እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ምስጢረ ተክሊል - ትርጉም፣ ዝግጅት፣ ችግርና መፍትሔ

ምስጢረ ተክሊል - ትርጉም፣ ዝግጅት፣ ችግርና መፍትሔ

Teklilምስጢረ ተክሊል ብለን ለመናገር ስናስብ በጣም ሰፊና ለብዙ የተለያየ ትርጉም የሚዳርገውን ጋብቻ ወይም ትዳር የሚለውን ሃሳብ ወደ አንድ አቅጣጫ ወዳተኮረ ሃሳብ እንድናመጣው ያግዘናል። ምክንያቱም ተክሊል የሚለው ቃል ትርጉም በቤተ ክርስቲያን በኩል ካህናት በሙሽሪትና ሙሽራው ላይ የሚፈጽሙት ሊፈርስ የማይችል የሕግ ጋብቻ ነው። ይህን ቃል ኪዳን ተክሊል ያሰኘው ሙሽሮቹ በዚያ ሥርዓት ላይ የሚደፉት የአበባው ተክሊል ሲሆን ይህም ዘውድ የራስ ጌጥ ሽልማት የክብር ጉልላትን ያመለክታል (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ)።

ስለዚህ በዚህ ርእስ ሥር በቀጥታ ክርስቲያናዊ የሆነውን የጋብቻ ትርጉም፣ ቅድመ ሁኔታዎች፣ በዘመናችን ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ሥርዓት የተጋረጡበት ችግርና መፍትሔዎቹን በአጭሩ እንነካካለን።

ጋብቻ ጥሪ ነው!

በክርስቲያናዊ እይታም ቢሆን ጋብቻ ለአንተ/ለአንቺ ምንድነው ተብለን ብንጠየቅ ምላሻችን ሊለያይ ስለሚችል የጋራ ትርጉሙ ይኖረን ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን የምትለንን እንይ። ምስጢረ ተክሊል ከሌሎች ነገሮች ሁሉ አስቀድሞ ለሰው ልጅ  ከእግዚአብሔር የተሰጠው ስጦታ ነው። “እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረ… ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው።” ዘፍ. 1፡27 “ብዙ ተባዙ ምድርን ሙሏት” ብሎ ባረካቸው፡፡ ዘፍ. 1፡28

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በራሱም የአንድነትና የፍቅር ምስጢር ሆኖ ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር በአምሳያው የሰውን ዘር ሲፈጥር … በወንድና በሴት ባሕርይ ላይ ጥሪን ቀረጸ፤ በዚያም መሠረት የፍቅርና፣ የአንድነት አቅምና ኃላፊነት ሰጣቸው… በጋብቻ አማካይነት የሚፈጸመው የወንድና የሴት አንድነት የፈጣሪ ልግስናና ፍሬያማነትን በሥጋ መፈጸም ነው፡፡ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡” ዘፍ. 2፡24 የሰው ትውልዶች ሁሉ ምንጭም ይኸው አንድነት ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የፍቅርና የአንድነት ጥሪ የሰውን መላ ማንነት ይገዛ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፤ ጾታዊ ባህርይ ማለትም ወንድና ሴት መሆን በሰው አጠቃላይ ገጽታ፤ በሰው አካልና ነፍስ ባለው አንድነት ላይ በሁሉ አንፃር ከፍ ያለ ተጽእኖ አለው፡፡ ጾታዊ ባህርይ በተለይ የፍቅር ስሜትን፣ የመዋደድና የመውለድ ችሎታን፣ እንደሁም በጠቅላላ ሲታይ ደግሞ ከሌሎች ጋር ትስስር የመፍጠርን ተሰጥዖ ያመለክታል፡፡” (የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ /ካ.ቤ.ት.ክ./ 6ኛዪቱ ትእዛዝ)

መሠረታዊ የሰው ወንድና ሴት ሆኖ መፈጠር ዓላማ ይህ ሆኖ ሳለ ምስጢረ ተክሊል ደግሞ ይህን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ ይከናወናል። እንደ እግዚአብሔር የፈጣሪነት የፍቅርና፣ የኅብረት ምሳሌ እንሆን ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ጋብቻ ይከናወናል። እዚህ ላይ ፈጣሪነት የእግዚአብሔር አብ፣ ፍቅር የወልድ ኅብረት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ መገለጫ መሆኑን እናስተውል - የምስጢረ ተክሊል ሕይወት የዚህ ነጸብራቅ መሆኑ ነው። {jathumbnail off}

በዚህም የመፈጠራችን ጥሪ ላይ ጥልቁ ክርስቶሳዊ ጥሪ ይጨመርበታል፡- “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።” ማቴ. 5፡48 ይህ ሁሉን የሕይወት አቅጣጫ የሚያቅፍ ጥሪ ነው በተለይም የጥሪዎች ሁሉ ቀዳሚ የሆነውን ጥሪ፡- ምስጢረ ተክሊል። ስለዚህ ወንጌላዊውና የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ጋብቻን ወንድና ሴት የእግዚአብሔርን የመፍጠር፣ የማፍቀርና የኅብረት አምሳል በመተግበር ለፍጽምና የሚመሠረት የኑሮ አቅጣጫ አድርጎ ያሳየናል። ይህም ተሞሻሪዎች የተፈጥሯዊ የሆነውን የአብሮ የመሆንና የመውለድን ብቻ ሳይሆን አናኗራቸውም ለቅድስና የሚመራቸው መሆን እንዳለበት ያስረዳል።

ቅድመ ሁኔታዎች

በመሠረቱ የጋብቻ ቅድመ ሁኔታዎች ከላይ ከጠቀስነው የጋብቻ ትርጉም ጋር የሚጋጩ ወይም ደግሞ የጋብቻን ምንነት የሚያደበዝዙ መሆን የለባቸውም። እውነተኛ ፈጣሪነትን አፍቃሪነትንና አጋርነትን የምንካፈለው በተክሊል ከሆነ ከጋብቻ በፊት ያለው ጊዜ እነዚህን ነገሮች የሚያዳብሩና መንገድ የሚጠርጉ ዝግጅቶችን የምናደርግበት ወቅት መሆን አለበት፤ ስለዚህም ቅድመ ጋብቻ ንጽሕና የጋብቻን ሕይወት ከሚያጣፍጡ ግብአቶች ተቀዳሚው ነው። ተክሊልን የሚመኝ ልብ ቅድመ ተክሊል ያለውን ጊዜም ለማክበር ዝግጁ መሆን አለበት።

“ኪዳናዊ ንፅሕናውን የሚያከብር ሰው የተሰጠውን የሕይወትና የፍቅር ኃይል እንዳለ ይጠብቃል፡፡ ይህ ጽናት የሰውየውን ምልአት ያረጋግጣል፤ ሊያደናቅፈው የሚሞክረውን ማንኛውንም ባህርይ ጠንክሮ ይቃወማል፡፡ መንታ ሕይወትን ይሁን የንግግር ድግግሞሽን አይቀበልም፡፡ ንጽሕና የሰብአዊ ነፃነት ሥልጠና የሆነውን የራስ ጌታ የመሆን - ራስን የመግዛት-  ትምህርት ያካትታል፡፡ አማራጩ ግልፅ ነው፤ ሰው ስሜቱን ተቆጣጥሮ ሰላምን ያገኛል፤ አልያ ደግሞ ለእርሱ ተገዢ በመሆን በኀዘን የኖራል፡፡ ነፃ በሆነና በንቃት ላይ በተመሠረተ ምርጫ ላይ ተመርኩዞ ድርጊቶችን ይፈጽም ዘንድ ሰውን ሰብአዊ ክብር ያስገድደዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ግላዊ በሆነ መንገድ ከውስጥ በመነጨ አኳሃን እንጂ በውስጥ ካለ ጭፍን ስሜት ወይም በውጫዊ አካሎች ሊሆን አይገባውም፡፡ ሰው ይህን መሰሉን ክብር መቀዳጀት የሚችለው ለፍትወት ካለው ባርነት ሁሉ ሲላቀቅ መልካም የሆነውን በፈቃዱ በመምረጥ ከግቡ ለመድረስ ጉዞውን በጽናት ሲቀጥል በትጋቱና በክህሎቱ ከዚህ ዓላማው ለመድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ሲያሟላ ነው፡፡” (ካ.ቤ.ት.ክ. 6ኛዪቱ ትእዛዝ)

መግቢያችን ላይ የምስጢረ ተክሊልን ስያሜ በሥርዓቱ ወቅት ተምሻሪዎቹ ከሚደፉት የአበባ ተክሊል መሆኑንና ይህም ዘውድ የራስ ጌጥ ሽልማት የክብር ጉልላትን ያመለክታል ያልነው ነገር በርግጥ ከጋብቻ በፊት ያለውን የዝግጅት ወቅት እንደሚገባው አሳልፈው ለዚያች የድል እለት የደረሱ ናቸውና አክሊል ይቀዳጃሉ። ቅድመ ተክሊል ያለውን የፈተናና የጽናት ጊዜ በድል ተወጥተዋልና በክብር ያጌጣሉ።

ከዚህም ባሻገር ምስጢረ ተክሊል የቤተ ክርስቲያንና የክርሰቶስን አንድነት ስለሚያንጸባርቅ ይህንን ምስል የሚያንጸባርቁ ሙሽሮች ክብርን በሚገልጹ ምልክቶች ያጌጣሉ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።” ኤፌ. 5፡31-32

የቅድመ ተክሊል ጊዜ ከሁሉም በላይ እጮኛሞቹ ስለ ፍቅር ያላቸው ግንዛቤ ላይ አቅማቸውን ማባከን አለባቸው። የትዳር ጊዜን እንደ አንደ መኪና ብንመስለው ስለመኪናው ምቾትና ውበት አውርተን ነገር ግን ስለ ነዳጁ ነገር ግድ የማንል ከሆነ መኪናው ውብና ምቹም ቢሆን ከቆመበት ፈቀቅ እንደማይለው ሁሉ ስለ ተክሊል በውበት በድግስ ዝግጅት በሀብት....ተዘጋጅተን ስለፍቅር ግን ትኩረት ከሌለን ተክሊሉ ሕይወት አይኖረውም ብቻም ሳይሆን ለመደረግም ብቃት የለውም። እንዲሁም አንድ ሊቀ ጳጳስ በአንድ ወቅት ክርስቶስን በሕይወት መመሪያ ስለማድረግ ሲናገሩ እንዳሉት በነዳጁ ምትክ ሽቱን ብንጨምርበት መኪና ሊንቀሳቀስ እንደማይችል ሁሉ በተክሊል ሕይወት በፍቅር ምትክ ሌሎች ነገሮችን ቅድሚያ ብንሰጥ ከተክሊል መሠረታዊ የመፋቀር፣ የመደጋገፍና የፈጣሪነት ዓላማ ጋር ይጋጫልና በቅድመ ተክሊል ወቅት ሌሎች ዝግጅቶች እንዳሉ ሆነው ስለፍቅር ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ አስፈላጊ ነው።

ፍቅር የሚለውን ነገር ስናነብ ወይም ስንሰማ ወደ አእመሯችን ስንት ሃሳቦች መጥተው ይሆን? ብዙ ጊዜ በተለያየ መልኩ ከመጠራቱ የተነሣ ቀላልና ጣፋጭ የሚመስለው ይህ ቃል በዚሁ ምክንያት ለብዙ የተሳሳተ ትርጉሞች የተዳረገ ነው አንድ ካህን ሲጽፉ ስለፍቅር ትክክለኛ ትርጉም ከመናገራቸው በፊት ሦስት የተሳሳቱ የፍቅር ግንዛቤዎችን ይጠቁማሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ፍቅር ሴሰኝነት አይደለም ይላሉ። ስለዚህም ፍቅር ሙሉ ለሙሉ ራስ ወዳድነት በሆነ ዓላማ የወሲብ ፍላጎትን ማርካት ብቻ ማሰብ አይደለም። በዚህ ዓይነቱ አንዱ ሌላውን የመደሰቻ መሣሪያ ማድረግ ዓላማ ላይ ራሱን የመሠረተ ጋብቻ ብዙ ይቆያል ብሎ ማሰቡ ይከብዳል።

ሁለተኛው ፍቅር መጎተት ወይም መሳብ አይደለም። ይህም ማለት በሌላኛው ሰው በውጪ በሚታዩ ነገሮች በቀላሉ መሳብ ሲሆን አነጋገሩ፣ አለባበሱ፣ አረማመዱ...ወዘተን የመሰሉ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። በርግጥ እነዚህ ነገሮች ወደ ፍቅር ሊመሩ ይችላሉ ነግር ግን ፍቅር ከነዚህ በላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ነገሮች ተክሊልን ወደፊት የማስገፋት አቅም ብቻቸውን የላቸውም፤ ምክንያቱም በአንድ ወቅት ውጫዊ እይታዎች ሁሉ በጤና እክል ወይም በእርጅና ወይም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ይበናሉ ያም የተደገፍንበትን ነገር እንድናጣና እንድንገዳገድ ብሎም  ምናልባትም ልጆቻችንንም በሚያሰጋ ሁኔታ እንድንወድቅ ያስገድደናል።

በሦስተኛነት ፍቅርን ከጓደኝነት መለየት መቻል አለብን። ባልንጀርነት ሁለት የተለያየ ወይም ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎች  አንደኛው ለሌላኛው የሚጋሩት ተፈጥሯዊ መቀራረብ ወይም መሳሳብ ነው። በአብዛኛው ባልና ሚስት ይህ ባልንጀርነት ይኖራቸዋል ግን የግድ አይደለም። ባልንጀርነት በራሱ ውብ የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ ሆኖም ባልንጀራሞች የሆኑ ወንድና ሴት ልጆች የግድ የፍቅር ሕይወት ውስጥ መሆን የለባቸውም እንዲሁም በፍቅር ያሉ ሁሉ ጓደኛሞች መሆን የለባቸውም።

እነዚህ የዘረዘርናቸው ሦስቱም በጋራ የሚካፈሉት ነገር ቢኖር ራስ ወዳድነተን ነው። ባልንጀራ ከጓደኛው ጋር መሆንን እንደሚፈልግ ሁሉ በሌላ ሰውም የተሳበ ሰው አብሮነትን ይሻል፣ ሴሰኛ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ራስ ወዳድ ነው። እውነተኛ ፍቅር ግን ከአጉል ራስ ወዳድነት የጸዳ ነው። “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።ዮሐ. 15፡12-13    /R. H. Lesser/

ቀጥለውም በተክሊል ውስጥ መኖር ስላለበት ፍቅር ሲናገሩ ከእንስሶች በተለየ ሁኔታ የወንድና የሴት ግንኙተነት የሙሉ ሕይወትን መሰጠት የሚጠይቅ ነገር መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም አባትና እናት አንድ ላይ መቆየት ያለባቸው ከእንስሳት ልጆች በተለየ ሁኔታ የሰው ልጆች /ሕፃናት/ ለማደግ ረጅም ዓመታት ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ ተክሊል ወሲብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም የግድ ስለሚያካትት ነው። እንስሶች በአንጻሩ ስለወሲብ እንጂ ስለፍቅር ግድ የላቸውም፤ ከወሲብ በኋላ የልጄ እናት ናት ወይም ሚስቴ ናት ብሎ መንከባከብ እንሰሳዊ ተፈጥሮ አይደለም። በአንጻሩ ሰው ግን ከእነርሱ የሚለየው ለትዳሩና ለልጆቹ በሙላት ራሱን መስጠት ስላለበት ነው።

የሰው ልጅ በተክሊል ሕይወቱ እውነተኛ ፍቅር የሚያስፈልገው አንዱ ለሌላው ሙሉ ለሙሉ ራሱን መስጠት ስላለበት ነው። ሙሉ ለሙሉ ስንል በነፍሱ፣ በአእምሮው፣ በስሜቱ፣ በአካሉ...መሆኑን ማስተዋል አለብን፤ ይህ ባህሪው ደግሞ ተክሊልን የሙሉ ሕይወት ጉዞ ያደርገዋል። ለጋብቻ ቀጣይነት አብረን የምንጋራቸው ነገሮች ወሳኝነት አላቸው። ስለዚህም ነው በእምነት፡ በስሜት በአብሮነት እውቀት የተቃኘ የዝግጅት ጊዜና ተክሊልን ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው። ይህም የእድሜ ልክን መሰጠት የመጠየቅ የተክሊል ትርጉም ይህን ጥሪ ካባድ ያደርገዋል ለዚህም ነው እጮኛሞች መታገዝና መዘጋጀት የሚያስፈልጋቸው። እግዚአብሔር የተክሊል ሕይወትን እንደመሠረተው ሁሉ አስጀማሪና አጽኚም ነውና በየአንዳንዱ የምርጫ፣ የዝግጅት፣ የውሳኔና አብሮ የመኖር  ሂደት ላይ  በጸሎት በምስጢራትና በቅዱስ ቃሉ የእርሱን ህልውና የመስማት ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል።

ችግርና መፍትሔዎቹ

በተክሊል ሕይወት ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የችግሮቹ ሁሉ ተቀዳሚ ሊሆን የሚችለው ፍቅር ለሚለው ሃሳብ የምንሰጠው ቀለል ያለ ትርጉም ነው፤ ይህም ሲሆን መሠረቱን ሙሉ ለሙሉ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የጣለው የተክሊል ሕይወት ግንዛቤያችንም ቀለል ያለ ይሆንና በተጨባጩ ሲታይ ግን መስዋእትነትን የሚጠይቅ ነገር ስለሆነ ችግሮች እዚያ ላይ ይመሠረታሉ። የትኛውም ሕይወት ቀላል ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ያ ማለት ግን ያ ከባድነትን መሻገር ወይም ትርጉም መስጠት አንችልም ማለት አይደለም። ስለዚህመ የተክሊልንም ከባድነት የምንሻገረው ቀላል እንዳልሆነ አምነን ትርጉም ስንሰጠውና ስንቀበለው ነው። እግዚአብሔር በእጃችን የሰጠን ትልቁ መሣሪያ ራስን መግዛት ነው። ከላይ ስለንጽሕና ስናይ “ንጽሕና የሰብአዊ ነፃነት ሥልጠና የሆነውን የራስ ጌታ የመሆን ትምህርት ያካትታልብለን ነበር። የራስ ጌታ መሆን ማለት አእምሮን ስሜትን አካልን ነፍስን...ቆም ብሎ ለመምረጥና ለመወሰን የሚያግዙ ልምዶችን ማሳደግ መቻል ማለት ነው። አንድ የአፍሪካ አባባል “የሚወዳትን ያገባ ደስተኛ ነው፤ ያገባትን የሚወድ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነው” ይላል። ይህ የምናደርገው ውሳኔ ምን ያህል አናኗራችንን እንደሚወስን ያሳየናል። ይህ የሚያሳየን ፍቅር ምን ያህል ራስን ከመግዛት ጋር ማለትም ውሳኔያችንንና ምኞታችንን ከመቆጣጠር ጋር እንደሚስማማና ውሳኔያችንም የፍቅር ብሎም የተክሊል ሕይወታችን ላይ መሠረታዊ መሆኑን ነው።

ብዙ ጊዜ ለተክሊል ስለሚዘጋጁና ስለሚኖሩ ሰዎች ፍቅር ሲነገር ሁለት ነገሮች ላይ ልዩነት ይደረጋል። መጀመሪያ በፍቅር መያዝና ሁለተኛው ደግሞ ማፍቀር! በፍቅር መያዝ መግቢያው ሲሆን ወደ እውነተኛ ፍቅር ሊያደርስም ላያደርስም ይችላል፤ ፍቅር ያዘኝ የሚለው ገለጻ ብዙ ጊዜ ከውጫዊ መሳብ ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁልጊዜ ፍቅር የሚል ትርጉም አለው ማለት አይደለም። ከልጆቻችን ጋር ፍቅር አይዘንም ግን እንወዳቸዋለን፤ ስለዚህ ፍቅር ያዘን ከምንለው ሰው ጋር ሁሉ እውነተኛ ፍቅር ላይ ነን ብለን ራሳችንን ማጨናነቅ አይገባንም። ከብዙዎች ልምድ በአንድ ደረጃ ላይ በፍቅር መያዙ ያከትምና የመለቀቅ ስሜትን ይፈጥራል፤ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት ፍቅርን ጨረስኩ፣ የመጀመሪያዬ 2ኛዬ...የበፊት፣ የድሮ.... የሚሉ አገላለጾች እየተለመዱ የመጡት ከዚህ ዓይነት ደረጃ ወደ እውነተኛው የፍቅር ደረጃ መሻገር ሲያቅት የተቋረጠ ግንኙነቶች ነው። በፍቅር ተይዣለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው የሆነ ግንኙነትን የሚያሻክር ሁኔታ ሲያጋጥመው ለውሳኔ ይጋበዛል የዛኔ ነው እውነተኛ ፍቅርን መቀጠል ወይም ማቆምን የሚጠይቀው። በሌላ አባባል በፍቅር መያዝ ሲያልቅ እውነተኛ ፍቅር ይጀምራል።  /ከቅርፊት መውጣት፣ Ego boundaries/

ስለዚህ ፍቅር እውነተኛ ሲሆን ህልውናውን በሚፈታተኑ አጋጣሚዎች ሁሉ ቆም ብሎ ወስኖ መጓዝ ይችላል። ቆም በሎ መወሰን በሁሉም አጋጣሚዎች የሚመች ነገር አይደለም በተለይም በፍቅር ሕይወት ላይ ስቃይ መቀበልን ይጠይቃል። ስቃይ የሚያስከትላቸውን ችግሮች በጣም ከመፍራታችን የተነሣ ከውሳኔ ይልቅ ስሜቶቻችንን መከተል ስንጀምር ችግሮቹን ያለመጋፈጣችን ችግሮችን ማስወገጃ ጥሩ መንገድ ይመስለናልከዚህም የተነሣ በተራቸው ከባድ ችግር የሆኑትን ለመርሳት የሚያግዙንን ድርጊቶች እናዘወትራለን። እዚህ ላይ “የምትጠጣው ነገሮችን ለመርሳት ያግዘኛል ብለህ ከሆነ ሂሳብ በቅድሚያ!” የሚለውን የአንዳንድ መጠጥ ቤቶች ማስታወቂያ ልብ ይሏል። በእምነት ወደ ሁሉን ቻይ አምላክ ችግራችንን ከማሳረግና እንደ ሰውም ቆም ብለን ተመካክረን ከመወሰን ይልቅ የሕይወት እውነታን ለመሸሽ የምናደርገው ጥረት ነው አብዛኛውን ጊዜ የማንነት፣ የእምነትና የተክሊል ሕይወት መቃወስን ያስከትልብናል።

ራስን መግዛት በተወሰነ መልኩ ለመሰቃየት ቢዳርግም ትርጉም ያለው ስቃይ ደግሞ ካለመሰቃየት ይቆጠራልና ስለ ተክሊል ሕይወት ማለትም ስለራስ፣ ስለትዳር አጋር፣ ስለልጆችና ስለክርስቶሳዊ እምነታችን የምንከፍለው መስዋእትነትን አውቀን መዘጋጀት ያስፈልጋል። አንድ ደራሲ /M. Scott Peck/ ራስን ለመግዛት አራት አጋዥ ነጥቦችን ይሰጠናል፡- ርካታን ማዘግየት፣ ኀላፊነትን መልበስ፣ ለእውነት መሰጠትና ሚዛናዊ መሆን ናቸው። እንደ ደራሲው ሃሳብ እነዚህ መሣሪያዎችን መጠቀም ከባድ ነገር የሚሆነው ፈቃደኝነት ከሌለን ብቻ ነው፤ በነዚህ መሣሪያዎች ችግሮችን ማስወገድ ሳይሆን መጋፈጥ እንችላለን፤ ይህንንም በማድረግ አላስፈላጊ የሆኑ ችግሮችን ከመጨመር እንቆጠባለን። ርካታን ማዘግየትም ሆነ ኀላፊነትን መልበስ እንዲሁም ለእውነት ራስን ማስገዛትና መጠናዊ የሆነ አናኗርን መምረጥ የምንችለው ደግሞ ከፍቅረኛችን ጋር አብርን በመጸለይ በእግዚአብሔር ቃል የተመራና በምሥጢራት የተመገበ ከዚህም የተነሣ ለእውነተኛ ፍቅር ማለትም ክርስቶስ ላስተማረን ራስን ለሌሎች የመስጠት ሕይወት መኖርን ስንለማመድ ብቻ ነው

ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ካቶሊካውያን ተመራቂ ተማሪዎች ሽኝት የተዘጋጀ

ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ሲታውያን ገዳም ጎንደር።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት