ቤዛችሁ ሕይወታችሁ፣ ትንሣኤያችሁ እኔ ነኝ

የሳርዲሱ መሊጦን ስለ ፋሲካ ከጻፈው ድርሳን የተወሰደ ንባብ - "የክርስቶስ ውዳሴ"

Christ is Risen 1

ወዳጆች ሆይ የፋሲካ ምስጢር እንዴት አዲስና አሮጌ፣ ዘለዓለማዊና ኃላፊ፣ የሚበሰብስና የማይበሰብስ፣ ሟችና ዘለዓለማዊ እንደሆነ መረዳት አለባቸው፡፡

በሕጉ መሠረት አሮጌ ነው፣ ነገር ግን በቃል መሠረት አዲስ ነው፡፡ በቀዳሚነቱ ጊዜያዊ ነው፣ ነገር ግን በጸጋው ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በበጉ መሰዋት ጠፊ ነው፣ ነገር ግን በአምላክ ሕይወት ነዋሪ ነው፡፡ በመሬት ውስጥ በመቀበሩ ምክንያት ሟች ነው፣ ነገር ግን ከሙታን በመነሣቱ ዘለዓለማዊ ነው፡፡

ሕግ አሮጌ ነው ቃል ግን አዲስ ነው፤ ቀዳሚው ጊዜያዊ ነው፣ ጸጋ ግን ዘለዓለማዊ ነው፣ በጉ ጠፊ ነው አምላክ ግን ኗሪ ነው እርሱ እንደ በግ ተሠዋ ሆኖም እንደ አምላክ ተነሣ፡፡እንደ በግ ወደ ማረጃው ስፍራ ተነዳ፣ ነገር ግን በግ አልነበረም፣ ድምፅ እንደሌለው ጠቦት ነበር፣ ነገር ግን ጠቦት አልነበረም፡፡ ምስሉ አልፎ እውነቱ ተገልጧል፡፡ በጠቦቱ ፋንታ የመጣው እግዚአብሔር ነው፣ በበጉ ፋንታ የመጣው ሰው ነው፣ ይህም ሰው ሁሉንም ነገሮች የሚይዘው ክርስቶስ ነው፡፡

ስለዚህ የበጉ መሰዋት የፋሲከ አከባበርና የተጻፈው ሕግ በክርስቶስ ከፍጻሜ ደርሰዋል፡፡ በአሮጌው ሕግ ውስጥ ያለው ሁሉም ነገርና በተለይ በአዲሱ ሕግ ውስጥ የሚገኘው ሁሉም ነገር ወደርሱ ያመለክታል፡፡

 ሕግ ቃል ሆኗል፣ አሮጌውም አዲስ ሆኗልና ትዕዛዝ ጸጋ ሆኗል፣ ምስል የነበረው እውነት ሆኗል፣ ጠቦቱ ወልድ ሆኗል በጉ ሰው ሆኗል ሰውም እግዚአብሔር ሆኗል፡፡

አምላክ ቢሆንም ሰው ሆነ፣ በስቃይ ላይ ለነበሩት ተሰቃየ፣ ለእስረኞች ታሰረ፣ ለተፈረደባቸው ተፈረደበት፣ ለተቀበሩት ተቀበረ፣ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት "ከኔ ጋር የሚፎካከር ማነው? እስቲ ይቋቋመኝ፡፡ እኔ እስረኞችን ነፃ አድርጌያለሁ፣ ሙታንን ወደ ሕይወት ጠርቻለሁ፣ የተቀበሩትንም አስነስቻለሁ፤  እኔን የሚቃወም ማነው? ብሎ ጮኸ፡፡ "እኔ ክርስቶስ ነኝ" "ሞትን ያጠፋሁኝ፣ ጠላትን ድል ያደረግሁት፣ መቃብርን ከእግሬ በታች የረጋገጥኩት፣ ብርቱውን ያሰርኩትና ሰውን ወደ ከፍተኛው ሰማይ ቀምቼ የወሰድኩት እኔ ክርስቶስ ነኝ" ይላል፡፡

"እንግዲያውስ እናንተ በኃጢአት የረከሳችሁ ሕዝቦች ኑ፣ የኃጢአታችሁን ይቅርታ ተቀበሉ፡፡ ስርየታችሁ፣ የደኅንነታችሁ ፋሲካ፣ ለእናንተ የተሠዋሁ በግ፣ ቤዛችሁ ሕይወታችሁ፣ ትንሣኤያችሁ፣ ብርሃናችሁ፣ ደኅንነታችሁና ንጉሣችሁ እኔ ነኝ፡፡ ወደ ከፍተኛው ወደ ሰማይ እወሰዳችኋለሁ፣ ዘለዓለማዊው ወደ ሆነው አብ አቀርባችኋለሁ፣ በቀኝ እጄ አነሳችኋለሁ"