ለሚያምኑት የዘለዓለም ሕይወት ተረጋግጧል

Written by Super User on . Posted in የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች

ለሚያምኑት የዘለዓለም ሕይወት ተረጋግጧል

Tinsaeእግዚአብሔርን በሙሉ ለመግለጽ የሚበቃ አንደበት ያለን ፍጡራን መሆን ባንችልም ስለተደረገልን መልካም ነገር ሁሉ ስሙን ስንጠራ፣ ስንወድሰው፣ ስለ ኃጢአታችን ተንበርክከን ሥርየት ስንማጸነው ከምናገኘው የመተማመን የመወደድና ፍርሃት ያለማሳደር ስሜት ከሚሰጠን የውስጥ እርካታ ባሻገር በምላሹ ታላቅነቱን በሕይወት የዘወትር እንቅስቃሴያችን በጥቂቱም ቢሆን ሳንገልጸው አናልፍም፡፡ ይህ ታላቅ ስጦታ የተገኘው ደግሞ እግዚአብሔር ልጁን በእውነተኛ ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን እስከሞት አሳልፎ ሲሰጥ በተገኘው የከበረ የጽድቅ ሥጦታ አማካኝነት ነው፡፡ በተጋድሎና በጾም የአባቱን ፈቃድ ሳይታክት ለመፈጸም የተጋውን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ስብዕና ተቀርጸን በምድር ሕይወቱና በተጓዘባቸው መንገዶች ተጉዘንና ተማርከን የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረን ተጋብዘናል፡፡

በዓለ ትንሣኤ ወይንም ፋሲካ ለክርስቲያኖች ሁሉ የመታደሻ ወቅት ነው፡፡ በኃጢአት የቆሸሸው ማንነታችንን አስወግደንና አሮጌ የሆነውን ልማዳችንን ጥለን የመስቀሉን ሕማማት፣ ሥቃይና መከራ ተካፋዮች ሆነን፣ "ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።" ፊሊ 3፡ 9-11 የትንሣኤ ክርስቶስ ተቀብለንና ለብሰን በጸጋው ለምልመን ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሻግረን የመዳን ድልድይ ያየንበት የመታደሻ ወቅት ነው ትንሣኤ፡፡ በክርስቶስ መወለድ ያኘነው ተስፋ ኃይል ሆኖ በትንሣኤው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳው ጌታ ጋር ተስማምተን ኃጢአትን በመናቅ ዘለዓለማዊ ሞትን ድል እንነሣለን ድላችንም በትንሣኤው የምንጊዜም በድን እስረኛ ኢምንት ቁስ አካል ሆኖ ላለመቅረት ከጨለማው ወህኒ የተስፋውን ጥሩር ታጥቀንና አጥልቀን ወደ ዘላለማዊና ሰማያዊ ነጻነት የምናመልጥበት መውጫ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አዘጋጀልን፡፡

ለሕይወት የምንሰጠው ፋይዳ ትርጉም የለሽ የሚሆነው ለመጪው ዘመን ታላቅ ራዕይ ሰንቀን ስንጓዝ ነው፡፡ በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ "እናንተ አባቴ የባረካችሁ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ" ማቴ 25፡ 34 በማለት የመጪውን ዘመን ብሩህነት ከምድር ኑሮአችን ባሻገር ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድንወርስ ይጋብዘናል፡፡ የሰው ዘር ሁሉ መጨረሻውም ይሁን ግቡ እግዚአብሔርን ካደረገ "የእግዚአብሔር ሃሳብ ግን ለዘለዓለም ይጸናል፤ የልቡም አሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው" መዝ 33፡11 እያለ ቃሉን ያጸናልናል፡፡ ሞት በታላቁ ኃይል ድል ተመቷልና ሳናወላውል አቋማችንን አጠንክረን ወደ ማይሻረው፣ ጥልቅ በሆነውና ሕያው ሕይወት በሚሰጠው በትንሣኤው ጌታ ላይ መተማመኛችንን ማጽናት ይገባናል፡፡ ምክንያቱም የዛሬ ድርጊታችንና ማንነታችን የነገ ቀጣይ የሕይወት እጣ ፈንታችን መሰረት የምናስይዝበት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የድል አድራጊነት መታሰቢያ በሆነው በዚህ የትንሣኤ በዓል ከምንጊዜም በላቀ ምሥጋናችንን፣ አምልኳችንን፣ እልልታችንን ብሎም ሙሉ ማንነታችንን የምናቀርብበት፣ እንደፈቃድህ ብለን ፈቃዳችንን የምንተውበት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ምሬት ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ምክንያት በሆን የሕይወት ምሥክርነት በኑሮአችን የምንሰጥበት፣ ፍጹም መንፈሳዊ ብርታት አግኝተን የልቦናችን የበጎነት፣ የፍቅር፣ የእውነት፣ የትህትናና የሰላም መዝገብ ከፍ ብሎ የሚታይ እንዲሆንልን ጽኑ ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሁላችሁም እኔን ስሙ አስተውሉም" ማር 7፡14 ብሎ እንዳስተማረን አንዲት ቅዱስት ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንም ቅን የእግዚአብሔር አገልጋዮችን በእምነት በማጽናት እንዲሁም ምሥጢራትን አዘውትረን በመጠቀም ከክፉ ሞት እንድንርቅ ትመክረናለች ትጠብቀናለች፡፡

ምንጭ፡ ፍቅርና ሰላም መጋቢት 2004 ዓ.ም.