ምስጋና፣ ተስፋና ተስፋ ቁርጠት

አንደኛው ከአንዱ በመመላለስ ብዛት ይበላለጥ ይሆናል እንጂ ሕይወታችን ለምስጋና፣ ለተስፋ ወይም ለተስፋ ቁርጠት መረማመጃነት የተመቻቸች ናት። ከተጨባጭ ሁኔታዎች ማዶ እምነታችንን በኖርነውና በጣርንበት መጠን የምስጋና ወይም የተስፋ ቁርጠት ሰዎች የመሆናችን ዕጣ ፈንታ ይወሰናል። ስለዚህ ምስጋና፣ ተስፋና ተስፋ ቁርጠት ምን እንደሆኑ በሰፊው ለማስተንተንና የምስጋና ሰዎች ለመሆን ይበልጥ ለመታገዝ በግሩም ሁኔታ በክቡር አባ አብነት አበበ ዘማኅበረ ልኡካን “በምስጋና ሕይወት የሚገኝ በረከት” በሚል ርእስ ያሳተሙትን መጽሐፍ (2000 ዓ.ም. አዲስ አበባ) እንዲያነቡ በመምከር ከዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የቃረምነውን እንደሚከተለው አቅርበናል። በዚህ አጋጣሚም ክቡር አባ አብነትን ከልብ እያመሰገንን አሁንም እግዚአብሔር ምርጥ መሣሪያው ያደርጋቸው ዘንድ ጸሎታችን ነው።

ምስጋና በእያንዳንዳችን ምርጫ የሚከናወን ነው

ምስጋና የእግዚአብሔርን ማንነትና ቸርነት የምናይበት ብቻ ሳይሆን የእኛንም ማንነት የምንገልጽበት ነው። እስቲ በስፋት እንመልከተው፦

ከለምጽ የነጹት ሰዎች አሥር አልነበሩምን ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? (ሉቃስ 17:17)

ምስጋና ግለሰቡ ከእግዚአብሔርና ከዎች ጋር ባለው ግንኙትነትና በግለሰቡ ባሕርይ እንጂ በሁኔታዎች አይወሰንም። ለዚህም ነው ኢዮብ ሁሉን ነገር ቢያጣም እንዲህ ሲል ያመሰገነው “ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ተወለድኩ፤ ስሞትም ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ወሰደ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!” (ኢዮብ 1:21)።

ያላቸው ነገር በጣም ትንሽ ሆኖ ሳለ ስዎች የሚሰጡትና ከሰዎች የሚቀበሉት ፍቅር እንዲሁም ነገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆናቸውን በመገንዘብ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ እንዳሉ ሁሉ፤ ምንም ሳይጎድላቸውና ከሚፈልጉት በላይ እያላቸው፤ ያላቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን በመዘንጋት ይበልጥ ሊኖረን ይገባል በማለት አሁን ካለኝ የበለጠ ቢኖረኝ ደስተኛ በሆንኩ ነበር በማለት ያላቸውን ነገር በመመልከት ከማመስገን ይልቅ በሌላቸው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ደስታን ከራሳቸው ያርቃሉ፤ ከማመስገንም ይቆጠባሉ።

እንደ ሰው ለመኖር ሁለት መንገዶች ብቻ አሉን፦ ስላሉን ነገሮች በሙሉ አመስጋኞች በመሆን ምስጋናችንን ለእግዚአብሔርና ለሰዎች በማቅረብ በምስጋና ሕይወት መኖር ወይም የሌሉንን ነገሮች በማሰብና ያሉንን ነገሮች ዝቅ አድርጎ በመመልከት የቅናት ሕይወት መምራት።

ምስጋና ደስታን ይሰጣል

ሰዎች ስላደረጉልን መልካም ነገር (ስለ ውለታቸው) ምላሽ መስጠት ወይም ውለታቸውን መክፈል ቢያቅተን እንኳ ማድረግ የምንችለው ነገር ነውና ማመስገን ይጠፋብናል ማለት ሐሰት ነው። ተደርጎልን ያለማመስገናችን በጎ ያደርግልንን ሰው ቅር እንደሚያሰኘው ሁሉ ማመስገናችን እንደሚያደስተው አያጠራጥርም። ተደርጎልን እንደተደሰትን ሁሉ አመስግነን ማስደስት ይጠበቅብናል ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ ማመስገን እንደሚገባ ይነግረናል። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር የእኛ ምስጋና ያስፈልገዋል ማለት አይደለም፤ ማመስገን መቻላችን እራሱ የእርሱ ስጦታ ነውና። ተርበን የምንበላው ምግብና ሳንራብ ሰዓቱን ጠብቀን የምንበላው ምግብ ጣዕሙ ይለያያል። የምናቀርበው ምስጋናም እንደዚሁ፤ ጤነኞች ሳለን ስለ ጤንነት ያለን አምለካከትና ታመን ከዳንን በኋላ ያለን አመለካከት ይለያያል። ልዩነቱን አይተነዋልና ከዳንን በኋላ ስለ ጤንነታችን የምናቀርበው ምስጋና ልዩ ነው።

ነገር ግን ስለ ጤንነታችን እግዚአብሔርን ለማመስገን የግድ እንታመምና የምንድንበትን ጊዜ እንጠብቅ ማለት አይደለም፤ ሁል ጊዜ ስለሁሉ ነገር እግዚአብሔርን አመስግኑ ይላልና ቃሉ (ኤፌ. 5:20)።

ምስጋና ነገሮችን በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ነው

ነገሮችን በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ስንጀምር ምስጋና ማቅረብ ይቻለናል። በክርስቶስ ያለን ቦታ ከሁኔታዎች ወይም ከክስተቶች በታች ከመሆን ነጻ የሚያወጣ ነው። ይህ ማለት ደግሞ በአንደበት ማመስገን ብቻ ሳይሆን መጸለይ መቻል፣ ደስተኛ መሆንና በሁሉም አቅጣጫ በምስጋና ሕይወት የተሞላ ኑሮን መምራት ማለት ነው።

ምስጋና ተስፋን ያዘለ ነው

አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን? (መዝ.397)። ሰው ያለ አየር ለአምስት ደቂቃ መቆየት ይችላል፤ ያለ ተስፋ ግን ለአንድ ሴኮንድ እንኳ ሊቆይ አይችልም። ተስፋ ሕይወት ሕይወትም ተስፋ ነውና።

ተስፋ ማለት በየዕለቱ ሊገጥሙን ለሚችሉ ስቃዮችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፍትሔ ብቻ ሳይሆን ምንም እንኳ አስቸጋሪ ቢሆንም ሊሆን የሚችል በጎ ነገርን መጠበቅ ነው። ለዚህም ነው ተስፋችን ሕያው፣ ጠንካራ፣ ጽኑና የማይናወጥ መሆን ያለበት። ተስፋ እስካለን ብዙ ንገሮች አሉን፤ የምንሄድበት አቅጣጫ የምንንቀሳቀስበት ኃይል፣ አማራጮች፣ ሺህ መንገዶችና ሊገመቱ የማይችሉ ህልሞች አሉን። ተስፋ እስካለን ድረስ መሄድ ወደምንፈልግበት ቦታ ግማሽ መንገድ ላይ ደርሰናል ማለት ሲሆን ተስፋ ከሌለን ወይም ተስፋ ከቆረጥን ግን ለዘለዓለሙ ጠፍተናል ማለት ነው።

ተስፋ

“ተስፋ” የሚለውን ቃል ሲፈታው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፦

  • ተስፋ ምኞትና ናፍቆት ብቻ ሳይሆን አለኝታና መተማመን የሚገኝበት ነው (ሮም.15:13)።

  • የክርስቲያን ተስፋ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው (1ጴጥ. 1:3-5)።

  • ተስፋ በዚህ ዓለም አይወሰንም (1ቆሮ.15:19)።

  • በሚመጣው ዓለም የእግዚአብሔር መንግሥት ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛም ለሌሎችም ተስፋ አለን (ኤፌ.1:18፤ 1ተሰ.2:19)።

  • ተስፋችን ምንም እንኳን አሁን ባይታይም የተረጋገጠና የማይጠፋ ነው (ዕብ.11:1፤ ሮም 5:5)።

  • እግዚአብሔር ስለማይዋሽ ተስፋችን ከንቱ አይሆንም (1ጢሞ.1:1፤ ቲቶ 1:1-2)።

  • ተስፋ ከእምነትና ከፍቅር ጋር የተያያዘ ነው (1ቆሮ.13:13)።

  • ተስፋ በቅድስና እንድንኖር መከራን እንድንታገስ ያበረታታናል (1ዮሐ.3:3፤ ሮም 8:18)።

  • እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ ተካፋዮች መሆናችንን በመንፈስ ቅዱስ አረጋግጧል (ሮም 8:14-16፤ ኤፌ.1:13-14)።

  • ሆኖም ተስፋው ፈቃዱን ለሚያደርጉ መሆኑን አውቀን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መትጋት አለብን።

  •  

    ሰዎች ለምን ተስፋ ይቆርጣሉ?

    ተስፋ የመኖር አለኝታ ሆኖ ሳለ ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሣ “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል፤ ድኻ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል” እንዲሉ የተስፋ ድኻ የሆኑ አሉ።

    መኖር ለምኔ? በማለት የሞትን ጽዋ በፈቃዳቸው የሚጎነጩም ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፤ ግን ለምን? ሰዎች ነንና ተስፋ የሚያስቆርጡን ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ፦

  • የት ይደርሳሉ ብለን ተስፋ የጣልንባቸው “ተስፋችን እናንተ ካልሆናችሁ ሌላ ማን ነው?” ያልናቸው ሰዎች ወደ ኋላ ሸርተት ሲሉ (1ተሰ.2:19)።

  • ከዛሬ ነገ ይሻላል፤ ይህም ያልፋል ብለን ተስፋ በማድረ ለመኖር ስንታገል ያልፋል ያልነው ነገር ማለፉን ትቶ የቆመ እስኪመስለን ድረስ ድካማችን ውጤት አልባ ሲሆን

  • የምንሰማውና የምናየው ነገር ሁሉ ተስፋ ሰጪነቱ ቀርቶ ተስፋችንን ሲያደበዝዘው፤ መኖርም ሲሰልቸን “እግዚአብሔር ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ የምኖረው ምን ያህል ጊዜ? ነው የምሞተውስ መቼ ነው? የሕይወቴ ፍጻሜ መቼ እንደሆነ አስታውቀኝ” እስከማለት ስንደርስ (መዝ.39:4)።

  • በመከራችንና በጭንቀታችን ጊዜ መከታ ጋሻችን ናቸው ብለን የተመካንባቸው፣ ተስፋችን ናችሁ ያልናቸው ሰዎች ድንገት በሞት ሲለዩን

  • ነገ ይሻሻላሉ፣ ይለወጣሉ ብለን የጠብቅናቸው ሰዎች ከመሻሻል ፋንታ ጥረታችንን ከምንም ሳይቆጥሩት የኋልዮሽ ሲሄዱ ስንመለከት

  • ባለን ዕውቀትና በተሰጠን ስጦታ አገራችንን፣ ሕዛባችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ለማገልገል ፈልገን ደጅ ላይ ቆመን ስናንኳኳ የአገልግሎት በሮችን የሚክፍትልን ስናጣ

  • ነገ ያገለግሉናል፣ የተሻለ ነገር ያሳዩናል ብለን ሳንማር ያስተማርናቸው ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ ያገዝናቸ ሰዎች የጣልንባቸውን ተስፋ ጥለው የሌሎች ተስፋ መሆንን እንደ ተራ ነገር ቆጥረውት ከእኔ ሌላሲሉ ስናይ

  • ስለ መልካም ሥራችን እንዳላሞጋገሱን ሁሉ ሰው እንደ መሆናችን መጠን ስንሳሳት ስህተታችንን አጉልተው ሲኮንኑን፤ ከስህተታችን የማንማርና ዘላለም አጥፊዎች አድርገው ሲያዩን

  • ትላንት ሁሉ ነገር በነበረን ጊዜ ይወዱንና ይቀርቡን የነበሩ የእኛ የምንላቸው ሰዎች ዛሬ እጅ ሲያጥረን፣ ስንታመም…እንደማያውቁን ሲሆኑ፣ ሲርቁን፣ ሲያገሉን ስናይ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ የተወንና የረሳን ሲመስለን

  • ተስፋ ያደርግንባቸው ሰዎችና ተስፋችን ያልናቸው ነገሮች ተስፋ ሊሰጡንና ተስፋ ሊሆንን ካልቻሉ አሁንስ ተስፋችን ማነው? ዘማሪው ለዚህ መልስ አለው፦ “አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?” ይላል። አዎን ተስፋችን እግዚአብሔር ነው። እርሱን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩምና (መዝ.25:3) ።

  • እውነተኛ ተስፋ በእግዚአብሔር እንጂ በወርቅ ወይም በሀብት ብዛት (ኢዮብ 31:24፣25፣28)፣ በሰው (ኤር.17:5)፣ ወይም በመልካም ሥራ (ሕዝ.33:13) ወይ ደግሞ በሐሰት ቃል በመመካት (ኤር.7:4) አይደለም። “የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ!” (2ቆሮ.10:17)። በአምላኩ በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረገ ሰው ደስ ይበለው (መዝ.146:5)።