እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ኦ ቅዱስ ቁርባን! የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ትርታ!

ኦ ቅዱስ ቁርባን! የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ትርታ!

Libeyesus Kurbanኢየሱስ በምድር ከሐዋርያት ጋር ይመላለስ በነበረበት ቆይታው እንደ ነገ ዓርብ ከመሰቀሉ በፊት ሐሙስ ምሽት የመጨረሻው ራት ዝግጅት ላይ ብዙ ጥልቅ ትርጉም ያላቸውን ተግባሮች አከናውኗል፤ ፎጣ አሸርጦ የሐዋርያቱን እግር ጎንበስ ብሎ አጥቦ ከእነርሱ ጋር የነገ ስቅላቱንና መስዋእትነቱን እያሰበ ማእድን ተቋደሰ። በዚህ ማእድ ዙሪያ የተደረጉ ነገሮችና ንግግሮች ልብን የሚነኩ ነበሩ። ሐዋርያት ጌታና መምህር የሚሉት በውስጣቸው ብዙ ልእልናን የሰጡት እርሱ ጎንበስ ብሎ ሲያጥባቸው “ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” ቢሉትም ጌታ ብቻም ያይደል መምህርም ነውና አደረገው።

ቀጥሎም በውስጡ ከአባቱ ፈቃድ ጋር የሚያታግለው መስቀልን የሚያስበው የልቡ ትርታ በውስጥ እየቀጠለ ኢየሱስ ለደቀ መዛምርቱ ልዩ ማእድን አዘጋጀ! በዚህ ማእድ ላይ ተላልፎ እንደሚሰጥ፣ ያም ሰው እዛው ማእድ ላይ እንዳለ ነገር ግን ይህ ቢሆንም ቅሉ በዚያች ምሽትና ማእድ እርሱ እነርሱን እስከ ዘላለም እንደሚያፈቅራቸውና የዚህ ፍቅር መገለጫ የሚሆነውንም በቅዱስ ሥጋውና ደሙ ከእነርሱ ጋር በቀጣይነት የሚገኝበትን የቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ሠራላቸው፣ ሠራልን።

ይህ ሁሉ ሲሆን የውስጥ የልብ ትርታውን የሚሰማ አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ “ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው። እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው። ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው።” /ዮሐ 13:23-27/

ይህ በኢየሱስ ደረት ተጠግቶ የነበረ ሐዋርያ ያዳምጥ የነበረው ከኢየሱስ አንደበት የሚወጣውን ቃል ብቻ ሳይሆን የኢየሱስንም የልብ ትርታ እንደነበር ማሰብ እንችላለን፤ ስለዚህም ከቃሉ በላይ የቃሉን ንዝረትና ሕይወት ሰጪ የሆነውን የኢየሱስን ደም ዝውውር ያዳምጥ ነበር። በዚህ ልብ ውስጥ የሚረጨው ደም ምን ዓይነት ይሆን ብሎም አስቦ ተመስጦ ይሆናል። ያ በቅፍርናሆም በምኩራብ ኢየሱስ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል” /ዮሐ 6:54-55/ በማለት ያስተማረውን ሐዋርያው እየዘከረ ከደረቱ የዚያን ክቡር ደም እንቅስቃሴ አስተውሏል። ግን አ’እምሮው እንዴት ይሆን ይህ በኢየሱስ ልብ በመረጨትና በአካሉ ውስጥ የሚዞረውን እኔ ልጠጣ የምችለው ብሎም በውስጡ ጠይቋል።

ብዙም አልቆየም ኢየሱስ በዚያው ማእድ ለደቀ መዝሙሩ ግልጽ መልስ ሰጠው፤ ቃሉ እንደሚለን “ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው።” /ማር 14:22-24/። ራሱ በግልጽ ይህን ደምካልጠጣችሁ የዘላለም ሕይወት የላችሁም ብሏልና እንግዲህ ከኢየሱስ ልብ ትርታ የሚመነጨውን ይህን ደም በቅዱስ ቁርባን መቀበል መቻል ምንኛ መታደል ነው!

ያ በኢየሱስ ደረት ላይ ተንተርሶ የቅዱስ ልቡን ትርታ ያዳመጠ ሐዋርያ ቅ. ዮሐንስ ሌላም ድንቅ ነገር መሰከረልን “አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል።” /ዮሐ 19:31-35/።

ይህ የተወጋው የኢየሱስ ጎን የቅዱስ ልቡ መስኮት ነበር! በዚያ በኩል ውሃና ደም ወጣ፤ የጥምቀታችንና የቅ. ቁርባን በር! ጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንብት ምስጢርና ክቡር ደሙ /ቅ. ቁርባን/ እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ለማደግ የምንመግብበት! ስለዚህ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ እንደ ክርስቲያን የህልውናችን ምንጭና ግብ ነው፤ እንደ ካቶሊክነታችን ቅዱስ ቁርባን በሕይወታችን ትልቁን ቦታ መያዝ እንዳለበት የምንመኘውም ለዚሁ የወንጌል እውነት ነው። የክርስቶስ ክቡር ደም ሁሌም ሕያው ነውና እርሱ ከእኛ ጋር አንድ መሆንን የመረጠበትም መንገድም ነውና በማያወላዳ መልኩ በግልጽ እኔን ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም ብሎናል፤ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።” /ዮሐ 6:53/።

በአንድ አጋጣሚ ከዚህ ክቡር ምሥጢር ማለትም ሥጋሁ ወደሙ ተሳትፎ የሚያውቅ አሁን ግን በተለያየ ምክንያት ከቅ. ቁርባን ለራቁ ልበ ኢየሱስ ዛሬም ይጣራል፤ የልቡን ትርታ ጠጋ ብላችሁ አዳምጡ በማለት ይጋብዛል። ስለዚህ ከዚህ ምሥጢር ለራቁት እየጸለይን እኛም የዚህን ድንቅ ምሥጢር ትርጉም ማለትም ፍቅርን፣ ምሕረትን፣ ይቅርታን፣ ትእግሥትን፣ ገርነትን፣ ቸርነትን...ከሌሎች ጋር እየተካፈልን ለመኖር እንትጋ።

Write comment (0 Comments)

“ቅዱስ ቁርባን ቤተክርስቲያንን ይሠራል፤ ያንጻል፤ ቤ/ያን ደግሞ ቅ. ቁርባንን ትሠራለች”

“ቅዱስ ቁርባን ቤተክርስቲያንን ይሠራል፤ ያንጻል፤ ቤ/ያን ደግሞ ቅ. ቁርባንን ትሠራለች” ካርዲናል ሄንሪ ዴ ሉባክ - ኢየሱሳዊ /1896-1991/

Eucharist Churchአንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሰው ሠራሽ ተቋም ብቻ የሚያስቡ ሰዎች “ክርስቶስ እምነትን፣ ሕይወትን እንጂ ሃይማኖትን/ቤተክርስቲያንን/የእምነት ተቋምን አላመጣም” እና መሰል ዓረፍተ ነገሮችን ሲናገሩ ይደመጣሉ። በርግጥ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ይህን ለማለት እውነተኛ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ባናውቅም ስለራሳችን እምነት ካወራን ግን ኢየሱስ በተደራጁ ሰዎች (በሐዋርያት፣ በደቀመዛሙርት፣ በአርድእት...) መካከል እንደነበርና በዚያ መልኩም ይቀጥሉ ዘንድ እንዳዘዛቸውእናነባለን። ለምሣሌም በዮሐ 21፡15-17 ላይ ስምዖን ጴጥሮስን ክርስቶስ ግልገሎቹን፣ ጠቦቶቹንና በጎቹን እንዲያሰማራና እንዲጠብቅ አደራ እንደሰጠው ፤ እንዲሁም በማቴ 16፡18-19 ላይም «18 እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።» ማለቱን ልብ ይሏል።

ሐዋርያቱም የዚህን አደራ ኀላፊነት ለመወጣት ሲሰባሰቡና ሲጸልዩ፤ ወሳኝ የእምነት አንቀጾችን ሲወስኑ፤ ከጌታ የተቀበሉትን አገልግሎታቸውን እነርሱም ለቀጣይ ትውልድ በአደራ ሲያስተላልፉና መሰል ትውፊቶችን አክብረው ሲያስከብሩ በሐዋርያት ሥራ እና በተለያዩ የአዲስ ኪዳን መልእክቶቻቸው ውስጥ እናነባለን። በርግጥ ክርስቶስ በአካል ከሰዎች ጋር ኑሮ እንዴት መኖር እንደሚገባ ኖሮ ያሳየ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው እንጂ መንፈስ ብቻ ወይም የሆነ የአእምሮ ውልብታ ምትሐት አይደለም።

ይህንን እውነት ስንናገር በወንጌል ጊዜና በሐዋርያት ጊዜ ብቻ እንዲህ ነበር ለማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ክርስቶስ በስሙ በሚሰበሰቡ ሰዎች መካከል ይገኛል «ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።» ማቴ 18፡20። ቤተ ክርስቲያናችን ይህን መገኘት በብዙ መልኩ ታስተምራለች። ከእነዚህም መገኘቶች መካከል ደግሞ ክርስቲያናዊ መሠረት አድርጋ የክርስቶስን በቅ. ቁርባን መገኘት ታስተምራለች፤ ምክንያቱም እሱ ራሱ ለዘለዓለማዊነታችን አንድ ዋስትናን ያደረገልን፣ በምንም መልኩ ሊቀየርና ሊደራደር የማይችለው ቅ. ቁርባን በመሆኑ ነው (ዮሐ 6)። እንደ ቤ/ያናችን እምነት ቤ/ያን በክርስቶስ ዙሪያ የሚሰባሰቡ የአማኞች ስብስብ ነው። ከዚህም እውነት የተነሣ “ቅዱስ ቁርባን ቤተክርስቲያንን ይሠራል” የሚለው ሃሳብ ግልጽ ነው። በክርስቶስ ሥጋና ደም ዙሪያ የእርሱ የሆኑት ይሰበሰባሉ፤ ያም የክርስቶሳውያን ስብስብ ናቸው።

በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ በሥጋውና ደሙ ዙሪያ የሚሰበሰቡ ሰዎች ወይም ቅ. ቁርባንን የሚቀበሉ ሰዎች ኃይል ያለውን አካል ይቀበላሉና ወደ ክርስቶስ ወገንነት ይለወጣሉ፤ የክርስቶስ ፈቃድና ሕይወትን ይማራሉ፤ ከቃል በላይ የሆነውን ትስስርና ቅርበት ይቀምሳሉ። ቅዱስ ሥጋውና ደሙ ከአካላቸው ጋር በመዋሐድ ነፍሳቸውን ለበለጠ ፍጽምና ያነሣሣል፤ ይህን መሰል ሕይወትም እንዲቀጥል ቅ. ቁርባንን ዘወትር ይናፍቃሉ፤ ይሰባሰባሉ፤ ለቅ. ቁርባን መገኘት ራሳቸውን ያስገዛሉ። የሁለተኛው ቫቲካን ሰነድ “በቅ. ቁርባን ኅብስት የክርስቲያኖች አንድነት እውን ይሆናል፤ እነርሱም ከክርስቶስ አካል ጋር አንድ ይሆናሉ” ይላል /LG, ስለቤ/ያን ቀኖናዊ አቋም ቁ.3/። ይህም 1ቆሮ 10፡16-17ን ያንፀባርቃል፡- «የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 17 አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።»

ቅ. ቁርባን ቤ/ያንን ይሠራል ሲባል የክርስቶስ ህላዌ ክርስቲያኖችን የአካሉ ክፍል ያደርጋቸዋል ማለት ነው፤ ይህንን እውነት ማወቅ በራሱ በቤ/ያን ስም የሚከሠቱ ስህተቶችን እንድናስወግድ ያግዘናል። የአምልኮ ሥርዓታችን ምንጭና ግብ በቀራንዮ በመስቀል፣ በቅዱስ ቁርባን ዛሬም ራሱን የሰጠን ጌታ ነው። መጸለያችንና መሰባሰባችን በርሱና ለርሱ ትኩረትን በሰጠ ሁኔታ ነው። የመሰባሰባችን ግብም በቅዱስ ቁርባን ራሱን የሰጠንን ጌታ ለማምለክና በሕይወታችን ለማክበር ነው።

ቤ/ያን መቼውንም ቢሆን ከክርስቶስ ውጪ የእገሌ መሆን አትችልም፤ መሥራቿ፣ ማእከሏም ሆነ መድረሻዋ ራሱ ክርስቶስ ነው። ቅ. ጳውሎስ ይህን ትምህርት ጎላ በማድረግ ከሰዎች ጋር የተጣበቁ «ክርስቲያኖችን» እንዲላቀቁ ይገስፃቸዋል። ሰው የመከተል አባዜ ለተጠናወታቸው የቆሮንጦስ ክርስቲያኖች እውነቱን ለመናገር ምንም ያህል ጊዜ አላባከነም በመጀመሪያ መልእክቱ 1፡10-17 ላይ እንዲህ ይላቸዋል፤

«10 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11 ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። 12 ይህንም እላለሁ። እያንዳንዳችሁ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ። 13 ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? 14-15 በስሜ እንደ ተጠመቃችሁ ማንም እንዳይል ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ አንድን እንኳ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 16 የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ እንደ ሆነ አላውቅም። 17 ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም።»

እርሱ እንደተረዳው ከሆነ የቆሮንጦሷ ቤ/ያን የመከፋፈል ስጋት ከትምህርት ወይም ከሥርዓት ሐቀኛነት የተነሣ ሳይሆን የተለያዩ የቤ/ያን መሪዎች ጋር የመጣበቅ ዝንባሌ ያመጣው ነበር፤ ልክ ሐዋርያት በክርስቶስ ማንነት ተማርከው እንደተከተሉት ሁሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ወደ ክርስቶስ ሊመሩ በሚገባቸው ሰዎች ብቻ ራሳቸውን ገድበው ወደ ክርስቶስ መዝለቁ ያዳግታቸዋል።

አጵሎስ በሐሥ 18፡24-28 ላይ የዮሐንስ መጥምቅ ተከታይ የነበረ መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ የተማረና ጥሩ የመናገር ችሎታ ያለው አይሁድ መሆኑ ተጠቅሷል፤ በተጨማሪም ስለጌታ በመንፈስ የተቃጠለ ሆኖ በትክክል የሚሰብክና የሚያስተምር ነበር። ጵርስቅላና አቂላ ይበልጥ ወደ ክርስቲያናዊው መንገድ እንዲገባ አስተምረውት የቆሮንጦስ ቤ/ያንን ተቀላቅሏል። «ኬፋ» የተሰኘውም ጴጥሮስ፣ ስምዖን የዮና ልጅም ተብሎ የተጠራው ነው። ኬፋ የሚለው የአረማይስጥ ቃል ክርስቶስ ስምዖንን «ዓለት» «ጴጥሮስ» የሚለውን ትርጓሜ ለመስጠት የተጠቀመበት ስም ነው (ማቴ 16፡18)። ቅዱስ ጴጥሮስ በቆሮንጦስ አገልግሎ ባይሆንም ወይም እርሱ ከሰበከበት የመጡ ክርስቲያኖች በዚያ የሚገኙ ስለሆነ ቢሆንም ምናልባት ቅ. ጳውሎስ የኬፋን ስም የሚጠቅሰው የአማኞቹን እይታ ለማስፋት እንዲያግዝ ብሎ ይሆናል። ስለዚህ እንደ ሰው እይታ ከሆነ እነዚህ መሪዎች ሰው በቀላሉ ይከተላቸው ዘንድ የሚያበቃ ሰዋዊ መስፈርት ነበራቸው፤ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስም ቢሆን በትምህርቱም ሆነ በሌሎች ብቃቱ ሰዎች ሊያነጻጽሩት የሚችል ዓይነት ሰው ነበር፤ ሆኖም ግን ይህ ዓይነት አካሄድ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰቃይ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፤ እንደ አንድ አካል የምትቆጠረው ቤተ ክርስቲያን አንድ ራስ ብቻ ይኖራት ዘንድ አግባብ ነው።

1ቆሮ 3፡1-9/4፡6-7 ላይ ለቆሮንጦስ ቤ/ያን የመከፋፈልን ጉዳት ያደረሰው የጳውሎስና አጵሎስ መሆኑ ግልፅ ነው። «1 እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። 2 ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ 3 ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? 4 አንዱ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም። እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? 5 አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። 6 እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ 7 እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። 8 የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። 9 የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።» ጳውሎስ እዚህ ላይ በክርስቶስ ሳይሆን በአገልጋዮች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሰዎችን እንደ ሕፃናት እንጂ እንደ መንፈሳውያን ለማየት እንደሚቸገር ገልጿል፤ ቅ. ቁርባን የቤ/ያን ማእከል መሆኑን ማስተዋል ከዚህ ስህተት ይታደገናል። በተመሳሳይ ሁኔታም በክርስቶስ አገልጋይነት ስም ራሳቸው ላይ የስምና የቅጽል ብዛት ለሚከምሩት እንዲህ ይላል፡- 4፡6-7 «6 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 7 አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?» በዚህ መልኩ ሰዎች በእግዚአብሔር ስም በእነርሱ በኩል አንዳች ቢከናወን ምንጩ እግዚአብሔር መሆኑን መዘንጋት እንደሌለባቸው ያስተምራል፤ ከምንጭነቱም ባሻገር ክብሩ ሁሉም ወደ አንድ ግብ ማለትም ወደ እግዚአብሔር መቃኘት እንዳለበት ያሳያል፤ ለዚህም ነው ቅ. ቁርባን የነገሮቻችን ምንጭና ቁንጮ መሆኑን መዘንጋት የሌለብን።

ቅ. ጳውሎስ ሰው ዓይኑን ከክርስቶስ አንስቶ በሰው ላይ ማድረግ ከጀመረ «ክርስቲያን» ወይም የክርስቶስ ተከታይ ተብሎ መጠራቱ የማይስማማ መሆኑ ገብቶታል። በዚያው መልእክቱ 1፡12 ላይ የተጠቀሰው «እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ» የሚለው አባባል ለማለት ብቻ እንደሚሉት እንጂ ሰው ላይ ማተኮራቸውን ለመግለፅ የተጠቀመበት ነው። ቅ. ቁርባንን መሠረት፣ ማእከልና መድረሻ አደረግን ማለት ሙላት እንጂ መጉደል እንዳልሆነ በጳውሎስ ንግግር ውስጥ ማየት እንችላለን «ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ 22 ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥23 ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው» 1ቆሮ 3፡21-23። 

Write comment (0 Comments)

መሳጭ የቅዱስ ቁርባን ታሪኮች - ክፍል - ፩

መሳጭ የቅዱስ ቁርባን ታሪኮች

ቅዱስ ቁርባናዊ ሴቶችና ቅ.ቁርባን በሶቪየት ኅብረት የአፈና ዘመን

(Dominus Est ከሚል በረዳት ጳጳስ አታናሲየስ ሽኔይደር መጽሐፍ የተወሰደ)

Eucharistic Womenከ1917-1990 ዓ.ም. ድረስ የቆየው የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስታዊ አገዛዝ በምድር ላይ ገነትን መመሥረት የሚመስል ሃሳብ ነበረው። ሆኖም ግን ይህ አገዛዝ በውሸት ላይ፣ በሰብአዊ ክብር ጥሰት፣ እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያኑን በመካድና ብሎም በመጥላት ላይ የተመሠረተ ነበርና ብዙም ሊዘልቅ አልቻለም። በዚህ አገዛዝ ሥር ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እሴቶች ቦታ ሊኖራቸው አይችልም፣ አልቻለምም ነበር። ሰውን ስለ እግዚአብሔር ህላዌ፣ ስለ ክርስቶስ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያስታውሱ ነገሮች ሁሉ ከሕዝቡ ሕይወት እንዲጠፋና ከሰዎች እይታ እንዲርቅ ተደርጎ ነበር። ቢሆንም ግን ሰዎችን ስለ እግዚአብሔር መኖር የሚያስታውስ እውነታ ነበር፤ ይህም የካህን መኖር ነበር። ሰዎች ካህንን ሲያዩ የእግዚአብሔርን ህላዌ ሊያስታውሱ ግድ ነበርና እግዚአብሔር የሚለውን ሃሳብ ከሰዎች ለመፋቅ ካህንም ለሰዎች መታየት የለበትም፣ ከመኖር መወገድ አለበት።

የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን አሳዳጆች በውስጣቸው ካህን ብቻ እግዚአብሔርን ለሰዎች መስጠት እንደሚችል፣ ክርስቶስን በቀጥታና በተጨባጭ መልኩ ማለትም በቅዱስ ቁርባን ለሰዎች መስጠቱን ስለሚያውቁ ካህንን ከሁሉ የበለጠ አደገኛ ሰው አድርገው ይቆጥሩት ነበር። በዚህ ምክንያት መሥዋዕተ ቅዳሴን መቀደስ ክልክል ነበር። ይህ ሁሉ ቢደረግም ቅሉ፣ በቤተ ክርስቲያን በተለይም ደግሞ በምሥጢራት በኩል በሥራ ላይ የነበረውን መለኮታዊ ኃይል ማንኛውም ዓይነት የሰው ኃይል ሊያስቀረው አልቻለም።

በነዚያ ጨለማ ዓመታት በሰፊው የሶቪየት ኅብረት ግዛት ቤተ ክርስቲያን በድብቅ ውስጥ ውስጡን መኖርን ተገድዳ ነበር፤ ምንም እንኳ ሊታዩ የሚችሉ ገሃዳዊ መዋቅርና ሕንጻዎች ባይኖሯትም፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአገልጋይ ካህናት ቁጥር እጥረት ቢኖርም ወሳኝ ነገሩ ግን ቤ/ያን ሕያው ነበረች፣ እንደውም እጅጉን ሕያው ነበረች። ቤ/ያን እንዲህ ሕያው የሆነችው ቅዱስ ቅርባንን በቋሚነት አላጣችም ነበር፤ ምንም እንኳ ምእመናን ብዙ ጊዜ የመቁረብ እድል ባይኖራቸውም በምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን ላይ የተደላደለ እምነት ያላቸውን ምእመናን ቤ/ያን አላጣችም ነበር፤ ባብዛኛው እናቶችና አያቶች የነበሩ በክህነታዊ እምነት ነፍሳቸው የታነጸች ቅ. ቀርባንን ከጥቃትና ከመጥፋት የሚከላከሉ እንዲሁም ላቅ ባለ ፍቅር፣ ክብርና በሚቻላቸው ሁሉ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ፤ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የክርስቲያኖች መንፈስ የተሞሉና «በፍቅርና በፍርሃት» ቅዱስ ቁርባንን ለሌሎች የሚያድሉ አማኝ ሴቶችን ቤ/ያን አላጣችም ነበር።

በጊዜው በሶቪየት ኅብረት ድብቋ ቤ/ያን ውስጥ ከነበሩት ብዙ ተምሳሌውያት ሴትች ቅዱስ ቁርባናዊ ሴቶች መካከል የሦስቱን ሕይወት እናያለን። እነርሱም ማሪያ ሽኔይደር፣ ፑልኬሪያ ኮችና ማሪያ ስታንግ ይባላሉ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የስታሊን አገዛዝ ብዙ ጀርመናውያንን ለጉልበት ሥራ በማለት ጥቁር ባሕር ከሚባለው አካባቢ ወደ ቮልጋ ወንዝ አጋዛቸው። ከከተማ በተገለለና በደኸየ ኑሮም ይገቡ ዘንድ ተገደዱ፤ በነዚህም ውስጥ በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ ካቶሊካውያን ነበሩ። አንዳንድ ካህናት የራሳቸውን ሕይወት በሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥም አስገብተው ቢሆንም እንኳ በድብቃዊ ሁኔታ ለነዚህ ጀርመናውያን ካቶሊኮች ምሥጢራትን በማደል ያገለግሉ ነበር። በዚህ ሁኔታ አዘውትረው ይመጡ ከነበሩት ካህናት መካከል እ.ኤ.አ. በጥቅምት 1963 ዓ.ም.  ካራጋንዳ በሚባል አካባቢ አቅራቢያ በሰማዕትነት ያረፉት ዩክሬናዊው ካህን አባ አሌክሲጅ ሳሪትስኪ ይገኙበታል፤ እኚሁ ካህን እ.ኤ.አ. በ2001 ዓ.ም. በቅ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፅእናቸው ታውጇል።

እኚህን ሰማዕት ካህን በዚያ ሁኔታ ውስጥ እየመጡ ያገለግሏቸው የነበሩ ክርስቲያኖች ይወዷቸው ነበር እናም «የእግዚአብሔር ወሮበላ» ብለውም ይጠሯቸው ነበር። እ.ኤ.አ. ጥር 1958 ዓ.ም. በስደት ከሚኖሩበት አካባቢ በድንገት ተደብቀው ካዛክስታን ውስጥ ወዳለችው ወደ ካራጋንዳ ከተማ መጡ። አባ አሌክሲጅ በተቻለ መጠን ብዙ ምእመናን ይቆርቡ ዘንድ ያለምግብና ያለእንቅልፍ ቀን ከሌሊት ያናዝዙ ነበር፤ ምእመናኖቹም «አባ፣ መብላትና መጠጣት አለበዎት» ሲሏቸው የእርሳቸው መልስ «አልችልም፣ ምክንያቱም ፖሊሶች በየትኛውም ሰዓት ሊመጡ ይችላሉ፤ ይሄ ማለት ደግሞ መናዘዝና መቁረብ የነበረባቸው ሰዎች ይህን ሊያጡት ነው» የሚል ነበር።

መናዘዝ የሚፈልጉ ምእመናን ሁሉ ከተናዘዙ በኋላ አባ አሌክሲጅ መሥዋዕተ ቅዳሴ ማሳረግን እንደጀመሩ «ፖሊሶቹ መጡ!» የሚል ድምፅ አስተጋባ። በዚያ ከሚገኙት ምእመናኖቹ ውስጥ ማሪያ ሽኔይደር አንዷ ነበረችና አባን «እንሂድ አባ! እኔጋ ይደበቃሉ፤ እናምልጥ!» አለቻቸው። ስለዚህም ይህች ሴት አባን ከዚያ አካባቢ ራቅ ወዳለ አንድ ቤት ወስዳ በአንድ ክፍል እንዲሸሸጉ አደረገች፤ ወዲያውኑም ምግብ እያቀረበችላቸው «አሁን እንኳ መብላትና ትንሽም ማረፍ ይችላሉ፤ መሸትሸት ማለት ሲጀምር በአቅራቢያ ወደሚገኘው ከተማ እናመልጣለን» አለቻቸው። ቅዳሴ እንደተጀመረ ፖሊሶቹ በመምጣታቸው በመቋረጡ ምንም እንኳ ሰዎቹ የተናዘዙ ቢሆንም ባለመቁረባቸው ምክንያት አባ አሌክሲጅ አዝነዋል። ማሪያ «አባ! ምእመናኖቹ ሁሉ በትልቅ እምነትና መንፈሳዊነት መንፈሳዊ ቁርባን ይሳተፋሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተመልሰው እንደሚያቆርቡን ተስፋ እናደርጋለን» አለቻቸው።

ዕለቱ ማመሻሸት ሲጀምር ለሽሽቱ ዝግጅት ተጀመረ፤ ማሪያ የሁለት ዓመትና የስድስት ወር ልጆቿን ከእናቷ ጋር በቤቷ ትታ ፑልኬሪያ የተባለች ሌላ ሴት ዘመዷን በመጥራት አባ አሌክሲጅን በጫካ ውስጥ ከዜሮ በታች ሠላሳ ዲግሪ በሆነ ከባድ በረዷማ ቅዝቃዜ አሥራ ሁለት ኪ.ሜ. በመጓዝ ወደተባለችው ከተማ ሦስቱም ደረሱ። በዚያም ወደ አንድ ባቡር ጣቢያ ሄደው ሁለቱ ሴቶች ለአባ የጉዞ ቲኬትን ገዙላቸው፤ በመጠበቂያ ክፍልም ባቡሩን መጠበቅ ጀመሩ። አንድ ፖሊስ ወደዚያ ክፍል ገባና በቀጥታ አባን «ወዴት እየሄዱ ነው?» ብሎ ሲጠይቃቸው አባ ከድንጋጤ የተነሣ በፍጥነት መልስ መስጠት አልተቻላቸውም ነበር። ይህም የሆነው ስለራሳቸው ሕይወት ያይደለ አብራቸው ስላለችው የልጆች እናት የሆነችው ወጣቷ ስለማሪያ ሕይወት እጣ ፈንታ በማሰብ ነበር። ይህች ወጣት ራሷ ለፖሊሱ «እሳቸው ወዳጃችን ናቸው፤ እኛም እየሸኘናቸው ነው፤ ይኸው ቲኬታቸውን ተመልከት» በማለት ቲኬቱን ሰጠችው። ፖሊሱም ቲኬቱን ከተመለከተ በኋላ አባን «የባቡሩ የመጨረሻ ፉርጎ በሚቀጥለው ፌርማታ ተገንጥሎ ስለሚቀር እዚያ ላይ እንዳይሳፈሩ! መልካም ጉዞ!» በማለት ክፍሉን ለቆ ወጣ። አባ አሌክሲጅም ማሪያን እየተመለከቱ እንዲህ አሏት «እግዚአብሔር መልአክ አድርጎ አንቺን ላከልኝ! ለእኔ ያደረግሽውን በፍጹም አልረሳውም፤ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ ሁላችሁንም ለማቁረብ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በእያንዳንዷም ቅዳሴዬ ላንቺና ለልጆችሽ እጸልያለሁ።»

ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ ማሪያ ወደምትገኝበት ወደ ክራስኖካምስክ አባ አሌክሲጅ መመለስ ቻሉ፤ አሁን መሥዋዕተ ቅዳሴ መቀደስና ምእመናንን ማቁረብ ችለዋል። ማሪያ ግን አባን አንድ ውለታ ያደርጉላት ዘንድ ጠየቀቻቸው፤ እንዲህ ብላ «አባ! እናቴ በጣም ታማ ነው ያለችው፣ ከመሞቷ በፊት ትቆርብ ዘንድ ለርሷ የሚሆን ቅ.ቁርባንን ሊሰጡኝ ይችሉ ይሆን?» አባም ማሪያ ለእናቷ የሚቻላትን ጥንቃቄ ሁሉ አድርጋ በሚገባው ክብር ማቁረብ የምትችል ከሆነ ጠይቀዋት ተስማምተው ቅ. ቁርባንን ሰጧት። ማሪያም የታመሙ እናቷን ለማቁረብ በእጇ ላይ ነጭ ጓንት አጠለቀች፣ ቅ. ቁርባኑን በወረንጦ ነገር ይዛም አቆረበቻቸው፤ ከዚያም በኋላ ተጠቅልሎበት የነበረውን ወረቀት አቃጠለችው።

የማሪያና የፑልኬሪያ ቤተሰቦች ወደ ኪርጊሰታን መኖሪያቸውን ቀየሩ። እ.ኤ.አ. በ1962 ዓ.ም. አባ አሌክሲጅ ወደዚች ከተማ በድብቅ መጥተው ማሪያና ፑልኬሪያን አገኟቸው፤ አንዴ በማሪያ ሌላ ጊዜም በፑልኬሪያ ቤት ቀደሱ። አባም በዚያ በረዷማ መሽት ያን ሁሉ አደጋ ተጋፍጠው የሸኟቸውን የእምነት ውለታ አስታውሰው፤  ከግልጽ መመሪያ ጋር ለፑልኬሪያ ቅ. ቁርባንን ትትውላት ለመሄድ ወሰኑና እንዲህ አሏት «ቅ. ቁርባንን ትቼልሽ እሄዳለሁ፤ ለዘጠኝ ተከታታይ ወራት በመጀመሪያዎቹ ዓርቦች ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ አክብሮት መንፈሳዊነትን አድርጉ። የወሩ መጀመሪያ ዓርብ ሲሆን በቤትሽ ቅ. ቁርባንን በመግለጥ በሚታይ መልኩ ከፍ አድርገሽ በማስቀመጥ በሁሉ ነገሮች ታማኝ የሆኑና ምሥጢር የሚጠብቁ ምእመናንን ጠርተሽ አብራችው እንዲሰግዱ ጋብዢ። ዘጠኝ ወር በዚህ መልኩ ከተካሄደ በኋላ ቁረቢው፤ ግን በጥልቅ አክብሮት ይሁን።» እንደተነገራት ሁሉ ነገር ተከናወነ። ለዘጠኝ ወራት በዚያ ቤት ድብቅ የቅ. ቁርባን ስግደት ተደረገ፤ ማሪያም ከሰጋጅ ሴቶች አንዷ ነበረች።

እነዚህ ቅ. ቁርባናዊ ሴቶች (ለቅ. ቁርባን ልዩ መንፈሳዊነትና አክብሮት የነበራቸው ሴቶች) በዚያ ቅዱስ ቁርባን ፊት በአምልኮ በሰገዱ ቁጥር ጥልቅ የሆነ የመቁረብ ምኞት ነበራቸው። ሆኖም ግን ይህ ፍላጎት የነበራቸው ሴቶች ቁጥርና የቅ. ቁርባኑ ብዛት ያለመመጣጠን ይህን አልፈቀደም፤ አባ አሌክሲጅ በዘጠነኛው ወር መጨረሻ ላይ ፑልኬሪያ ብቻ እንድትቆርብና የተቀሩት ደግሞ መንፈሳዊ ተሳትፎ እንዲያደረጉ የወሰኑበት ምክንያትም ይኸው ነበር። ይህም ቢሆን እነዚህ ሴቶች ሁሉ ለቅ. ቁርባን ያላቸው መሰጠት ልዩ ነበር፤ ሁሉም ለልጆቻቸው የቅ. ቁርባንን ጥልቅ እምነት ልክ እንደ እናታዊ ወተት ለልጆቻቸው ለማስተላለፍ በቅተዋል። 

(ይቀጥላል)

Write comment (0 Comments)

ከአንድ ሺህ ኪ.ሜ. በላይ አስቸጋሪ ጉዞ ቅዱስ ቁርባንን ፍለጋ!

መሳጭ የቅዱስ ቁርባን ታሪኮች - ክፍል ፪

ቅዱስ ቁርባናዊ ሴቶችና ቅ.ቁርባን በሶቪየት ኅብረት የአፈና ዘመን

(Dominus Est ከሚል በረዳት ጳጳስ አታናሲየስ ሽኔይደር መጽሐፍ የተወሰደ)

ከ መሳጭ የቅዱስ ቁርባን ታሪኮች - ክፍል - ፩ የቀጠለ

Eucharistic Women 2ለፑልኬሪያ ቅ. ቁርባንን ለመስጠት የሄዱበት ወቅት ለአባ አሌክሲጅ የመጨረሻ ሐዋርያዊ አገልግሎት ነበር፤ ከዚያን ጊዜ በኋላ ወደዚያ አልተመለሱም። ከዚያ ቦታ ወደ ካራጋንዳ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 1962 ዓ.ም. እንደተመለሱ በድብቅ ፖሊሶች ተይዘው አባ ዶሊነካ ወደሚባል ማጎርያ ካምፕ እንዲገቡ ተደረገ። ከብዙ እንግልትና መዋረድ በኋላ አባ አሌክሲጅ ከእስር ቤት ስቃይ ብዛት የተነሣ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 1963 ዓ.ም. የሰማዕትነትን ሞት ተጎናፀፉ፣ ብፅእናቸውም በዚሁ ቀን ይከበራል። ቅ. ቁርባናዊ ቅዱስ ካህን በመሆናቸውም መሰል እናቶችን አፍርተዋል። እነዚህ ቅ. ቁርባናዊ ሴቶች ጨለማና ምድረ በዳ በሆነ ድብቅ አናኗር እንዳበቡ አበባዎች ሆነው ቤተ ክርስቲያን እጅጉን ሕያው እንድትሆን አብቅተዋታል።
ሦስተኛዋ ቅ. ቁርባናዊ ሴት ማሪያ ስታንግ ትባላለች፤ እርሷም ከጀርመን አገር ወደ ካዛክስታን የተጋዘች ናት። ይህች ቅድስት የሆነች አያት ሊታመን የማይችል ቀጣይ የሆነ የስቃይ፣ ራስን የመካድና የመስዋዕትነት ሕይወት ነበራት። ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ሕይወቷን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ትመኝ ነበር። ሕይወቷም እንዲህ የመከራ ጉዞ የሆነባት ከኮሙኒስታዊ ግዞትና ስድት የተነሣ ነው። በዜና መዋዕሏ ማሪያ እንደጻፈችው «ካህናትን አጠፏቸው፤ ከመንደራችን አቅራቢያ ቤ/ያን ነበር፣ ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ካህንም ሆነ ቅ. ቁርባን በዚያ አልነበሩም። ያለነዚህ ህላዌም ቤተ ክርስቲያኑ ዖና ነበር፤ ይህም እጅጉን ያስለቅሰኝ ነበር።» ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማሪያ በየእለቱ የራሷን መሥዋዕት እያቀረበች እንዲህ በማለት በእግዚአብሔር ፊት ጸሎቷን ታደርስ ነበር «ጌታ ሆይ! እባክህ ዳግም ካህናትን ስጠን! ቅ. ቁርባንንም ስጠን! እጅግ የተቀደስክ የኢየሱስ ልብ ሆይ! ስቃዮችን ሁሉ ስላንተ ፈቃድ ስል በጸጋ እቀበላቸዋለሁ።»
በግዞት በሄዱበት በሰፊው ምሥራቃዊው የካዛክስታን አካባቢ ማሪያ ስታንግ በየሰንበቱ በቤቷ ሌሎች ሴቶችን በድብቅ ለጸሎት ትስበስብ ነበር። በነዚህ የሰንበት መሰባሰቦች ሴቶቹ እንዲህ እያሉ አምርረው ይጸልዩ ነበር «እጅግ ተወዳጇ እናታችን ማርያም ሆይ! አሳዛኝነታችንን ተመልከቺ! ካህናትን፣ መምህራንንና እረኞችን ዳግም ስጪኝ!»
በስደት ያሉ ካቶሊክ ካህን በኪረጊስታን ስለነበሩ እ.ኤ.አ. ከ1965 ዓ.ም. ጀምሮ ማሪያ ስታንግ ከአንድ ሺህ ኪ.ሜ. በላይ ወደሚርቀው ወደዚያ መጓዝን ጀመረች፤ ምክንያቱም እርሷ በቋሚነት በምትኖርበት አካባቢ ያሉ ጀርመናውያን ስደተኞች ካህንን ካዩ ሃያ ዓመታት አልፈዋል። ስለዚህ እውነታ ማሪያ እንዲህ ጽፋለች «በኪርጊስታን ወደምትገኘው ፍሩንስ በደረስኩ ጊዜ ካህን አገኘሁ፤ ወደ ካህኑም ቤት ስገባ መንበረ ቁርባን አየሁ። ይህን ነገርና በቅ. ቁርባን ያለውን ጌታ ዳግም ማየቱ በሕይወቴ ይሆንልኛል ብዬ አስቤውም አላውቅም ነበር። በዚያ ተንበረከኩና ተንሰቅስቄ አለቀስኩ፤ ወደ መንበረ ቁርባኑም ቀርቤ ሳምኩት።»
ማሪያ ስታንግ ወደ ካዛክስታን መንደሯ ከመመለሷ በፊት ካህኑ በጻህል አድርገው ቅ. ቁርባንን ሰጧት። እነዚያ በየሰንበቱ በቤቷ የሚሰበሰቡ ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በቅ. ቁርባን ዙሪያ ተሰባሰቡ፤ ማሪያም እንዲህ አለቻቸው «ማንም ሊገምተው የማይቻለው ደስታና ርካታ አለን፤ ጌታ በቅ. ቁርባን አብሮን ነው እናም እርሱን መቀበል እንችላለን»። ነገር ግን በዚያ የነበሩ ሴቶች ምሥጢረ ኑዛዜን ካደረጉ በጣም ስለቆዩ «ለብዙ ዓመታት ኑዛዜ አላደረግንም እናም መቁረብ አንችልም» አሏት። ከዚህ በኋላ ስብሰባ አደረጉና መከሩ፤ የሚከተለውንም ሃሳብ ወሰኑ «ያለንበት ሁኔታ እንደፈለግነው ለመናዘዝ የማይመች ነው፤ ቅ. ቁርባንም ስለኛ ከሺህ ኪ.ሜ. ርቀት በላይ ተጉዞ እዚህ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ይህ ሁሉ ይረዳዋልና ይምረናል። በመንፈስ ራሳችንን ወደ ምሥጢረ ኑዛዜ እናቅርብ፤ ባደረግናቸውም ኃጢአቶች ከልብ እንጸጸት፤ እያንዳንዳችንም ራሳችን ላይ ያመንበትን ካሣ »(ቀኖና) እንፈጽም»። በዚህም መሠረት ሁሉም የተስማሙበትን አከናወኑ፤ በመቀጠልም በእንባ ሆነው ተንበርክከው ቅ ቁርባንን ተቀበሉ። እንባቸው የንስሐና የደስታ በአንድ ነበር!
ማሪያ ስታንግ ለሠላሳ ዓመታት አማኝ ሴቶቹን በየሰንበቱ በቤቷ መሰብሰቡንና መጸለዩን፣ ለሕፃናትና አዋቂዎች ትምህርተ ክርስቶስ ማስተማሩን፣ ለምሥጢረ ተክሊል ማዘጋጀትን፣ የቀብር ሥርዓት መፈጸምንና ቅ. ቁርባን ማደሉን ቀጠለች። ቅዱስ ቁርባንን ዘወትር በእምነት በተቀጣጠለ ልብና አክብሮታዊ ፍርሃት በተሞላበት መንፈስ ታድል ነበር። እርሷ ካህናዊ ነፍስ ያላት ቅ. ቁርባናዊት ሴት ነበረች።

መሳጭ የቅዱስ ቁርባን ታሪኮች - ክፍል - ፩

Write comment (0 Comments)

ጠጠር ያለ ንግግር ግን የማይለወጥ እውነት!

"እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም!" ዮሐንስ 6:53 
Kidus Kurban 1ሌሎች ምሥጢራት ጸጋን ይሰጡናል፤ ቅዱስ ቁርባን ግን ራሱን የጸጋ ባለቤቱን፣ ሰውና አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ይሰጠናል። ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውም ሆነ አላት የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ማእከል ቅዱስ ቁርባን ነው።
ቅዱስ ማርቆስ የጸሎተ ኀሙስ ራት ሂደትን ሲገልጽ “ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው ብሎ ሰጣቸው” ይላል (ማር.14:22)። ከአራቱ ወንጌል ውስጥ ሦስቱ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን በግልጽ ይተርካሉ፦ ማቴ.26:25-29፣ ማር.14:22-25፣ ሉቃ.22:19-23። ቅዱስ ጳውሎስም በመጀመሪያ ቆሮንጦስ 11:23­-25 ጽፎልናል። ቅዱስ ዮሐንስ ከሌሎቹ ሁሉ በመጨረሻ የተጻፈ ወንጌል ስለሆነ (90-100 ዓ.ም.) ምናልባት ሌሎቹ ያልገለጿቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ይመስላል። ከላይ በተጠቀሱት ስለ ቅዱስ ቁርባን የተጻፉት ምንባባት ሁሉ የተንጸባረቀ አንድ እውነት ቢኖር “ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ…ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ” የሚለው ነው። 
 በዮሐንስ 6:53 ላይ ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም” ይላል። ይህ ጥቅስ በራሳቸው ባልሆነ ጥፋት ይህን ቃል ወይም መልእክት ያልሰሙት አይድኑም ለማለት ሳይሆን ይህን እውነት እያወቁና እየሰሙ እንዳልሰሙ የሚሆኑትን ለማመልከት ነው።
 ከስንዴ በተዘጋጀ ኅብስትና የተፈጥሮ ወይን ጭማቂ ላይ ዘላለማዊ የሆኑትን “እንካችሁ…” የሚሉትን የክርስቶስ ቃል ካህን ሲደግም ቅዱስ ቁርባን ዛሬም ለሰዎች ሁሉ ክርስቶስን ሕያው ያደርግልናል። በመሥዋዕተ ቅዳሴያችን የሚከናወነው ነገር ክርስቶስ ራሱ ካደረገው የሚለይ አይደለም። እሱ ኅብስቱን አንሥቶ “ይህ ሥጋዬ ነው” ወይኑንም አንሥቶ “ይህ ደሜ ነው” ሲል የመለወጡ ሂደት ተከናወነ። ይህ እንዴት ይሆናል ካልን እሱ ራሱ ባለቤቱ ያደረገውና ዘወትርም ሊያደርገው ቃል የገባልን ጉዳይ መሆኑን እንጂ አእምሮ ብቻውን እስከ ጥግ ድረስ ሊዘረዝረው አይችልም። ይህን አድርጉ ብሎ ሕያው አደራውን ተወልን፤ ስለዚህም ዛሬም የክርስቶስ ቃል የኅብስትና ወይኑን ውጫዊ ነገራቸውን ብቻ በማስቀረት ማንነታቸውን ግን የራሱ ሥጋና ደም ያደርገዋል። 
 በአንድ ወቅት እውቁ ሊቀ ጳጳሳት ፉልተን ሺን እንዲህ ብለው ነበር ፦ 
በቀን ነገሮችን ለማየት የምትጠቀምበት ዓይንህ ማታም አለህ፤ ሆኖም ግን የቀኑ የፀሐይ ብርሃን የለምና በምሽት ያው ዓይንህ ነገሮችን ማየት አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታም ተመሳሳይ የማሰብ ብቃት፣ እኩል ትምህርት፤ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሁለት አእምሮዎች (ሰዎች) በመንበረ ታቦት ላይ ያለውን “ኅብስት” ሲመለከቱ አንደኛው የስንዴ ኅብስትን ሲያይ ሌላኛው ክርስቶስን ሊያይ ይችላል። የተመለከቱት አንደኛው በሥጋ ዓይን ሌላኛው ደግሞ በእምነት ዓይን ነው ማለት ነው። የዚህ ልዩነት ምክንያት ይህ ነው፦ ክርስቶስን መመልከት የቻለው ሰው ሌላኛው የሌለው ብርሃን አለው - የእምነት ብርሃን! 
በዮሐንስ ወንጌል 6:47-67 ውስጥ ክርስቶስ ይህን መሰል ጠጠር ያለ የ “ሥጋና ደም” መመገብን ጉዳይ ሲናገር ብዙዎች እንኳን ማድረጉ መስማቱ አልዋጥላቸው ብሎ ከብዷቸው እሱን ትተውት ቢሄዱም መደራደርንና እንተወው ወይ ቀለል ላድርግላችሁ ብሎ አላመነታም።
ክርስቶስ ይህን ያህል ትኩረት የሰጠበትን እውነታ ቤተ ክርስቲያንም ትኩረት መስጠቱን ቀጥላበታለች። በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ይፈጸም የነበረውን የጌታ ትእዛዝ ተከትለው አበው ቅዱሳን ጥንታዊ ምስክርነታቸውን በጽሑፋቸው ትተው አልፈዋል። ከነዚህም መካከል ክርስቲያን በመሆኑ ለዱር አውሬዎች ምግብ ይሆን ዘንድ የዘመኑ ባለሥልጣናት የወረወሩትና በሰማዕትነት የሞተው ቅዱስ ኢግናጽዮስ ዘአንጾኪያ በ107 ዓ.ም. አካባቢ “ቅዱስ ቁርባን የአዳኛችን ኪየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ነው” ብሎ ጽፎ ነበር። እንዲሁም ስለ እምነቱ ሰማዕትነትን የተቀበለው ሌላ መስካሪ ቅዱስ ዩስጢኖስ በ145 ዓ.ም. ገደማ “የምንመገበው ሰው የሆነው የክርስቶስ ሥጋና ደም መሆኑን ተምረናል” በማለት ጽፏል። ከዚያም ይህ እምነት እንዳለ ሆኖ በ16ኛው ክ.ዘ. ከፕሮቴስታንቶቹ አካባቢ ቅዱስ ቁርባንን የሚቃወሙ ትምህርቶች በመስተጋባታቸው በ1551 ዓ.ም. በትሬንት በተካሄደው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቅዱስ ቁርባን ርግጠኛ የክርስቶስ ሥጋ፣ ደም፣ ነፍስና መለኮታዊ ህልውና መሆኑና ክርስቲያኖችም ሊከተሉት የሚገባ እምነት መሆኑ ይፋና ወጋዊ በሆነ መልኩ ጸደቀ።
እንግዲህ በቅዱስ ቁርባን የክርስቶስ ህልውና ይህን ያህል ወንጌላዊ፣ ታሪካዊ፣ ግልጽና ቀጣይ እውነት ከሆነ ዛሬም በየቤተ ክርስቲያኑ መንበረ ታቦት ላይ በኅብስትና ወይን ውጫዊ መገለጫ የሚገኘው ክርስቶስ ተገቢ የሆነ አምልኮና ስግደት ይገባዋል። እንዲሁም ዘላለማዊውና ሁሉን አዋቂው “ሐኪም” ክርስቶስ “ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ.6:54) ካለን እሱ ፈጥሮናልና የሚበጀንን አብጠርጥሮ ስለሚያውቅ በሚቻለን አቅምና ሁኔታዎች ራሳችንን ያለቀጠሮ አዘጋጅተን እንታዘዘው።
እምነታችንን፣ ፍቅራችንን፣ ተስፋችንን እና ይቅር ባይነታችንን በቅዱስ ቁርባን እንጂ በስሜቶቻችንና በሃሳባችን ልናጸናቸው አንችልም። ሁል ጊዜ የጋለ ልብና ግልጽ የሆነ ሃሳብ ሊኖረን አይችልም፤ ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን መንገድ ስለማወቃችንም ዘወትር ርግጠኞች መሆን አንችልም። እንዲሁም በአናኗራችንና በስብእናችን እምነታችን ምን እንደሚጠይቀን መመዘኑ ሁሌም አይሳካልንም። ነገር ግን ጥልቅ በሆነ መልኩ ርግጠኛ ልንሆንበት የምንችለው አንድ ነገር አለ፤ ያም ወደ ቅዱስ ቁርባን ዘወትር መሄድ መቻላችንን ነው። (ፍቅር ትዳርን ያጸናዋል ብለን ዘወትር ከማለት ትዳርም ፍቅርን ያጸናዋል ብሎ እንደማሰብ ነው። በተመሳሳይ መልኩም ያለማቋረጥ ስለምናምን ወደ ቅዱስ ቁርባን በቋሚነት እንሄዳለን ማለት ሳይሆን በቀጣይነት ወደ ቅ.ቁርባን በመሄዳችን እምነታችን ይጸናል ማለት ነው) ሮናልድ ሮልሃይዘር (አባ)  
Write comment (0 Comments)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት