15 - ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?››

15 - ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?››

-    ኢየሱስ በዮሐንስ እጅ ጥምቀት ከተቀበለ ጊዜ ጀምሮ፣ ማኅበራዊ ሕይወቱን በጀመረ ጊዜ፣ ማርያም ከባድ ጊዜያትን ማሳለፍ ነበረባት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስን ይቀበሉትና ያወድሱት ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ደገሞ በገዛ ከተማው በናዝሬት ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር (ንጽ. ሉቃሽ 4፡ 28-30)፤ በዚህን ጊዜ ማረያም በልጇ ምክንያት በከባድ ጭንቀት ውስጥ ነበረች፡፡

-    ማርያም፣ እናቱ፣ ሁሉም ኢየሱስን ሲከዱትና ጥለውት ሲሸሹ፣ ከእርሱ ጋር ነበረች፡፡ እርሷ በመስቀሉ ሥር ስለነበረች የኢየሱስን የመጨረሻ ቃሎቹን መስማትና ፍቃዱን ለመቀበል ቻለች፡፡ እርሷ ኢየሱስ ይህን መዝ. 22 ሲጸልይ ሰማች፣

1 አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።

2 አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፤ በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም።

3 በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅድስና ትኖራለህ።

4 አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው።

5 ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ አንተንም ተማመኑ አላፈሩም።

6 እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።

7 የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ።

8 በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው።

9 አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ።

10 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ።

11 ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ።

12 ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም ፍሪዳዎች ያዙኝ፤

13 እንደ ነጣቂና እንደሚጮኽ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ።

14 እንደ ውኃ ፈሰስሁ፤ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ።

15 ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ።

16 ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።

17 አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።

18 ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።

19 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አንተ ጕልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

20 ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥ ብቻነቴንም ከውሾች እጅ።

21 ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ብቻነቴንም አንድ ቀንድ ካላቸው።

22 ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።

23 እግዚአብሔርን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፤ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት።

24 የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእኔ አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኽሁ ጊዜ ሰማኝ።

የልጇን ሥቃይና ሞት አጠገቡ በመሆን በማርያም ላይ የደረሰው ሥቃይና ሐዘን እንዲሁ በብዙ ቤተሰቦች ላይ ይደርሳል፤ ወጣቶች በቲቢ፣ በካንሰር፣ በኤች አይ ቪ፣ አየተሰቃዩና እየሞቱ ናቸው፡፡ አባቶችና እናቶች ልጆቻቸውን ያለረዳት ብቻቸውን ጥለው እየሞቱ፤ ልጆችም በጥቂት ቀናት ውስጥ እየሞቱ ናቸው፡፡ በእድሜ የገፉ ያለበቂ ህክምና ከነሕመማቸው ለብዙ ዓመታት እየኖሩ ናቸው፡፡

በተጨማሪ ብዙ ከቤተሰብና ከአንዳንድ ጎረቤት በስተቀር፣ ሌሎች ሰዎች በእነዚህ ሰዎች ችግርና ሥቃይ የሚገቡና የሚስማቸው አይደለም፡፡ ሌሎች ዘመዶች ለመርዳት ጊዜና ገንዘብ የላቸውም (ነገር ግን ለለቅሶና ለቀብር ይመጣሉ)፣ ዶክተሮች ደግሞ በአንዳንድ ሆስፒታል በቂ ሰው፣ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ትክክለኛ መድሐኒት የላቸውም፣ ነገር ግን በግል ክሊኒኮች ክፍያ ይጨምራሉ፣ ‹‹ሁሉን ነገር ማግኘት ትችላለህ … አለበለዚያም አዲስ አበባ መሄድ ትችላለህ›› ይላሉ፣ ነገር ግን ያለ ዘመድና አንዳንድ ጊዜ ያለ ሙስና በሆስፒታሉ በቀላሉ አልጋ ማግኘት ትችላለህ ወይ? በሙያቸው በግድየለሽነት ለገንዘብ ሲሉ የሚሰሩ ስለሚጨነቁ በሽተኞች የማያስቡ ስንት ሰዎች አሉ!? ለኢየሱስም በመስቀል ዙሪያ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ኢየሱስ እየሞተ ነበር ነገር ግን ጥቂት ሰዎች ብቻ ለእርሱ ይራሩና ይጨነቁ ነበር፡፡

እንጸልይ፡-

ቅድስት ማርያም ሆይ ምስኪኖችን እርጂ - ደካሞችን ደግፊ - የተጨነቁትን አጥናኚ - ስለ ሕዝቡ ሁሉ ጸልዪ - ስለቤተ ክርስቲያን አስቢ - ስለ ኃጢአተኞች አማልጂ፤ የሚያከብሩሽ ሁሉ ጥበቃሽ አይለያቸው፡፡

የምሕረት እናት ንግሥት ሆይ! ሰላም ላንቺ ይሁን - ሕይወታችን ደስታችን ተስፋችን ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን - እኛ የሔዋን ልጆች ስደተኞች ጩኸታችንን ወዳንቺ እናቀርባለን - በዚህ በለቅሶ ቆላ እየተጨነቅንና እያለቀስን ወዳንቺ እንማጠናለን - እንግዲህ እባክሽን የኛ ጠበቃ ሆይ በምሕረት ዓይኖችሽ ወደ እኛ ተመልከች፤ ደጊቱ፣ ቸሪቱ፣ መሐሪቱ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረከውን የሆድሽን ፍሬ ኢየሱስን ከዚህ ከስደት በኋላ ለኛ እባክሽ አሳይን፡፡ አሜን፡፡