If our pages are illegible, please download fonts here: Visual Geez Unicode

 

 

 

ካቶሊካዊነት

 

በልጅነታችን በአንድ ወቅት እንደተነገረን ወይም በቤተሰብም ይሁን በሆነ አጋጣሚ ብለን በምንተረጉመው ነገር ግን እውነቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንነውን ክርስቲያንነት እንደ ካቶሊክነታችን መኖር ካለብን ቆም ብለን ካቶሊክነት ለኛ ምን ትርጉም አለው ብለን መጠየቅ የግድ ነው፤ ምክንያቱም ወንጌልን ከጌታዋ ተቀብላ የሰጠችንን ቤተ ክርስቲያናችንን ለይቶ ማወቅ ራሷ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እውቀት እንደሚያደርሰን እሙን ነው። እንደው በድፍኑ ሁሉም አንድ ነው የሚል የዘመኑ አባዜን በዋዛ ወስደን ማስተጋባት ትተን ሁሉም ያው ነው ማለትና ሁላዊነት ልዩነት ስላለው ማንነታችንን ማወቁ ተገቢ ነገር ነው።

ካቶሊክ የሚለው ስም ሁነኛ ትርጉሙ ጠቅላላ፣ ሁላዊነት፣ ሁሉን አቀፍ... የሚል ጽንሰ ሃሳብ የሚያስተላልፍ ሲሆን መሠረቱም ከግሪክ ካቶሊኮስ የሚል ቃል የተወረሰ ነው። ቤተ ክርስቲያን በጥንታዊው ዓለም በኃያልነት ተንሰራፍቶ በነበረው የሮማ ግዛት ሙሉ ለሙሉ ተሰራጭታ ትገኝ ስለነበረ ካቶሊክ የሚል ስያሜን በዚያን ዘመን አገኘች። በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ካቶሊክ የሚለው ቅጽል ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቶ የምናገኘው በ110 ዓ.ም. ገደማ በቅዱስ ኢግናጽዮስ ዘአንጾኪያው ጽሑፍ ውስጥ ነው።

በክርስትና ታሪክ ውስጥ ካቶሊክ የሚለው ቃል የተለያዩ አጠቃቀሞች አሉት። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል:-

  1. በአቅራቢያ ወይም በአካባቢ ከምትገኘው የክርስቲያን ማኅበር ወይም ቤተ ክርስቲያን በተለየ ሁኔታ በሁሉ አካባቢ የምትገኘዋን ሁሉን አቀፍ ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት ሲሆን በዚህም አጠቃቀም የመላዪቱ ቤተ ክርስቲያንን እምነት ያመለክታል።
  2. የሐሰት ትምህርትን አንግበው ይነሡ ከነበሩ መናፍቃን እና ከቤተ ክርስቲያን የተነጠሉ ቡድኖች (Schismatical) ለመለየት ሐቀኛ - Orthodox - ትምህርትን የያዘች ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት፤
  3. በታሪክ ጸሐፊያን አገላለጽ ቤተ ክርስቲያን በ1054 ዓ.ም. በምሥራቅና በምዕራብ ሳትከፋፈል በፊት የነበረችውን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለመግለጽ ሲጠቀሙበት፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ለሁለት ከተከፈለች በኋላ በምሥራቅ ያለችው ኦርቶዶክስ በምዕራቡ ደግሞ ካቶሊክ የሚለውን ስያሜ ይዘው ቀጥለዋል።
  4. ከ16ኛው ክ.ዘ. ወዲህ ደግሞ የምዕራቧ ቤተ ክርስቲያን በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ... በተሐድሶ - Reformation - ዘመን በተለያየ ምክንያቶች ስትከፋፈል እነዚህ የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን ስያሜ ሲያገኙ አሁንም ከነርሱ የተቀረችው ቤተ ክርስቲያን ካቶሊክ በሚለው ስያሜ ቀጠለች፤ ከዚህ እንቅስቃሴም በኋላ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ በተወራራሽ መልኩ ቀጠለ። ምክያቱም እነዚህ የተለዩ ወገኖች ከጴጥሮስ ወንበር ማለትም በቫቲካን ከምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በመውጣት የየራሳቸውን አስተዳደር ስለጀመሩ ነው።
  5. በአሁኑ ዘመናችን አጠቃቀም ደግሞ ካቶሊክ የሚለው ስያሜ ለሁለት ሺህ ዓመታት ቀጣይ የታሪክ፣ የእምነት፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የትውፊት ሀብትን ይዛ የምትጓዝ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል። ይህም ከክርስቶስ ልደት በኋላ 1600 ዓመታት እና ከዚያ በኋላ የተነሡ ከፕሮቴስታንቶች ልዩ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ያመለክታል

በ325 ዓ.ም. በኒቅያ በጊዜው የነበረችውን ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ያካተተ የመጀመሪያው ጉባዔ ሲካሄድ የተሰበሰቡት አባቶች የወሰኑት አንቀጸ ሃይማኖት ለመላዪቱ ቤተ ክርስቲያን የእምነት መገለጫ ይሆን ዘንድ ወሰኑ። ይህም በአጭር መልኩ ዘወትር በቅዳሴ ጊዜ የምንደግመው ጸሎተ ሃይማኖት ነው።

ዛሬም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ እምነትና እይታ መለያዎቿ ናቸው። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሃገራዊት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፤ ፖለቲካዊም ሆነ ሀገራዊ ማንነትንና ልዩነትን ወደ ጎን በማድረግ ዘወትር ቅድሚያ ለሰው ልጅ እንደ ሰውነቱ ትሰጣለች። ይህን ሐቅ እውን ለማድረግ በዘር፣ በፖለቲካ ወይም በሃይማኖትና መሰል ነገሮች የሰው ልጅን ክብርና ስብእና የማያስከብሩ ሁኔታዎችን፣ የፍትሕና የሰላም መረገጥን...ወዘተ እንደታዛቢ አትመለከትም። በቃሏና በጸሎቷ አጽንዖት ሰጥታ የሰው ልጅን ሕይወት ተቀዳሚነት ታውጃለች።

የቤተ ክርስቲያናችን ሁላዊነት ታሪክ ያወረሳት ክስተት ሳይሆን ክርስቶስ የተሰዋበትና ያወረሳት የፍቅር እውነተኛ መገለጫ ልዩ ተፈጥሮዋ ነው። ሰው ራሱ እንዲመቸው በሠራቸው ድንበርና ወሰን የክርስቶስን ፍቅርና የማዳን ኃይል መወሰን ክርስቲያናዊ ትምህርት ሊሆን አይችልም። ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጥሩ ቃላት እንደገለጹት <<ወገንተኝነት/ዘረኝነት ክርስቶስን ያቆስለዋል>>።

ካቶሊካዊነት ማለት ዓለም አቀፋዊነት መሆኑን ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ትመሰክራለች። በየትኛውም የዓለም ጫፍ ቢኬድ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በሥርዓቷና በጸሎቷ፤ ያለምንም መሠረታዊ ለውጥ በቅዳሴና በምሥጢራቷ ትገኛለች።

ከመረጃ መለዋወጫና ከመጓጓዣ ዘዴዎች እድገት አኳያ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበችና መንደር እየሆነች በመጣችበት ሰዓት ለክርስቲያንነት ብሎም ለካቶሊካዊነት የወንድማማችነትን ስሜት ለማሳደግ ይበልጥ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቢመስልም ቅሉ በዘመናችን ያለው የአስተሳሰብ ጫና ራስ ወዳድነት ዘወትር እንዲያድግ የሚያግዝና ግላዊነት ላይ ያተኮረ ስለሆነ እንደ ስማችን ካቶሊክ ክርስቲያን ማለትም የክርስቶስና የሁሉም ሆነን መገኘት ዛሬም የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ነው።

 

የሰው እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታ    

ከአዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የተወሰደ    ምዕ. 1 ቁ.27-35

1.የሰው እግዚአብሔርን መሻት

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን መሻቱ በልቡ ተጽፎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔርም ሰውን ወደ ራሱ ከማቅረብ ከቶ አይቆጠብም። ሰው ያለ ማቋረጥ የሚፈልገውን እውነትና ደስታ ሊያገኝ የሚችለው በእግዚአብሔር ብቻ ነው።

የሰው ክብር ዋና መሠረቱ ከሁሉ በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖረው መጠራቱ ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲነጋገር ለሰው የቀረበለት ጥሪ የደረሰው ሕልውናውን እንዳገኘ ወዲያውኑ ነው። ሰው ሕያው ሆኖ የሚኖረው እግዚአብሔር በፍቅር አማካይነት ስለፈጠረውና በፍቅረ አማካይነት በሕይወት ስለሚጠብቀው ነው።

በታሪክ ሂደት እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች እግዚአብሔርን መሻታቸውን በበርካታ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውና ድርጊታቸው በጸሎታቸው፣ በመሥዋዕታቸው፣ በአምልኮአቸው፣ በአስተያየታቸው፣ ወዘተ. ሲገልጹ ኖረዋል፣ በዚህ ዓይነት ሃይማኖታዊ መግለጫዎች አንዳንዴ አሻሚነት ቢኖራቸውም በመላው ዓለም የሚስተዋሉ በመሆናቸው ሰው ሃይምኖታዊ ፍጡር ነው ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ይችላል።

(እግዚአብሔር) እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ቅመአያት ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤የሚኖሩባቸውን ዘመናትና ቦታዎች ሰጣቸው፣። ይህንንም ያደረገው ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈልጉና ምናልባትም ዳሰው እርሱ ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳዳንቸን የራቀ አይደለም። “ሕይወት የምናገኘውና የምንቀሳቀሰው የምንኖረውም በእፉሱ ነውና።”

ነገር ግን ይህ “ቅርብና እጅግ አስፈላጊ የሆነ የሰውና የእግዚአብሔር ትስስር” ሊረሳ፣ ቸል ሊባል፣ ወይም ጭራሹኑ በግልጽ በሰው ዘንድ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል፤ የዚህ ዓይነት አመለካከቶች የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሯቸው ይችላል፤ እነርሱም በዓለም ላይ ባለው ክፋት ላይ ማመጽ ሃይማኖታዊ ማይምነት ወይም ግዴለሽነት፣ የዚህ ዓለም ሃብትና ምቾት፣ ከምእመናን በኩል በመጥፎ ምስላሌነት የሚመጣ እንቅፋት፣ ሃይምኖትን የሚጻረሩ አስተሳሰቦች፣ በመጨረሻም እራሱን ከፍርሃት የተነሣ ከእግዚአብሔር እንዲደብቅ እና ጥሪውን እንዲሸሽ ከሚያደርግ የኃጢአተኛ ሰው አመለካከት የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ።   

“ጌታን የሚፈልጉ ልቦች ሐሴትን ያድርጉ።” ምንም እንኳን ሰው እግዚአብሔርን ሊረሳ ወይም ላይቀበለውም ቢመችልም እርሱ ግን፣ እያንዳንዱን ሰው እርሱን በመሻት ደስታን ሕይወትን ያገኝ ዘንድ መጣራቱን አያቋርጥም። ሆኖም ይህ እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ የሰውን ልጅ ከፍተኛ ጥረት ጽኑ ፍላጎት “ንፁህ ልብ” እና እግዚአብሕIርን ስለመፈለት የሚያስተምሩ የሌሎችን ምስክርነት ይጠይቃል።

ጌታ ሆይ አንተ ታላቅ ነህ ከፍ ከፍም ልትል ይገባሃል፣ ኃይልህን ታላቅ ጥበብህም ወሰን የለውም። የፍጥረትህ ትንሹ አካል ሰው ሊያስመሰግንህ ይሻል። በርግጥም ይህ ሰው ፈራሽ ነው። የኃጢያትን ምልክትና አንተ ትዕቢተኛውን የምታቃወም መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም የተሸከመ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ሰው ምንም እንኳ የፍጥረትህ ትንሹ አካል ቢሆንም ሊያመሰግንህ ይሻል። አንተው ራስህ በምስጋና ሐሴት እንዲያገኝ ታበረታታዋለህ። እኛን ለራስህ ሠርተኸናልና ልባች ባንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት የለውም።

2. እግዚአብሔርን የምናውቅባቸው መንገዶች

በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ እርሱን ለማወና ለመውደድ የተጠራ፣ እግዚአብሔርን የሚሻ ሰው እርሱን የሚያውቅባቸው አንዳንድ መንገዶችን ያገኛል። እኒህ መንገዶች የእግዚአብሔር ህላዌ ማረጋገጫዎች ተብለው ይጠራሉ፤ ይህም በተፈጥሮ ሳይንሶች እንደሚታወቀው አይነት ሳይሆን “በሚጣጣሙና በአሳማኝ ክርክሮች” ላይ ተመስርቶ ስለ እውነታው እርግጠኛ እንድንሆን የሚያስችለን ነው።

እነኝህ እግዚአብሒርን ከፍጥረት አንጻር የመመርመር “ዘዴዎች” ሁለት አቅጣጫዎች ኣሏቸው። ቁሳዊው ዓለምና ሰብአዊው ፍጡር።

ዓለም ከእንቅስቃሴ፣ ከመሆን ፣ ከአጋጣሚና ከዓለም ሥርዓትና ውበት በመነሣት ማንም ሰው እግዚአብሔር የዓለም መነሻና መድረሻ የመሆኑን ዕውቀት መጨበጥ ይችላል።

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አሕዛብ እንዳለው፤ ስለ እግዚአብሒር ማወቅ የሚቻለው ሁሉ ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኣሳይቷቸውዋልና። ዓለም ከተፈጠረ ጀመሮ የርሱ ስውር ባሕርይ፣ ማለትም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ በፍጥረታቱ ሁሉ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታያል።

ስለዚህ ቅዱስ አውግስጢኖስም ይህን መጠይቅ ያቀርባል፤ እስቲ የመሬትን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የባሕርን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ ራሱን በራሱ የሚያሠራጨውንና የሚሰበስበውን የአየር ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የሰማዩንም ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ እነዚን ሁሉ እውነቶች ተጠራጠሩ፣ ሁሉም “እኛ ውብ ነን” ይላሉ። ውብታቸውን ምስክርንተ ነው። እነዚህ ውበቶች ለለውጥ ተገዥዎች ናቸው። ለለውጥ ተገዢ ካልሆነው ከአንዱ ውብ አምላክ በቀር ማን ሊሠራቸው ይችላል?

ሰብአዊ ፍጡር። ለእውነትና ለውበት ካለው ግልጽነት፣ ለበጐ ምግባር ካለው ስሜት፣ ከነጻነቱና ከሕሊናው ድምፅ በሚመነጭ ለዘለላለማዊነትና ደስታን ለመላበስ ካለው ጉጉት የተነሣ ሰው ራሱን ስለ እግዚአብሔር ህልውና ይጠይቃል። በእነዚህ ሁሉ የራሱን ረቂቅ ነፍስ ምልክቶች ይረዳል። “ቁሳዊ ወደ ሆነው ብቻ የማይሸነሸነውና በውስጣችን ያለው የዘላለማዊት ዘር” ነፋስ ምንጩ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ዓለምና ሰው በውስጣቸው የመጀመሪያው ጥንስስም ሆነ መጨረሻ እንደሌላቸው፤ ነገር ግን መጀመርያና መጨረሻ በሌለው ራሱ በህላዌ እንደሚሳተፉ ይመሰክራሉ። ስለዚህ የፍጥረታት ሁሉ መጀመርያና መጨረሻ የሆነ ሰው ሁሉ “ ‘እግዚአብሔር’ ብሎ የሚጠራው” አንድ እውነት እንዳለ ሰብአዊ ፍጡር በብዙ መንገዶች መገንዘብ ይችላል።

የሰው ልጅ አእምሮ አካላዊ አምላክን ሊያሳውቀው የሚያስችል ብቃት አለው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመፍጠር እንዲችል እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ለመግለጥና ሰውም በእምነት እንዲቀበለው የሚያስችል ጸጋውን ለመስጠት ፈቀደ። የእግዚአብሔር ሕልውና ማረጋገጫዎች አንድን ሰው ከእምነት እንዲደርስና እምነት ከአመክንዮ ጋር እንደማይፃረር እንዲያይ ያግዙታል።

 

 

 

 

 

አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ጠቃሚ የሚሉት ጽሑፍ ካለዎ ኢሜይል ለመላክ አያመንቱ  contact@ethiocist.org