ቀዳም ስዑር - ከጥንታዊ ድርሳን

የፋሲካ ዋዜማ ቅዳሜ  - ከጥንታዊ ድርሳን የተወሰደ ንባብ  -  “የአምላክ ወደ ሲኦል መውረድ”

Kedam Siurምን እየተደረገ ነው? ንጉሡ አንቀላፍቶአልና ዛሬ በምድር ላይ ታላቅ ጸጥታና እርጋታ አለ፣ እግዚአብሔር በሥጋ አንቀላፍቷል ለዘመናት አንቀላፍተው የነበሩትንም አስነሥቷልና፡፡ ምድር በድንጋጤና በጸጥታ ላይ ነበረች፣ እግዚአብሔር በሥጋ ሞቷል፣ የመቃብር ዓለምም ተሸብሯልና፡፡

በእውነት እርሱ የመጀመሪያውን አባታችንን እንደ ጠፋ በግ ሊፈልግ ሄደ፣ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ያሉትን ሊጐበኝ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርና የአዳምን ልጅ የሆነው እርሱ እስረኛውን አዳምንና አብራው የታሰረችውን ሐዋንን ሊፈታ ሄደ፡፡

አምላክ ድል አድራጊ መሣሪያውን፣ ይኸውም መስቀሉን ይዞ ወደነሱ ይሄዳል፡፡ የመጀመሪያውን ፍጡር የሆነውን አዳም ሲያየው ደረቱን በድንጋጤ ይመታና ለሌሎች “የኔ አምላክ ከናንተ ከሁላችሁ ጋር ይሁን” ብሎ ይጮኸል፡፡ ክርስቶስም ለአዳም “ከመንፈስህም ጋር” ብሎ ይመልስለታል፣ እጁንም አጥብቆ ይዞ “የተኛኸው ከእንቅልፍህ ተነሥ፣ ከሙታን ተነሥ፣ ክርስቶስም ብርሃን ይሰጥሃል” እያለ ያስነሳዋል፡፡

ንግግሩን በመቀጠል “እኔ ላንተ ስል ልጅህ የሆንኩት አምላክህ ነኝ፣ ላንተና ለልጆችህ ለእነዚህም በእስር ቤት ላሉት፣ ኑ ውጡ፣ በጨለማም ውስጥ ላሉት ብርሃን ይብራላችሁ በእንቅልፍ ላሉት ተነሡ ብዬ የማዘው እኔ ነኝ፡፡

“የተኛኸው ሆይ ተነሥ በመቃብር ዓለም ውስጥ እስረኛ ሆነህ እንድትያዝ አልፈጠርኩህም፡፡ ከሙታን ተነሥ፣ እኔ የሙታን ሕይወት ነኝ፡፡ የእጄ ሥራ የሆንከው ሰው ሆይ ተነሥ በኔ አምሳል የተፈጠርከው ሆይ ተነሥ፡፡ ተነሥና ወደ ፊት እንሂድ አንተ በእኔ እኔም በአንተ የማንለያይ አንድ ሰው ነንና፡፡

“ላንተ ስል፣ እኔ አምላክህ ልጅህ ሆንኩኝ ላንተ ስል እኔ የሁሉ ጌታ የሆንኩት የአሽከር ምስል ወሰድኩኝ፣ ላንተ ስል ከሰማያት በላይ የነበርኩት ወደ መሬትና ከመሬት በታች ወረድኩኝ፣ ሰው ሆይ ላንተ ስል ከሙታን መሃል ነፃ እንደሆነና እርዳታ እንደሌለው ሰው ሆንኩ፣ የአትክልት ቦታ ትተህ ለመጣኸው ላንተ ከአትክልት ቦታ ለአይሁዶች ተሰጠሁ፣ በአትክልት ቦታም ተሰቀልኩ፡፡ አንተን ወደዚያ የመጀመሪያ አምላካዊ እስትንፋስ ለመመለስ የተቀበልኩትን ፊቴ ላይ ያለውንና የተተፋብኝን ተመልከት፡፡ የተበላሸውን ቅርጽህን በራሴ አምሳል እንደገና ለመቅረጽ የተቀበልኩትን በፊቴ ላይ ያለውን ጥፊ እይ፡፡ በጀርባህ የተሸከምከውን የኃጢያት ሸክም ለማቅለል የተቀበልኩት በጀርባየ ላይ ያለውን የመገረፍ ምልክት ተመልከት፡፡ እጅህን ለመጥፎ ተግባር ወደ ዛፉ ለሰደድከው ላንተ ከዛፍ ጋር በምስማር የተያያዙትን እጆቼን እይ፡፡

በገነት ለተኛኸውና ከጐንህ ሔዋንን ላወጣኸው ላንተ በመስቀል ላይ ተኛሁ በሰይፍም ጐኔን ተወጋሁ፡፡ የኔ ጐን ያንተን ጐን አዳነ፣ የእኔ እንቅልፍ በመቃብር ውስጥ ካለህ እንቅልፍ ይቀሰቅስሃል፣ የኔ ሰይፍ ባንተ ላይ የተነሳውን ሰይፍ ገትቷል፡፡ ነገር ግን ተነስ፣ ከዚህ እንሂድ፡፡ ጠላት ከገነት ምድር አወጣህ፣ እኔ ግን ወደ ገነት ሳይሆን ወደ ሰማይ መንግስት እመልስሃለሁ፡፡ ምልክት ብቻ የነበረውን የሕይወትን ዛፍ ከለከልሁህ አሁን ግን እኔ ራሴ፣ ሕይወት ሰጭ የሆንኩት ካንተ ጋር ተሳስሬአለሁ፡፡ ባሮችን እንደሚጠብቁ ሁሉ ኪሩቤል አንተን እንዲጠብቁ አደረኩ፣ አሁን አምላክህን እንደሚያመልኩ አንተንም እንዲያመልኩ አድርጌአለሁ፡፡ 

የኪሩቤል ዙፋን ተዘጋጅቷል፣ መልእክተኞቹ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፣ የሙሽሮቹ ክፍል ዝግጅቱ ተጠናቋም፣ ምግብ ቀርቧል፣ ዘላለም የሚኖሩት ቤቶች ተዘጋጅተዋል፣ የጥሩ ነገሮች ሃብት ተከፍቷል፣ የሰማይ መንግስት ከዘመናት በፊት ተዘጋጅቷል፡፡ 

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።