤ በቅዳሴያችንም የምንለው ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ኦቶም ሞትን ረገጠ ነውና፤ እኛም ክፉ የሚመስሉ ነገሮች በተለያየ መልኩ ሲመጡብን የተጠራነው በተሸናፊነት አሸናፊ እንድንሆን ነው። “የሚያሳድዷችሁን መርቅ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ” (ሮሜ 12:14)።


እነዚህ ሰዎች ይህን ያደረጉት ቅዱሳን ስለሆኑ ነው አንበል፤ ይልቁንስ ነገሩ በተቃራኒው ነው፤ ይህን ስላደረጉ ነው ቅዱሳን የሆኑት። ክፉ ነገሮች ባጋጠሙን ቁጥር እግዚአብሔር አንድ ልጁን እንድንመስል እድል እየሰጠን ነው። ብፅእት እማሆይ ተሬዛ “ክርስቶስን ለመምሰል ያገኛችሁትን አጋጣሚዎች ሁሉ አታሳልፉ - ተጠቀሙበት” ይሉናል። እግዚአብሔር እስከዚህ ቸር ሆኖ ክፉ የምንላቸውን ነገሮች ተጠቅመን ክርስቶስን መምሰል ከቻልን “ሁሉ ለበጎ ነው የሚለው” አባባል ምንእውነት ነው!

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት