If our pages are illegible, please download fonts here: Visual Geez Unicode

 

 

ዜና ዕረፍት

 

ሢመተ-ክህነት በደብረ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን ካቶሊክ ቤ/ያን አዲስ አበባ

     መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና ከተለያዩ ቁምስናዎችና ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ብዙ ምእመናን ደናግላንና ካህናት በተገኙበት ሦስት ዲያቆናት ማለትም ዲ. ዮሓንስ (ደገለ) ፍራንሶ፣ ዲ. ገ/እግዚአብሔር (መኰንን) ዘውዴ፣ ዲ. ብርሃነትንሣኤ (ተስፋዬ) ኬኔ ሢመተ-ክህነት እንዲሁም ወንድም (ገ/ሰንበት (ደርቤ) ሰሙ) ሢመተ-ዲቁና በብፁዕ አባታችን አቡነ ብርሃነ-ኢየሱስ ደ.ሱራፌል እጅ ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕ አባታችን በበዓሉ ለይ እነዚህን መነኮሳን ኮትኩተው ላሳደጉ ቤተሰቦቻቸው፣ለመምህራን፣ ለገዳመ ሲታውያን አባቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ እንደዚሁም ለአዲሶቹ ካህናትና ዲያቆኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተጣለባቸውን የአገልግሎት ኃላፊነት ለሰው ልጆች ደኅንነትና ለእግዚአብሔር ክብር በታማኝነትና በጽናት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ በሢመት ቅዳሴው ላይ የነበረው ሥርዓት የሕዝበ-እግዚአብሔር መንፈሳዊ ስሜትን የሚያነቃቃ ነበር፡፡

 

አባ ዮሐንስ (ደገለ) ፍራንሶ ታኅሣሥ 28 ቀን 1965 ዓ.ም በደቡብ ሸዋ በሃዲያ ዞን በሸለላ ተወለዱ፡፡ ምስጢረ ጥምቀትን፣ሜሮንንና ቅዱስ ቁርባንን የተቀበሉት በሸለላ ቅድስት ማርያም ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩትም በሸለላ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ በዋቸሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ ለክህነት በነበራቸው ጽኑዕ ፍላጎት የተነሳ ከቅድመ ተመካሪነት እስከ ክህነት (ከ1988-1999 ዓ.ም) በገዳመ ሲታውያን ማኅበር የሚጠበቅባቸውን ሥልጠናና ትምህርት ካጠናቀቁ በኃላ መስከረም 11-2001 ዓ.ም ሢመተ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

 

 

 

አባ ገ/እግዚ/ር (መኰንን) ዘውዴ ሰኔ 26 ቀን 1967 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ አደረ ብለት በሚባል ቀበሌ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና ትምህርት የተከታተሉት ደጎማ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ እስከ አስራሁለተኛ ክፍል የተማሩት ደግሞ በገዳመ ሲታውያን በመንዲዳና በአዲስ አበባ ነበር፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ከ1990-1992 ዓ.ም በቅድመ ተመክሮና በተመክሮ ካሳለፉ በኋላ ለሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ የፍልስፍናና የንባበ መለኮት ትምህርት በቅዱስ ፍራንቺስኮስ የፍልስፍናና የንባበ-መለኮት ተቋም አጠናቅቀው መስከረም 11-2001 ዓ.ም ሢመተ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

 

 

 

አባ ብርሃነትንሣኤ (ተስፋዬ) ኬኔ በሰሜን ሸዋ በዋዩ ሙጢ ቀበሌ በ1968 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት እዚያው በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩት ደግሞ በመንዲዳ ገዳመ-ሲታውያን ት/ቤት በአዳር ተማሪነት ነውነበር፡፡ ቀጥሎም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ በአዲስ አበባ በገዳመ ሲታውያን ሆነው በካቶሊክ ሴሚናሪ ት/ቤት ነበር፡፡ በ1990 ዓ.ም ለአንድ ዓመት በመንዲዳ የተመክሮ ሕይወት ካሳለፉ በኋላ ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ለሢመተ-ክህነት የሚያበቀ የፍልስፍናና የንባበ መለኮት ትምህርትና ሥልጠና አጠናቅቀው መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም በብፁዕ አባታችን አቡነ ብርሃነ-ኢየሱስ እጅ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

 

 

ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን!!!

 

 

---------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ዜና ዕረፍት

የሲታውያን ገዳም መነኩሴ የሆኑት ክቡር አባ ተኽለዝጊ ዑቑባጊዮርጊስ ነሐሴ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. በዕለተ ሰንበት በደረሰባቸው ከባድ የመኪና አደጋ በ60 ዓመት ዕድሜያቸው ነፍሳቸው እንዳለፈች ማወቅ ተችሏል።

ክቡር አባ ተኽለዝጊ በተወለዱበት በኤርትራና በኋላም በኢትዮጵያ የተለያዩ ገዳሞቻችን ሲያገልግሉ የቆዩ ሲሆን ይህ ድንገተኛ አደጋም እስኪደርስባቸው ድረስ በአሜሪካ ኒው ጄርሲ በሚገኘው የሲታውያን ገዳም በማገልገል ላይ ነበሩ።

በዕለቱ የምስጢረ ተክሊል ቃልኪዳን አስደርገው ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ አደጋው እንደተከሰተና የተጋጩት መኪና ውስጥ ከነበሩትም የአንደኛው ነፍስ ስታልፍ ሁለተኛዋ ቀድመው ከመኪናዋ በመውጣታቸው መትረፋቸውና አሽከርካሪውም በከባድ ሁኔታ እንደተጎዱ ታውቋል።

አስክሬናቸው ወደ አሥመራ የተላከ ሲሆን መስከረም 13 2001 ዓ.ም. በደብረ ፍልሰታ ዘገዳመ ሲታውያን ቤተ ክርስቲያን እጅግ ብዙ ሰው የተሳተፈበት ጸሎተ ፍትኀትና መሥዋዕተ ቅዳሴ ከተደረገ በኋላ አሥመራ በሚገኘው መካነ መቃብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተከናውኗል።

ባጠቃላይ በአደጋው ለሞቱት ነፍስ ይማር፣ ለተጎዱትም ቀላሉን ያድርግላቸው እያልን አባም ሕይወታቸውን ለአምላካቸው በመስጠት ለእግዚአብሔር ቃል መስፋት በዕድሜያቸው የሮጡለት ጌታ በምሕረቱ ነፍሳቸውን በመንግሥቱ ይቀበልልን። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለማኅበራቸው መነኮሳን፣ በእምነት እህትና ወንድሞቻቸው ለሆኑት ሁሉና ለወዳጆቻቸው እግዚአብሔር የመጽናናትን መንፈስ እንዲሞላቸው እንመኛለን፣ እንጸልያለንም። ....

ተጨማሪ ለማንበብ ይህን ይጎብኙት http://mountlaurelmonks.blogspot.com/2008/09/death-notice-father-teclezghi.html

www.elilta.org

 

አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ጠቃሚ የሚሉት ጽሑፍ ካለዎ ኢሜይል ለመላክ አያመንቱ  contact@ethiocist.org