የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ
የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ለማየት ሲሞከር ዘወትር የመጀመሪያ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው መቼ ነው የሚለው ነጥብ ሊሆን ይችላል ነው። ለዚህ ጥያቄ አንድ መልስ መስጠት ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ይህ ነጥብ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ምንድናት ወደሚለው ጥያቄ ስለሚያመራን ማለት ነው። ስለዚህ ይህንንና መሰል ጥያቄዎች ውስጥ ጠለቅ ብለን ሳንገባ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ስምና ቃል በዙሪያው በመሰብሰብ ትምህርቱን የሕይወታቸው ተቀዳሚ ፋይዳ ያደረጉ፤ በእርሱም የእግዚአብሔርንና የሰውን ምንነት ይበልጥ የተረዱ፣ በእምነት አንድ በመሆን እርሱን ለመከተል የሚጥሩ ስብስብ ናት በሚል የጋር ግንዛቤ ከተስማማን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ታሪክ ጋር ብለን መጀመር እንችላለን።
ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ስም ስናስተውል በቀላሉ የሚያስተላልፍልን ትርጉም የክርስቲያኖች ቤት፣ ኅብረት ሲሆን ይህ ኅብረት ወይም መሰባሰብ ደግሞ በምን ዙሪያ ወይም ዓላማ ነው የሚለውን ሃሳብ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ ይመልስልናል። ክርስቲያን የሚለው ቃል ክርስቶስ በአካል ከተገለጠበት ዘመን አንሥቶ በስሙ እየተጠሩ የርሱ ተከታይ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰዎችን ለማመልከት የሚያገለግል ነው። በዚህም መሠረት የቤ/ያን ታሪክ በቀጥታ ወደ ክርስቶስ ታሪክ ያመራናል። በርግጥ በእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ መሰባሰብ በአዲስ ኪዳን የሆነ ነገር ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም ሕዝበ እስራኤል በእርሱ ቃል የተሰባሰበ ሕዝብ እንደነበር እናነባለን፤ ሆኖም እንደተቀሩት ነገሮች ሁሉ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ሊሆን ያለው ነገር ጥላ እንጂ በራሱ ሙሉ አልነበረም። ይህ በእግዚአብሔር ቃል መሰባሰብ ሙሉ እውነታ የሚሆነውና ሕዝበ እስራኤል በቤተ ክርስቲያን የተተካው በክርስቶስ ቃልና በራሱ በክርስቶስ አካል ዙሪያ መሰባሰብ ከተጀመረ ወዲህ ነው።
በታሪክ እይታ ሲታይ ስለ ክርስቶስ ታሪክ ማውራት በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በርሱ ዘመን የተጻፈ በቂ የጽሑፍ ምንጭ የለንም፤ ክርስቶስ ራሱም የጻፈልን ነገር የለም። በአጭሩ ዘግየት ብለው ከተጻፉት ወንጌሎች ውጭ ስለ ክርስቶስ የተጻፈ ዓለማዊ ታሪክ ምንም የለንም። ወንጌሎች ደግሞ የታሪክ መጽሐፍት አይደሉም፤ ማስተላለፍ ያለሙትም የክርስቶስ ታሪክን ሳይሆን ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የመሆኑን እምነትን ነው። ክርስቶስ ከሞተ 90 ዓመታት ገደማ በኋላ ቢያንስ ክርስቶስ እንደ ነበረ የሚመሰክሩ በጣም ጥቂት አንዳንድ የሮማውያን ዓለማውያን ታሪክ ጸሐፍትን እናገኛለን። ስለዚህም ወንጌልም ሆነ በጠቅላላ አዲስ ኪዳን የሚያስተላልፉት ታሪካዊ እውነት ቢኖራቸውም ሙሉ ታሪክ አልተዘገበባቸውም።
እንደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤተ ክርስቲያን አንዲት መንፈሳዊት ብቻ የሆነች ማኅበር ሳትሆን ሰብአዊነትና መለኮታዊነት ያላት፤ ክርስቶስ ራሷ ሆኖ የተለያዩ አካላት ያሏትና ሁሉም እርስ በርሳቸው በመዋቅር የተያያዙ አባላትን ያሰባሰበች መሆኗን ታስተምራለች። ይህችን መሰል ቤ/ያን ክርስቶስ ራሱም እንደመሠረታትና በአዲስ ኪዳንም እንደተንጸባረቀች ይታያል። ሐዋርያት እንደ በጳጳሳት ሲወከሉ ከሐዋርያትም ደግሞ ጴጥሮስ የመሪነቱን ስፍራ እንደተሰጠው ክርስቶስ ለጴጥሮስ ቁልፍ በሰጠው ወቅት ተገልጿል(ማቴ.16:16-19)፤ ቁልፍ ደግሞ የኀላፊነትና የመሪነት ምልክት ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ቃል፣ ፈቃድና ተግባር በዘመናት እያስተላለፈች የቆመች የርሱ አካል ናት፤ ስለዚህ ይህ እውነት ራሱ የቤተ ክርስቲያን መሠረት በክርስቶስ እንደሆነና በአዲስ ኪዳንም የአባላትና የአስተዳደር ሁኔታዋ እያደገ መምጣቱን በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ባህሪይ ብቻ ያላት ብትሆን ኖሮ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብሎ ማውራቱን ትርጉም የለሽ ነገር ያደርገዋል።
የኢየሩሳሌም ጉባኤ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በታሪክ የምናውቃት ቤተ ክርስቲያን መልክ በዝርዝር ባይሆንም በጅማሬ ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እናገኛታለን። መለኮታዊ ግልጸት የሆነ ነገር ሁሉ በጊዜ ሂደት ይበልጥ ግልጽ ሆኖ እንደሚታይ ሁሉ በጽሑፋቱ የምናገኛት ቤተ ክርስቲያንም በታሪክ ውስጥ መልክ እየያዘች ፍጽምት ወደ ሆነችው ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ትደርሳለች። ይህ እስኪሆን ግን አባላቶቿ ሰዎች ናቸውና ድካምና ብርታት፣ ቅድስናና ውድቀት፣ ብርሃንና ጨለማ…ይፈራረቁባታል። ይህም ተፈጥሮዋ በየጊዜው ራሷን እንድታይና መንገዷን ወደ ጌታዋ ለማቅናት ቆም ብላ እንድትወያይና ራስ የሆነውን ክርስቶስን ለማዳመጥና የርሱን ፈቃድ ለዘመኑ ለማስተላለፍ የተለያዩ መንገዶችን ትጠቀማለች። ከነዚህም መንገዶች አንዱ ጉባኤ መጥራት ሲሆን ይህም ከሐዋርያት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። በግልጽ በብዙ የታሪክ ሰነዶች የምናገኛቸው የቤ/ያን ጉባኤዎች ጥቂቶቹ በኒቅያ 325 ዓ.ም.፣ በኬልቄዶን በ451 ዓ.ም.፣ ላተራል፣ ቶሮንቶ…በቅርብ ክፍለ ዘመናትም የቫቲካን ጉባኤ 1ኛና 2ኛ… ሲሆኑ ባጠቃላይ ሀያ ሁለት ጉባኤያት ናቸው። በሐዋርያት ሥራ ደግሞ የነዚህ ጉባኤዎች ሁሉ ፈር ቀዳጅ የሆነውን በምዕ.15 ላይ እናገኛለን።
ይቀጥላል...

የብጹዕ ገ /ሚካኤል አጭር የሕይወት ታሪክ
<ስምዓ ጽድቅ ኮንከ >
ብጹዕ ገ/ሚካኤል በ 1788 በጎጃም ልዩ ስሙ ዲቦ በተባለ አውራጃ ተወለዱ። ከልጅነታቸው ጀምረው የአገራችንን ትምህርት ማለትም ዜማ፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ቅኔ ወዘተ. . . ለመማር ተሰማሩ። በትምህርት ትጋታቸውና በውጤታቸው መምህሮቻቸው በጣም አደነቁዋቸው። ይህን ሁሉ መንፈሳዊ እውቀት ካካበቱ በኋላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በሙሉ ልባቸው ሊሰጡ ፍላጎት ዕቅድ ስለነበራቸው በ25 ዓመታቸው በመርጡለ ማርያም ገዳም ገቡ። በጣም ጎበዝና ከፍተኛ የዕውቀትና የእውነት ጥማት ስለነበራቸው ከገዳም ወደ ገዳም ይዘዋወሩ ነበር። እንደዚህም እያሉ ሲታገሉ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሕሊናቸውን ያስጨንቅ የነበረው የሃይማኖት ልዩነትና ጭቅጭቅ ገጠማቸው።
በዚህም ዕረፍት አጥተው ተጨንቀው "ጌታዬና መድኃኒቴ፡ ጽድቅ የት እንደምትገኝ ግለጥልኝ፡ አንተ ጻድቅ እንደሆንክ አምናለሁ። ጻድቅ ነኝ፤ ትክክለኛው የኔ ነው ወዘተ . . . የሚሉኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ጽድቅን ሳትበላሽ ከምንጭዋ ላገኛት እፈለጋለሁ" እያሉ ጸለዩ። እግዚአብሔርም ጸሎታቸውንና የልባቸውን ምኞት ሰምቶ ከቅዱስ ኣቡነ ያዕቆብ ጋር አገናኛቸው። ብጹዕ ገ/ሚካኤል በቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ሕይወት ዘመን በብዙ የሃይማኖት ትምህርት ታነጹ።
በ 1851? በሀገሪቱ ፓትርያርክ ስላልነበር በደጃች ውቤ ተመርጠው ወደ እስክንድርያ ፓትርያርክ እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ መልእክተኛ ሆነው ወደ አሌክሳንድርያ ተላኩ :: ከመልእክተኞቹ አንዱ ደግሞ በዛን ግዜ ጥሩ ዝናና ተቀባይነት የነበራቸው ካቶሊካዊው አባ ያዕቆብ (አሁን ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ) አንዱ ነበሩ :: በዚህ አጋጣሚ ስለሃይማኖታቸው ለመወያየት ጥሩ አጋጣሚ አገኙ :: አባ ያዕቆብ ለሚያቀርቡላቸው ለነበረው <ክርስቶስን > በሚመለከት በደንብ ያውቁ ስለነበረ፤ እነሱን ለማስረዳት የሰጡት መልስ <ስለ ሥላሴ በምታስተምሩት ትምህርት ላይ: አንድ አምላክ ሦስት አካላት ትላላችሁ:: ታዲያ የኢየሱስ አንድ አካል ሁለት ባሕሪ እንዴት ሊከብዳችሁ ቻለ?> እንደዚህ እየተጠያየቁ: አንዱ ከአንዱ እየተማረ ከእስክንድርያ ወደ ቤተልሔም: ቅ .ጴጥሮስ ንግደት በአንድ ላይ ፈጸሙ ::
ከ1846-1854 ካቶሊክ ስለሆኑና በፓትርያርክ አቡነ ሰላማ ትእዛዝ በተለያየ ጊዜ ወደ እስር ቤት ወረዱ:: በእስር ቤት ውስጥ በጣም በሚያሰቅቅ ሁኔታ በዱላ ተደበደቡ:: ምንም ለውጥ ስላላሰዩና በእምነታቸው ጸንተው ስለተገኙ እንደገና ለማረጋገጥ ብለው አቡነ ሰላማ: አባ ገ/ሚካኤልን ከእስር ቤት አስጠርተው ስለእምነታቸው ጠየቁዋቸው:: ምንም ለውጥ ስላላገኙባቸው ወደ ንጉሡ (አጼ ቴዎድሮስ) አሳልፈው ሰጡዋቸው:: ንጉሡም በግርፋት እንዲቀጡ አዘዙ:: አሁንም ከእምነታቸው ነቅነቅ ስላላሉ ንጉሡ ወታደሮቹን ሁላችሁም በአንድ ጊዜ ግረፉዋቸው ሲሉ አዘዙ:: 150 ጅራፍ ፊታቸው ላይ ተገረፉ (ያቺ የቀረችውን አንድ ዓይናቸውን ሊያጠፉ):: በዛ የነበሩ ስቃያቸውን የሚመለከቱ የነበሩ ሲመሰክሩ <የገራፊዎቹን ብዛት : የግርፊያውን ቁጥር : ይህን ያህል ተብሎ መናገር አይቻልም > በማለት የግርፊያውን አሰቃቂነት ይገልጻሉ:: በዛ የነበሩ ሰዎች በቃ <ሞተዋል >: እያሉ እየተነጋገሩ እያሉ : ሰማዕቱ (አባ ገ/ሚካኤል ) ከዛ ሁሉ ድብደባና ግርፊያ በኋላ : ምንም እንዳልሆኑ፡ ፊታቸው ላይ ቁስል የምትባል ሳትታይባቸው : አይናቸው ከበፊቱ የበለጠ ብሩሕና ደስተኛ ሆነው ወደ እስር ቤት ሲያመሩ አይዋቸው። ከሁለት ቀን በኋላ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት በሰንሰለት ታስረው ከወታደሮች ጋር በእግር እንዲጓዙ ተደረገ :; በዚህን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ 60 በላይ ነበር:: ይህንን ስቃያቸውን የተመለከቱ ወታደሮች በጣም ከመገረምና ከመደነቅ የተነሳ አባ ገ/ሚካኤልን <ቅዱስ ጊዮርጊስ > በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸው ጀመር:: ምክንያቱም ቅ .ጊዮርጊስ 7 ጊዜ ሞቶ ተነሳ የሚባል ታሪክ ስላለ:: እንደገና ንጉሡ አጼ ቴዎድሮስ እና አቡነ ሰላማ በተገኙበት እንደገና አባ ገ/ሚካኤልን ስለእምነታቸው ጠየቁዋቸው:: አባ ገ/ሚካኤልም "አምባገነኑና እውነተኛው የክርስቶስ ጠላት ሆይ ስማ! ዛሬ በር.ሊ.ጳ. ፒዮ 9ኛ በምትመራውና በምታስተምረው ካቶሊክ ቤ/ያንና: እኔ የእምነት ልጁ - እስከመጨረሻው የሕይወት እስትንፋሴ ድረስ - ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው በሆነው ክርስቶስ አምናለሁ - ደግሞም መሞት የምፈልገው በዚህ እምነት ነው " ሲሉ መሰከሩ :: በዚህ ምስክርነታቸው ደግሞ ሞት ተፈረደባቸው: :: ነሐሴ 23 ደግሞ ስለ ካቶሊካዊ እምነታቸው ብለው በሰማዕትነት ሕይወታቸውን ኣሳልፈው ሰጡ ::
ጥቅምት 3/1926 እ.ኤ.አ. በቅዱስ ጴጥሮስ ቤ/ያን በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ብጽዕነታቸው ታወጀ:: የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ካህናት አርአያና ባልደረባ (patron) ይባላሉ ።
ሰላም ለሞትከ ዕረፍተ ጻድቃን ዘኮነ :
አምሳሊሁ ለኢየሱስ ዘሞተ በእንቲአነ :
ለነኒ ሀበነ ገ/ሚካኤል አቡነ
ለነፍስነ ሞገስ ወለልብነ ዛህነ
ወኅሉቀ ንርከብ ዘነፍስነ ድኂነ ::
የጻድቃን እረፍት ለሚመስለው ሞትህ ሰላም ይሁን፡አባታችን ገ/ሚካኤል ሆይ ! ሞትህ ስለ እኛ የሞተውን የክርስቶስን ይመስላል፡አባታችን ሆይ ለነፍሳችን ድኅነት እንድናገኝ ለልባችን ጸጋና እረፍት ስጠን።
የሀገራችን ቅዱስ : ስለ ሀይማኖታቸው ብለው በመስዋዕትነት የሞቱት የብጹዕ ገብረሚካኤል በዓል ነሐሴ 23 ይከበራል ::
ዋዜማው <ተሰአሎ ንጉሥ ለብጹዕ ገብረሚካኤል : ወይቤሎ ንግር ሃይማኖተከ : አውሥኦ ብጹዕ አአምን በኢየሱስ አምላክ ወሰብእ : ወበአሐቲ መንበረ ጴጥሮስ : ሰማዕተ ኮነ በሃይማኖት ወወረሰ መንግሥተ ሰማያት > እየተባለ ይከበራል ;;
ትርጉሙ : <ንጉሡ (አጼ ቴዎድሮስ) ብጹዕ ገብረሚካኤልን ሀይማኖትህን (እምነትህን) ተናገር ብለው ጠየቁት : ብጹዑም አምላክና ሰው በሆነው ኢየሱስና በአንዲት መንበረ ጴጥሮስ አምናለሁ ብሎ ተናገረ : በሰማዕትነት ሞተ : በእምነታቸው ደግሞ መንግሥተሰማይን ወረሱ >
አባ ጸሊ በእንቲአነ : እስመ ጸሎተ ጻድቅ ይሰምዕ እግዚአብሔር