If our pages are illegible, please download fonts here: Visual Geez Unicode

 

 

በመንገድ ሲነግረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠል አልነበረምን? (ሉቃ. 24:32)

በዚህ ዓምድ በዕለታዊ ሕይወታችን ይበልጥ ክርስቶስን መምሰል እንድንችል ቅዱስ ቃሉን በመመርኮዝ መንገድን የሚጠቁሙ ሃሳቦች ይስተናገዳሉ። የ2001 ዓ.ም. ሁለተኛ አስተንትኖ ይሆን ዘንድም ይቅር ስለማለት የሚያሳስበውን የሚከተለውን ጽሑፍ ጋብዘንዎታል።

(በብሥራተ ገብርኤል)

የበደለኝን ይቅር ብዬ እንዳልፈው

የአፈጣጠራችንና የተክለ ሰውነታችን ጉዳይ ሆኖ እጆቻችንን ወደ ፈጣሪ አቤት ለማለት ስናነሣ እግረ መንገዱን ወደ ጎን ወደ ወንድሞቻችን መዘርጋቱ ግድ ነው። ጌታችን ያስተማረን ጸሎት የሚለውም “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደሚንል፤ በደላችንን ይቅር በለን” ነው። ጸሎቱንም “አባታችን” ሆይ ብለን በመጀመራችን እርስ በርሳችንን ወንድማቾችና እህትማማቾች ያደርገናል። ስለዚህ ምሕረቱን ከእርሱ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታው፤ እኛን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከበደሉን ጋር ሰላም መፍጠር ነው። በስብከተ ወንጌሉም ያስገነዘበን “ለራስ መባ ከማቅረብ በፊት ከባላጋራችን ጋር መታረቅ” እንዳለብን ነው። በዚህ ምክንያት መስዋዕተ ቅዳሴ ለፈጣሪያችንም ስናቀርብ ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ቅዱስ ሥጋውና ደሙ እንዲቀይረው ከመጸለያችን በፊት ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “በተቀደሰ አሳሳም እርስበርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ” ብሎ እንደመከረው እርስ በርስ ሰላምታ እየተሰጣጣን ይቅር መባባል ይጠበቅብናል። ጌታችን ስለ ስርየተ ኃጢአት ሲያስተምረን “ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት” እንዳለ እንገነዘባለን።

        ከዚህም በተጨማሪ አጋጣሚ በተገኘ ቁጥር ሁሉ ሌሎችን ይቅር ማለት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። አለበለዚያ ኢየሱስ የነገረን ምሳሌ ንጉሡ የባለሟሉን ዕዳ ሙሉ በሙሉ ሲሰርዝለት እርሱ በፈታው እዳ ያለበትን ባልንጀራውን በማስቃየቱ የደረሰበት በኛ ላይ ሊፈጸም እንደሚችል “እንግዲህ እያንዳችሁ ወንድማችሁን ይቅር ባትሉ በሰማይ ያለው አባቴም እንዲሁ ያደርግባችኋል” በማለት አስጠንቅቆናል።

        በዓለም ዙርያ አብረን ስንኖር ያለውን ውሱን የማቴርያል፣ የጊዜ፣ የጉልበት . . . ወዘተ ምጣኔ ሃብት በጋር እንቋደሳለንና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ገና ከኦሪት አንስቶ እግዚአብሔር ለራሱ የመረጠውን ሕዝብ የሚተዳደርበት ሕግ በሙሴ አማካይነት ሲደነግግ “በማንም ላይ ቂም አትያዝ፣ በእርሱ ምክንያት በደል እንዳትፈጽም ከእርሱ ጋር ያለህን አለመግባባት በስምምነት አስወግድ” ነው ያለው።

        ሁሉን ታግሰን ለማለፍ በሞከርን ቁጥር አጅሬ መፋቀራችንን አይወድምና በሰበብ አስባቡ እንድንናቆር ይፈታተነናል። በአንዴ ብቻ አያቆምም፤ በተደጋጋሚ። ኢየሱስ የቅዱስ ጴጥሮስን “ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ግዜ ልማረው?” ጥያቄ “ሰባ ጊዜ ሰባት” ብሎ በመመለሱ ትንሽም ትልቅም በደል በደረሰብን ቁጥር የቂም ማሕደራችን ከኮሮጆ ወጥተን እየመዘገብን በሒሳብ መደመርያ እንድናሰላው ሳይሆን በተቻለ አጋጣሚ ሁሉ ምሕረት እንድናደርግ ነው። “በሰይጣንን እንዳንታለልም፤ እርስ በርስ ይቅር መባባል እንዳለብን” ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል። ምክንያቱም በሩቅ በሰማይ ለሚኖረው እግዚአብሔር ያለንን ፍቅር መግለጽ የምንችለው በቅርባችን የሚገኙትን የእርሱ ፍጡራን በማፍቀር ብቻ ነው። ያለበለዚያማ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ያላየውን እግዚአብሔር እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው።”  በማለት ይወቅሰናል። የሙሴ ሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ ቀርቦ ከሁሉ የሚበልጠው የመጀመርያው ትእዛዝ የትኛው ነው ብሎ ሲጠይቀው ፈጣሪ አምላክህን መውደድ መውደድ መሆኑን ከመለሰለት በኋላ በማስከተል አይነጣጠልምና፤ ባልንጀራን መውደድ ያልተናነሰ ሁለተኛ ትእዛዝ መሆኑን ገልጾለታል።

        አንዳንድ ጊዜም በተለያዩ ነገሮች ህሊናችን እየሻከረ፣ ትንሿም ኣንከን ጎልታ እየታየችን፣ የተመኘነው ሳይሳካ ሲቀር ሌሎችን ለመወንጀል እንነሳለን። ለምሳኤ ያህል፤ የትምህርት ቤት ፈተና ውጤቱ ያማረ ከሆነ “A” አገኘሁ ስንል፤ ያልተሳካ ጊዜ ግን “F” ሰጠኝ ብለን ኃላፊነቱን ወደሌላው እናሸጋግራለን። አመልካች ጣታችንን በሌላ ሰው ላይ በቀሰርን ቁጥር ሌሎቹ ሦስት ጣቶች የሚያመለክቱት ወደኛው መሆኑን እናስተውል። አውራ ጣታችን ደግሞ ከላይ ሆኖ የሚያየን ሁሉ ፈራጅ ወደሆነው የሠራዊት ጌታ ነው።

        ይቅር መባባሉ ጠቀሜታው የጋርዮሽ ነው። ለተበዳይ በልቡ እያመረቀዘ ያለውን የጥላቻ መንፈስ ሲያሽቀነጥርለት ለበዳይ ደግሞ ሰላምን ይሰጣል። ዘወትር የሚፈሰውን የእግዚአብሔርን ፀጋ እንዲጠቀመበት ያስችለዋል። ጣራ ቀደው ያመጡለትን በሽተኛ ኢየሱስ እጅና እግሩ ካሰረው ደዌ ከማላቀቁ በፊት አምላኩን በመበደል ለሰራቸው ስህተቶች ይቅር አለው። ይህን በማድረጉም ይቅርታ ታላቅ የደኅንነታችን ሚስጥር እንደሆነ አስተማረን። ምክንያቱም ሙሉ አካል ኖሮት፤ ዘላለማዊ ሕይወትን ካላገኘ ፋይዳ አይኖረውም።

        ጥፋት የሠራ ሰው በጥፋቱ ተሸማቆ ሳለ የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ልንቀየመው ወይንም ልንቀበለው ብንነሳ በእርጥብ ቁስል እንጨት እንደመስደድ ይቆጠራል። ነገር ግን ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚያስተምረን “እኔ የምደግፈውና የመረጥኩት በእርሱም ደስ የሚለኝ አገልጋዬ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን እንኳን አይሰብርም።” እኛም ነገ አጥፍተን ምሕረትን ፈላጊ እንሆናለን ወይንም ከዚህ ቀደም ምሕረትን አግኝተናንልና ለመቀበል ከመነሳት በፊት “በሰፈርንበት ቁና መሰፈራችን” አይቀሬ መሆኑን በማሰብ “ሰዎች ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም እንዲሁ ማድረግ እንደሚኖርብን” ከአዳኛችን ትምህርት መረዳት ይኖርብናል።

        ይቅር ለመባባል ፈቃዱም ኖሮን ብዙ ጊዘ የሚቃጠለውና ይህንን ፀጋ ሳንጠቅመቨት የሚቀረው ማን እንዳጠፋ ስንመረመር፣ ያጠፋ ቀድሞ ይቅርታ ይጠይቅ ስንባባል  ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ግን በተደጋጋሜ የሚያስተምረን በጎ ለመስራት መሽቀዳደም እንዳለብን፤ “ክርስቶስ ይቅር እንዳለን ይቅር እንድንባባል” ነው። ክርስቲያንነታችንንም የምንመስከረው አስፈላጊ ከሆን ተበዳይ እኛ ሆነን ሳለን ይቅርታ ጠያቂዎችም ሆነን ስንገኝ ነው። በተራራው ስብከቱ ላይ “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አለው? ኃጢአተኞችስ ይህንን ያደረጉ የለምን?” ባንጻሩ ግን “የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ” ይለናል።

        ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ ለብሱ ገፈው ለባርነት ሸጠውት ነበር። ነገር ግን በሀገራቸው ድርቅ ገብቶ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እጁ ላይ በወደቁ ጊዜ ከመቀበል ይልቅ ያለምንም ክፍያ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እህል ሰጣቸው።

ንጉሥ ሳዖል ክፉ መንፈስ እየተጠናወተው ታማኝ አገልጋዩን ዳዊትን ብዙ ጊዜ ለመግደል ይነሣሣ ነበር። በተደጋጋሚ ጦር አዝምቶበታል። ነገር ግን ሳዖል በእጁ በገባ ጊዜ ዳዊት ጠላቱን ከማጥፋት ታቅቧል።

ትንሽም ትልቅም ክፉ ሥራ የሠሩብንን ሰዎች ይቅር ማለት ከባድ መስሎ ሊታየን ይችላል። ኢየሱስ ግን ከጥፋት የመጨረሻ ደረጃ ያዘውን ያለ ኃጢአቱ የስቅላት ሞት እየፈጸሙበት ያሉትን ሰዎች ምሕረት አድርጎላቸዋል። የእርሱን ፈለግ የተከተሉት እንደ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ የመሳሰሉትም ያደረጉት ይህንኑ ነው። በስሙ እስከተጠራን ድረስ ከእኛ የሚጠበቀውም ከዚህ ያላነሰ ነው።

እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን ከሆነ፤ ባንጠቃ የተሻለ ቢሆንም አጥቂ መሆኑ አይመረጥም። የአንጾኪያው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ሐሳብ ሲያብራራ “በብዙ ሺህ ተኩላዎች የተከበብን በጎች ብንሆንም እረኛችን ኢየሱስ ያድነናል፤ ነገር ግን እኛ ራሳችን ተኩላ ከሆንን የሚደርስልን የለም” ይለናል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን “መበቀል የእግዚአብሔር ፋንታ ነው፤ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” ይለናል፤ የሰላም ንጉሥ ኢየሱስ በልባችን ነግሦ የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለማችን እንዲስፋፋ ያቅማችንን እንጣር።

የበደለኝ ይቅር ብዬ እንዳልፈው፤ ቂመኛ ልቤን ጌታ ሆይ ለውጠው!

 

 

 

ወዮልኝ ለእኔ ሥጋውን ለምቦጫጭቀው!

(በብሥራተ ገብርኤል)

መሥዋዕተ ቅዳሴ በሚደረግበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑ ድምጽ ማጉያ መሣሪያ ትንሿንም ኩሽታ ሳትቀር አጋኖ የሚያሰማ በመሆኑ ተባርኮ ወደ ጌታችን ሥጋ የተለወጠውን ኅብስት ቀዳሹ ካህን እየጸለየ ሲቆራርሰው በጆሮዬ አስተጋባ። ገባሬ ሠናዩ ካህን ቅዱስ ቁርባንን ለተጠሩት ሊያዳርስ ነው። እኔ ግን በክፋትና በእኩይነት ዕለት ዕለት የጌታዬን ሥጋ እየቆራረስኩት፣ እየቦጫጨቅኩት እንደሆነ ተረዳኹ። <<ከታናናሾቹ ለአንዱ ያላደረግኸው ለኔ እንዳላደረግኸው እቆጥረዋለሁ>> (ማቴ. 25:42-43) ሲለኝ ተሰማኝ። <<ምንድር ነው ጌታዬ ላንተ ያላደረግኹት? ሰንበትን አከብራለሁ፣ ጾምንም አልገደፍኩ፣ አሥራትም የአንድ ወር ብቻ ነው የዘገየብኝ>> ብለው <<መጾም መጸለይ ባልከፋ ነገር ግን መብአ ከማቅረብህ በፊት ከባልንጀራህ ጋር ታረቅ>>(ማቴ.5:24) አለኝ።

በትላንትናው ዕለት ቢሮ ውስጥ ስብሰባ ሲካሄድ በተፈጠረው ያለመግባባት ብዙ ኃይለ ቃል እንደተሰነዛዘርን ትዝ አለኝ።

በነቢዪ ሳሙኤል አፍ ለንጉሥ ሳዖል <<መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል>> (1ሳሙ.15:22) ያለው ለኔም ጭምር ይሆን ብዬ ራሴን ጠየቅኹ። እስቲ የዕለት ተዕለት ሕይወትህን መርምረው አለኝ። ዲያቆኑ ቃጭሉን ሲያቃጭል በጆሮዬ የሚደውለው <<ከታናናሾቹ ለአንዱ ያላደረግኸው…>> የሚለው መልእክት ነው።

መቼለታ ምሳዬን በሚገባ በልቼ ማኪያቶ ለመጠጣት ኬክ ቤት ጎራ ብል የዕድሌ ነገር ሆኖ ኬኩም ያደረ ነው መሰል አልጣፈጠምና ቀምሼ ተውኩት። ወተቱም ጎርንቷልና አልጠጣሁትም። ከፈልኩና ወደ መኪናዬ ሳቀና <<ስለ ኢየሱስ ርቦኛል፣ ተመጽወተኝ>> እያለ አንዱ ወተወተኝ። እኔ የታየኝ ግን የእሱ መራብ ሳይሆን በአዳፋ ቡቱቶው መኪናዬን እየታከከ ማቆሸሹ ነው። ከኦሪት ጊዜ አንሥቶ የተነገረውን <<አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ ልብህን አታጽና፤ በድኻው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ፤ ነገር ግን እጅህን ለርሱ ክፈት>> (ዘዳግ.15:7) የሚለውን ባስተውል ኖሮ እኔ ወተት እየደፋሁ ወገን ሲራብ ንቄው ባላለፍኹ።

የቁምስናችን ንግሥ በዓል የተከበረለታ ያ ሁሉ ምግብ ሲትረፈረፍ በር ላይ ተኮልኩለው ለነበሩት የኔ ቢጤዎች ያለመታደሉ የጠቢቡ ሰሎሞንን <<ድኻን ወግድ አትበለው፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው>> (ምሳሌ 22:22) የሚለውን ምክር ያለመቀበሌ ዘገነነኝ።

ወዮልኝ ለኔ ሥጋውን ለምቦጫጭቀው!

የዛሬ ወር ገደማ መኪናዬ የተበላሸች ጊዜ በጠዋት አሮጌ ሸሚዝ ቀደድኩና ጫማዬን ጠራርጌ ከቤት ስወጣ ከደጅ ያደረው የኔ ቢጤ <<በርዶኛል፤ እራፊ ጨርቅ ካለህ ጣልብኝ>> ሲለን ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ ገሰገስኩ። ዲያቆኑ ግን ማቃጨሉን አላቆመም፤ አሁንም ይደውላል <<ታርዤ አይታችሁኝ….>>። አውራ ጎዳናው ላይ ስወጣ አንዲት የሞላች ውይይት ታክሲ <<አንድ ሰው የቀረው>> እያለች አጠገባችን ስትቆም ከእኔ ቀድሞ ታክሲ ቦታ የደረሰውን እግረ በሽተኛ ሰውዬ አንከስ አንከስ ሲል በፍጥነት ቀድሜው ዘው ብዬ ስገባ እንኳን <<ጌታዬ ታምሞ ልጠይቀው>> ቀርቶ ርኅራኄ እንደነገፍኩ የተረዳሁት አሁን ነው።

የበሽተኛ ነገርስ ከተነሣ ባለፈው ሰሞን ከቤት በአልጋ የዋለችው አያቴ ዛሬ ለሕሙማን ልዩ ቅዳሴ አለ ተብሏልና ወደ ቢሮ ስትሄድ እግረ መንገድህን በተስኪያን ጥለኸኝ እለፍ ብትለኝ፤ ብርቱ ስብሰባ ስላለብኝ አንቺ እስክትዘጋጂ ከጠበቅኹኝ ይርፍድብኛል ብዬ ዓይኗ ዕንባ እንዳዘለ ትቻት መሄዴ እንደ ርኅሩኁ ዋምራዊ (ሉቃ.10:33-35) የሚያስፈልጋትን ሁሉ ማድረጉ ቀርቶብኝ አምስት ደቂቃ እንኳን ያለመስጠቴን ዲያቆኑ ኅሊናዬ ላይ እየደወለ አስገነዘበኝ።

ያለፈው ቅዳሜ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ስንጨዋወት ገርበብ ባለው በር አንገቱን ስግግ አድርጎ <<የሩቅ መንገደኛ ነኝ ውሃ አጠጡኝ>> ሲል ይሄኔ አጋጣሜ የሚጠብቅ ሌባ ነው ብለን የዘጋንበት፤ ሳምራዊቷን ውሃ አጠጪኝ ያላት ኢየሱስን ተመስሎ ተምልሶ መምጣቱ ዘግይቶ ነው የገባኝ። <<ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም>>…

ቀዳሹ ካህን ኅብስቱን እየቆራረሰ ጸሎቱን ማሳረጉን ቀጠለ። በጆሮዬ ድምጽ ማጉያው የሚያስተጋባው ግን አሁንም <<ታስሬ አልጠየቃችሁኝም>> የሚለውን የፍርድ ቃሉን ነው። እውነት ነው። የቁምስናችን ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው የቅዱስ ጳውሎስ የሕግ ታራሚዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት ጥሪ ከዲያቆኑ ቃጭል ጋር አብሮ ሲያቃጭልብኝ፤ ወገኔ በየወኅኒ ቤቱ ስብእናውን እስኪስት ድረስ መንገላታቱ ለኔ ደንታ ያለመስጠቱ ኮሰኮሰኝ።

በስንቱ ነገር ነው ሥጋውን የቦጫጨቅኩት! ይስሐቅ ራሱ የሚሰዋበትን እንጨት እንደተሸከመ (ዘፍጥ.22:6) ሁሉ ለካስ ኢየሱስም በጀርባው የተሸከመው የኔኑ ኃጢአት ኖሯል! እናቱም በመስቀሉ ሥር ቆማ ያነባችው (ዮሐ.19:25) እንባ ስምዖን ልብሽ በኀዘን ሰይፍ ይወጋል ያላት (ሉቃ.2:35) በኔው ሳቢያ ሆኗል። ኢየሱስ ልጁን ያዳነለት የመቶ አለቃ <<ወደኔ ቤት ትገባ ዘንድ እኔ የተገባሁ አይደለሁም>> (ማቴ.8:8) ያለው ለኔ መሆኑ ገባኝ።

ወዮልኝ ለኔ ሥጋውን ለምቦጫጭቀው!

የዲያቆኑ ደወል፣ በእናታቸው ደረት ተደግፈው የሚያለቅሱት ልጆች ጩኸት፣ የመዘምራኑ የፍርድ ቀን መዝሙር፣ ከቤተ ክርስቲያኑ ውጪ የሚሰማው ጫጫታ፣ በውስጤ የታመቀው የጸጸት ድምጽ… አንድ ላይ ተደማምሮ ናላዬን አዞረው።

ካህኑ በመስቀል ምልክት ጽዋውን እየነቀነቀ <<ይህ ከሰማይ የወረደ ለብዙዎች ቤዛ የሚፈስ ደም ነው>> (ማር. 14:24 ) ሲል <<ከጥፋት ጉድጓድ፣ ከረግረግም ጭቃ እንደሚያወጣኝ>> (መዝ.40:2 )ተረዳኹ። <<አቤቱ እንደ ቸርነትህ ብዛት ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ>>(መዝ.51:1 )።

 

ዲያቆኑ <<በንስሐ ላይ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ>> ሲል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካይነት <<ኃጢአተኛ ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ እንዲሞት አልፈቅድም>> (ሕዝ.33:11)ማለቱን አስታወሰኝ። ዳዊት <<በደሌን እናገራለሁ፤ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ>> (መዝ.38:18 ) ያለውን እያሰላሰልኹ ወደ መንበረ ኑዛዜው አመራኹ።

በርግጥ እሩ ክኔ የሚፈልገው <<የተሰበረና የተዋረደ ልብ>> (መዝ.51:17) ብቻ ነውና ኃጢአትን መናዘዝ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፤ ቅዱስ አውጎስጢኖስ አምላካችን መሐሪና ታግሽ መሆኑ እንዳሻኝ ኃጢአትን ለመሥራት ነጻ ቲኬት (ሊቼንሳ) እንደማይሰጠኝ ያስተማረኝን ራሱ ጌታዬ <<ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኃጢአት አትሥራ>> (ዮሐ.5:14) ያለኝን በጽሞና አስተዋልኹ።

ነቢዩ ሚክያስም ያለኝ ይህንኑ ነው፤ <<መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔር ካንተ የሚሻው ምንድን ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትን ትወድ ዘንድ፣ ከአምላክህ ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?>> (ሚካ.6:6) ዳግም እንዳልወድቅ ቁርጥ ፈቃድ አደረግኹ።

እንደ ኃጢአቴ ብዛት ሳይሆን ፍቅር አስገድዶት (ዮሐ.3:16) እጁን ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ዘርጋና አንገቱን ዘንበል አድርጎ መሢሁ ለኔ ሞተልኝ። በሞቱም <<ያዕቆብ በሕልሙ ያያት ከምድር ወደ ሰማይ የምትደርስ የመዳኛዬ መሰላል>> (ዘፍ.28:12) ተዘረጋችልኝ።….

መጻኢ ሕይወቴን በክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃን ተስፋ ለመጓዝ ጭላንጭሉ በሩቁ ታየኝ።

 

 

 

 

 

 

 

      

ለአእምሮህ ጠባቂ አኑርለት

ወንጌለ ማቴዎስ 24:36-ፍጻሜው

የዛሬው ወንጌል በጌታ መምጣት ጊዜ ስላለው ሁኔታ በማስረዳት በዚያን ወቅት በዕለታዊ ሕይወታችን የምንሠራውን በማድረግ ላይ ሳለን ፍጻሜ እንደሚሆን ያስረዳናል። በዚያ ወሳኝ ሰዓት ምንም ማድረግ እንደማንችልም ይነግረናል። በሌላ አባባል ቅዱስ ጳውሎስ በዛሬው መልእክቱ <<ጥቂት የዘራ ጥቂት መከር ይሰበስባል፤ ብዙ የዘራ ብዙ መከር ይሰበስባል።>>  እንደሚለው ነው። ስለዚህ በዕድሜያችን ሁሉ  አእምሯችንንና ልባችን ውስጥ በየወቅቱ የሚዘራውን ለእግዚአብሔር ቃል ጊዜ በመስጠት በአኗኗራችን መተግበር ይኖርብናል።

     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ምሳሌዎች ስለቃሉና ስለ እኛ ባሕሪይ ሲናገር አእምሯችን በተለያየ ኃይሎች ተወጥሮ የእግዚአብሔር ቃልን ለማስተናገድ አቅም እንደሚሳነው ያስረዳናል። ሆኖም ግን ለእግዚአብሔር ቃል እንደተመቻቸ ማሳ በመሆን ለፍሬ የሚያበቃ ዓይነት አእምሮና ልቦና እንዳለም አልሸሸገንም። እንዲሁም ሁላችንም ሰው ነን አእምሯችንም ደካማ ነው ብለን በሰለቸና ተስፋ በቆረጠ አስተሳሰብ ሌሎችን መስለን እንዳንመላለስ የሚያግዘን የእግዚአብሔር ቃል <<በአእምሯችሁ መለወጥ ታደሱ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ>> ይለናል(ሮሜ 12:2)።

    አእምሯችን እንዳይታደስ የሚያደርጉንን ምክንያቶች ብናስብ ተንትነን መዝለቅ ያዳግተን ይሆናል፤ በርግጠኝነት ግን አእምሯችንን ከእግዚእብሔር ቃል በማራቅ በተስፋ ቁርጠትና ጨለማ ውስጥ ሆኖ ርካታን በማጣት እንዲመላለስ የሚያደርገው  መልኩን በመለዋወጥ የሚታገለን ብቸኛ ጠላታችን ሰይጣን  ነው። ቃሉም <<በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና>> በማለት ይመሰክርልናል። የዲያብሎስ ዋነኛ ተቃውሞ ስለ እግዚአብሔር መኖር ወይም ደግሞ ኑሯችን እንዴት እንደሚሻሻል እንዳናስብ ለማድረግ ሳይሆን፤ ተቃውሞው የሚበረታብን ስለራሳችን ምንነት፣ ከየት እንደመጣንና ወዴት እንደምንሄድ ማሰብና ማስተንተን ስንጀምር ነው። ምክንያቱም ማንነታችንን ማወቅ ስንጀምር በላዩ ላይ ሥልጣን እንዳለን ማወቅ ስለምንጀምር ማለት ነው። ይህ እውቀት ከአእምሯችን ተሰውሮ እንድንኖር ይፈልጋል። በተቃራኒው ደግሞ ይህን እንድናውቅ ማለትም ራሳችንንና ያለንን ሥልጣን ለማወቅና የአእምሮ መታደስን ማግኘት የሚያስችለን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።

     ምንም ዓይነት እውቀቶችን ብናከማች በቃለ እግዚአብሔር ላይ ካልተመሠረት በስተቀር ራሳችንን ማወቅ አንችልም። ስለዚህ በዓለማችን የእግዚአብሔርን ቃል ከሕይወታቸው ያወጡ ሰዎች ምንም ያህል እንኳ ምሁራን ወይም ሀብታም ቢሆኑም የኅሊና ዕረፍትን አጥተው በመባዘን ይኖራሉ፤ ሕይወታቸውን እስከማጥፋትም ይደርሳሉ። መልካምን የሚያስብ የነፃ አእምሮ ሊኖረን የሚችለው ቃሉን አንብበን በማስተንተን መኖር ስንጀምር ነው።

     በዓለም አስተዳደር በኩል የሚደረገውን ካስተዋልን፤ ብዙ ጊዜ የነበረን መንግሥት ሽሮ አዲስ ዘመነ ሥልጣን ላይ የሚወጣ መንግሥት አዲሱ ሥርዓት መስመር እንዲይዝለት በማለት በየአንዳንዱ ቦታ ካድሬዎቹን በመላክ ሕዝቡን እንዲያነቃቁት ያደርጋል። ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ንቃተ ኅሊና... በማለት ሕዝቡ የቀድሞ ሥርዓትን በመተው አዲሱን ሥርዓት እንዲከተሉለት ይጥራል። ታዲያ የዓለም መንግሥት ንቃተ ኅሊና ካስፈለገው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስማ ምን ያህል ንቃተ ኅሊና ባስፈለገን! በዚህ ምክንያት ነው የእግዚአብሔር ቃል አሮጌ አስተሳሰባችንን አስወግደን አእምሯችንን እንድናድስ የሚጋብዘን።

     በዚህ ዘመነ ክረምት ሊጡርጊያችን (ሥርዓተ አምልኳችን) ንባባት መሠረት እግዚአብሔር ቃሉን በእርሻ ሲመስል በምስባኩም ዳዊት <<ምድርም በትሰጣት በረከት ትሞላለች...>> እንደሚለው ቃሉ ዘወትር በዓለም አስተሳሰብና ወግ የታፈነው አእምሯችንን ችላ እንዳንለው ይጠራናል። በዘፈቀደ ሳይሆን እንደቃሉ ፈቃድ እንድንመላለስ መወሰን እንዳለብንም አስተውሉ ይለናል። ዘወትር የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ሲዘራ በጨለማና በጥርጣሬ የተሸፈነ ባለቤት የሌለው ማሳ(እርሻ) ይመስል ይህ ኃያል ዘር እንዳይባክን ለአእምሯችን ጠባቂ እናበጅለት። ከቃሉ ጋር በተባበርን ቁጥር የአእምሯችን ባለቤት እሱ ራሱ እግዚአብሔር ይሆናልና በውስጣችን ያለንን ትልቅ ሀብት ማለትም አእምሯችንን አጥር የለሽ ማሳ አድርገን ዘሩንና ፍሬውን ለጠላት አሳልፈን አንስጥ።

    ቅዱስ ጳውሎስ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ አእምሮ ይኖረኝ ዘንድ ተጋሁ እንዳለ ሁሉ እኛም ለዚህ የምንተጋበትንና ለአምላካችን ንጹሕ አምልኮ እንድናሳርግ ራሱ እግዚአብሔር ያግዘን አሜን።

አባ መስፍን ጸጋይ ሲታዊ 

 

አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ጠቃሚ የሚሉት ጽሑፍ ካለዎ ኢሜይል ለመላክ አያመንቱ  contact@ethiocist.org