እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ኪዳነ ምሕረት፡- የሕይወት ስጦታ በማርያም እሺታ!

ኪዳነ ምሕረት፡- የሕይወት ስጦታ በማርያም እሺታ!

Kidanemhret 001በኪዳነ ምሕረት በዓል በሚነበበው የመጀመሪያንባብላይየተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ላከልን” (ገላ 44) የሚል ሃሳብ እናገኛለን፤ ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣው እኛ ሁላችን በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እግዚአብሔር ለልጆቹ ያዘጋጀውን ነገር ሁሉ እንድንወርስ ነው፡፡ በኪዳነ ምሕረት በኩል የቀረበልን የሕይወት ስጦታ ዘላለማዊና በጸጋ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንን ስጦታ ለመውረስ አስፈላጊ የሆነው የሕይወት መርሕ በሁለተኛው ንባብ ላይ ተገልጧል፡፡ 2ኛ ዮሐ 1፡4-7 ውስጥ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን የተጠሩ ሁሉ አንድ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም ትዕዛዝ “እርስ በእርሳችን መዋደድ ነው!”

          ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍፃሜ ነውና በፍቅር እንደ እግዚአብሔር ልጆች በመመላለስ የእግዚአብሔርን ልጆች ዘላለማዊ ሀብት ለመውረስ ተጠርተናል፡፡ ዮሐንስ በመልእክቱ “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (2ኛ ዮሐ 1፡8) በማለት ፍቅር የድካማችንና የጉዟችን ፍሬ ሙሉ ደመወዝ የሚያስገኝልን ይሆን ዘንድ በጥንቃቄ እንድንጓዝ ይመክረናል፡፡

          በዚህ ጉዞ ውስጥ ሁለት ነገሮች አጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ከሐዋሪያት ሥራ የተነበበልን ሦስተኛው መልእክት ይህንን ይገልጥልናል፡፡ ሐ.ሥ 1፡13-14 “አንድ ልብ ሆነው በተሎት ይተጉ ነበር “ይላል በአንድ ልብ ሆኖ በጋር መጓዝ  እና ጸሎት ለክርስትና ሕይወት እጅግ መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱ ሁል ጊዜ በአንድነት እንዲሆኑ እና በጸሎት እንዲተጉ ያስተምራቸው እንደነበረ ሁሉ ለእኛም ዛሬ የሚያሳስበን በአንድነት እንድንጸና እና ሁል ጊዜ በጸሎት እንድንተጋ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሥርዐተ አምልኮ የዐብይ ጾም ውስጥ እንገኛለን፡፡ ጾም የጸሎት፤ የተጋድሎ እና ወደ እግዚአብሔር የመመለስ ልዩ የተቀደሰ ወቅት ነው፡፡ ዐብይ  ጾም በሀገራችን በእጅጉ የምንዘጋጅበት፤ ወደ ፋሲካ የምናደርገውን ጉዞ የምንጀምርነት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም በዐብይ ጾም ከሥጋ ፈቃድ ጋር ትግል በማድረግ ለነፍስ ድህንነት የምንዋጋበት ወቅት ነው፡፡ ወደ ፋሲካ የምናደርገው ጉዞ በባሕርዩ የመስቀል መንገድ በመሆኑ ውጊያ አለበት፡፡

በሥጋ እና በነፍስ መካከል ጦርነት ይደረጋል፤ ይህ የጾም ጊዜ ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት፤ የሥጋን ገደብ የለሽ ጩኸት ቀንሰን የነፍስን መቃተት የምናዳምጥበት ጊዜ ነው፡፡ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ስጋችን እንደራበው ይናገራል፡፡ ስለዚህ ቁርስ እንበላለን፤ ትንሽ ቆይቶ ጠማኝ ይላል፤ እንጠጣለን፤ ትንሽ ቆይቶ ሥጋችን ደከመኝ ይላል እናርፋለን፡፡ የቀኑን አብዛኛውን ክፍል የሥጋችንን ምኞት ስንፈጽም እንውላለን፡፡ ሥጋችን ሲገዛን ይውላል፤ አብዛኛውን ጊዜ በሥጋ እና በነፍስ መካከል ያለውን ጦርነት የሚያሸንፈው ሥጋችን ነው፡፡

ሥጋ ልክ እንደ ገንዘብ ነው፡፡ በጣም ጠቃሚ አገልጋይ ሆኖ ሳለ በተመሳሳይ ጊዜ እጅግ ክፉ ገዢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የዐብይ ጾም ወቅት ይህንን ጦርነት ከሌላው ጊዜ በተለየ በቆራጥነት ለመፋለም፤ የአሸናፊነታችንን ክንድ የምናነሳበት ጊዜ ነው፡፡

ስለዚህ የክርስቲያናዊ ሕይወት ጉዞ ትግሉ፤ ፈተናው፤ጦርነቱ ሁሉ ከገዛ ራሳችን ጋር ነው! ጠላቶቻችን  ያሉት በውስጣችን ነው፡፡ እነርሱም ትዕቢታችን፤ ቅናታችን፤ ስስታችን፤ ንፍግነታችን ሀኬታችን ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አርዕስት ኃጢአቶች መካከል በእኛ ላይ ገዢ ሆነው የሚገኙት የትኞቹ ናቸው? በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ስንመረምር የትኞቹ ኃጢአቶች ባርያ አድርገው እየገዙን እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ምናልባትም እነዚህ ኃጢአቶች አብረውን ለዘመናት የተጓዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዛሬ ውጊያው ካልተጀመረ ባርነቱ በራሱ አያበቃም፡፡ ስለዚህ ውጊያው አሁን መጀመር አለበት፡፡ ሐዋርያው እንደሚለው “የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው” (2ኛ ቆሮ 6፡3) ስለዚህ ለውጊያው ምን ያስፈልጋል? ወይንም ምን ማድረግ አለብን?ብለን ብንጠይቅ ሓዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልክ እንድንዘጋጅ ይመክረናል፤ “በቀረውስ ወንድሞቼ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ፤የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ በሙሉ ልበሱ” (ኤፌ 6፤10-11)

ሕይወታችን ቁጥቋጦ እንደበዛበት እርሻ ነው፤ በእርሱ ውስጥ ከሚበቅሉት እሾኾች አንዱና የተቀሩት ኃጢአቶች ሁሉ አባት ትዕቢት ነው፡፡ ይህም የሌሎች የኃጢአት ቁጥቋጦዎች ዘር፤ ሥርና ግንድ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔርና ከባልንጀራችን ጋር የሚያራርቀንና ስምምነት የሚያሳጣን የትዕቢት መንፈስ ነው፡፡ ሳጥናኤል ከሰማይ የወደቀበት፤አዳም ከገነት የተባረረበት ምክንያት ትዕቢት ነው፡፡ ዓለምና እያንዳንዱ ኅብረተሰብ ፍቅርና ሰላ የሚያመጣበት ዋነኛው ምክንያት ትዕቢት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጣላት ጋር በጥብቅ መዋጋት አለብን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢተኛ ሰው ወደ ጥፋት ያመራል፤ትሑት ሰው ግን ክብርን ይጎናጸፋል“ (ምሳ 18፤12) እያለ ያስተምራል፡፡

የሉቃስ ወንጌል 1፡46-55 የማርያም የምስጋና ጸሎት

በዚህ የምሥጋና ጸሎት ውስጥ የማርያም በእግዚአብሔር ስለመመረጧ የምሥጋና መዝሙር ታቀርባለች፡፡ ይህ የምሥጋና መዝሙር የዚህችን  ወጣት ልብ ከፍቶ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሔርን ስለ ድንቅ  ሥራው ምታመሰግን ነፍስ ምን እንደምትመስል በማርያም ምሥጋና ውስጥ መመልከት ይቻላል፡፡  ይህንን የምሥጋና ጸሎት የበለጠ ለመረዳት ጸሎቱን በሁለት አንጓ ከፍሎ መመልከቱ ይጠቅመናል፡፡

በመጀመሪያው  ክፍል ማርያም እግዚአብሔር ስለደረገላት ድንቅ ነገር ምሥጋና ታቀርባለች፡፡ምንም እንኳን እርሷ ዝቅተኛ የእግዚአብሔር አገደልጋፈይ ብትሆንም እግዚአብሔር በእርሷ ታናሽነት ውስጥ ታላቅ ነገር እንዳከናወነ አውቃለች፡፡ በዚህ ታላቅ ስራው አማካኝነት እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ስላደረጋት፤ ከእርሱ ምሕረት የተነሳ “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ 1፡48) እያለች በደስታ ትዘምራለች፡፡ እርሱ ለተለየ ተግባር መርጧታል፡፡ ስለዚህ በሁሉ ነገር ከኃጢአት ነፃ አድርጎ እና ፍጹም ንጸሕት አድርጎ ጠብቋታል፡፡ ማርያም “ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ስትል ( ሉቃ 1፡48) በራሷ ጥረት ስላገኘችው ነገር አልተናገረችም፤ ይልቁንም “ብርቱ የሆነው እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና “ብላ ምሥክርነቷን ለእግዚአብሔር ትሰጣለች፡፡ ስለዚህ ማርያን ብፅዕት ብለን መጥራታችን እግዚአብሔር በእርሷ ውስጥ ስላከናወነው ነገር እውቅና መስጠታችን ነው፡፡ ማርያምን ብፅዕት ብለን መጥራታችን ከእርሷ ጋር በመተባበር ታላቅ ነገር ላደረገው ለእግዚአብሔር ከፍ ያለ ምሥጋና መስጠታችን ነው፡፡

በጸጋው ስለተሞላች የእርሱን ጥሪ በታዛዥነት “እሺታ” ተቀብላ ለምሕረት በሯን ከፍታለች፡፡ ከግርግም እስከ መስቀል ድረስ ለእግዚአብሔር ጥሪ ታማኘ በመሆን በመፍሕረት ሥራ ውስጥ  ፍጹም ተባባሪነቷን  በተግባር ገለጠች፡፡

 በሁለተኛው ክፍል ማርያም ስለ እግዚአብሔር “ሁሉን ቻይነት “ ትዘምራለች፡፡ ይህ መሐሪ አምላክ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ የነገሮችን መዘበራረቅ ያስተካክላል፤ ሰባራውን ሰብዓዊነታችንን ይጠግናል፡፡ ትዕቢተኞችን ያዋርዳል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ታላላቀ ገዢዎችን ከዙፋናቸው ያወርዳቸዋል፤ የተራቡትን ግን በመልካም ነገር ያጠግባቸዋል፡፡ እርሱ ይቅር ሲሰው የማይችለው ኃጢአት  ቀንበር የለምና ወደ እርሱ የሚቀርቡትን ይቅር ይላል፤ ሸክማቸው የከበደባቸውን ያሳርፋቸዋል፡፡ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ “ማርያም ወሰን የለሽ ሰሆነው ለእግዚአብሔር ምሕረት ምሥክር ነች” በማለት የእግዚአብሔር ምሕረት /ከምድራዊ ነገሮች/ ሁሉ በላይ/ያለ ልዩነት/ ያለ ልዩነት/ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ/ ስለመሆኑ ይናገራሉ (የምሕረት ፊት ቁጥር 24)፡፡

ይህ የማርያም የምሥጋና ጸሎት የእግዚአብሔር ምሕረት ከትውልድ እስከ ትውልድ የሚዘልቅ እንደሆነ (1፡50) ሲናገር ሁላችንንም ጠቅልሎ በእግዚአብሔር ምሕረት ሥራ ውስጥ ተባባሪዎች እንድንሆን ግብዣ ያቀርብልናል፡፡ እግዚአብሔር በማርያም እሺታ ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን እንዳደረጋ ሁሉ ዛሬም ግብዣውን በሚቀበሉትና በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች አሺታ ውስጥ የምድርን ገጽ ማደስ ይፈልጋል፡፡ የማርያም የምሥጋና ጸሎት የእግዚአብሔርን ወሰን አልባ ምሕረት የሚወድስ፤ ለምሕረት ሥጦታው የቀረበ ምሥጋና ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረት በሕይወቷ ውስጥ በመለማመዷ ማርያም  የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመሸከምና ለማንጸባረቅ በቃች፡፡ እርሷ ምሕረትን እንደምንታንጸባርቅ መስታዋት ለእያንዳንዳችን እና ለቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ምሕረት አብነት ሆናለች፡፡ በሕይወት ዘመኗ  ሁሉ ለዚህ የምሕረት ሥጦታ ታማኝ አገልጋይ በመሆን ልጇን እስከመስቀል ድረስ በማጀብ ለሁላችንም የምሕረት ተባባሪነቷን ገልጣለች፡፡ በምድር የነበራት የደስታ፤ የሕማም እና የክብር ጉዞ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምሕረት መከናወን ራሷን አሳልፋ የሰጠችበት ጉዞ ነበር፡፡

በዚህ ዓይነት እያንዳንዳችን በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመቀበል እና ለሌሎች ለማካፈል ቦታ ሊኖረን ይገባል። ይህንን ቦታ በውስጣችን የሚያዘጋጀውና ለአዲስ ስብእና የሚጋብዘን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ማርያም የእግዚአብሔርን ጥሪ በተቀበለች ጊዜ “እኔ ወንድ አላውቅም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብላ ላነሳችው ጥያቄ ያገኘችው መልስ ይህንኑ ያረጋግጥልናል፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑልም ኃይል ይጋርድሻል” (ሉቃ 1፡35)፡፡

መንፈስ ቅዱስ ጠማማውን የሚያቀና፤ ሸለቆውን የሚሞላ፤ ድኃ የነበረውን የሚያበለጽግ፤ የደረቀውን የሚያለመልም አምላክ ነው፡፡ እርሱ በመጣ ጊዜ ሁሉ የምድርን ገጽ ያድሳል (መዝ 104፡30)፡፡ በመሆኑም ምሕረት በዓለማችን ውስጥ  እንዲሰፍን፤የምድርም ገጽ እንዲታደስ መንፈስ ቅዱስ መምጣት አለበት፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በታዛዥነት ወደተዘጋጀት ነፍስ ይፈጥናል፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ታዛዥነት፤ ትሕትና እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መዘጋጀት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሌለው ክርስትያናዊ ጉዞ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው፡፡

ኪዳነ ምሕረት

የኪዳነ ምሕረት በዓል ስናከብር “ምሕረት ለዘለዓለም ይመሰረታል፣ እውነትህም በሰማይ ይጸናል፤ ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” (መዝ 89፡2-3) የሚለውን የመዝሙር ክፍል እናስታውሳለን፡፡ እግዚብሔር በማርያም በኩል በኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረተውን አዲስ ኪዳን እናከብራለን፡፡ እግዚአብሔር የፈለገውና የወደደው ነገር ሁሉ ማርያም “እሺ” በማለቷ በሰው እና በአምላክ መካከል የምሕረት ቃልኪዳን ተመሠረተ፡፡ በመጽሐፈ ቅዳሴ ተጽፎ እንደምንጸልየው “አዳም ከገነት በተባረረ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነበርሽ” እያልን እግዚብሔር ለአዳም የሰጠው ተስፋ በኪዳነ ምሕረት መፈጸሙን እንመሰክራለን፡፡ ማርያም የሰማይና የምድር ዕርቅ የተከናወነባት በመሆኗ እርሷ የፈጸመችውን ተግባራት የሚገልጹ ልዩ ልዩ ስሞች ይሰጧታል፡፡ የኪዳን ታቦት፣ የኃጢአተኞች መማጸኛ ወ.ዘ.ተ እያልን እንጠራታለን፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን የአምላክን ሕላዌ የተሸከመው የቃልኪዳኑ ታቦት ከሁሉ ነገር የበለጠ፣ ከፍ ያለ ክብር ነበረው፡፡ በቃልኪዳኑ ታቦት ውስጥ መሠረታዊ ነገሮች ነበሩ፡፡ አስርቱ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት፣ የአሮን በትር፣ ሕብስተ መና፡፡ በዚህ መሰረት እስራኤላውያን አምላክ በመካከላቸው መኖሩን ይተማመኑ ነበር፡፡ ለእስራኤላውያን የቃልኪዳኑ ታቦት እምነታቸው፣ ታሪካቸው፣ ማንነታቸው፣ በአጠቃላይ ሁሉ ነገራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከእርሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

እኛም ከማርያም ጋር ያለንን ግንኙነት ስንመለከተው እርሷ በማኅጸኗ የተሸከመችውንና የወለደችውን ቃለ እግዚአብሔር ያማከለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቃልኪዳኑ ታቦት የማርያምን ማንነት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ እርሷ በድንጋይ ላይ የተቀረጸውን ሳይሆን ዘላለማዊውን፣ ከእርሷ ሥጋ ለብሶ በመካከላችን ያደረውን ቃል ተሸክማለች፡፡ ስለዚህ ይህ ቃል በእርሷ ውስጥ ስለኖረ፣ አምላክ በማኅጸኗ ስላደረ የአምላክ እናት ብለን እንጠራታለን፡፡

እስራኤላውያን በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ ለቃልኪዳኑ ታቦት ማረፊያ ይሆን ዘንድ ከሁሉ የተለየ ቦታ ያዘጋጁ ነበር፤ ለመጸለይ እና ከአምላክ ጋር ለመገናኘት የፈለገ ሰው ወደዚያ ድንኳን በመሄድ ይጸልይ ነበር፡፡ ሙሴም በድንኳኑ ውስጥ ከአምላክ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፡፡ ታቦተ ኪዳኑ ሲንቀሳቀስ ሕዝቡ በታላቅ አክብሮትና አጀብ ይከተል ነበር፡፡ ይህ እስራኤላውያን ለኪዳን ታቦት የሚሰጡት ከፍ ያለ መንፈሳዊ ክብር ለእመቤታችን ልንሰጣት የሚገባውን ምሉዕ ክብርና ውዳሴ የሚገልጽ ነው፡፡ እርሷ ኪዳነ ምሕረት፣ የአምላክ እናት በመሆኗ ከሁሉ የላቀ ክብር ታድላለች፡፡

ነገር ግን ማርያም ይህንን ሁሉ ነገር በልቧ ትይዘው እና ታሰላስለው እንደነበረ ወንጌል ይናገራል፡፡ ይህ የማርያም የጸሎትና የጽሞና ሕይወት እኛም ዛሬ ከኢየሱስ ጋር ጥልቅ ውይይት የምናደርግበት፣ የእርሱን ምላሽ የምንሰማበት ጊዜ እንደሚያስፈልገን ያስተምረናል፡፡ ከኢየሱስ ጋር መገናኘት፣ በተለይ በቅዱስ ቊርባን ከሚገኘው ኢየሱስ ጋር በጥልቅ መወያየት፣ ልባችንን ከፍተን ማሳየት፣ በውስጣችን በጥያቄ ተሞልተው የተዘጉ በሮችን በኢየሱስ ፊት መክፈት፣ አለማወቃችን ሳያሳፍረን፣ ዝናችን አንቆ ሳያስቀረን፣ ዛሬ ታይቶ ነገ የማይደገመው የሰዎች ከንቱ ውዳሴ ሳያታልለን በኢየሱስ ፊት በትህትና መቅረብ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ በዐብይ ጾም ጊዜ ጥያቄዎቻችንን ይዘን ከኢየሱስ ጋር ጥልቅ ውይይት ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ለራሳችን ጥያቄዎች ራሳችን መልስ እየሰጠን እንጓዛለን፡፡ የራሳችን ድምጽ ብቻ ይሰማል፡፡ በራሳችን መልስ እንዳንጠፋ ያሰጋል፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ከምድራዊ ቋንቋ ባሻገር መለኮታዊ ድምጽ፣ መለኮታዊ ቋንቋ ሲገባን ህይወታችን በዚያ ደረጃ ይለወጣል፤ የኢየሱስ ድምጽ፣ የእውነት ድምጽ ሲመጣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይለውጠናል፡፡ነገር ግን እንደማርያም ልብ የእኛም ልብ በሩ ወለል ብሎ መከፈት አለበት፡፡ ሰማያዊውን ቋንቋ ለማድመጥ መዘጋጀት አለብን፡፡ በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ይህንን መለኮታዊ ድምጽ በትጋት መፈለግ፣ እርሱም ሲናገር በአግባቡ ማድመጥ እንችል ዘንድ ምድራዊውን እውቀት፣ ሁካታ መልስ ሁሉ ጸጥ ለማሰኘት እንበርታ፡፡

          በዚህ በዐብይ ጾም ጊዜ በክርስትያናዊ ሕይወታችን ትሕትናን በመላማመድ፣ ዝቅ በማለት በእግዚአብሔር ጸጋ መታመን ለውይይት በር መክፈት አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ካልጠበቀን በስተቀር እኛም የከፋ ኃጢአት ከመፈጸም የሚያስጥለን ኃይል የለንም፡፡

        በተለይ ለመሪዎች መጸለይ አለብን፡፡ እንደ መሪ በጥበብና በማስተዋል ማስተዳደር የሚያስችላቸው እውቀታቸው፤ ትምህርታቸው፤ የሚገኙበት የሥልጣን እርከን ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ ይህ ጸጋ በሀገራችን እንዲሰፍን የእያንዳንዳችን ጸሎት ወሳኝ ነው፡፡ የጸሎት ሰዎች ሆነን ሁሉን ነገር በጸሎት እንድንታገል እመታችን ታስታውሰናለች፡፡

ከኢየሱስ ጋር ለብቻችን የምናሳልፈው የጸሎት፣ የጽሞና፣ የአስተንትኖ ጊዜ የብርሀን ጸጋ የምናገኝበት ጊዜ ነው፡፡ እርሱ የተፈጥሮአችንና የህይወታችን ምንጭ በመሆኑ እውነተኛውን መልካችንን የምናገኘው ከኢየሱስ ጋር ልብ ለልብ የምንገኛኝበት ጊዜ ሲኖረን ነው፡፡ ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ሁሉ ሁላችንም ውስጣዊ ጥያቄ አለን፣ ጥልቅ ፍላጎት አለን፣ ሸክም ሆኖ የሚያስጨንቀን ቀንበር አለን፣ ባርያ አድርጎ የሚገዛን ኃጢአት አለ፡፡ ይህንን ይዘን እንቅረብ፡፡

ኢየሱስ ልባችን ስለሚፈለግ “እናንተ ሸክም የከበዳችሁ ወደ እኔ ኑ! እኔም አሳርሃችኋለሁ” ይላል (ማቴ 11፡28)፡፡ ኢየሱስ በምሥጢረ ቊርባን ሆኖ የእያንዳንዳችንን መመለስ፣ የእያንዳንዳችንን መምጣት ይጠባበቃል፡፡ ወደ ኢየሱስ መጥተን አዲስ ሕይወት አግኝተን በዳግም ልደት ታድሰን፣ በሰማያዊ ድምጽ ተሞልተን እንድንጓዝ ወደ ኢየሱስ እንቅረብ፡፡

ወጣት ሳምሶን ደቦጭ ከቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት