If our pages are illegible, please download fonts here: Visual Geez Unicode

 

 

የምንኩስና ሕይወ
1.  ምንኩስና
2.  የሰው ተፈጥሮና የምንኩስና ሕይወት
3.  ቡድሃዊ ምንኩስና
4.  ምንኩስና በሂንዱዊዝም
5.  ጄይኒዝም
6.  እስልምና እና ምንኩስና
7.  ሸማኒዝም - ቅድመ ታሪክ ምንኩስና?
8.  ምንኩስና እና የአይሁድ ማኅበረሰብ
9.  ክርስቲያናዊ ምነና
10. 

ክርስቲያናዊ ምንኩስና

11.

ቅዱስ አንጦንዮስ

ምንኩስና

መሠረታዊ የምንኩስና ሕይወት ሀሳብን በበለጠ ለመረዳት የቃሉን አመጣጥ አስቀድሞ ማየቱ ጠቃሚ ነው። በሃገራችን መነኩሴ ብለን የምንጠቀምበት ቃል <<ሞኖስ>> ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ብቻ፣ብቸኛ ማለት ነው። እንዲሁም ምንኩስና <<ሞናኮስ>> ከሚለው ተመሳሳይ የግሪክ ቃል የተገኘ ሆኖ ትርጉሙም ለብቻው የሚኖር ማለት ነው።

        ብቻ፣ ብቸኛ ከሚለው ቃላዊ ትርጉም ስንነሣ ምንኩስና ሰው ከሌሎች ነገሮች ራሱን ገለል አድርጎ ከአምላኩ ጋር ሙሉ ኅብረት ለመፍጠር የሚኖረው የሕይወት ዘይቤ ማለትን ያሰማል። በቋንቋ አጠቃቀማችን የምንኩስናን ሕይወት በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገልጹ ሌሎች ቃላት ምነና እና ብህትውና ናቸው። እነዚህም ቃላት  የሚገልፁት እውነታ ሰው ቁሳዊና አላፊ ነገሮችን መንኖ ወይም ንቆ ከነርሱ በላይ ለሆነ ዓላማ ራሱን የሚሰጥበት ሁኔታ ነው። የምንኩስና ሕይወትና አጀማመርን ስናስተውለው መሠረታዊ ዓላማው ለብቻ የመሆን፣ የመናቅና የመሸሽ ግብ ብቻ ሳይሆን በነዚህ መመሪያነት ከእግዚአብሔ ጋር አንድነትን መፍጠር ብሎም ከእግዚአብሔር ፍጡራን ጋር ሰላማዊ ትስስር ላይ መድረስ ነው። ይህም እውነታ በጥንታዊ የክርስቲያን ምንኩስና ሕይወት ውስጥ የመጀመርያው ታሪካዊ ጽሑፍ ተብሎ የሚታመነው የቅ. አትናትዮስ አገላለፅ ውስጥ ይገኛል። እሱንም ቅ. አውጎስጢኖስ <<አንዳንድ ብቸኝነቶች ከሌሎች ጋር አንድ ያደርገናል>> በማለት ይገልጸዋል። ስለዚህም የምንኩስና ብቸኝነት ከሌሎች የሚያርቅ ሳይሆን ይበልጥ የሚያስተስር ነው፤ መነኩሴም ብቸኛ የመሆኑ ዓላማ ከሁሉም ጋር አንድ ለመሆን በማለት ነው። ጥንታውያን መንኮስት የምንኩስናን ሕይወት ሲጀምሩ ከነበረው ጊዜያዊ ዓለም በመራቅ ወደ ምድረ በዳ፣ በርሃ ወይም ጫካ ውስጥ መሄዳቸው የእግዚአብሔር ፍጥረት የሆነችውን ዓለም በመጥላት ሳይሆን ይበልጥ በእግዚአብሔር ዓይን ስላይዋት ስለርስዋ ለመጸለይ እንዲመቻቸው ነው።

 የሰው ተፈጥሮና የምንኩስና ሕይወት

         የሰው ልጅ ሰው መሆኑን ማወቅ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ራሱንም ሆነ በዙሪያው ያሉ ነገሮችን ተፈጥሮ ለማወቅ ጥረትን ያደርጋል። ይህ ጥረት በውስጡ ለሚነሡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስን ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን እያበዙበት ይሄዳሉ። ስለዚህም ቶሎ የሚረዳው ነገር ቢኖር ቁሳዊ ነገሮችም ሆኑ የራሱ ማንነት የሕይወት ጥያቄዎችን ለመመለስ አቅመ ቢስ መሆናቸውን ነው። አንዳንዴም ሰው የሕይወት ጥያቄው በሥጋዊ ምኞት፣ በእውቀት፣ በሃብት ወይም በሥልጣን እና በመስል ነገሮቻቸው መልስን የሚያገኝ መስሎት በእድሜው ይዳክራል፤ ማንነቱንም ያባክናል። ተስፋ አድርጎ መልስ ይሆኑኛል ብሎ የሚጓጓላቸው ነገሮች ጋር ሲደርስ ይበልጥ ባዶ ፍጡር መሆኑን ሲነግሩት፤ ሰው ርካታንና የማንነቱን ሙላት ጠለቅ ባለ ዓላማ ውስጥ እንደሚገኝ ያየዋል። ስለዚህ በዘመናት ሂደት ወይም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሰው ሕይወቱን ይሞላልኛል ብሎ ላመነበት ዓላማ ማንነቱን መስጠቱ የተለመደ ክስተት ነው። ምክንያቱም የሰው ሕይወት ቁምነገሩ ኖሮ ማለፉ ብቻ ሳይሆን በዓላማ መኖሩ ነው። ስለዚህ ከዚህ ሰዋዊ ዝንባሌ አንጻር ስናየው ሰው ብቻውን ገለል ብሎ በሆነ ዓላማ ለመኖር መወሰኑ የምንኩስና ሕይወት በተወሰነ መልኩ ተፈጥሮአችን ውስጥ አለ ለማለት ያስደፍራል።

        ሰው በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ በተለያየ ስምና ከብዙኃኑ ሕዝብ ተለይተው በአንድ ግብ የሚጓዙ የማኅበረሰብ ክፎሎች ነበሩ። በትዳር መተሳሰርን ትተው፡ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በመራቅ ከሃብትና ንብረት ይልቅ ለአንድ ዓላማ የሚኖሩ ጥንታውያን ግሪካውያን፡ ሮማውያን . . . ነበሩ። አንዳንዶቹ በሚያጠኑት የእውቀት ዘርፍ ፍጹም የሆነ እውቀትን /ጥበብን/ ለመገብየት፣ በያዙት ሙያ ጫፍ ላይ ለመድረስ /በስፖርት፣ በፖለቲካ/ ለብቻቸው የሚኖሩ ነበሩ። በፕሌቶ /አፍላጦን/ <<ሪፐብሊክ>> በሚለው መጽሐፉ እንደተገለጸው ለፍትሐዊና ሰላማዊ የሕዝብ አስተዳደር ራሳቸውን ከብዙኃኑ ለይተው - ወላጆቻቸውን እንዳያውቁ ተደርገው፣ ለ30 ዓመታት ያህል ልዩ ትምህርት እየተሰጣቸው፣ የግል ንብረት ሳይዙ በጋራ በመኖር ሙሉ ሕይወታቸውን ለፖለትካዊ ፍልስፍና የሚሰጡ ወንዶችና ሴቶች እንደነበሩ እናነባለን። እንዲሁም ከማኅበራዊ ሕይወትና ራስን በማግለል ሁሉን ነገር በመመነን ውስጣቸው ያገኙትን እውነት /እውቀት/ ሙሉ ለማድረግ የሚጥሩ ፈላስፎች እንደነበሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክ.ዘ. መጀመርያ ላይ የነበረው ዲዮጋን የሚባል ግሪካዊ ፈላስፋ ምሳሌያዊ ነው። ዲዮጋን ሙሉ ምርምር ለማካሄድና በነጻነት ጥልቅ ሃሳቦችን ለማሰላሰል ያግዘው ዘንድ በማሰብ ውሃ ከሚጠጣባት ጣሳ በስተቀር ሁሉን ነገር መነነ። ይጓዝ የነበረውም ባዶ እግሩን ሲሆን ቀንም ሌሊትም የሚለብሳት አንዲት ካባ ነገር ብቻ ነበረችው። ዲዮጋን ፈላስፋው በዚህ ሁኔታ ሳለ አንድ ቀን አንድ ሕፃን ልጅ በአንድ የወንዝ ዳርቻ ሆኖ በእጁ ውሃ እየጨለፈ ሲጠጣ አየው። ይህንንም ሁኔታ ፈላስፋው በማስተዋል <<ይሄ ልጅ አዲስ ጥበብ አስተማረኝ>> በማለት ለመጠጫነት ይጠቀምባት የነበረችውንም ጣሳ እንደተዋት ይነገራል።

        ይህንን እና መሰል ቅድመ ክርስትና ታሪኮችን ስናስተውል ገለል ብሎ ተፈጥሯዊ ስሜቶችን በመቆጣጠር ከነርሱ ባርነት ነፃ በመሆን የሆነ ዓላማን የመከተል ሕይወት በክርስቲያናዊ ምንኩስና ያልተጀመረና ሁሉን አቀፍ መሆኑን ያስረዳናል። በዚህም ምክንያት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላም የተነሡ ሃይማኖቶች ዓላማቸውና መልካቸው ቢለያይም የየራሳቸው የምንኩስና ሕይወት አላቸው። ስለዚህም የክርስቲያናዊ ምንኩስናን ልዩ ተፈጥሮ ለማየት እንችል ዘንድ አስቀድመን የሌሎች ዐበይት እምነታት ምንኩስናዊ ገጽታ በጣም አጠር አጠር ባለ መልኩ እንመልከት።

 ቡድሃዊ ምንኩስና

         ወንዶችና ሴቶች መነኮስንን የሚያቅፈው የቡድሂዝም ምንኩስና ሕይወት የተመሠረተው ከክ.ል. በፊት ከ 500 ዓመታት አስቀድሞ ጋውታማ ቡድሃ ማለትም የቡድሂዝም መሥራች በሕይወት በነበረበት ዘመን ነው። ይህ ምንኩስና ሲጀመር ምነናዊና ብሕትውናዊ ገጽታዎች ነበሩት። በጣም ጥቂት ነገሮች ካልሆነ በስተቀርም ንብረት አይዙም። ያልመነኮሱ አማኞች ለነዚህ መነኮሳን ዕለታዊ ምግባቸውንና አስፈላጊም ከሆነ መጠለያ ያዘጋጁላቸው ነበር።

        ከቡድሃ ሞት በኋላ ይህን የምንኩስና አኗኗር ከብሕትውና ወደ ማኅበራዊ ምንኩስና ተለውጦ መነኮሳን በኅብረት መኖር ጀመሩ። ለዚህም እንዲያግዛቸው የተለያዩ ደንቦችን አዘጋጁ። የቡድሂዝም መነኮሳን በመጀመርያ ደረጃ የቡድሂዝምን እምነት መመሪያና ሥርዓት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ከሌሎች አማኞች የሚለያቸው በመሆኑ ጋብቻ አይፈጽሙም። በሕይወታቸውም ለሌሎች ዓለማውያን አብነታዊ መሆን አለባቸው። በዚህም ምክንያት ለየት ያለ የአስተንትኖና ግብረገባዊ አኗኗር ይጠበቅባቸዋል፤ ምንም እንኳ ቢለያይም መነኮሳን በቀን አንድ ጊዜ የምግብ ሰዓት አላቸው። የተቀሩት አማኞች በበኩላቸው መነኮሳኑ ለነርሱ የምሕረት መመርያ እንደሆኑ ስለሚያምኑ አስፈላጊውን ነገር ለኑሮዋቸው ያሟሉላቸው ነበር።

 ምንኩስና በሂንዱዊዝም

        እንደ ቡድሂዝም ከክ.ል.በፊት ከ2500 ዓመታት ጀምሮ የተዘወተረው የሂዱዊዝም ምንኩስናዊ ሕይወት ለጥንታዊውም ምንኩሳንዊ ሕይወት ዐቢይ ምስክር ነው። በዚህ ምንኩስና ወንዶችም ሴቶችም በየጎራቸው የመንፈሳዊ ሕይወት ጫፍ ላይ መድረስ በሚል ዓላም ይመነኩሱ ነበር። የአምላካቸውን ነገር ለማስተንተን ዓለምን ከመከተል ተቆጥበው ራስን በማያወሳስብ የአኗኗር ሁኔታ ነገሮችን በመመነን ያለ ጋብቻ ይኖሩ ነበር። ይህም አኗኗራቸው ራስ ወዳድ ወይ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚፈልጉ ያለመሆናቸውን ያሳይ ስለነበር፡ በኅብረተሰባቸው ዘንድ ይከበሩ ነበር። አንዳንድ መነኮሳን የአምላካቸውን አዘጋጀነት፣ አሳቢነት ተማምነው ምንም ሳይዙ /ያለንብረት/ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ ነበር። ሕዝቡም ለመነኮሳኑ ምግብናና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ ታላቅ ተግባር እንደሆነ ይቆጠር ነበር። እነዚህ መነኮሳን ለምስጋና ሆነ ለመዋረድ እንስዲሁም ለተድላም ሆነ ለስቃይ ግድ የለሽ ሆነው ይኖሩ ነበር። የተለየ ዓይነትም የፀጉር አቆራረጥ ነበራቸው።

        እነዚህ መነኮሳን ከተወሰኑ ነገሮች ለመቆጠብ /ለመራቅ/ መሐላ ያደርጉ ነበር። መሐላቸው ከሚያካትታቸው ነገሮችም ውስጥ ለመጠጫ ከሚያገለግል ኩባያ፣ ከሁለት ልብሶችና የሕክምና መገልገያ በስተቀር ምንም የግል ንብረት እንዳይዙ፤ ተቃራኒ ጾታን ከመመልከት፣ ከማሰብና በአንድ ቦታ አብሮ ከመገኘት መከልከል፣ ምግብን ለደስታ ምንጭ አድርጎ ያለመመገብ፣ በማንኛውም ሁኔታና ቅርጽ የገንዘብ ወይም ውድ የሆኑ ነገሮች ባለቤት ያለመሆን ብሎም ያለመንካት የመሳሰሉት ይገኙበታል።

 ጄይኒዝም

         በጄይኒዝም ሁለት ዓይነት የምንኩስና ቅርንጫፎች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ዲጋምባራ የሚባል ሲሆን ምንም ልብስ የማይለብሱ ናቸው። ሆኖም ግን ራሳቸውን እርቃናቸውን እንደሆኑ አድርገው አያስቡም። ምክንያቱም አካባቢን/ ተፈጥሮን ለብሰናል ይላሉ። ይህንንም በማድረጋቸው ሰውነታቸውን ከድሎትና ምቾት እንዲሁም ከግል ንብረት እንደታደጉት ያምናሉ። ሁለተኞቹ ዓይነት መነኮሳን ሽቬታምባራስ ሲባሉ፡ ባለመልበስ እንደመጀመርያዎቹ አያምኑም። ብዙ ጊዜም ፊታቸው ላይ ጭምብል መሰል ነገር በማጥለቅ ይሸፈናሉ። ይህም ወደ ውስጥ ሲተነፍሱ ጥቃቅን ነፍሳትን በድንገት እንዳይገድሉ በማሰብ ነው።

 እስልምና እና ምንኩስና

         በመሠረቱ ሙስሊሞች በምንኩስና ሕይወት አያምኑም። ለዚህም በቁራን አላህ የምንኩስናን ሕይወት እንደ ሰው ሠራሽ ልማድ ስለገለጸው ነው ይላሉ። /ሱራ 52፡27/ ሆኖም <ሱፊ> ወይም <ጣሪቃ> የሚባሉ የእስልምና ክፍሎች በሌላ እምነቶች ምንኩስናዊ የሚባሉትን የሚመስሉ ተመሳሳይ አኗኗሮችን ያበረታታሉ። ከነዚህም ውስጥ <<ዴርቪሽ>> የሚባልት በድህነት ለመኖር መሃላ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ በምነና እና በልመና ሲኖሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ተራ የሆነ ሥራን በመመረጥ ይተዳደራሉ፤ ቤተሰብ ያላቸው ሲሆኑ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት መኖር ይጠበቅባቸዋል። ይህ <ጣሪቃ> የሚባለው ምንኩስናዊ መሰል የሆነ እስላማዊ የአኗኗር ዘይቤ በ8ኛው ክ.ዘ. የተጀመረ ሲሆን በ13ኛው ክ.ዘ. በጣም ያበበት ጊዜ ነበር። በዘመናችንም በሰሜን አፍሪካ፡ በመካከለኛው እስያ፣ በቱርክ፣ በዓረቢያና በፓኪስታን በመስፋፋት ላይ ነው።

 ሸማኒዝም - ቅድመ ታሪክ ምንኩስና?

        በዓለም ታሪክ ከሚታወቁ ዓበይት ሃይማኖቶች በተሟላ መልኩ ሃይማኖት ተብለው ሊጠሩ ከሚችሉት ጥንታዊና ቀዳማዊ የሚባለው ሂንዱዊዝም ነው። በምንኩስና ሕይወት ታሪክም ጥንታዊ የምንኩስና ሕይወት የሂንዱዊዝም ምንኩስና እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል። ነገር ግን የተዋቀረና መልክ ያለው ሃይማኖት ከመኖሩ በፊት ለሂንዱዊዝምም ሆነ ለሌሎች ጥንታውያን ሃይማኖቶች ምንኩስና መሠረት የሚሆን አንደርዳሪ እውነታ ነበረ ወይ ብለን ብንጠይቅ በቅርብ የተደረጉ ጠለቅ ያሉ የታሪክ ዳሰሳዎች - አዎን ይሉናል።

        ሸማኒዝም ይባላል ይህ ቢያንስ 10,000 ዓመታት ከክ.ል.በፊት እድሜ ያለው መንፈሳዊ ልምምድ። ይህ በሰ ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ ቅድመ ታሪክ ተብሎ በሚጠራበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለተወሰነ የቤተሰብ ሐረግ የተሰጠ ልዩ ጥሪ ተብሎ የሚታሰብ ነው። ይህ ጥሪ የነበረው ሰው ለተለየ አገልግሎት ከሕዝቡ የተለየ ይሆናል - በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አባባል በዓለም ይሆናል ግን የዓለም አይደለም። ሸማን - ማለትም የዚህ ጥሪ ባለቤት የሆነ ሰው - በህዝቡና በፈጣሪያቸው መካከል የመለኮታዊ ኃይል ክፍል ሆኖ የሚያገናኝ ሲሆን - ከካህናት ግን የተለይ ሚና ነበረ። አብዛኛውን ጊዜ ሸማን ለሕዝቡ የፈውስን ሚና ይጫወት ነበር።

        አብዛኞቹ ሸማኖች ከማንኛውም ዓይነት ሥራ ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን የሆነ ሙያ መሥራት ካለባቸውም ሕዝባቸው የተስማማበትና ያጸደቀው መሆን ነበረበት። በርግጥ ሸማኒዝም ማኅበራዊ ሕይወት እንደነበረው በግልፅ ታሪካዊ መረጃ ባይኖርም አኗኗራቸው ግን ማኅበራዊ ትስስር እንዳለው ግልፅ ነው። በዚህም በሰው ልጅ ውስጥ ላለው መንፈሳዊ ጥማት መልስ ለመሆን በሕዝባቸው መካከል ለሕዝባቸው ተለይተው መኖር ነበር።

ምንኩስና እና የአይሁድ ማኅበረሰብ

      በአይሁዳዊ ታሪክ ውስጥ የምንኩስና ሕይወት ይዘወተር እንደነበር አስረጂ የሚሆን ጽሑፍ የለንም። ነገር ግን እንደፍንጭ የሚጠቆመው የናዝራውያን ሕይወት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን መሰል የምንኩስና ሕይወት የነበራቸው አሴናውያን፣ ቴራፐውት እና የቁምራን ማኅበረሰብ የሚባሉ ነበሩ።

      ከአይሁዳውያን ወገን አሴናውያን የሚባሉ በአዲስ ኪዳን እንዴት ሳይጠቀሱ እንደቀሩ የሚገርም ነው። ምክንያቱም የነበሩበት ጊዜ ከ2ኛ ክ.ዘ. ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 2ኛው ክ.ዘ. ከክርስቶስ በኋላ ነው። ይኖሩ የነበሩትትም በፖለስቲና (በሙት ባሕር አካባቢ) በሶሪያ ሲሆን ቁጥራቸው እስከ አራት ሺህ ይደርስ ነበር ይባላል። አሴናውያን ተጋድሎን በበለጠ የሚያዘወትሩ በውንድማማነት የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። በብዙ ወገኖችም የተለያዩ /የተከፋፈሉ/ ነበሩ። አንዳንዶቹ ደጋጎች አንዳንዶቹ ዝምተኞች የድሮ ቅዱሳን ወይም ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ንጹሐን አዕምሮ አንዳንዶቹ ደናግል ሌሎች መጠነኞች ወይም ትክክለኖች የሚባሉ ነበሩ።

      የእነዚህ የተለያዩ የአሴናውያንወገኖች ዋናና መሠረታዊ መምሪያቸው እግዚአብሔርን ማፍቀር፣ በጎ መንፈሳዊ ኃይላትን ማፍቀርና የሰው ልጆችን ማፍቀር የሚል ነበር። ንብረታቸው /ገንዘብ፣ ሃብት/ የጋራ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም ለእናይዳንዱ ይሰጥ ነበር። ቅዳሜንም በጥብቅ የሚያከብሩ፣ ጽዳትን በሚመለከት ጉዳይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ፣ በቀዝቃዛ ውሃ የሚታጠቡ፣ ነጭ ልብስ የሚለብሱ፣ የማይምሉ፣ ከማኅበሩ ውጭ የማይበሉ፣ የእንስሳን መሥዋዕት የማይቀበሉ፣ መሣርያ /ሰው ማጥቂያ/ የማይታጠቁና የማይነገዱ ሰዎች ነበሩ።

      የማኅበሩ አባሎች የሚሆኑት በሕፃንነት እድሜያቸው ወይም ትልልቆች ሆነው የዓለምን ነገር ሲመንኑ ነበር። አንድ ሰው የማኅበሩ አባል ከመሆኑ በፊት ለ3 ዓመት ተመክሮ ያደርጋል። ከዚህ በኋላ መሐላ ያደርጋል። መሐላውም ታዛዥ እንዲሆንና ምሥጢርንም እንዲጠብቅ ያስገድደዋል። መሐላውንም ካፈረሰ ከማኅበሩ ይባረራል። በማኅበር ደረጃ ሰውን መሸጥ ወይም ባርነትን ለመቃወም አሴናውያን የመጀመርያዎቹ ናቸው። ባሮች የነበሩትን በገንዘብ እየገዙ ነጻ ያደርጓቸው ነበር። አሴናውያን የሚሠሩት ሥራ እርሻና የእጅ ሥራ ነበር።

      ከአሴናውያን ወገን የሆኑት ቴራፐውት የሚባሉት በግብፅ በእስክንድርያ ይኖሩ እንደነበር ፊሎ የተባለ ጥንታዊ አይሁዳዊ ጸሐፊ ያስረዳል። እንደ ፊሎ አጻጻፍ በአሴናውያንና በቴራፐውት ልዩነት ነበር፤ ቴራፐውት የሳምንቱን ቀኖች በተናጥል በአስተንትኖ ያሳልፉት ነበር። ቅዳሜ ግን ባንድነት ተሰብስበው ይጸልያሉ፣ ይመገባሉ፤ እንዲሁም ፍልስፍናዊ ውይይት በማድረግ ቀኑን ይዘጉት ነበር።

      አሴናውያን ምንም እንኳ ከአይሁድነት /ከአሁዳውያን/ የሚያገናኛቸው ብዙ ነገሮች ቢኖራቸውም ከምሥራቅ ሃይማኖቶችም የወሰዷቸው ነገሮችም ነበሩ። ለምሳሌ ፀሐይን እንደ መለኮታዊ ነፀብራቅ ይቆጥሯት ስለነበር ጧት ስትወጣ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አቅንተው ጸሎት ያደርጉ ነበር።

      የአሴናውያን መቋረጥ ወይም መጥፋት እንዴት እንደሆነ ምክንያቱ አልታወቀም። አንዳንዶቹ እንደሚሉት ግን በመጨረሻ ብዙዎች ወደ አይሁዳዊነት ወይም ወደ ክርስትና ገብተዋል ነው።

      ምንም እንኳ በአዲስ ኪዳን ባይጠቀሱና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእርሱ ባይነገርም፤ ክካህናት ወገን ስለነበሩ <የሳዶቅ ልጆች> ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ሳዶቅ በሰሎሞን ጊዜ የነበረ ሊቀ ካህን ነው።

      መጥምቁ ዮሐንስ ከካህናት ወገን እንደነበር የታወቀ ነው። ሉቃስ 1፤15 መጥምቁ ዮሐንስ ያሳለፈው ሕይወትና ይኖርበት የነበረ በረሃ ከአሴናውይና ኑሮ ሕይወት ጋር የሚመሳሰል ነው። በረሃውም የሙት ባሕር አካባቢ ነው። አሴናውያን ይኽንን ቦታ የመረጡበት <በምድረ በዳ የጌታን አንገድ አዘጋጅ> የሚለውን የኢሳይያስ ቃል እንዲፈፀም ነው 40፤3። በዚህም ምክንያት መጥምቁ ዮሐንስ ከአሴናውያን ወገን ነበር ወይም ደግሞ ከነርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው ለማለት ይችላል። ለዚሁ ማስረጃ ቅዱስ ሉቃስ <ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ ለእስራኤልም እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ> 1፤80 ያለው ነው። ሕፃኑ የት እንዳደገ ወንጌሉ ግልፅ ባያደርግም በምድረ በዳ ነው - አንድ ሕፃን በምድረ በዳ በጽሞናና በብቸንነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። አሴናውያን ሕፃናትን፣ ትንንሽ ልጆችን ይቀበሉና ያሳድጉ ስለነበር ያደገው ከእነርሱ ጋር ነው ሊባል ይቻላል።

      አሴናውያን በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በበለጠም በወንጌል ያልተጠቀሱበት ምክንያት አንዳንዶቹ እንደሚሉት ከሆነ ምናልባት የወንጌልን ትምህርትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላልተቃወሙ ሊሆን ይችላል። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የጌታን ትምህርት ይቃወሙ ስለነበሩ በወንጌል ብዙ ግዜ ተጠቅሰው ይገኛሉ። አንዳንዶቹም እንደሚሉት አሴናውያን ከኅብረተሰቡ የተለዩና የተነጠሉ ስለነበሩ ኅብረተሰቡ እስከዚህም ግምት አልተሰጣቸውም ይሆናል፤ ከሕግ እንደወጡ ቆጥረው ንቀዋቸው ከግምት ሳያስገቧቸው ቀርቶ ይሆናል የሚል አስተሳሰብም አለ።

      ከአይሁዳውያንና ከቅዱስ መጽሐፍ ግንኙነት ያልነበራቸው እንደክርስትያን መነኮሳን ይኖሩ የነበሩ የግሪክ ፈልስፋ የፓይታጎረስ /580-500 ከ.ል.በፊት/ ተማሪዎች ወይም ተከታዮች እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይቻላል። ፓይታጎረስ ምንም እንኳ የሒሳብ ሊቅና ፈላስፋ ቢሆንም የሃይማኖት መሪና ግብረገብን ብዙ ያስተማረ፤ ማኅበርንም /በአንድነት መኖርን/ የመሠረተ ነበር። በደቡባዊ ኢጣልያ በፓይታጎረስ ስም የሚጠራ ትምህርት ቤት ነበር። እነዚህ የፓይታጎረስ ደቀመዝሙሮች ወይም ተማሪዎች የተመክሮ ዓመት ነበራቸው፣ ንብረታቸውም የጋራ ነበር። የነፍስ ወህኒ ቤት ነው ብለው ከሚያስቡት ከሥጋ ወጥመድ /ማሰሪያ/ ነስፍን ነፃ ለማውጣትና ለማላቀቅ ብዙ ተጋድሎ ያደርጉ ነበር። ጥበብን ለማግኘት እንዲሁ ጠንካራ ተጋድሎን ያደርጉ ነበር። 

ክርስቲያናዊ ምነና

 

 
 

አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ጠቃሚ የሚሉት ጽሑፍ ካለዎ ኢሜይል ለመላክ አያመንቱ  contact@ethiocist.org