የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው!

የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው!

KibrLeMariamእያንዳንዱ ቋንቋ እንደ የባህሉ፣ ታሪኩና እምነቱ የሚጠቀምባቸው የአነጋገር ዘይቤዎች አሉ፡፡ በአማርኛ ቋንቋም ከክርስትና እምነት መንፈሳዊ ልማዶች ወደ ቋንቋው አባባልነት የተቀየሩ ብዙ ሐረጎች አሉ፡፡ በእመቤታችን ማርያም ስም ቋንቋችን ውስጥ ከምናገኛቸው አገላለጾች ከላይ ለርእስነት የተጠቀምንበት አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማርያም ትማርሸ፣ ማርያም በሽልም ታውጣሽ፣ ማርያም ጭንሽን ታሙቀው የሚሉ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ሲኖሩ ማርያም ታኑርሽ ወይም ታኑርህ የሚሉ ተመሳሳይ ምላሾችን እናገኛለን፡፡

ከነዚህ መሰል እምነትንና ባህልን ካቆራኙ አገላለጾች በስተጀርባ ብዙ ሊባል የሚችል ነገር ይኖራል፤ “የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው” ግርድፍ በሆነ አፈታት ትርጉሙ እንዲገባን በምን ዓይነት መቼት (ጊዜና ሁኔታ...) እንደሚባል እናስታውስ፡፡ አንድ ሰው ስሙ ሲጠራ ሰምቶ ወይም መስሎት የጠራውን ሰው ለማየት ዙሪያ ገቡን ሲያማትር የሰው ሽታ ሲጠፋበት የማርያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው ብሎ የመመለስ ልማድ አለ፡፡ ይህ ሁለት ነገር ሊያመላክተን ይችላል፤ ማለትም ጠሪ ብለን ያሰብነው ማንነትንና ተጠሪው የሚሰጠውን ምላሽ፤ አለሁ ብሎ ጠርቶ ዞር ስንል የለሁም የሚለውን በተለያየ መልኩ የሚጎትተንን ጠላት አታላይ ሰይጣንንና ይህን አታላይ የሚያሸንፈው ደግሞ የአዳኙ ክርስቶስ እናትና የእግዚአብሔር ቃል እንደሚላት “የልኡል ኃይል የጋረዳት” “የዘንዶውን ራስ የሚቀጠቅጠውን” የወለደች የእርስዋ ክብር ነው፡፡

“ማርያምን ለማክበር በስምዋ ጽዋ እደግሳለሁና ለዚህ በዓል ዝግጅት የሚሆነኝን ብቅል እያዘጋጀሁ ነው አንተ ክፉ ከኔ ራቅ!” የሚል አንድምታን የያዘው ይህ አባባል ዛሬም እኛ እመቤታችንን ስናከብር ዘወትር ከርስዋ የማይለየውንና በምድርም በሰማይም ያከበራትን ሁሉን ቻይ ልጅዋን፣ የማዳን እቅዱን በርስዋ ያከናወነውን አብንና ከሥጋ እድፈት ጠብቆ የክርስቶስን ሰው መሆን እውን ያደረገውን መንፈስ ቅዱስን በአንድነት እናከብራለን፤ በርግጥም ይህን የመሰለ ክብር ሰይጣንን ማስደንገጥና ማሸነፉ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ስለዚህም እመቤታችንን የልባችን ንግሥት ባደረግናት መጠን  ክርስቶስንም የሕይወታችን ንጉሥና ገዢ እናደርገዋለን፡፡

እግዚአብሔር ራሱ እመቤታችን የአካሉ እናት ትሆን ዘንድ ፈቅዶ በቅዱስ ዮሐንስ አምሳል “እነሆ እናትህ፤ እናትሽ!” ሲለን ምንኛ መታደላችንንና ልዩ መብት መጎናጸፋችንን አስተውለን “እነሆኝ ልጅሽ” እንበላት፡፡ ከርስዋና ከልጅዋ ርቀን በሄድን ወይም ያለምንም የሕይወት ለውጥ በሌላ ጊዜያችን ማለትም እድሜያችን እየተነነ ከሆነ አታላዩ እየጠራ ዞር በማለት ሲያከራትተን ይኖራል፡፡ የእመቤታችንን ዱካ በመከተል እጅዋን ከያዝን እርስዋ ክርስቶስን አቅፋለችና የታላቁ ቤተሰብ ክፍል እንሆናለን፡፡

ይህ ከላይ ለማለት የሞከርነውን ጭብጥ አቅፎ በያዘው በቅዱስ በርናርዶስ ምክር እንደምድም

“ወደ ክዋክብት ተመልከትና ማርያምን ጥራ!

በአደጋ፣ በችግር ወይም በጥርጣሬ ጊዜ ማርያምን አስብ፡፡

ስምዋን በከናፍርህ አኑረው፡፡ የእርሷ ስም ከልብህ በፍጹም አይውጣ!

በእግር ዱካዋ የአንተን እግር አኑር ከቶ አትጠፋም፡፡

ወደርሷ ተማጠን ተስፋ ቁርጠት አይጠናወትህም፡፡

እርሷን አስብ አትሳሳትም፤

እርሷ እጅህን ይዛህ መውደቅ አይቻልህም፣

አትታክትም፣ አትፈራም፣ በጥበቃዋ እየተደሰትክ ወደ ግብህ ትደርሳለህ፡፡"