እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

መንፈስ ቅዱስ - ቸል የተባለ አምላክ? - ስጦታዎቹና ፍሬዎቹ በክርስቲያን ሕይወት

መንፈስ ቅዱስ - ቸል የተባለ አምላክ? -  ስጦታዎቹና ፍሬዎቹ በክርስቲያን ሕይወት

Holy Spirit“ሁሉም ሁሉን ይወቅ” በሚል ርእስ በ1987 ዓ.ም. ዓለማየሁ ሞገስ የተባሉ ጸሐፊ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን የታዘቡትን ሲጽፉ እንዲህ ብለው ነበር “በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈስ ቅዱስ ችላ የተባለ ወይንም ያልታወቀ ከሦስቱ አካላት የለም። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ 56 አብያት ክርስትያናት አሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም የታነጸ ግን አንድም የለም። የሥላሴ ሁለት፣ የእግዚአብሔር አብ ሦስት፣ መድኃኔ ዓለም ሰባት... የተቀረው ግን በማርያም፣ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት ስም ነው። ምስኪን የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድም አንድም እንኳን የለውም፤ የዓመት እንጂ የወር በዓልም የለውም። ሰዎች ሲደነግጡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሲሉ በቀር ሰሙን ማን አንስቶት አያ! ከእነዚሁም በጣም ካልደነገጡ በስመ አብ ብቻ ብለው ዝም የሚሉ አሉ።” ይህ የ1980ዎቹ መጨረሻ ትዝብት ሲሆን ምናልባትም ዛሬ አዲስ አበባ የመለጠጧን ያህል የተለያዩ አብያት ክርስቲያናት ቁጥር እየጨመረ መጥቷልና ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ ስም የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን መኖር ያለመኖሩ ሌላ ጥያቄ ነው፤ ሆኖም ግን በዚያን ጊዜ እውነት መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ እናስገባና ወደራሳችን ነጥብ እንመለስ

ይህንን ጽሑፍ እዚህ ላይ ስናጣቅሰው ማለት ያለብን ነጥብ በቤተ ክርስቲያኗ አምልኮና የጸሎት ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ መሆኑን ነው። የጸሐፊው ምልከታ እኛን የሚያሳስበን አንድ ነገር አለ፤ ያም እያንዳንዳችን ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለን ግንዛቤና ሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል ቦታ እንደምሰጠው ለማሰብ ይጋብዘናል። 

መንፈስ ቅዱስ እንደ ጸሐፊው አገላለጽ “ችላ የተባለ” ወይም እንደ አንዳንድ የውጭ ጸሐፊዎች ደግሞ “የተረሳ አምላክ” የሚል ትዝብትን የሚፈጥረው ለምን ይሆን ካልን እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ መልስ ሊኖረው ይገባል። እንደው በጠቅላላው ስናስበው ግን ምናልባትም “መንፈስ ቅዱስ” የሚለው ስሙ ራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችል ይሆናል። ለምሳሌ “እግዚአብሔር አብ” ስንል አብ ማለት አባት ነውና ለአእምሯችን ይመቻልና ስለእግዚአብሔር አባትነት በቀላሉ ሊረዳንና ጸሎትም ልናደርስ እንችል ይሆናል። እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ስናስብ ከኃጢአት በቀር እኛን ሆኖ ተወልዶ፣ በሥጋ ኖሮ፣ ተጠምቶ፣ ተርቦ፣ ተሰቃይቶና ሞቶ ከዚያም ከሞት በድል የተነሣ አምላክ ስለሆነ ከተፈጥሯችን ጋር በጣም ቅርብ ሆኖ ስለሚሰማን ለእርሱ አምልኳችንና መንበርከካችን ከባድ ነው ማለት አንደፍርም። ስለ እመቤታችን፣ ቅዱሳንና ሰማእታትም እንዲሁ የምድር ገድላቸውን በድል ያጠናቀቁ “ሩጫቸውን እንደሚገባ የሮጡ” ናቸውና ይበልጥ የኛን ጉዳይ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርቡልን እናምናለን፤ ስለመንፈስ ቅዱስ ስናስብ ግን መገለጫው ራሱ “መንፈስ” የሚል ነውና የራሱ ህልውና በውስጣችን ገብቶ ብርሃኑን እንዲያበራ ፈቃደኛ ካልሆንን በስተቀር ሰዋዊ ተፈጥሯችን ቶሎ ሊገነዘበውና አምልኮውን ሊለማመድ ይከብደዋል።

በሌላ መልኩ ደግሞ ስናይ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መንፈስ ቅዱስ ከፍ ባለና ሊረዳ በማይችል ሁኔታ ብቻ ሊገለጽ የሚችል እስኪመስል ድረስ ከቋንቋ ጀምሮ እስከ አካል መደበላለቅ መታየት የመንፈስ ቅዱስ አምልኮ ብቸኛ መስፈርት ተደርጎ ይታያል፤ የሁከት ያልሆነው ነገር ግን የሕይወት የሆነው አምላክ ከሁሉም በላይ በእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ መደበኛ በሆኑት ሀሳቦቻችን፣ ስሜቶቻችንና ድርጊቶቻችን ሊመለክ እንደሚፈልግ እናውቃለን።  

እንደ ካቶሊካውያን ክርስቲያኖች ማሰብና ማስተንተን ያለብን መንፈስ ቅዱስ ከተፈጥሯዊ በላይ በሆኑ ምልክቶች ብቻ የሚመለክ አምላክ ያለመሆኑን ነው። አንዳንድ ጊዜ በተወሰነ ወቅትና ሁኔታዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚሰጡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የሁል ጊዜ መስፈርት አድርገን በመውሰድ መሳሳት የለብንም። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም መልክ ይገለጻል፤ ይመለካልም። ይበልጥ ለብዙሃን በሚጠቅም መልክ መንፈስ ቅዱስ ሕያው ነው።

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልዩ ለሆኑ ምልክቶች ብቻ የሚሆን አምላክ ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ የእኔ መሄድ ለናንተ ይሻላችኋል፤ ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ አጽናኙ ወደናንተ አይመጣምና አይለንም ነበር /ዮሐ. 16፡7/። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በእለታዊ ሕይወት ትግሉ የክርስቶስን ሕይወት በመኖር ወደ ዘለዓለማዊ ክብር ይሻገር ዘንድ ነው፤ ብቸኛ የመንፈስ ቅዱስ ዓላማም እኛን ለዚህ ግብ ማብቃት ነው።

በአስፈላጊው ሰዓትና ሁኔታ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ድንቅ አድራጊና ከአእምሮ በላይ የሆኑ ተአምራቱን እንደሚያደርግልን እናምናለን። በተለይም ከተአምራት ሁሉ በላይ ተአምር የሆነውን የክርስቶስ በእኛ መካከለ በየእለቱ መገኘት ኅብስትና ወይኑን በመቀየር፣ ኃጢአታችንን በኑዛዜ በማስተሥረይ እውን የሚያደርግልን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። በተራ ወረቀት ላይ የተጻፈውን ቃል ቀይሮ የእግዚአብሔር ቃል በማድረግ ለሕይወታችን መሪ እንዲሆን የሚሰጠንም ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። እንዲሁም እንደ እኛ ተራና ደካማ በሆኑት ወንድሞችና እህቶች ውስጥ ክርስቶስን እንድናገለግል የሚያስጎነብሰን መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው። “ጌታ ሆይ መች ተርበህ፤ ተጠምተህ፣ ታርዘህ፤ ታስረህና እንግዳ ሆነህ አይተን ከለከልንህ” እንዳንል በየእለቱ በፍቅር ሆነን ሁሉን አቀፍ ክርስቶሳዊ ሕይወትን እንኖር ዘንድ የሚያደርገን አሁንም መንፈስ ቅዱስ ነው።

እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያናችን ማለትም በያንዳንዳችን ሕይወት በሥራ ላይ መሆኑን የምናውቀው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ስንገነዘብ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን “የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች” በማለት ከትንቢተ ኢሳያሳያስ የወሰደቻቸውን ትዘረዝርልናለች፤ እነርሱም ፡- ጥበብ፣ ማስተዋል፣ ምክር፣ ጽናት፣ እውቀት፣ እምነትና ፈሪኀ እግዚአብሔር ናቸው። /ካ.ቤ.ት. 1831/  እነዚህ ስጦታዎች ለመንፈስ ቅዱስ የምንገኝና የምንታዘዝ ሰዎች ያደርጉናል።

የጥበብ ስጦታ ክርስቲያናዊ ፍቅራችንን ፍጹም በማድረግ ሌሎቹን ስጦታዎች እንድንቀበል ያደርገናል። ጥበብ ከሰባቱ ስጦታዎች ላቅ ያለ ነው። አእምሮን በማብራት ተሻጋሪና ዘላለማዊ ወደሆነው አምላካዊ ጥበብ ያደርሰናል። ጥበብ እምነትን ያጠነክራል፣ ተስፋን ያጸናል ፍቅርንም ፍጽምት ያደርጋል።

የማስተዋል ስጦታ እምነታችንን ፍጹም ያደርጋል። ማስተዋል የእምነታችንን እውነታዎች በተለይም ግልጸቶችን እንረዳ ዘንድ ያስችለናል። በማስተዋል ስጦታ ጥልቅ የሆኑትን ተደራራቢ የእውነት ደለሎች ጠለቅ ብለን እንድንገባና የእምነታችንን ሰፊ ትርጉም ለመረዳት እንችላለን። ማስተዋል ደረቅና መካን የእምነት ሕይወትን ወደ ጉልበታም የምስክር ሕይወት ይቀይርልናል።

የምክር ስጦታ የማገናዘብ ብቃታችንን ፍጹም ያደርጋል። በነገሮች ሁሉ ሚዛናዊ ፍርድ እንድናደርግ ያስችለናል። የእውቀት ስጦታን ተግባራዊ እንድናደርግና በእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተጋድሮቶች እንድንረዳ ያደርገናል።

የጽናት ስጦታ ተፈጥሯዊ የሆነውን ጽናት ሙሉ በማድረግ ከሚያስፈሩን ነገሮች በላይ እንድነሄድ ያደርገናል። በአስቸጋሪና አደገኛ በሆነ ነገር መካከል ስንገኝ ስንገኝም ሆነ በቀጣይት በሕይወታችን ሁሉ ፈተናዎችን ለመጋፈጡ ብርታትን ይሰጠናል።

የእውቀት ስጦታ ከእምነታችን የምናገኘውን ተስፋ ፍጹም በማድረግ የፍጡራንንና የጊዜያዊ ነገሮችን በራሳቸው ብቻ ባዶ መሆናቸውን ይገልጽልናል። እነዚህን ጊዜያዊ ነገሮች ምንንታቸውን በማየት በእግዚአብሔር ዓይን ለማየት ያበቃናል፤ ከዚህም የተነሣ በእውነተኛ ዓላማቸው በአግባቡ እንድንጠቀምባቸው ያደርገናል።

የየዋህነት ስጦታ ከእምነት የሆነው የፍትሐዊነት አቋማችንን ሙሉ ያደርግልናል፤ እግዚአብሔርንም እንደ አባታችን የምናውቅበትን ፍቅር ይሞላናል። የዋህነት ስለ እግዚአብሔር ብለን ሰዎችንና ነገሮች ለማፍቅርና ለማክብር ያበቃናል። የየዋህነት ስጦታ በየዋህነት የምናደርጋቸውን የሃይማኖት ልማዶችና አምልኮ ደስታን ወደ ተሞላ የእግዚአብሔር አገልግሎት ይቀይርልናል።

የፊሪኀ እግዚአብሔር ስጦታ በተመጣጠነ ሁኔታ የመኖር ብቃታችንን ፍጹም ያደርግልናል። ይህ ስጦታ በነገሮች ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር እንዳንነፍግ ያስችልናል። እግዚአብሔር ከማፍቀራችን የተነሣ እሱን ማሳዘንን እንድንፈራ ያደርገናል። ትክክለኛና ተገቢ የሆነ እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው።

እንግዲህ ልባችንን ለነዚህ መሰሉ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከከፈትን ምን ዓይነት ክርስቲያኖች መሆን እንደምንችል መገመት እንችላለን። በርግጥም የነዚህ ስጦታዎች ህልውና አንድን ክርስቲያን በገላትያ 5፡22-23 የተዘረዘሩትን የመንፈስ ፍሬዎች በሕይወቱ ይታይ ዘንድ ያስችሉታል። 12ቱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሚከተሉት ናቸው፡- ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትእግስት፣ ደግነት፣ በጎነት፣ ርኅራኄ፣ ጨዋነት፣ ታማኘነት፣ ትሕትና፣ ራስን መግዛትና ንጽሕና /ካ.ቤ.ት. 1832/። እነዘህም የዘላለማዊ ክብር የመጀመሪያ ፍሬዎች ተብለው በትምህርተ ክርስቶሳችን ውስጥ ተገልጸዋል።

ከላይ የጠቀስናቸው 7ቱ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና የነርሱ ውጤት የሆኑት 12ቱ ፍሬዎች ከምንም በላይ በዚህች ዓለም ውስጥ ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች እንዲሁም ከአምላካችን ጋር ለሚኖረን ግንኙነት አንገብጋቢና አስፈላጊ ሲሆኑ ሁላችንም በምስጢረ ጥምቀትና ቅዱስ ሜሮን የተቀበልናቸው ናቸው። ከዚህ ውጪ ግን እንደ ለሁሉም አንገብጋቢና የግድ ያልሆኑ ራሱ መንፈስ ወደ ፈለገው ነፍሶ የሚሰጠው ስጦታዎች አሉ፤ እነዚህም በጣም ጊዜያዊ ሂደቶች ላይ የተመሠረቱ ሲሆን ለእለታዊ ሕይወታችን ሁል ጊዜ ሊሆኑ የግድ አይደልም። በ1ኛ ቆሮ. 12፡8-11 ላይም እንዲህ ይላል፡- “ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።”

ስለዚህ እንደመደምደሚያ ማሰብ የሚገባን ስንት የመንፈስ ቅዱስ በዓላትና ቤተ ክርስቲያን አሉ ወይም ይህ ይደረጋል አሊያም አይደረግም ሳይሆን፤ ለሁላችንም በእለታዊ ሕይወታችን ክርስቲያናዊ ማንነታችንን እንደሚገባ ለመኖርና ወደ ዘላለማዊው ክብር ለመሻገር ብቁ እንድንሆን ከተሰጡን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና ፍሬዎች የጎደለንንና በእኛ የማይንጸባረቀውን እናስተንትን፤ በርግጥም ደግሞ የምንኖራቸውን ይበልጥ እንዲያዳብርልን ልባችንን ከፍተን እንለምነው። 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት