የልደተ ክርስቶስ ድባብ በቫቲካን መንበረ ጴጥሮስ
የልደተ ክርስቶስ ድባብ በቫቲካን መንበረ ጴጥሮስ አደባባይና ቤተ ክርስቲያን...(ፎቶዎች)
በቫቲካን ከተማ የሚገኘው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ደብር - መንበረ ቅዱስ ጴጥሮስ - በዓለማችን ካሉ ተጎብኚ ቦታዎች የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ ቀዳሚው መሆኑ ይታወቃል። ከአደባባዩ ጀምሮ እስከ ደብሩ ሥነ ሕንፃው ቅርጽና ውበት፣ እንዲሁም በውስጡ ያሉ ዓለማችን ያፈራቻቸው ታላላቅ ሥነ ጥበብት የሳሏቸውና የቀራረጿቸው የጥበብ ሥራዎች፣ የተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶችና ንዋየ ቅዱሳት...ወዘተ በተለያየ መልኩ ብዙ ሰዎች በቦታው ሲገኙ ከጊዜና ቦታ ውጭ የሆነ ወደሚመስል ስሜት ፈጥነው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል።
ከነዚህ ተያዥና ተጨባጭ ነገሮች ባሻገር ለመላው ክርስቲያኖች በተለይም ደግሞ ለካቶሊካውያን ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን እኔም እንዲህ እልሃለሁ፦ ጴጥሮስ አንተ ዓለት ነህ፤ በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያን የሞትኃይል እንኳ አያሸንፋትም። እነሆ ለአንተ የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል ማቴ.16:17-19 በማለት ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ በማያልፍ ቃሉ የሰጠውን ተስፋ ተቀብሎ እስከ ሰማዕታዊ ሞቱ ድረስ ለክርስቶስ የኖረው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተቀበረበትና ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ ይህን የርሱን ኃላፊነት ያለማቋረጥ በመቀባበል በመተግበር ላይ ያሉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚቀመጡበት ስፍራ ስለሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ልዩ ሞገስን ያላበሰው ደብር መሆኑን አብዛኛው ሰው የሚመሰክረው እውነታ ነው።
ከዚህ በታች የሚመለከቷቸው ፎቶዎች ከላይ የገለጽነውን እውነታ ለማስተላለፍ አቅም ባይኖራቸውም፤ የዘንድሮውን የክርስቶስን ልደት በዓል -ገና- ምክንያት በማድረግ በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ደብርና አደባባይ የተዘጋጀውን ጌታ ሲወለድ የነበረውን ድባብ የሚያሳይ ዝግጅት ለማሳየት እንሞክራለን። ወንጌሉ እንደሚለው በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ በመላእክት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ዮሴፍ መታጀቡን፤ በእረኞችና በነገሥታት መጎብኘቱን...ያሳያሉ። መልካም ቆይታ።
ክፍል 1 - የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተ ክርስቲያን ከውስጥ በኩል በመጠኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች (ይጫኑት)
Last Updated (Monday, 18 January 2010 22:09)


