በሁለንተናችን እንጡም - ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው!!

በሁለንተናችን እንጡም - ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው!!

Yohannes Afeworkጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳሰድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒትየሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱ እንደምትወሰድ፣ በምን ያህል መጠን እንደምትዋጥ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው ወራትና በየትኛው የአየር ሁናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎች ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡

እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብተን የማንወስዳት ከሆነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡ ስለዚህ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት በትክክል ከወሰድነው ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ የነፍሳችንን ደዌ ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡

ጾም ሁለመናችንን የምንለውጥበት መሣርያ ነው፡፡ ምክንያቱም የጾም መሥዋዕት ማለት ከምግብ ብቻ መከልከል ሳይሆን ከኃጢአት ሁሉ መከልከል ነውና፡፡ ስለዚህ እየጾምኩ ነው እያለ ራሱን ከምግብ ብቻ የሚከለክል ሰው ካለ እርሱ ጾምን እያቃለለና እያጥላላ ነው ማለት ነው፡፡ {jathumbnail off}

እየጾማችሁ ነውን?

እንግዲያስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ፡፡ "እንዴት አድርገን እናሳይህ?" ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡

እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡-ድኻው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርጉለት፤ የጠላችሁትን ሰው ካያችሁት ከእርሱ ጋር ፈጥናችሁ ታረቁ፤ ባልጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት አትያዙ፤ ቆነጃጅትን በመንገድ ሲያልፉ ስታዩ በዝሙት ዓይን አትመኙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ፡፡

በሌላ አገላለጽ አፋችሁ ብቻ ሳይሆን ዐይናችሁ፣ እግራችሁ፣ እጃችሁ፣ በአጠቃላይ የሰውነታችሁ ሕዋሳቶች በሙሉ መጾም አለባቸው፡፡

ጥሉላትን (የፍስክ ምግብ) እየበላችሁ አይደለም አይደል? እንግዲያስ በዐይኖቻችሁም ክፉ ነገርን አትብሉ፡፡ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸውና፡፡ ጀሮዎቻችሁም ይጹሙ፡፡ የጀሮ ጾም ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማትና ይህን የመሳሰለ ነው

አንደበታችሁም ከከንቱ ንግግር ይጹም፡፡

ዓሣንና ሌሎች ጥሉላትን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ነገር ግን ወንድሞቻችንን በሐሜት የምናኝካቸውና የምንበላቸው ከሆነ ምን ጥቅም አለው?

ወንድሙን የሚያማና የሚነቅፍ ሰው እርሱ የወንድሙን አካል ያቆስላል፤ ሥጋውንም ይበላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ይህን አስመልክቶ እጅግ የሚያስደነግጥ ንግግርን እንዲህ ሲል የተናገረው፡- "እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" /ገላ.5፡15/፡፡

ስታሙ በጥርሳችሁ የወንድማችሁን ሥጋ አትነክሱም፡፡ በክፉ ንግግራችሁ ግን የወንድማችሁን ነፍስ ትነክሳላችሁ፤ ታቆስሉትማላችሁ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ራሳችሁን፣ ወንድማችሁንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ትጎዳላችሁ፡፡
አንደበታችሁ ክፉ ነገርን ከመናገር ካልጦመ ጉዳቱ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሐሜታችሁ እናንተን የሚሰማ ወንድማችሁም የሐሜታችሁ ተባባሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እርሱንም በደለኛ ታደርጉታላችሁ ማለት ነው፡፡ እርሱም የራሱን ኃጢአት እንዳይመለከት ስላደረጋችሁት ሳያውቅ ከሐሜተኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡ በዚህ ሰዓት የሌሎች ወንድሞቹን ድካም እየተመለከተ እርሱ ግን በመጦሙ ትልቅ የጽድቅ ሥራን እንደፈጸመ ቆጥሮ ይኩራራል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ሌላ ትልቅ ቁም ነገርም አለ፡፡ ይኸውም እናንተ ወንድማችሁን ስታሙ የሚያደምጧችሁ ሰዎች የምታሙትን ወንድማችሁን በመንቀፍ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ይልቅ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንንም ጭምር ይነቅፋሉ እንጂ፡፡ በተለይ ሰማዕያኑ ኢ-አማንያን ከሆኑ ያንን የምታሙት ሰውዬ ብቻ "አመንዝራ" ብለው አያበቁም፡፡ ከዚያ አልፈው ቤተ ክርስቲያንም የአመንዝራዎች ቤት እንደሆነች ያስብዋታል እንጂ (ሎቱ ስብሐት!)፡፡ ስለዚህ እንዲህ ስታደርጉ የእግዚአብሔርን ስም ታሰድባላችሁ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መልካም ስናደርግ እግዚአብሔር በእኛ ምክንያት እንደሚመሰገን ሁሉ ክፉ ስናደርግም በዚያው ልክ ስሙ ይዋረዳል፤ ይሰደባልምና፡፡

ሌላው ይህ እናንተ የምታሙት ወንድማችሁ በልቡ እናንተን መጥላት እንዲጀምርና የባሰ ኃጢአት እንዲሠራም ትገፋፉታላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት በማይመለከታችሁ ነገር እጃችሁን በመክተታችሁ በራሳችሁ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድን ታመጣላችሁ፡፡ ያውም በወርሐ ጦም!

ከእናንተ መካከል፡- "ዋሽቼ ስለ ወንድሜ ክፉ ነገርን ካልተናገርኩ ነገር ግን እውነት የሆነውን ነገር ብናገር (የሠራው ኃጢአትም ቢሆን) ምን ነውር አለው?" የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ግድ የላችሁም! የምታወሩት ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ አሁንም ንግግራችሁ ከነቀፋ አያመልጥም፡፡ "እንዴት ሆኖ?" ብላችሁ ልትጠይቁኝ ስለምትችሉ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ልስጣችሁና ንግግራችሁ እንዴት ብሎ ክፉ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ስምንት ላይ የምናገኘው አንድ ፈሪሳዊ አለ፡፡ ይህ ፈሪሳዊ ስለ ቀራጩ ወንድሙ የተናገረው ነገር እውነት ነው አይደል? ታድያ እውነቱን ስለተናገረ ተጠቀመ ወይስ ተጎዳ? ንገሩኝ እንጂ? ፍጹም አልተጠቀመም! እንዲህ በማለቱ (እንደ እናንተ አባባል "እውነትን በመናገሩ") ባዶ እጁን አልተመለሰምን? በመጸለዩና በመጦሙስ ምን ረብሕ አገኘ? እስኪ አሁንም ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ፡፡ ቀራጩ ኃጢአተኛ አልነበረምን? ከወንጌሉ እንደምናነበው ያ ቀራጭ ኃጢአተኛ እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ፈሪሳዊው በጸሎቱና በጦሙ መካከል የራሱን ኃጢአት ከማሰብና ከማሳሰብ ይልቅ ወንድሙን እያማ ስለነበረ ወደ ቤቱ የተመለሰው የጦምን ዋጋ ሳያገኝ ባዶውን ነው፡፡

ወንድሞቼ! "እገሌ እኮ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ሠርቷል" ብላችሁ የምታሙትን ወንድማችሁ ከዚያ ኃጢአቱ ነጻ እንዲወጣ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያስ ስለ ኃጢአቱ አልቁስለት፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩለት፤ ለብቻ ወስዳችሁም ምከሩት እንጂ አትሙት፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፎላቸው ነበር፡- "ነገር ግን ወዳጆች! እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። ስመጣ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል፤ እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፡፡ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፡፡ እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬእፈራለሁ" /2ቆሮ.12፡19-21/። ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በትልቁ ደግሞ እንደ ጌታችን "ኃጢአተኛ ነው" የምትሉትን ወንድማችሁ ውደዱት፡፡ ለብቻው አድርጋችሁ ስትነግሩትም አመጣጣችሁ እርሱን ለመምከርና ለመገሰጽ ደግሞም ከኃጢአቱ እንዲመለስ እንጂ እርሱን ከመጥላታችሁ የተነሣ እንዳልሆነ አስረዱት፡፡ ስለዚህ በትክክል ካለበት ደዌ እርሱን መፈወስ ስትፈልጉ ወደ እርሱ መሄድን አትፍሩ፤ ጥፋቱን ለመንገርም አትፈሩ፡፡

ሐኪሞችን አይታችሁ ከሆነ አንድ አስቸጋሪ ታማሚን ለማከም መጀመርያ ቀስ ብለውና ጊዜ ወስደው ታማሚዉን ያሳምኑታል፤ ከዚያም መራሩን መድኃኒት ይሰጡታል፡፡ ታካሚውም በሽታው የሚድን ከሆነ ይፈወሳል፡፡ ሐኪሙን የሚያመሰግነው ግን ሲድን ነው፡፡ እናንተም እንደዚህ ሐኪም መሆን አለባችሁ፡፡ ከምታሙት ይልቅ የወንድማችሁን ቁስል የበለጠ እንዳይመረቅዝ ፈጥናችሁ ወደ ሐኪም ቤት (ወደ ቤተ ክርስቲያን) ውሰዱት። ከዚያም ሐኪም (ካህን) እንዲያየው አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ እናንተም ወንድማችሁም በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡ እውነተኛ ጦም ጦማችሁ ማለትም እንዲህና ይህን የመሰለ መልካም ምግባር ስታደርጉ ነው፡፡

ሐሜተኞችን ብቻ ሳይሆን ክፉ ንግግርን የሚያደምጡትንም ጭምር ጀሮዋቸውን ከዚሁ ቆሻሻ እንዲያርቁ እጽፋለሁ፡፡ ከመዝሙረኛው ጋር በመሆን እንዲህ በሉ፡- "ወንድሙን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ" /መዝ.101፡5/፡፡ ከእናንተ ጋር ወንድሙን ለማማት ብሎ የመጣ ካለ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፡- "ስለ እርሱ መልካም ነገር የምትናገርለት አሊያም ደግሞ የምታመሰግነው ወንድም ካለህ መልካም መዐዛ ያለው ጨዋታህን ለማድመጥ ጀሮዬ ክፍት ነው፡፡ ክፉ ንግግርን የምታወራ ከሆነ ግን ይህን ቆሻሻ ወደ ጀሮዬ አስገባ ዘንድ ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ወንድምህ ክፉ መሆኑን ብትነግረኝ ምን ይረባኛል? ይልቁንም እንዲህ ስታደርግ ራሴን እንድጎዳና ያለኝን እንዳጣ ታደርገኛለህ፡፡ ወንድሜ! ስለ ወንድማችን ጥፋት ከምናወራ ይልቅ ስለ ራሳችን ኃጢአት ብናወራ የተሻለ ነው፡፡ የሠራናቸውን ጥፋቶች ይቅርታ እንዴት እንደምናገኝባቸው ብንጨነቅ መልካም ነው። ስለ ራሳችን ኃጢአት ብቻ ብንነጋገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ወንድሜ! ንገረኝ እስኪ! በዓይናችን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ሳናጸዳ የወንድማችንን ጕድፍ በማውራታችን የሚደረግልን ምሕረት ይኖራልን? በልቡናችን ጀሮ ላይስ ለምን ሌላ ኵክ እንጨምራለን? ..."

እንግዲያስ ይኸንን አውቀን በሁለንተናችን እንጡም፡፡ ክፉ ከመናገር እንጡም፤ ክፉ ከመስማት እንጡም፤ ክፉ ከማየት እንጡም፤ ወደ ክፉ ከመሄድ እንጡም፤ ክፉ ከማድረግ እንጡም ... የአዋጅ ጦም ሲገባ መንፈሳዊ የበጋ ወራት እንደገባ ልብ እንበል፡፡ የጦር መሳሪያችንን እንወልውል፤ ከእርሻቸው አዝመራውን የሚሰበሰቡት ገበሬዎች ማጭዳቸውን ይሳሉ፤ ነጋዴዎችም በከንቱ ገንዘባቸውን ከማባከን ይከልከሉ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባትም መንገዳቸውን ያቅኑ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምትወስደው ጎዳና ቀጭንና ጠባብ ናትና በጥንቃቄ እያስተዋልን እንጓዝ ...
ወንድሞቼ! በበሽታ ምክንያት ከምግብ ባለ-መከልከላችን የሚወቅሰን ጤናማ ሰው የለም፡፡ ከዚሁ በላይ ደግሞ የዋህና ሰውን አፍቃሪ ደግሞም ከምንችለው በላይ ምንም የማይጭንብን አምላክ አለንና፡፡ የእርሱ ፍላጎት እኛ ከምግብ እንድንከለከል፤ ወይም እንዲሁ "ሰው ምን ይለኛል" ብለን እንድንጦም፤ ወይም ሆዳችን ባዶ ሆኖ የረሀብ ስሜት እንዲሰማን ማድረግ ሳይሆን ከማንኛውም ክፉና ዓለማዊ ምግባር ጦመን ለትሩፋተ ሥጋ ለትሩፋተ ነፍስ እንድንተጋ ነውና፡፡

ራሳችንን በተስተካከለ ሕይወት የምንመራ፣ መብላት ያለብንን ያህል መጥነን የምንበላ፣ ፍላጎታችንን ሁሉ ወደ ሰማያዊ ነገሮች የምንመልስና መላ ዘመናችንም መልካም ነገርን ብቻ የምናደርግ ብንሆን ኖሮ እሴተ ጦምን (የጦምን ዋጋ) ለማግኘት ብለን መጦም ባላስፈለገን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሰው ልጆች ስንባል በተፈጥሮአችን ግዴለሾችና ምቾትን የምንሻ ስለሆነን ከምድራዊ አባትም ሆነ ከምድራዊት እናት በላይ ስለ እኛ የሚጠነቀቀው ሐኪማችን (እግዚአብሔር) ይህንን ግዴለሽነታችንና አላስፈላጊ ቅምጥልነትን ፈውሰን ከዓለማዊ ምግባር ወደ መንፈሳዊ ምግባር እንድንገባ ጦም የተባለች መድኃኒትን አዘጋጀልን፡፡

ስለዚህ በበሽታ ምክንያት ራሳቸውን ከምግብ መከልከል ያልቻሉትን እንዲበሉ ነገር ግን ደግሞ ከክፉ ምግባር እንዲጦሙ እመክራቸዋለሁ፡፡ ከምግብ በቀር በሌላው መንፈሳዊ ነገር አብልጠው እንዲተጉ እመክራቸዋለሁ፡፡ በሽተኞች ከምግብ መከልከል ባይችሉም በእውነት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚያስከፍቱ ሌሎች አማራጮች አሉላቸው፡፡ ስለዚህ በሕመም ምክንያት ከምግብ መከልከል ካልተቻላችሁ አብዝታችሁ ምጽዋትን ስጡ፤ ከምግብ መከልከል ባትችሉ አብልጣችሁ ጸልዩ፤ ራሳችሁን ከምግብ መከልከል ባትችሉ ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር የተጋችሁ ሁኑ፡፡ በሽታችሁ ይህን ሁሉ ከማድረግ አይከለክላችሁምና... እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እውነተኛ ጦምን ጡማችኋል፡፡ እግዚአብሔርም ከዚህ የበለጠ ከእናንተ የሚሻው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሐኪማችን ከጥሉላት እንድንከለከል የሚያዘን ፈቃደ ሥጋችን ደክሞ ፈቃደ ነፍሳችን እንዲበረታ በዚያም ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ ነውና...

ስናጠቃልለው በጦም ሰዓታችሁ ይሁን በሌላ ጊዜ ይሁን ሦስት ነገሮችን በሕሊናችሁ ትይዙ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ እነርሱም ክፉ ከመናገር መከልከልን፣ ማንንም ሰው እንደጠላት ከማየት መቆጠብንና፣ እንደ ልምድ አድርጋችሁ ከያዛችሁት መሐላ ትርቁ ዘንድ፡፡ በአጨዳ ላይ ያለ ገበሬ እህሉን ከማሳው በአንዴ እንደማይሰበስብ ነገር ግን በጥቂት በጥቂቱ እንደሚሰበስብ ሁሉ እኛም እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በዚህ የጦም ወቅት ልንለማመዳቸው እና መልካም ልምዶቻችን ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ እንዲህም በማድረጋችን በቀላሉ መንፈሳዊ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ ይቻለናል፡፡ በዚህም ዓለም ሳለን መልካም ተስፋ ያለውን አዝመራ እናፈራለን፡፡ በሚመጣውም ዓለም በክርስቶስ ፊት ያለፍርሃት በደስታ ተሞልተን እንድንቆም ይረዱናል፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃንን ጸጋ አግኝተን የክብሩ ወራሾች ያድርገን፡፡

ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ለዓለም ወለዓለም አሜን፡፡

ከ http://tesfalem7.blogspot.com/ የተወሰደ