እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

በትልቁ እሳት መያያዝ

17.2 - በትልቁ (መለኮታዊው) እሳት የተያያዘውን አማኝ ትንሹ እሳት ሊጎዳው አይችልም

ጌታ ኢየሱስ እንደጸለየው "እነርሱም በዓለም ናቸው... እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው፡፡ ... እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም፡፡" (ዮሐ. 17፡11፣ 14፣ 16) እኛም በውስጣችን መለኮታዊው እሳት የሚነድብን ከሆንን በርግጥ በዓለም ውስጥ እንኖራለን ነገር ግን ከዓለም አይደለንም፤ በትንሹ እሳት ፈተናዎች ውስጥ እናልፋለን፡፡ ነገር ግን የትንሹ እሳት ወገኖች አንሆንም፡፡ እንዲያውም "አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ" (ይሁዳ 23) ተብለን የታዘዝነውን ትዕዛዝ በማክበር ነፍሳትን ከሥጋ እቶን እየነጠቅን ወደ ጌታ ፍቅር እሳት እናመጣለን፡፡ በያንዳንዳችን ልብ ውስጥና በኅብረታችን መካከል በሚነደው የጌታ ፍቅር ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን ሲመላለስ አሕዛብ ዓይተው የጌታ ደቀ መዛሙርትነታችንን ያረጋግጣሉ፤ ይማረካሉ፤ ወደ ጌታም ይመጣሉ፡፡ ናቡከደነፆር ስለ ሦስቱ ወጣቶች በመገረም "እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቆሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል" ብሎ ተናግሮ ነበር (ዳን. 3፡25)፡፡ እኛም በመንፈስ ቅዱስ እሳት ተቀጣጥለን በዚህ ዓለም እሳቶች መካከል ሰንጥቀን ስናልፍ የሚያዩ ሁሉ ይህን ይመሰክራሉ፡፡ ሦስት ሰዎች ወደ እሳቱ ተጣሉ፤ እሳቱ ውስጥ ግን አራት ሆነው ተገኙ፡፡ እኛም ስለ ጌታ ፍቅር በግዙፍ ፈተናዎች ውስጥ ስናልፍ፥ ከኛ ቁጥር በላይ አንድ ሌላ ተጨማሪ ቁጥር አብሮን ይገኛል፡፡ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ከነአብደናጎ ጋር የነበረው አንድ መልአክ ነበር፡፡ ከኛ ጋር ግን የሚገኘው የነገሥታት ንጉሥ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ጣዖት አምላኪው ናቡከደነፆር የመለኮታዊውን እሳት ኃይል በዓይኑ ከተመለከተ በኋላ "በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና..." (ዳን. 3፡28-29) ብሎ የጌታን ስም ባረከ፡፡ በኛ ሕይወት ውስጥስ ይህንን አዳኝ አምላክ ዓይተው ኢአማንያን የጌታን ስም የሚባርኩት መች ይሆን?

መለኮታዊው እሳት በኛ ላይና ውስጥ ካልነደደ በስተቀር ይህ የማይታሰብ ሕልም ነው፡፡ ስለ መለኮታዊው እሳት ኃይልና ሥጋዊ (ፍጥረታዊ) እሳት ዳን 3 በሚገባ ሊያስረዳን ስለሚችል ሙሉውን ምዕራፍ ደጋግመን እናንብበው፡፡

"ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ፡፡ መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዣቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጉር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ፡፡" (ዳን. 3፡26-27) ብዙ ጊዜ በአስተሳሰባችን፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ጉብኝት እንደ አዲስ የተለወጡ ወይም የተወለዱ ሰዎች ከዚያ ልምድ በኋላ ምንም ችግር እንደማይደርስባቸው አድርገን እንገምታለን፡፡ እውነቱ ግን ፈተናውና መከራው፣ ችግሩና ስደቱ በፊት ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ የሚጨምር መሆኑ ነው፡፡ እነሚሳቅ የጌታ እግዚአብሔር ብቻ አምላኪዎች መሆናቸውን በንጉሡ ፊት ከመመስከራቸው በፊት የእሳቱ ኃይል እምብዛም ነበር፡፡ ኋላ ግን ሰባት እጥፍ እንዲነድ ተደረገ፡፡ (በዕብራውያን ሐሳብ ሰባት እጥፍ ማለት እጅግ በጣም ከፍተኛ ማለት ነው፡፡) ለአንድ አማኝም እንዲሁ ነው የሚያጋጥመው፡፡ ዳሩ ግን የፈለገውን ያህል የፈተናው ግለት ቢጨምርም መለኮታዊው እሳት መዳንን ይሰጠዋል፡፡ ፈተና የበለጠ በርትቶ ይመጣል፤ ድሉ ግን የአማኙ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ለልጆቹ ይህን ለማረጋገጥ የተስፋ ቃሉን ሰጥቶናል፡፡ "አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥! እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‹ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፡፡ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም፡፡ እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፡፡" (ኢሳ. 43፡1-3) እግዚአብሔር ልጆቹን ከፈተና ነፃ እንደሆኑ አይናገርም፡፡ ግና ከፈተናው ኃይል በላይ በእነርሱ ውስጥ ያኖረው ኃይል እንደሚበረታ ስለዚህም ድሉ የነሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በእሳት ውስጥ እናልፋለን ግን አንቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጀንም፡፡ ለምን? እነ ሲድራቅ በእሳት ውስጥ ተጣሉ ግን እሳቱ በነርሱ ላይ ኃይል አልነበረውም፤ እንዲያውም ጭራሽ የእሳቱ ሽታ አልደረሰባቸውም፡፡ ለምን? ሌላ ማብራሪያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አይታየኝም፤ ትልቁ እሳት ከትንሹ እሳት ስለሚበረታ ነው፥ ማለቱ በቂ ይመስለኛል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ቃላትም ጥሩ መልስ ይሆኑናል፡- "ልጆቼ ሆይ! እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ፤ በእናንተ ያለው መንፈስ በዓለም ካለው መንፈስ ይበልጣል፡፡" (1ዮሐ. 4፡4) አዎ! በእኛ ያለው የመንፈስ ቅዱስ እሳት በዓለም ካለው ሥጋዊ እሳት እጅግ ይበልጣል፡፡ ስለዚህም የዓለም እሳት ኃይል በኛ ላይ ኃይል ሊኖረው አይችልም፡፡

ፍጥረታዊው እሳት በመለኮታዊው እሳት ፊት ሊቆም አይችልምና፥ ጌታ ኢየሱስም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠምቆ መንፈስ ቅዱስ ወርዶበት በዚሁ መንፈስ ምሪት ወደ ምድረበዳ ሄዶ የሰይጣንን ፈተናዎች ሁሉ አሸንፎ የበለጠ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እያንጸባረቀ ወደ ምኩራብ ገባ፡፡ አጋንንትም እየጮሁ ይወጡ ጀመር፤ በሽተኞችም ሁሉ ተፈወሱ፡፡ ከምኩራብ ወጥቶም ወደ ስምዖን (ጴጥሮስ) ቤት ሲገባ የስምዖን አማት "በብርቱ ንዳድ (ትኩሳት) ታማ" ትቆየዋለች፡፡ ጊዜ አላጠፋም ንዳዱን (ትኩሳቱን) ገሰጸው፣ ትኩሳቱም ወዲያውኑ ለቀቃት (ሉቃ. 4፡38-39)፡፡ የእርሷ ትኩሳት በቴርሞ ሜትር ቢላካ እጅግ ቢበዛ 40-42 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊያልፍ አይችልም (ከዚያ ቢያልፍ ኖሮ ትሞት ነበር፡፡) ጌታ ኢየሱስ ይዞት የመጣው እሳታዊ ኃይል ግን በሰው መለኪያ የሚለካ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በዚህ እሳት ፊት ንዳድ ምን ቁም ነገር ሊኖረው? በእርግጥም መድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ምድራዊ ትኩሳቶቻችንን በሙሉ በሰማያዊው ግለቱ ያጠፋቸዋል፡፡

በመልእክት ዕብራውያን ላይም ይህ ሐቅ ተንጸባርቋል፡፡ ስለ ታላላቅ የእምነት ሰዎች የድል ገድል በሚተርክበት ምዕራፍ 11 ላይ፥ ይህ መልእክት ስለነዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹም የእምነት ኃይል፥ በአጭሩ "እነርሱ በእምነት... የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ..." (ዕብ. 11፡ 33-34) በሚል ቃላት ይገልጻል፡፡ ግን እንዴት ነበር የእሳትን ኃይል ያጠፉት? መቼም በእሳቱ ላይ ውኃ አፍስሰው እንዳላጠፉት በፊት ያነበብናቸው ጥቅሶች ይነግሩናል፡፡ እሳትን በእሳት ነበር ያጠፉት፡፡ ትንሹን እሳት በትልቁ እሳት ነበር ያሸነፉት፡፡ እኛም ብንሆን ሌላ አማራጭ የለንም፤ እሳትን የምናሸንፈው በእሳት ብቻ ነው፡፡ ምድራዊ ምኞቶቻችንን በሙሉ ማጥፋት የምንችለው፥ በመለኮታዊው ፍቅር ስንነድ ብቻ ነው፡፡

ጌታ ሆይ፥ ጥቃቅን የእሳት ፍንጣሪዎች እኛን ከማጋየታቸው በፊት፣ ዘለዓለማዊ ፍቅር በሆነው በመንፈስ ቅዱስህ እሳት አንድደን፡፡ አዎ ጌታ ሆይ ቀድመህ አንድደን፡፡ አሜን፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት