በዝምታ ውስጥ ያለ ኃይል

በዝምታ ውስጥ ያለ ኃይል

በምድረበዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አባቶች የሕይወት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ተጽፎ እናገኛለን፤ አንድ ወጣት መነኩሴ ወደ ምድረ በዳ በአንድ ወቅት ሄዶ አባ መቃሪዮስ የተባሉትን መነኩሴ ስለ መንፈሳዊ ሕይወቱ ምክር እንዲሰጡት ጠየቃቸው፡፡ እኚህም ሽማግሌ ባህታዊ “ተመልሰህ በምንኩስናህ ጐጆ ውስጥ ተቀመጥ፣ ጐጆህም ሁሉን ነገር ታስተምርሃለች” ብለው መለሱለት፡፡

ጽሞና ከhttp://www.varbak.com/immagine/fotografie-nella-solitudine-del-deserto የተወሰደዝምታ ወይም ጸጥታ ታላቅ መምህር ናት፤ ከርሷም ልንማረው የምንችለው የመጀመሪያው ነገር ሰላምና ጸጥታ እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ሰው በሥጋና በነፍስ የቆመ ነው፡፡ ሥጋችን እራሱን ለማደስ ከግዙፋዊ ተግባሮች ገለል ብሎ ማረፍን ይፈልጋል፡፡ እንዲሁም ነፍሳችን እንድትረካና እንድትታደስ ሰላምንና ዝምታን ወይም ጸጥታን ትፈልጋለች፡፡

እረፍት ካላገኘ ግዙፋዊ አካላችን ሊወድቅና ሊፍረከረክ ግድ ነው፡፡ እንደዚያውም አእምሮአችን በእንቅልፍ እንዲያርፍ ካልተደረገ መስመሩን ስቶ ለውጥንቅጥ ይዳረጋል፣ ስለዚህም ትክክለኛ ፍርድን ማስተላለፍ አይቻለውም፡፡ ከዚህም በላይ በግዴታ በሚደረግ ንቃትና ከእንቅልፍ በመከልከል አእምሮአችንን የማሰብ ችሎታውን ከማዳከሙ በላይ በሕሊና ላይ የማይጨበጥ የሕልም ዓለም ክስተት እንዲጫንበት ያደርገዋል፡፡ ያለ እንቅልፍ መጓዝ ወደ ቅዥት ዓለም እንድንገባ ያደርገናል፤ ነገሮችን ባሕሪያዊ ቅንጅታቸውን በማጣት ይዘበራረቁብናል፤ ስለዚህም ከዚህ የተዘበራረቀ ሁኔታ ለማምለጥ ዓይናችንን ጨፍነን ትንሽ ማሸለብን እንናፍቃለን፡፡ የአእምሮን ጉዳይ ለማምለጥ የግድ ትንሸ እንቅልፍ ያሰፈልገናል፡፡

ክርስቶስ የአገልግሎቱ ወቅት ተአምራቶቹ ዝና ተስፋፍቶ በተሰማ ጊዜ “ወሬው አብዝቶ ወጣ፣ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው  ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር” ይለናል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ የሚፈልጉትን ሕዝብ ትቶ “ወደ ምድረበዳ ፈቀቅ ብሉ ይጸልይ ነበር” ሉቃ 5፡ 15-16

በገሊላ ባሕር ዳርቻ እንደዚሁ ሲያደርግ እናያለን፤ “ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ” ማቴ. 8፡18 ይህን ለምን አደረገ? ኢየሱስ ይህን በማድረጉ በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ሊያስተምረን ይፈልጋል፡፡ ይኼውም እራሳችንን ማዘጋጀት እንዳለበን፣ መጸለይ እንዳለብን፣ አሳቦቻችንን ማሰባሰብ እንዳለበንና በጣም አስፈላጊና ትልቅ ከሆነ ተግባር በፊት ኃይላችን ማሳደስ እንዳለብን ሊያስተምረ ይፈልጋል፡፡ ይህም ደግሞ ወይም አገልግሎት በፊት ብቻ ሳይሆን ከአገለግሎቱም ፍጻሜ ወይም ድምዳሜ በኋላም መሆን እንዳለበት ያሳየናል፡፡ ሐዋርያት ወደ ኢየሱስ ተመልሰው በመሰብሰብ ያደረጉትንና ያስተማሩትን በነገሩት ጊዜ የሆነው ነገር ይህንን ያስተምረናል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረበዳ ኑ እና ጥቂት ዕረፋ አላቸው፡፡” ስለዚህም “በታንኳም ብቻቸውን  ወደ ምድረበዳ ሄዱ፡፡” ቅዱስ ማርቆስ ይህንን ሊያደርጉ ለምን እንደ ተገደዱ ሲነግረን እንዲህ ይለናል፣ “የሚሄዱና የሚመጡ ብዙዎች ነበሩና ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ፡፡” ማር. 6፡3ዐ-32 በዕረፍት ወይም በመዝናኛ ጊዜያቸው በእርግጥም ሥጋቸውንም ሆነ ነፍሳቸውን መመገብ ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ስለሚል ነው፡፡ ዘዳ. 8 ፣ ማቴ. 4፡4 ሉቃ፡4 የአካላችንን ጤንነት ከምግብና ከዕረፍት እናገኛለን፡፡ የእግዚብሔርን ቃል የነፍሳችን ምግብ ከሆነ ዘንድ ጸጥታም ነፍስን የሚያጠነክረው ዕረፍት ነው፡፡

“ደሴቶች ሆይ በፊቴ ዝም በሉ፣ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፡፡” ኢሳ. 41፡1

“በጸጥታና በመታን ኃይል ይሆንላችኋል፡፡” ኢሳ. 3ዐ፡15

“የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፡፡” ኢሳ. 1፡1ዐ ኤር. 2፡4 የሚለው ነቢያዊ ጩኸት እንድንሰማ የተደረገ ጥሪ ብቻ ሳይሆን በወገናችንም ዝም በማለት በጸጥታ እንድንሰማ የተደረገውን ጥሪም ጭምር ነው፡፡ እኛ ጸጥ ስንል ብቻ ነው የእግዚብሔር ቃለ ሲናገረን መስማት የምንችለው፡፡ ማርታ የዘነጋችው፣ ማርያም ግን የመረጠችው የበለጠ ምርጫ፣ ጌታ እንዲናገር የገፋፋው፣ በጸጥታና በማስተዋል ከእርሱ ሥር የመቀመጧ ሁኔታ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው በጸጥታ የመቀመጥ ሁኔታ የእግዚብሐርን ቃል ማቀፍና መያዝ የሚያስችለው፡፡ ሉቃ. 1ዐ፡ 38-42 ይህ “ሕያውቃል” በፍላጐት፣ በልዩ ፍቅርና ናፍቆት ከመስማት የበለጠ ምን ሊፈልግ ይቻለዋል? አትክሮት ያለው ጸጥታ ከመምህሩ የሆኑን መመሪያን ያካተቱ ቃላቶችን አንዲደመጡ ያደረጋቸዋል፡፡

“ኢዮብ ሆይ አድምጥ እኔንም ስማ፣ ዝም በል፣ እኔም እናገራለሁ፡፡” ኢዮብ 33፡31

“… ዝም በል እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ፡፡” ኢዮብ 33፡33

የእግዚአብሔር ቃል በውሳጣዊ ማንነታችን ላይ ሊያስተጋባና በጥልቅ ሁኔታ ሊሰማ የሚችለው በዝምታ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ቃሉ በጌታ ዕውቀት አማካይነት ወደ አዲስ ሕይወትና ብርታት ሊመራንና ሊያነቃቃን ይቻለዋል፡፡ ይህም ዕውቀት በጸጥታ ከቃሉ ዳቦ ወይም እንጀራ ወይም ምግብ እንድንሳተፍ ያደርገናል፡፡ ይህም የቃሉ ማዕድ ተሳትፎ ዕውቀትን እንድናገኝ ያደርገናል፡፡ ቃሉ ለነፍሳችን ምግብና ብርታት ወይም ጥንካሬዋ ነው፡፡

የጌታን ቃል መገንዘብ ወይም መረዳት ማለት ለነፍሳችን ብርታትን የምናገኝበትን በውስጡ ያለውን እውነት፣ ጥበብና ዕውቀት መገንዘብ ወይም መረዳት ማለት ነው፡፡

ጸጥታ ወይም ዝምታ ሊያስተምረን የሚተለው ትልቁ ትምህርት ቃሉን ከመገንዘብ ወይም ከመረዳት እንዴት ጌታን ወደ ማወቅ መሸጋገር እንደምንችል ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመሰማት ዋነኛውና አንደኛው እርመጃ በውስጣዊ ሕይወት ውስጥ ጸጥታን ማግኘት ነው፡፡

በመጨረሻ የዕውቀት ሁሉ ፍጻሜ በሆነው በእርሱ ግልጽነት እንረካለን፡፡


ምንጭ፡ ሰሊሆም ቁጥር 5

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።