ወደ እልፍኝህ ግባ - ወደ ልብህ ግባ
የዛሬው ወንጌል ስለጸሎት የሚለን ነገር አለው። እንደውም መጀመሪያ ላይ “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና” ሲል እንዳንጸልይ ሰበብ የሚያዘጋጅልን ይመስላል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስቦ መጸለዩ፣ በየመንገዱ ማማተቡና መስገዱን ትርጉም የለሽ እያደረግን ከጸሎት ለማፈግፈግ ይዳዳን ይሆናል። ነገር ግን ክርስቶስ በሕዝብ ፊት መጸለይን በራሱ አላወገዘም፤ የተቃወመው የምንጸልይበት ሀሳብን ነው:- “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” የሚጸልዩበት ዓላማ በሰው ይታዩ ዘንድ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘትን አላሰቡም ስለዚህም ይህ ዓይነቱ ጸሎት ዋጋ እንደሌለው ነው ወንጌሉ የሚያስተምረን። በማቴ. 11:25 እና በዮሐ. 11:45 ላይ እንደምናገኘው ክርስቶስ ራሱ በሕዝብ ፊት ጸልይዋል። እንዲሁም ጳውሎስ በሐዋ. ሥራ 27:35 ላይ እንደምናነበው በሕዝብ ፊት ጸሎት አድርጓል።
የሚቀጥለው የወንጌል ጥቅስ ይበልጥ የላይኛውን ሀሳብ ያብራራልናል:- “አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” የጸሎታችን ግብ ወደ አባታችን መጸለይ ነው፤ ለእይታ፤ ለቃላት ድርደራ… ችሎታ ሳይሆን ናፋቂ አባት እንዳለው የሚያምን ልጅና አባቱን እንደሚናፍቅ ልጅ ሆነን ማንነታችንን በፊቱ እንድናደርግ ነው። ስለዚህም ክርስቶስ ያስተመረን ትልቁ የመጀመሪያ ነጥብ “ወደ እልፍኝህ ግባ” የሚለው ነው፤ ያም ወደ ልብህ ግባ፤ ውስጥህን ስማ፤ ከውስጥህ በሸሸህ ቁጥር ከእግዚአብሔር ትሸሻለህና ወደ እልፍኝህ ግባ ይለናል። ልባችን ውስጥ የተከማቸው የሚያስጠላ፣ ጥሩ ስሜት የማይፈጥርልን ወይም ደስ የማይል ነገር ይሆናል፤ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ያንን ማንነታችንን ይፈልገዋል። ምክንያቱም እሱ ካልሆነ ሌላ ማንም ሊያሳምርልን የሚችል የለምና ልባችንን ደብቀን በውጫዊ ነገር ብቻ ልናገኘው አንችልም። ባለመጸለያችን ከርሱ የሸሸን መስሎን ወደ ሌላ ነገሮች በሄድን ቁጥር ውስጣችን እጥፍ ሸክም ይሆንብናል። ብንደብቀውም እንኳ እሱ ያውቀዋል ግን የደበቅነው መስሎን ራሳችንን እናታልላለን እንጂ መፍትሔው እንካ ደካማነቴን ማለት ነው። ዳዊት ይህን እውነት በተረዳ ጊዜ እንዲህ አለ:-
“ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?
ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ።
እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥
በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።” መዝ. 139:7-10
ጸሎት ከተውኩ ስንት ዓመቴ፣ አሁን ሌላ ዓለም ላይ ነው ያለሁት ምናልባት ወደፊት እድሜየም ገፋ ሲል ወደ ጸሎት እመለሳለሁ… የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ግን ከራስና ከእግዚአብሔር የመሸሽ ሕይወት ነውና ጎዶሎነትን ያለማምደናል። በዛሬው ወንጌሉ ክርስቶስ ያን ዓይነት ኑሮ አይመኝልንም። ወደ ልብህ ግባ በዚያም አባትህን አናግር። የሚያስብላቸው አምላክ እንደሌላቸው ሰዎች አትባክን። በጣም ቅርብህ የሆነ አባት አለህ ይለናል።
አንድ ካህን ላለመጸለይ ያሉንን ምክንያቶች እንዲህ ጽፍውታል:-
ቀጣይ የሆነ የጸሎት ሕይወት መጓዝ አዳጋች ነው። አንዳንድ ምክንያቶች ግልጽ ናቸው:- የሥራ ብዛት፣ ድካም፣ ዘወትር የሃሳብ መበታተን (ቀጣይ ራስን መሰብሰብ ያለመቻል)፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ስንፍና (ሀኬት)፣ የሚያሰለቸን ዓይነት ሥርዓተ አምልኮ፣ ምንም ትርጉም የማይሰጡን ዓይነትና የማይስቡ ጸሎት አደራረጎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ሌላ የምክንያት ዓይነትም አለ። ይህም ስለ ጽሎት ያለን ግንዛቤ ሲሆን ጸሎት ደስ የሚል፣ የሚስብ፣ የሚያነቃቃ መሆን አለበት ብለን እናስባለን። ሆኖም ግን ሁል ጊዜ ይህን ዓይነት ጸሎት ማድረግአይቻልም።
ለመጸለይ ውስጣዊ ተነሳሽነትና ፍላጎት አይኖረንም፤ ጸሎት ግን ይህን ሁሉ ተፈጥሯችንን ያከብራል። ጸሎት ቅልል ሲለን፣ ሀሳብችንና ልባችን ወደ እግዚአብሔር ሲያቀና ብቻ፣ ከመሰላቸት፣ ከቁጣ፣ መጥፎ ከምንላቸው ስሜቶቻችን ነጻ ስንሆን የሚጸለይ ቢሆን ምን ያህል ቀናት ብቻ መጸለይ ይቻል ነበር ብለን ማሰብ አለብን። እንዲህማ ከሆነ እግዚአብሔር እኛ ጥሩ ስንሆን ብቻ ሊያየን የሚፈልግ አባት አደረግነው ማለት ነው።
በእውነት በሕይወታችን ውስጥ የሚካሄደውን መሸፈን ፈልገን መሆን የሚገባውን ብቻ መጸለይ እንዳለብን እናስባለን። ጸሎት እሱ መስማት ያለበትን ለመንገር ዝግጁነት ስናደርገው መጸለይ ይከብደናል።
ስለዚህ ስለ ጸሎት ያለንን ግንዛቤ እንመርምር፤ እግዚአብሔር የሚጠብቀን፣ የሚሳሳልን፣ የሚናፍቀን አባት ነው እንጂ በዚህ ገባህ በዚህ ወጣህ ብሎ ሊያስጨንቀን የፈጠረን አምላክ እይደለም። እሱ አስቀድሞ እጅግ ስላፈቀረን እንድናፈቅረውና እንድንቀርበው ይጠብቀናል። ሸሽተን ከማንደበቀው አምላካችን ለየቀኑ ስጦታው በጸሎትና በመሥዋዕት ይልቁንም ከጸሎቶች ሁሉ ጸሎት በሆነው በልጁ መሥዋዕት ማለትም በቅዳሴ እንቅረበው፤ በልባችን ውስጥ ትንሽም ቢሆን ቦታ እንስጠው።
ዘጽጌ 5- ጥቅምት 30
የዕለቱን ንባባትና ምስባክ ከላይ ማውጫ ውስጥ በቀኑ ይመልከቱ።
ለራሳቸው ድጋፍ በሚያሻቸው ነገሮች አንደገፍ!
የዛሬው ወንጌል የመጀመሪያ ቁጥር <<ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? >> በማለት ይጀምራል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ይህን ሃሳብ ዝም ብሎ ማለፍ የሚከብድ ሃሳብ ነውና ቀላል መልስ ማግኘቱ ቢከብድም ክርስቶስ ለዚያ ዘመን ሰዎች ይህን ሲል ምን ማለት ፈልጎ ይሆን? ለኛስ ዛሬ ምን ይለናል? ማለት ይኖርብናል።
ወንጌሉ ከቁጥር 26 በፊት ባሉት ቁጥሮችም ቢሆን ስለ ሀብትና ገንዘብ፤ ስለጊዜያዊ ነገሮችና መያዝ ስላለባቸው ትክክለኛ ቦታ ይናገራል። ክርስቶስ ለሚያዝና ለሚጭበጥ ነገር ቅድሚያ በሚሰጥ ማኅበረሰብ መካከል ሆኖ ነበር ስለነዚህ ነገሮች አትጨነቁ ይል የነበረው። ይበልጥ ስለ ሕይወት አስቡ - እሱ ይበልጣል ይል ነበር። ይህን መሰል ትምህርቱ ለብዙዎቹ የሚመች ነገር አልነበረም፤ ስለዚህም በሱና በአድማጮቹ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠላትነት እያደገ መሄዱ ሊገባን ይችላል።የሁል ጊዜ መልእክቱ በእግዚአብሔር መደገፋችንን እንዳንተውና ለራሳቸው ድጋፍ በሚያሻቸው ሰዎች ወይም ነገሮች ላይ እንዳንደገፍ ለማሳሰብ ነው።
በዛሬው ዓለም ውስጥ ለምንኖር ለእኛም ይህ ወንጌል ይበልጥ ትርጉም ይሰጠናል። እግዚአብሔር አይረሳም አይንቅምም። በእሱ ፊት ችላ የሚባል ፍጥረት አንዳችም የለም።በሰው ዓይንና ግንዛቤ ግን በሆነ መስፈርት የምንንቀው እንደውም መኖሩንም የምንረሳው ሰው ስላለ እግዚአብሔርም እንዲሁ የሚያደርገን እየመሰለን እንፈራለን። ለርሱ ግን የዱር አበባና የሰማይ ወፎች እንኳ የተረሱ አይደሉም።
ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ልጅ ሕይወት ስትሟገት በጣም በቂ ምክንያት አላት። አንድ ሰው በየትኛውም የዕድገት ደረጃ ቢሆን ችላ ሊባል አይገባም፤ መናገር ቢችል ባይችል፣ ራሱን መከላከል ቢችል ባይችል፣ እኛ ልንረሳው ብንፈልግ ባንፈልግ…ወዘተ በእግዚአብሔር ፊት እንኳን ሰው የዱር አበባና አዕዋፍ ሁሉ ብርቅ ናቸው። ይህን መሰል እውነት ውስጣችን ካደገ ዓለም ብዙ ነገር እያሳየች ስትነሳን ወይም ሳታስጨብጠን ዞር ስትልብልን የእግዚአብሔር አሳቢነትና አዘጋጅነት ለኛ ደስታ ይሆናል።
ከሌላ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስናየው ደግም ዛሬ ዛሬ እኛም ራሳችን እየተራብን እንደውም ሩቅ ሳንሄድ በቅርብ በሀገራችን ሰው በምግብ እጥረትና እጦት ሲታመምና ሲሞት እያየን፣ እየሰማን እንዴት ስለ ምግብ ያለመጨነቅ ይቻላል? ምናልባት በዚህ ሁኔታ ሳለን ወንጌሉ <<በምትበሉትና በምትጠጡት አትጨነቁ…>> ሲል <<አታሹፍ>> የሚል እምርታዊ ምላሽ በውስጣችን ሊያጭርብን ይችላል።
እኛ በልተንና ጠጥተን ብናድር እንኳ ወገናችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ስለምናውቅ ያለመጨነቅ እንዴት ይቻለናል? ብለን መጠየቅ ጥሩ ነው። ለዚህ መልስ መስጠቱ ከባድ ቢሆንም ወንጌሉ ግን በማሰብና በመጨነቅ መካከል ልዩነት መኖሩን ያሳየናል። ይህን ልዩነት ማጉላት መቻል አለብን። <<አታስቡ>> አልተባልንም፤ አትጨነቁ ግን ተብለናል። ጭንቀት የሀሳብና የወኔ ልምሻን ስለሚያስከትል መሥራትን ይከለክለናል፤ ካልሠራን ደግሞ ለውጥ አይከተልም። ማሰብ ግን ሰዋዊ ነውና ማሰብ ትእዛዝ ሳይሆን ግዴታችንም ነው። ማሰብ ወደ ድርጊት ያንደረድረናል። መሥራትና አዲስ ነገርን ማግኘት ደግሞ ለውጥን ያስከትላል። ስለዚህ በችግሮች ፊት ጭንቀት ወደ ማሰብ ካልመራን ቀጣይ ሆኖ ማንነታችንን ይቀጨዋልና አትጨነቁ ተብለናል። ይበልጥ ደግሞ በእግዚአብሔር ያለን መታመንን መጋረድ የለበትም። ቁጭ ብላችሁ ከሰማይ መና ጠብቁ የሚል ወንጌል የለንም። ይልቁንም ከሰማያዊው አባታችን ጋር ዓለምን በመለወጥ እንተባበር ዘንድ ተጠርተናል።
ለሰው መሠረታዊ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ዓለም አልጎደሏትም፤ የጎደላት ግን ይህን የእግዚአብሔር ስጦታ በመልካም የሚያስተዳድርና የሚያካፍል ነውና በጎ አሳቢ ብቻ ሳይሆን በጎ አድራጊ ሰው ለመሆን ተጋብዘናል።ለዚህ ስኬት ወይም ጥፋት ሁላችንም አስተዋፅኦ አለን። ስለችግሮቻችን መጨነቅ ሳይሆን ማሰብ-በእግዚአብሔር መታመን-ማድረግ።
<<ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?>> ማንም የሚል የጋራ ምላሽ ይኖረን ይሆናል። ታዲያ ለምን ትጨነቃላችሁ ብንባል ግን የተለያየ መልስ ነው የሚኖረን። <<ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?>> እንበልጣለን ...ይሆን ይሆናል መልሳችን ግን እንጨነቃለን።መልሳችን በተጋጨ ቁጥር አናኗራችንም ከእምነታችን ጋር ይጋጫል።
የእምነት ሕይወታችን ያብብ ዘንድ እነዚህን በጣም በተስፋና በእምነት የሚሞሉ ጥቅሶች ሌላ ማንም ሳይሆን የተናገረው ክርስቶስ ነውና በልባችን ውስጥ እናስገባው። <<እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?>>።
ዘጽጌ 4- ጥቅምት 23
ያለ ሰንበተ ክርስቲያን (እሑድ) መኖር አንችልም!
በ304 ዓ.ም. አካባቢ በአቢቴኔ (አሁን ቱኒዚያ) ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ሰንበተ ክርስቲያንን ማክበር የተከለከለ መሆኑን እያወቁ ሲያከሩ ተከሰው ለፍርድ በቀረቡ ጊዜ የመለሱት መልስ ነው። “ያለ ሰንበተ ክርስቲያን መኖር አንችልም”።
ከላይ ያልነውን አባባል ለመመለስ ምክንያታቸው ምን ነበር ካልን መጀመርያ ይህች ቀን የክርስቶስ ስጦታ ነት። እርሱ ለራሱ እንድንሰጠው የሰጠን ቀን ናትና ለሌላ ሌላ ነገር ማዋል አያስቡም ነበር። ክርስቲያኖች ሰንበትን የሚቆጥሩት በልዩ ሁኔታ ከሙታን ከተነሣው ኢየሱስ አንድነታቸውን ጋር የሚገልጹበት ቀን አድርገው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሳምንቱን ሲዘጋጁና ሲያስቡበት ሰንብተው እሑድ ሲደርስ ከጌታ ጋር በማዕዱ የሚገናኙበት ዕለት ስለነበረም ነው። ስለዚህ ለነዚህ ክርስቲያኖች ሰንበትን ማክበር እንደ ሕግ ወይም ቀናትን የማክበር ግዴታ ሳይሆ አንድ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገርና የማንነታቸው መገለጫ ነው። ያለ እሱ ሕይወት ባዶ ናትና ቢከሰሱም በመልሳቸው አያፍሩም ነበር፤ “ያለ ሰንበተ ክርስቲያን መኖር አንችልም”።
ወደ ዛሬው ንባብ ስንመለስ ፈሪሳውያን ከሰው በላይ ሕግን ሲያከብሩ ኢየሱስ ደግሞ ሰንበት ለሰው ልጅ ነው የተሠራው ካላቸው በኋላ በሰንበት ቀን መጥፎ ነገር እንጂ ጥሩ ነገር ማድረግ የተከለከለ እንዳልሆነ ሲያስረዳቸው “ከእናንተ መካከል በሰንበት ቀን በጉ ጉድጓድ ውስጥ ብትገባበት የማያወጣት ማን አለ?” ብሎ በመጠየቅ ከእንስሳ በላይ በአምላክ አርአያና አምሳል የተፈጠረው ሰው ልዩ ክብር እንደሚያስፈልገው ይገልጽላቸዋል።
በሰንበት ክርስቲያን ከሙታን ከተነሣው ኢየሱስ ጋር በቃሉና በምስጢራት የምንገናኝበት ቀን ነው፤ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እሑድን <<የጌታ ቀን>> ብለው ይጠሩና ያከብሩት እንደነበር በሐዋርያት ሥራና ኋላም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንናነባለን፤ ለዚህ የጋራ ምክንያታቸው ክርስቶስ ከሙታን የተነሣበት ቀን መሆኑ ሲሆን ይህን ታላቅ ትንሣኤ በሕይወታቸው ሁሌ አዲስ ለማድረግ የወሰኑበት ቀን ስለነበረ የጌታ ቀን ይሉታል።እንዲሁም ደግሞ ቤተክርስቲያን ደግሞ ሰንበት እግዚአብሔር መፍጠር የጀመረት፤ “ብርሃን ይሁን” (ዘፍጥረት 1፤3) ያለበት የመጀመሪያው ቀን የፍጥረት ጌታ የሆነውን አምላካችንን የምታመሰግንበትና የምትደሰትበት ቀን ነው። ይህም ለኛ ሰንበት ከሌሎቹ ዕለታት በበለጠ የመፈጠራችንን ዓላማ የምናስብበትና የክርስቶስን ትንሣኤ የኛ የምናደርግበት ዕለት እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ ያሳስበናል።
በእሑድ ቀን ሆነ በበዓል ቀን ለእግዚአብሔር የሚገባ ኣምልኮን ከማቅረብ፣ በጌታ ቀን ከሚገኝ ደስታ፣ የምሕረት ሥራዎችን ከማከናወን፣ የአእምሮና የአካል ዕረፍትን ከማግኘት በሚያግዱ ሥራዎች ወይም እንቅስቃሴዎች በፈቃደኝነት መጠመድ የለብንም። ክርስቲያኖች ችግርን ለማቃላል ብለው የሚፈጽሙት ተግባራት ሃይማኖትን፣ ማኅበረሰብን፣ ቤተሰባዊ ሕይወትንና ጤናን ወደሚጎዱ ልማዶች የሚመሩ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
በክርስቲያናዊ መንፈሳዊ ባህል መሠረት እሑድ መልካም ሥራን ለማከናወን፣ እንዲሁም ሕሙማንን፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያን ለማገልገል የተወሰነ ዕለት ነው። እንደዚሁም በሣምንቱ ቀናት ውስጥ ይህን መሰሉን ሥራ ለመሥራት እጅግም አይቻላቸውምና ክርስቲያኖች ዕለተ እሑድን ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በመርዳትና በመንከባከብ ይቀድሱታል። ዕለተ እሑድ በጥሞና የሚታሰብበት የርጋታ ቀን ነው፤ እሑድ አእምሮና አካል የሚጐለብትበትና የሚታደስበት፤ ክርስቲያናዊው ውስጣዊ ሕይወት የሚዳብርበትና የሚኮተኮትበት ቀን ነው።
በአሁኑ ጊዜ እሑድ እንደ የመዝናኛ ጊዜ ነው የተወሰደው። በተለይ ሳምንት ሙሉ በስራ ለደከመ ሰው የመዝናኛ ወይም የእረፍት ጊዜ ጥሩና አስፈላጊ እንደሆነ ማንም ሊስተው የሚችል አይደለም። ይህ የእረፍት ጊዜ ውስጣዊ ሕይወታችንን በተለያየ አቅጣጫ እንድንመለከት - ከየት መጣሁ፣ ምንድነው የመኖሬ ዓላማ፣ ወዴት ነው የምሄደው ወዘተ ማለት - ካላስቻለን የዕረፍት ሳይሆን ከውስጣዊ ዕረፍት የሚያርቀን በከንቱ የሚጠፋ ጊዜ ብቻ ይሆንብናል። ስለዚህ ለእኛ ክርስቲያኖች ሰንበተ ክርስቲያን ነፍሳችንን የምንመግብበት ለስብእናችን ሙላት አስፈላጊ የሆነ ዕለት ነው። ስለዚህ ያለ ሰንበተ ክርስቲያን መኖር አንችልም።
አባ ክፍሎም ዮሴፍ - ሲታዊ
ዘጽጌ 3 - ጥቅምት 16
የዕለቱን ንባባትና ምስባክ ከላይ ማውጫ ውስጥ በቀኑ ይመልከቱ።
ሞኝነት ወይስ ስኬት?
የዛሬውን ወንጌል ምሳሌ ማለትም እርሻው በጣም ያፈራለት ሀብታም ሰውዬ ያለውን ጎተራ አፍርሶ ተለቅ ያለ ለመሥራት ማቀዱንና በዚያም እህሉን አከማችቶ ነፍሱ በደስታ ለዓመታት እንድታርፍለት መመኘቱንና እግዚአብሔርም ይህን ሰው እንደሞኝና ሰነፍ መገሰጹን ስናነብ ሞኝነት ምንደነው ብለን መጠየቁ ሞኝ ያለመሆን ዕድላችንን ያሰፋዋልና በዚህ ዙሪያ ትንሽ እናስተንትን።
የእግዚአብሔር ቃል ሀብታሙን ሰውዬ <<አንተ ሞኝ>> ብሎ ሲገስጸው እንሰማለን። በእኛ ዘመን ይህን የወንጌል ክፍል ለሚያነብ ሰው ወንጌሉ ሰውየውን ሞኝ ማለቱ ራሱ ሞኝነት ሊመስል ይችላል። አንድ ሰው ሠራ፣ ሀብት አጠራቀመ፣ መደሰት ጀመረ ደስታውም ቀጣይ እንዲሆንለት በልፋቱ ፍሬ ተስፋ አደረገ ታዲያ ይሄ ስኬት እንጂ ሞኝነት ሊባል ይችል ይሆን?
በርግጥ ወንጌል ውስጥ ያለው ሰው ሀብታም በመሆኑ ብቻ ሞኝ ቢባል ኖሮ ዛሬ ሀብታም የሆኑና ለመሆን የሚጥሩ ሁሉ ሞኝ እንዲሁም ድኻ የሆነው ሁሉ አስተዋይ፣ ብልህ በተባሉ ነበር። ልዩነት የሚፈጥረው ነገር ሀብታምነትና ድህነት በራሱ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከሕይወቱ፣ ከአጀንዳው፣ ከፕሮግራሙ… ውጭ ባደረገና ባላደረገ ሰው መካከል ነው።
አብዛኛዎቻችን እግዚአብሔርን ከሕይወታችን ውጭ አድርገናል የሚል ግንዛቤ ላይኖረን ይችላል። ቢያንስ በእቅድ ደረጃ ከርሱ መራቅ አንፈልግም። ትምህርቴን ስጨርስ፣ ትንሽ ፋታ የሚሰጥ ሥራ ላግኝና፣ ትዳር ስይዝ…ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር እቀርባለሁ፣ ቤተ ክርስቲያኔን እከታተላለሁ፣ ምሥጢራትን አዘወትራለሁ…ወዘተ እያልን እናስብ ይሆናል። ሆኖም ግን ለሥጋዊ ነገሮቻችን ቀጠሮ እንደማንሰጥ ሁሉ ለመንፈሳዊነታችንም ቀጠሮ መስጠቱ ሞኝነት ነው። አልበላም አልጠጣም አልተኛም አልተነፍስም…ብለን አይደለም ለዓመታት ለቀናት ቀጠሮ ብንይዝ ሞኝነታችን ምስክርም አያሻውም። በተመሳሳይ ሁኔታም ለተወሰኑ ጊዜያት አልጸልይም፣ ስለ ክርስትናዬ ማሰብ አልፈልግም፣ የእግዚአብሔርን ቃል አላነብም…ስንልም የዛሬው ወንጌል <<ሞኝ>> የማለቱ እውነት ይገባናል። ሀብታም ሆነ ድኻ ተማሪ ሆነ ሠራተኛ ባለትዳር ሆነ ላጤ በሕይወቱ እግዚአብሔርን ከሚያርቅ ሰው ሌላ ሞኝ የለም።
ስለዚህ ከዛሬው ወንጌል አንድ ነጥብ ብቻ እንኳ እንውሰድ ካልን ክርስትናችንን ካለንበት የአናኗር ሁኔታ ጋር እንዴት አስማምተንና አዋህደን እንደምንጓዝ ማስተዋልን ያመለክታል። እግዚአብሔር በተፈጥሮው ከቦታ ወይም ከጊዜ ውጭ ሊሆን የሚችል፤ እንዲሁም በጊዜና በቦታ ብቻ ሊወሰን የሚችል ማንነት የለውም። እሱን ያራቅነው ሲመስለን ራሳችንን ነው ከርሱ ይምናርቀው። እኛ ባለንበት እሱ አለ፣ በዛሬዋ ዕለትና በአሁኑ ሰዓት አለ። ይህ ለኛ አስጭናቂ እውነታ ሳይሆን ዕረፍት ሰጪ ስጦታ ነው። እሱን ለማግኘት መኳተንና ጊዜያት መጠበቅ አያስፈልገንም። እኛ እንወስን ብቻ እርሱ ዝግጁ ነው።
እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረገው ረጅሙ ጉዞ ወደ ልባችን የምናደርገው ጉዞ ነው ይባላልና በየዕለቱ ልባችን ውስጥ የመግባት ውሳኔንና ልምድን ካዳበርን በዚያ ሀብት አለን።
ዘጽጌ 2 - ጥቅምት 9
የዕለቱን ንባባትና ምስባክ ከላይ ማውጫ ውስጥ በቀኑ ይመልከቱ።
የእግዚአብሔር ክብር - ለድምጹ ታማኝ መሆን
የሰው ልጅ በሕይወቱ ለነገሮችም ሆነ ለሰው ማድረግ የሚገባውን ነገር ሲያደርግ ይበልጥ ደስታና የኅሊና ዕረፍት ይሰማዋል፤ በተቃራኒውም ማድረግ የሚገባውን ካላደረገ ውስጡ አያርፍም። ይህ እውነት ደግሞ ከፍ ባለ ደረጃ የሚጎላው በእግዚአብሔር ፊት ማድረግ ወይም መሆን የሚገባንን ካልሆንንና ካላደረግን ነው፤ ምክንያቱም ቋሚ ወይም ቀጣይ ጎዶሎነትን ስለምንሰንቅ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔርን በሕይወታችን የማክበርና የማስከበር ነገር ማድረግ የሚገባን ነገር ነውና ይህን ካልተለማመድን ነገሮች ሁሉ ቢሆኑልን እንኳ የጎዶሎነት ስሜታችን ሁሌም እየጎደለ ነው የሚቀጥለው።
እግዚአብሔርን ማክበር ሰው የመሆኔን ትርጉም የሚሰጠኝ ከሆነ ከዚህ ዓላማ የሚያስተጓጉለኝ ነገር ምንድነው ብለን ማሰብ ይኖርብናል። የዛሬው ወንጌል ለዚህ አጋዥ ነጥቦች አሉት።
መጀመሪያው ቁጥር ላይ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት የክርስቶስን ተከታይ ማግኘትና ማጥመቅ በማወቃቸው ዮሐንስ መጥምቁን ከኢየሱስ ጋር ማወዳደርና ምናልባትም የትኛው ነው ትክክለኛ በሚል ሃሳብ ውስጥ ሆነው <<መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ>> አሉት። ይሄ መስመር ለኛ ብዙ ሊለን ይገባል። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ እኛን የሚናገረንና ሰዎችም የሚከተሉት ኢይሱስ ብቻ ቢሆን ኖሮ የእሱ ተከታይነታችን ቀለል ባለ ነበር። እውነቱ ግን ከዚህም ከዚያም የሚናገሩን፣ ተስፋ እየሰጡን ተከተሉኝ በማለት ጊዜያችንንና ኃይላችንን እንድናባክንላቸው የሚጋብዙን የኑሮ ምርጫዎች ብዙ ናቸው። እውነተኛ ተፈጥሮዋቸው ግን ሁሌም አንድ ሆኖ ይቀራል፦ <<እኔ ክርስቶስ አይደለሁም>> (ቁ.28) ማለትም እነርሱ ክርስቶስ አይደሉም።
የምንሮጥላቸው ማናቸውም ነገሮች እውነተኛ መልስ እነሱ ክርስቶስ ያለመሆናቸው ነው። እድሜያችንን፣ ገንዘባችንን፣ እውቀታችንን፣ ጉልበታችንን… በጣም ካባከንንላቸውና ካሟጠጡን በኋላ እህሳ ብለን ብንጠይቃቸው መጨረሻ ላይ የሚሉን ነገር <<እኔ ክርስቶስ አይደለሁም>>ነው። ምክንያቱም መሆን ስላልፈለጉ ሳይሆን መሆን ስለማይችሉ ማለት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን በዕለታዊ ሩጫው ለማክበር የሚተጋ ክርስቲያን ከእንደዚህ ዓይነት የማንነት ኪሣራ ይድናል።
ክርስትናችንን ባመንን መጠን ብቻ ሳይሆን በኖርነው መጠን ፍጻሜያችን እየተወሰነ ይሄዳል፤ <<እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል>>(ቁ.30) እንዳለው ዮሐንስ መጥምቅ እኛም ክርስቶስ ሊልቅ፣ ከፍ ሊል እኔ ወይም እገሊት ወይም የሆነ የምናስቀድመው ነገር ካለም ዝቅ ሊል ያስፈልጋል ማለትን መለማመድ አለብን። ይህ ሲሆን ቁ.36 ላይ <<በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም>> እንደሚለው የጉዟችን ፍጻሜ ክርስቶስ ይሆናል። እምነታችም ፍላጎት ብቻ መሆኑ ቀርቶ ሕይወትና መዳንን ያጎናጽፈናል።
ስለዚህ በሕይወታችን ለሚጠሩን ነገሮች ሁሉ መልስ መስጠት አንችልም። ብንችልም እንኳ የነሱ ምላሽ ጊዜያዊ ነው። በመላ ማንነታችን ቀጣይና ሙሉ ምላሽን ልናገኝ የምንችለው በልባችን ውስጥ ክርስቶስ እንዳይቀመጥ ቦታ ያጣበቡ ነገሮችን ለማስወገድ ስንታገል የእግዚአብሔርም ጸጋ በቃሉና በምሥጢራቱ ለዚህ ግብ እንደሚያግዘን ስናምን ገና መጨረሻ ላይ ሳይሆን በየዕለቱ ሰላማችንና ዕረፍታችን በችግር መሐል ቢሆንም እየበዛ ይሄዳል።
እግዚአብሔር በብዙ መልኩ ይናገረናል፤ በእውነት እሱን በሕይወታችን ማክበር ጥማታችን ከሆነ ለድምጹ ታምኝ እንሁን። የቤተ ክርስቲያንም ጩኸት ከርሱ የተለየ ሌላ ድምጽ ሳይሆን የእርሱን ድምጽ ለዚህ ዘመን በሚሆን መልኩ የምታስተላልፍ የክርስቶስ አካል ናትና ወደ ማንም ሳይሆን ወደ ቃሉና ወደ ማዕደ ቁርባን የሚጠራንንን ድምጿን እናዳምጥ። ይህ ሲሆን በርግጥም ሌሎች ነገሮች ዝቅ ክርስቶስ ከፍ ሊል ይገባል የሚል ምስክርነትን ለዓለም መስጠት ጀመርን ማለት ነው።
ዘመስቀል 2ኛ - መስከረም 25
የዕለቱን ንባባትና ምስባክ ከላይ ማውጫ ውስጥ በቀኑ ይመልከቱ።
መሸከም ያለመሸከም ሲሆን።
የዛሬው ወንጌል ሲጀምር << ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።>> ይላል። ሰዎች ስለሆነ ነገር የሚሉትን መናገር አስቸጋሪ ሆኖ አይሰማንም። የሚሉት ነገር ይግባንም አይግባንም በመሰለን