እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ለአዲሱ ዓመት ጭምብላችን ይውለቅ!

ለአዲሱ ዓመት ጭምብላችን ይውለቅ!

ስለ አሮጌና አዲስ አመት ስናስብ ክርስቲያኞች ለየት ያለ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል እንደሚታሰበው ወይም እንደሚባለው ምን ያህል እቅድ አስፈጽሜአለሁ በዚህ አመት ምን ያህል ተሳክቶልኛል ምን ያህል አልተሳካልኝም የሚለውን እንድናስብ አይደለም፡፡ ያ የማስ ሚዲያ በአል ዝግጅት ነው፡፡  ይህ በራሱ አቅጣጫ ጥሩ ነው እንደ ክርስትያን ግን ከዛ በላይ ያስፈልገናል ለእኛ አንድ ዓመት አይደለም ጥያቄው አንድ ቀን ነው፡፡ አንድ ቀን ለእኛ አንድ ዓመት ነው አዲስ ሕይወት ነው ለኛ እግዚአብሔር ይህን እድል ሲሰጠን ያለፈውንና የሚመጣውን በጅምላ ለማሰብ ሳይሆን ዛሬን እንድናስብ ዛሬን እንደ እኔ እንዴት እየኖርኩ ነው? እንደ ክርስቲያን እንደ እምነቴ እንዴት እየኖርኩ ነው? ስለዚህ የሆነ እቅድ በሆነ ጊዜ ተሳካ አልተሳካ ሳይሆን የእያንዳንዱ ቀን ጥርቅሜ እንዴት ነበር? የህይወት ፍሰቴ ሰኞ ለማክሰኞ ማክሰኞ ለእሮብ እያስተላለፈ እንደዛ እያለ እዚህ የደረስኩበት ህይወት እንዴት ነው? ዛሬስ ለነገ ነገስ ለከነገወዲያ እንዴት ቀጣይ የሆነ ፍሰት መኖር አለበት? 9ዐ ከመቶ ተሳክቶልኛል ምናምን ብለን የምናወራው ነገር አይደለም ስለዚህ በዚህ መሰረት ሀሳብ ላይ እንዴት ብለን እናስብ እንደዛ አይነት ህይወት በእያንዳንዱ ቀን ራስን መገምገም እንዴት ይቻላል?

ቤተክርሰቲያን አዲሱን ዓመት በቅዱስ ዮሐንስ እንድንጀምር ታዘናለች:: ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስለ እውነት የተሰየፈ ስለ እውነት የመሰከረ ከእርሱ በላይ አብነት ሊሆን የማይቻል ትልቅ ሰው በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ቀን ላይ እንድናስብ ተሰጥቶናል:: ስለዚህ እንዴት የሚለው ምላሽ እዛ ላይ ይገኛል፡፡ አዲሱን ዓመት በቅዱስ ዮሐንስ እንጀምር ማለት አዲሱን ዓመት በእውነት እንጀምር ማለት ነው። እውነት የፍልስፍና ሳይሆን እውነት የአእምሮ ሳይሆን እውነት የፖለቲካ ሳይሆን እውነት የእምነት አቋሞት ወይም የጸሎተ ሃይማኖት ወይም ያድናል አያድንም እንደዚህ ሳይሆን የእኔነት ወይም የማንነት እውነት ማለት ነው።

ማቴ 3፡1-15 የቅዱስ ዮሐንስን ማንነት ይናገራል፤ አላማውን ተልእኮውን ማን ነው የሚለውን ነገር ምላሽ ይሰጠናል በተለይ ቁጥር 11 ላይ ራሱ መጥምቅ ዮሐንስ ምን ይላል “እነሆ እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ነገር ግን ከኔ በኋላ የሚመጣው በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል እርሱ ከእኔ እጅግ ይበልጣል እኔ የእግሩን ጫማ እንኳ ለመሸከም የተገባሁ አይደለሁም” ይላል፡፡ ሰዎቹ የልባቸውን ስለነገራቸው፡ ስለኮረኮራቸው ከፍ ከፍ ሊያደርጉት ፈልገው ነበር፤ ግን ሌላ የሚመጣ አለ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት የተገባሁ አይደለሁም አላቸው። በእውነት አዲስ አመትን መጀመር እንዲሁም የማንነት እውነት ማለት ይሄ ነው።

አሮጌ ዓመት ሲያልቅ አዲስ ዓመት ሲባል ምስጋና የምስጋና ቀን ቆንጆ ነው ግን ቀላል አይደለም ዐይን ጨፍኖ ምስጋና የለም። ያ ምስጋና ከተባለ ያለፈ ህይወቴን ማሰብ አልፈልግም ስለ እገሌ ስለ እገሊት ማሠብ አልፈልግም ተብሎ ሁሉ ተሰብስቦ ሆ ማለት ይቻላል እንደዚያ ሆነን እንድንለያይ እዚህ አልተሰበሰብንም ስለ ራሳችን እውነቱን አስበን እውነቱን አይተን እውነት ሆነን ለመውጣት እኔ ብለን እንውጣ። የእስከዛሬው እኔ እንዳለ ሆኖ እስቲ እኔ ብለን ራሳችን እንይ፤ እንዲህ ነህ/ነሽ በማለት ሰው የሚለን አይደለም፡ ጓደኛ የሚለን አይደለም፡ ወይም መስማት የምንፈልገው ነገር አይደለም፡ እኔ ስለ እኔ ሹክ የሚለውን ነገር ልስማ።

በቅዱስ ቁርባን ፊት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቁ እኔ ጫማውን ለመሸከም የተገባሁ አይደለሁም እንዳለ እኔ እንዲህ ነኝ ብለን እንውጣ ያ ነው ምስጋና! እኔ ላይ ነው ምስጋና የሚገነባው እኔ ላይ ነው ምስክርነት የሚሰጠው። የውሸት እኔ ላይ ምንም አይሰራም ውሸትን ከመደራረብ በስተቀር ውሸት ከመስማት በስተቀር! ስለዚህ ዓመቱን በቅዱስ ዮሐንስ ስንጀምር እኔ የሚለው እውነተኛ ስዕላችንን ለማየት እንነሣ፣ እንወስን በዛ ላይ የተገነባ እድሜ ጥሩ ነው፣ እዛ ላይ ያደገ ሰው ጥሩ ነው፣ በዛ ላይ የሚያረጅ ሰው ጥሩ ነው፣ በዛ ላይ የማይኖር ሰው ግን ዕድሜው ዋጋ የለውም፡፡ ጊዜው ትርጉም የለውም አዲስ ዓመትም ትርጉም የለውም ስለዚህ አሁን የምትለዋ ጊዜ ለኛ ትልቅ ግብዥ ነው።

ማር. 1፡2-3 “እነሆ መንገድን የሚጠርግ መጥቷል መልዕክተኛየ በፊቱ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ” በማለት እንደገና ዮሐንስ መጥምቅ ስለ ክርስቶስ መመስከሩን ይናገራል፡፡  ከእውነተኛ እኔነት በኋላ የሚመጣ ነገር ምስክርነት ነው። ስለዚህ ስለ ራሳችን ግምገማ ማድረግ፣ ስለራሳችን ማሠብ ከፈለግን እውነተኛ እኔነታችንን እናግኝ፤ በሰው ፊት ቀላል ነው ግን ያለንበትን ቦታ እናስብ፤ በእግዚአብሔር ፊት ነን፤ በማን ፊት ላይ እንዳለን እናስብ በቅዱስ ቁርባን ፊት ነን። ከዛ እኔ ብለን እንወስን ስለ ሌላ ሰው ወይም ነገር እውነትን  መናገር ቀላል ነው፤ ከኔ መጀመር ግን ቅድም እንዳልነው ከባድ ነው፡፡

ዮሐንስ መጥምቅ ፈሪሳውያንን፣ ቀራጮችንና ወታደሮችን እናንተ የእባብ ልጆች እፍኝቶች ከማለቱ አስቀድሞ ሄሮድስንም አንተ የወንድምህን ሚስት ታገባ ዘንድ ሕግ አይፈቀድልህም ብሎ እውነትን ከማስተጋባቱ በፊት የራሱን እውነት አይቶ ነበር፤ “እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ መፍታት የማይገባኝ ከኔ በኋላ ይመጣል” በማለት እውነተኛ ማንነቱን አጉልቶ ተናግሯል፡፡ እኛ እውነትን ስናወራ ራሳችንን እንዘላለን፤ ስለ እገሌ  ስለ እገሊት በደንብ እናወራለን ለምን ስንባል እንዴ ልክ ነው፣ እውነት እኮ ነው! እንላለን እውነት ሊሆን ይችላል እዚህ ጋ ግን የዘለልነው እውነት ሊኖር ይችላል ያም የራሳችን እውነት ነው፤ ስለ ሌላ በጣም ቀላል ነው፡፡

ስለዚህ ትልቁ መልእክት በእውነት አዲስ ዓመት እንጀምር ነው። እውነት ክርስቶስ ነው፤ ያንን እውነት በእውነተኛው እኔነቴ ላይ ገንብቼ ነው መመስከር የምችለው …. እኔ ዛሬ አምኜአለሁ ዛሬ ጌታን ተቀብያለሁ ብዬ ነገ መንገድ ላይ ድነሃል ጠፍተሃል እያልኩ ለመመሰክር አይደለም። ከራሴ ጋር እውነት ሆኜ  ትልቁን እውነት ከደረብኩ በኋላ ነው እውነትን ለሌላ የማካፍለው። ዘሎ እምነት የለም፣ ዘሎ ምስጋና የለም እንደው ተነስቶ ምስክርነት የለም፡፡  ስለዚህ ትልቁ የኛ እውነት ክርስቶስ ፊት እውነት ሆነን መገኘት ነው… በእንደዚህ ዓይነት ሕይወት  አዲስ ዓመትን መጀመር ትልቅ ትርጉም አለው። ሌላውን ነገር ተዉት ከአቅማችን በላይ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ በሌላ ነገር እኔነት አይሞላም በውጫዊ ነገር ውስጣችንን ላናሟላ እንችላለን፡፡ ውስጣችን በእውነት ከተሞላ ውጫዊ ነገር ባይሟላልንም ደስተኞች ነን፡፡ ስለዚህ ራስን መሆን እንዴት  መሆን ይቻላል? ብለን መጠየቅ አለብን።

የዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 4 ውስጥ የሳምራዊቷን ሴት ሕይወት ለውጥ ይተርክልናል። ይህችን ሴት ከወንጌል እናውቃታለን ታሪኩን ብዙ ጊዜ ሰምተነውም ሆነ አንብበነው ይሆናል። የእርሷ ታሪክ የእኔንት እውነታ ላይ የምንደርስበትን ሁኔታ ይናገራል። ከታከተ ኑሮና ራስን ከመደበቅ ሕይወት እስከ ምስጋና ብሎም እስከ ምስክርነት ድረስ እንዴት እንደ ሄደች ማወቅ እንችላለን፡፡ በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀምጣ ነበረ እኩለ ቀን አካባቢ ክርስቶስ ወደ እሷ ቀረበና ውሃ አጠጭኝ አላት ሌላ ሌላ ብዙ ንግግር ቀጠሉ እሷም ብዙ ውጫዊና ሥርዓታዊ እውነቶችን ተናገረች፤ አባቶቻችን በዛ በኮራዜም ይሰግዱ ነበር ነገር ግን እንደዚህ እንደዚያ አለች። ይሄ አንቀፅ ጸሎተ ሃይማኖት ነው ጥሩ ነው ጥሩ እውነት ተናግራለች ግን ትልቅ እውነት ደብቃ ነበር በጉድጓድ ላይ ተቀምጣ ጥልቅ በሆነና እስከወዲያኛው በማያረካ ባዶ ነገር ላይ ተቀምጣ ብዙ ነገር ታወራ ነበር። ኋላ ክርስቶስ የሸሸገችውን የጓዳዋን እውነትሲነግራት ከዚህ ዳግም ከማያስጠማኝ ውሃ ስጠኝ አለች። መመላለስ የታከታት ሴት፤ ከሰው ተሰውራ በቀትር በዚያ በአይሁድ የፀሐይ ሰዓት ነው ተሸሽጋ ውሃ ግድ ስለሆነባት ለመቅዳት የመጣችው… ሁሉ የታከታት ሴት እንደዚህ ዓይነቱን ዳግም የማያመላልሰውን የክርስቶስን ውሃ እባክህ ስጠኝ አለች። የተቀመጠችበት ጉድጓድ የማያረካት መሆኑን ስታውቅ፣ አሁን በቤትሽ ያለው ባልሽ ስንተኛሽ ነው ሲላት የደነገጠች ሴት ማንም አያውቀኝም ብላ ምትለውን ነገር እንግዳ ሳምራዊ ያልሆነ አይሁዳዊ ሲነግራት ተደናገጠች። ውስጧን የሚኮሰኩሳት እውነቷ ተነካባት። እውነት ሲነካ የምንደክምለት ነገር የማያረካ መሆኑን እናውቃለን፡፡

በማድረግ አይረካም፣ በመያዝ አይረካም፣ በመሆን ግን እርካታ አለ ባለመሆን ደግሞ እርካታ ቢስነት አለ። ስለዚህ የእኔነት ጥያቄ የእውት ጥያቄ ትልቅ ነገር ነው። የተቀመጥንበትን ጉድጓድ እንይ፤ ዛሬ ላይ ሆነን እንቀዳለን እንጠጣለን ያረካናል የምንልበት ግን ሌላ ትልቅ ነገር ስናገኝ ልንተወው የምንችለውን ነገር እናስተውለው። ተመችቶናል ብለን የምናስበውን ነገር፣ ዛሬ የተቀመጥንበትን ጉድጓድ እንይ በክርስቶስ ፊት ነን። ለዚያች ሴት እውነትን የገለጠላት ለዮሐንስ መጥምቅ እኔ ጫማውን ለመሸከም የገባሁ አይደለሁም ያስባለው ክርስቶስ ዛሬ እኛንም የሆነ ነገር ሳይለን ሂዱ አይለንም።

የስኬት ዓመትን ስናስብ ይኸን እናስብ:- እኔ እኔነቴን ካገኘሁ ስኬታማ ነኝ እኔ እኔነቴን ካላገኘሁ ሁሉም ነገር ቢደራረብ የከሰርኩ ሰው ነኝ! የኪሳራ ዓመት የኪሳራ ውሎ የኪሳራ አዳር! ስለዚህ ይህች ሳምራዊት ሴት የምትቀዳው ውሃና የምትመላለስበት ጉድጓድ የማያረካት መሆኑን ስታውቅ ክርስቶስን መከተል ጀመረች ሄዳ ለመንደሩ ሰዎች መሰከረች እነርሱም እግዚአብሔርን ማመስገንና መድኃኔዓለምን እዩት በማለት መመስከር ጀመሩ። እውነታቸው ከተነካ በኋላ ነው ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ የሚለን። ስለዚህም ነው ተነሥቶ ምስጋና የለም! አይን ጨፍኖ እናመስግን የለም እራስን እያታለሉ ማመስገን የለም የምንለው።

ስለዚህ ጭምብላችንን እናውልቅ እኔ በእናንተ ፊት መላ ገጽታዬን ሸፋፍኜና ዓይኔን ብቻ ገልጨ ብመጣ አታውቁኝ፤ ምናልባትም ዓይኔንም ሸፍኜ እዚህ ቆሜ ባወራ ምናልባት ትገምቱ ይሆናል ግን በርግጠኘነት አታውቁኝም። እውነተኛ ሕይወታችን ውስጥ ስንመጣ ምን አልባት እንደዛ እንዳይሆን፤ በሰው ፊት በክርስቶስ ፊት በጭንብል መቆም እና እርካታን በምንሰራው ነገር፤ እርካታን በያዝነው ነገር፤ እርካታን ሰው በሚያደርግልን ነገ፤ እርካታን በስሜቶቻችን ለማግኘት የምንደክም ሰዎች እንዳንሆን ማስካችንን እናውጣ። እውነተኛ ማንነታችንን የጋረደውን ነገር እናስወግድ፣ እንግለጠው። ደካማ ብንሆንም ኃይል እናገኛለን በሽተኞች ብንሆንም ፈውስ አለን ኃጢያተኞች ብንሆንም ስርየት አለን ተሸፋፍነን ከሆነ ግን ሳናውቀው ኖርን እያልን እንሞታለን። እንደዛ ዓይነት ሕይወት መኖር አይደለም ራሳችንን ሳናገኝ ራሳችንን ሳንሆን የምንኖረው ኑሮ ዓመት መቁጠር ነው። በአንድ ወቅት ከሞት በኋላ ህይወት አለ ወይ? ብሎ አንደ ደቀ መዝሙር  አንድ መምህርን ሲጠይቃቸው እንዳሉት ነገር ማለት ነው። እሳቸው ሲመልሱለት ግን ጥያቄው ከሞት በኋላ ህይወት አለ ሳይሆን ከሞት በፊት ህይወት አለ ነውን ነው ጥያቄው አሉት። በ2ዐዐ4  እኔ ሕይወት አለኝ ወይ? ሥጋዊ ሞትን ተዉት ቅድም ብለናል እያንዳንዱ ቀን ለእኛ ዓመት ነው። በሕይወት ሳለን እውነተኛ ማንነታችንን በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ለመኖር እንወስን።

በውጫዊ ነገር ካየነው አንድ ቀን ሙሉ መልካችሁን ሸፍናችሁ በሰው ፊት መመላለስን ማሰቡ ይከብዳል። ማስክ አድርጐ ከዚህ ፒያሳ ድረስ መሄድን ማን ያደርገዋል? እንዲሁ ለማድረግ በሚል ስሜት ካልሆነ በስተቀር እንደኑሮ ዘይቤ ማንም አይመኘውም። አሻጒሊት መስለህ ውጣ ብንባል ምን ያህል ይከብደናል? አይደለም እሱን የተፈጥሮ ፊታችንን ይዘን ከቤት ለመውጣት እንኳ የምናደርገውን ነገር አስቡት። ማንነት ላይ ስንመጣም ነገሩ እንደዛ ነው እንዳውም የከፋ ነው። ከቤት ሌላን ሆኖ መውጣት  ሌላን ሆኖ ሰውን ማግኘት ሌላን ሆኖ መመላለስ! 365 ቀናት ጨርሰን ድጋሚ አዲስ ዓመት ብለን ራሳችንን ሳንሆን ራስን ማታለል።

ስለዚህ እግዚአብሔር ዛሬን ሲሰጠን ለሌላ አይደለም ቅድም እንዳልነው የስኬት ወይም የኪሳራ ዓመት ብለን በሌላ ነገር ባንዳች እንድንመዝን አይደለም። እውነት እኔ ማን ነኝ ደካማ ከሆንኩ እግዚአብሔር ይመስገን እግዚአብሔር ጊዜን ሰጥቶኛል ራሴን እየወቀስኩ ወይም እያማረርኩ እንድኖር አይደለም ብለን ወደርሱ እንቅረብ። እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት የተገባሁ አይደለሁም ብሏል ቅዱስ ዮሐንስ ታዲያ እኔስ ማን ነኝ? እኔነታችንን ማንም ሊነግረን እንደማይችል እናውቃለን ከክርስቶስ በስተቀር ከዛ በኋላ ምስክርነት ይታሰባል፣ ከዛ በኋላ ማመስገን ይባላል። በእውነተኛ ማንነት ላይ ክርስቶስ ይገለጣል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የሚያስፈራ ሊቋቋሙት የማይችል የዛን ሰው ራስ ቆርጠህ አምጣልኝ የሚያስብል ዓይነት ክብር ይገለጣል። ኃጢያት የሚገለጠው እውነተኛ ውስጣችንን ማየት ስንችል ነው። ሰው ራሱን ሲሆን ክርስቶስ ይጠቀምበታል፣ ሰው ራሱን ካልሆነ ስሜት ይጠቀምበታል ሰይጣን ይጠቀምበታል ጓደኛ ይጠቀምበታል። ስለዚህ ቢያንስ ለሰው አይደለም ለራሳችን ጭምብላችንን እናውልቅ ለራሳችን ማስካችን አወለቅን ማለት ለሌላ ሰው ሆንን ማለት ነው እንደዚህ ሲሆን የስኬት ዓመት ነው የማስ ሚዲያ አይነት ስኬት ለኛ አይሰራም ወይም ተጨማሪ ነው። ሰው ይኸ ዓመት ተሳክቶልሃል ቢለን አይሰራም እውነተኛ ስኬት ከውስጥ ነው እውተኛ ስኬት ከክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ ሃሳብ መሠረት እውነተኛ ማንነታችንን የምናገኝበትና እግዚአብሔርን የምናመሰግንበትና ስለክርስቶስም አዳኝነት የምንመሰክርበት የስኬት ዓመት ያድርግልን፡፡

በቅዱስ ዮሴፍ ዘገዳመ ሲታውያን ቁምስና አዲስ አበባ የዓመቱ መዝጊያ ለምእመናን የተደረገ ሱባኤ። ጳጉሜን ፮ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት