If our pages are illegible, please download fonts here: Visual Geez Unicode

 

 

3ኛ ሰንበተ ጰራቅሊጦስ

2ኛ ሰንበተ ጰራቅሊጦስ

የበዓለ ጰራቅሊጦስ አስተንትኖ

የሰንበተ ዕርገት አስተንትኖ

የዘመነ ትንሣኤ 6ኛ ሳምንት

የዘመነ ትንሣኤ 5ኛ ሳምንት

የበዓለ ትንሣኤ አስተንትኖ

የበዓለ ሆሳዕናንና ሰሙነ ሕማማት አስተንትኖ

 

 

ሰንበት ዘክረምት  

 

ምስባክ:- ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፤ ዘያበቁል ሣዕረ ውስተ አድባር............እርሱ ደመናትን በሰማይ ላይ ይዘረጋል፤ ለምድር ዝናምን ይሰጣል፤ ተራራዎችንም በለምለም ሣር ይሸፍናል። መዝ. 147:8

 የቅዳሴ ንባባት   ሙሉ ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው

  1. 1ቆሮ. 15:33-51

  2. ያዕ. 5:16-ፍጻሜ

  3. የሐዋ. ሥራ 27: 11-21

  4. ሉቃስ 8: 1-22

  ያለመሰልቸት ራሳችንን እንጠይቅ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን ሊሰሙ ለመጡት ሰዎች እነርሱ ሊረዳቸውና ሊገባቸው በሚችል ምሳሌያዊ ቋንቋ ሲያስተምራቸው እንመለከታለን፤ ገበሬና ዘር።

         ገበሬ ዘሩን ሲበትን ሁሉም ዘር ሊያፈራ አይችልም። አንዳንዱን ወፎች መጥተው ወዲያው የሚለቅሙት አለ፤ አንዳንዱ አፈር ውስጥ በደንብ ባለመግባቱ ምክንያት ቶሎ ይበቅልና በፀሐይና በዝናም ሊበላሽ የሚችል አለ። አንዳንዱ ደግሞ ፍሬ የሚያፈራ አለ።

         በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ላይ፤ ገበሬው እግዚአብሔር፣ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል፣ መሬቱ ደግሞ የሰው ልጅ መሆኑ ተገልጿል። እዚህ ላይ ቃሉን ከሚሰሙት ሰዎች መካከል አራት ዓይነት ሰዎች እናስተውላለን።

1. ቃሉን የሚሰሙና ወዲያው ሰይጣን እንዳይድኑ ብሎ ከልባቸው የሚወስድባቸው፤

2. ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ሆኖም ግን ፈተና በደረሰባቸው ጊዜ ፈተናውን ብዙ ሳይታገሉ ቃሉን የሚክዱ ሥር የሌላቸው፤

3. በዚህ ዓለም ኑሮ በሃብት በንብረት የተዋጡ፤ ቃሉን በሕይወታቸው ለመተግበር ጊዜ የሌላቸው

4. ቃሉን ሰምተው የሚፈጽሙና - ፍሬ የሚያፈሩ

የእግዚአብሔር ቃል መልካም ዘር ነው። ይህ መለኮታዊ ቃል መጀመሪያ ዓለምን፣ ሰማይንና ምድርን ከኢምንት የፈጠረ፤ ለዕውሮች ብርሃንን ያሳየ፣ በሽተኞችን የፈወሰ፣ ሙታንን ያስነሣ ነው። ይህ ቃል ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ጠርቷል። የተጨነቁትንና ያዘኑትን አጽናንቷል፤ በአጋንንት የታሠሩትን ነጻ አውጥቷል። ይህ ዘር (የእግዚአብሔር ቃል) አሁንም ቢሆን ኃያል ነው። አመቺ ሁኔታ ካገኘ ምን ጊዜም ቢሆን ያለ አንዳች ጥርጥር የተጠበቀውን ፍሬ ይሰጣል። ይህ ቃል ፍሬ ማፍራት ካልቻለ ዘሩ የሞተና ኃይል የሌለው ሆኖ ሳይሆን የሚሰማው ወይም የሚቀበለው ሰው መልካም ፍላጎትና ትብብር እጦት ነው።

እኛንም እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ አድርጎ ተናግሮናል፤ እኛም ራሳችን ቃሉን አንብበነዋል። ይህን ምሳሌ በሰማን ቁጥር ያለመሰልቸት ራሳችንን መጠየቅ አለብን። እኛስ ከየትኞቹ ወገን ነን? ከሚያፈሩት ወይስ ከፍሬ አልባዎቹ ወገን? የትኛውን መሬት ነው የምንመስለው? ለሙን መሬት ወይስ ጭንጫማውን? ወይስ ሰው ሁሉ የሚተላለፍበት የሚረግጠውን መሬት? ፍሬ የማያፈራ ቅርንጫፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል ይላልና የእግዚአብሔር ቃል ራሳችንን እንመርምር(ዮሐ. 15:2)።

 

አባ ክፍሎም ዮሴፍ ሲታዊ 

ወደ ላይ ለመመለስ ይህንን ይጫኑት

3ኛ ሰንበተ ጰራቅሊጦስ  

  የቅዳሴ ንባባት   ሙሉ ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው

ሰላማችን ክርስቶስ ነው

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። (ዮሐ. 14፡ 27)

መጽሐፍ ቅዱስም ስለ ሰላም በብዙ ቦታና መልክ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፦

ኢሳ 9፡ 6 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል

ማቴ 5፡ 9 የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።

1 ቆሮ 14፡ 33 እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።

ገላ 5፡ 22 የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።

      የሰው ልጅ በሰላም እየኖረ ነው ለማለት በሶስት አቅጣጫ በሰላም ላይ መገኘት አለበት።

1.  ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር- ከእግዚአብሔር ጋራ በሰላም የምንኖርበት ሰላም

2.  ሰላም ከገዛ ራሳችን- ከገዛ ራሳችን/ከኅሊናችን/ ጋር በሰላም የምንኖርበት ሰላም

3.  ሰላም ከባልንጀራችን- ከባልንጀራችን ጋር በሰላም የምንኖርበት ሰላም

 

 1. ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር

መጀመርያ ከእግዚአብሔር ጋር የምናተሳስረው ሰላም አለ። የዚህ ዓይነቱ ሰላም እንዲገኝ በእግዚአብሔር ማመን፣ እግዚአብሔርን በሕይወታችን ላይ ማስገባት፣ እግዚአብሔርን ማወቅ፤ መውደድና መታዘዝ ያስፈልጋል። እግዚብሔር ከኛ ጋራ መሆኑንና ሰላማችን እሱ ራሱ መሆኑን መረዳትና መቀበል ይኖርብናል። ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ውስጣዊና ዘላቂ ሰላም ሊገኝ አይችልም። ሰላም የምትገኘው በሕይወታችን ላይ አንደኛውን ስፍራ ለእግዚኣብሔር ስንሰጥ ብቻ ነው። እግዚአብሔርን ከልብ መውደድ፡  የእግዚኣብሐርን ፈቃድ እየፈጸሙ መመላለስ፡ የማያሳስት የሰላም ጐደና ነው።

2. ሰላም ከገዛ ራሳችን ጋር

ከእግዚኣብሔር ጋር በሰላም በምንገኝበት ጊዜ ቀስ በቀስ ውስጣዊ ሕይወታችንም መንገዱን እየያዘ ሰላምን እንደ የሕይወታችን ዓላማ እያደረግን እንመጣለን። ሰላማችን የሆነው እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ሲነግሥ፡ ክርስቶስን የሕይወታችን ንጉሥ አድርገን በምንመላለስበት ጊዜ፡ ንጉሠ-ሰላም የሆነው ክርስቶስ ከኛ ጋራ ስላለ በገዛ ራሳችን፡ በሕይወታችን ሰላም ይነግሣል። በዚሁ መልክ ከገዛ ራሳችን ጋር በሰላም እንገኛለን። ይህ ግን የሕይወታችን የመጨረሻ ፍጻሜ አይደለም። የሰው ልጅ ዓላማው ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለአንዴና ለዘለዓለም በሰማያዊትና የማትለዋወጠው የሰማይ ሰላም ላይ እስኪደርስ ድረስ “በቃ አሁን ከዚህ በላይ የምፈልገው ነገር የለኝም” ብሎ ማረፍ አይገባውምም አይችልምም።

4.  ሰላም ከባልንጀራችን ጋር

ከባልንጀራችን ጋር ሰላም ሊኖረን የሚችለው ከእግዚአብሔርና ከገዛ ራሳችን ጋር ሰላም ሲኖረን ብቻ ነው። ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋርና ከገዛ ራሳችን ጋር ያለንን ሰላም ያንጸባርቃል። በውስጡ የታወከና ከእግዚአብሔርም የተለየ ሰው ከሌሎች ጋር በሰላም ሊኖር ኣይችልም።

ክርስቶስ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ብሎናል። ክርስቶስ ሰላም ሰጪአችን ብቻ ሳይሆን ሰላማችን ራሱ ስለሆነ፡ ሰላሙን ሲሰጠን የሚሰጠን የገዛራሱን ነው ። ለዚህም ነው መላእክተ ሰማይ ክርስቶስ በተወለደልን ጊዜ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” ብለው የዘመሩት። እንዲሁም ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሞቶ ከሞት በተነሣ ጊዜ የመጀመርያ ሰላምታው “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” የሚለው ነበር። ስለዚህም ነው ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስትያን የክርስቶስ አባሎች ለሆኑት ምእመናን፡ በቃሉና በሥጋሁ ወደሙ ገበታ ላይ ለመካፈል ሲሰባሰቡ “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” በማለት ክርስቶስ ከያንዳንዳችን ጋር የሚሆንበትን ምሥጢር በሚገልጽ መንገድ ሰላምታ የምታቀርብልን።

ስለዚህ ከእግዚአሔብር ጋር ሰላም እንዲኖረን ሕጉን እንጠብቅ፤ ከገዛ ራሳችን ጋር ሰላም ሊኖረን የምናምነውንና የምንሠራውን እናስማማ፤ ከባልንጀሮቻችን ጋርም ሰላም እንዲኖረን ደግሞ እነሱ ለኛ ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እናም ለእነርሱ እናድርግላቸው።

በመጨረሻም “የሰላም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።” (1 ተሰሎ 5፡ 23) አሜን።

 አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ 

ወደ ላይ ለመመለስ ይህንን ይጫኑት

2ኛ ሰንበተ ጰራቅሊጦስ  

  የቅዳሴ ንባባት   ሙሉ ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው

ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ (ዮሐ 14:15)

1.  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም።” (ዮሐ 8:51)
2.  እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ  (ዮሐ 15:10)
3.  አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸታም ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።(1 ዮሐ 2:4)
4.  ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። (ዮሐ 14: 21)
 

   እግዚአብሔርን እንደምንወድ የሚያመለክተው ተግባራችን ነው። እግዚአብሔርን የሚወድ እግዚአብሔር የሚወደውን፣ እግዚአብሔር የሚያዘውንና እግዚአብሐር የሚፈልገውን ይፈጽማል። ከልጅነታችን በትምህርተ ክርስቶስ ከተማርንበት ጊዜ ጀምሮ የምናውቀው እውነት አለ፤ ያም እግዚአብሔር የፈጠረን እሱን እንድናውቅ እንድንወድና እንድናገለግል መሆኑ ነው ። ስለዚህ እግዚአብሔርን መውድድና መታዘዝ የተፈጠርንበት ዓላማና የክርስትና ጥሪያችን ነው።

   አውቀንና ወደን ኃጢአትን ስንመርጥና ፍቅር የሆነው ሕጉንና ትእዛዙን በመጣስ ፈቃዱን ትተን ፈቃዳችንን በምንፈጽምበት ጊዜ እግዚአብሔርን በተግባራችን “አንወድህም” እንለዋለን ማለት ነው። እግዚአብሔርን መውደድ እንደሚገባን በደንብ እያወቅን ትእዛዙን በምንጥስበት ጊዜ ከሱ በላይ የምንወደው ነገር ወይም ሰው እንዳለን እንገልጻለን ማለት ነው። ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆነ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን ክፉን ከመሥራት እግዚአብሔርን ከማሳዘን ርቀን፤ ነፃ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን በምንሄድበት መንገድ እንመላለሳለን። 

     እግዚአብሔርን የሚወድ ሁለመናውን ለሱ ስለሚሰጥ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ይወጣል። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ራሳችንን ከክርስቶስ ነጥለን ለአንድ ነገር ወይንም ለአንድ ሰው እንሰጣለን ማለት ነው። ክርስቶስን በሙሉ ልባችን፤ ነፍሳችን፡ አእምሮአችንና ኃያላችን ከወደድነው ግን ከክርስቶስ በፊት በፍቅር የምናሰልፈው ስለሌለ ሁለመናችን ለሱ ይሆናል እሱ ደግሞ የኛ ይሆናል።

አንዳንድ ጊዜ “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት እንዲሉ ክርስቶስ ሰዎች መሆናችንን ያውቃል ይቅር ይለናል” የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን እናገኛለን። ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት አንጠራጠርም፤ ነገር ግን የምንወደው ከሆን ለምን እናሳዝነዋለን? ከኃጢአት ርቀን ከሱ ጋራ በሰላም መኖር ዛሬ በዚች ዓለም ነገም በሚመጠው በፍቅርና በሰላም ለመኖር እንችላለን። ስለዚህ እያሳዘነውና መሐሪ በመሆኑ ይቅርታን እየጠየቅን ከመኖር ኃጢአትን ከሕይወታችን አስወግደን ከፈተና ርቀን ከክርስቶስ ጋራ ዘላቂ አንድነትን ፈጥረን መኖርን እንደ ዓላማችን አድርገን በመምረጥ እንኑር።

     ክርስቶስን መውደድ ስንሞት የሚሆን ነገር ሳይሆን በየዕለቱ ኑሯችን ውስጥ መለማመድ ያለብን ነገር ነው፤ ማለትም ሕይወታችንን በመቀየር፤ ወደ ኃጢአት የሚመሩ ነገሮችን፡ ሰዎችና ቦታዎችን መተው፡ ክፉ ልማዶችን ከነሥራችው ነቅሎ ከሕይወታችን ማራቅ፡ ክርስቶስ እኛን እንዳፈቀረንና እነደሚያፈቅረን ሁሉ እግዚአብሔርንና ባልንጀራዎቻችንን መውደድ ማስከተል አለበት። ክርስቶስ በኛ ፍቅር ምክንያት ምን  ያህል እንደተሰቃየና የስው ልጅ ፍቅር በክርስቶስ ዘንድ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ተገንዝበን እኛም በሱ ፍቅር ተወስነን እንኑር።

አእምሮአችንንና ልባችንን በክርስቶስ ፍቅር ካስገዛን ሰዎችንና ነገሮችን በሱ ዓይንና በሱ አንደበት መመልከት እንችላለን። እግዚአብሔር አብንና ሰዎችን ለመውደድ ክርስቶስን ከልብ መውደድና ሕጉንም መፈጸም ያስፈልጋል።

     የእግዚአብሔር ፍቅርና ኃጢአት ባንድ ላይ በልባችን መኖር አይችልም፤ ምክንያቱም ባንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች ልንገዛ ስለማንችል ሕይወታችን ይከፈፈላል። ክርስቶስን የሚወድ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው ከሚችለው ነገር ሁሉ መለየት ይኖርበታል። ክርስቶስን መውደዳችን አስተሳሰባችንና አሠራራችንን ባጭሩ የኑሮ ዘይቤያችንን መለወጥ አለበት። ክርስቶስን መውደድ የክርስቶስን ፍቅራዊ ሕግ ከሁሉም በላይ ወደ ማስቀደም ይመራናል።

     ክርስቶስን የመውደዳችን ዋና ምልክት ያለው ምን ያህል ቃሉን ማወቃችን ላይ ሳይሆን ምን ያህል ትእዛዙን መፈጸማችን ላይ ነው። ክርስቶስ ራሱ በፈቀደው አሠራር መሠረት በቤተክርስትያኑ በኩል እነደሚመራን አድርገን መኖር ያስፈልገናል። ለሐዋርያቱ እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል እንዳላቸው ሁሉ ዛሬም ቤተክርስቲያንን የሚሰማ እሱን መስማት መሆኑን ሳናመነታ ይህንን ከፈጸምን ክርስቶስን እንወደዋለን ማለት ነው። ክርስቶስን እንወድሃለን እያልነው ካስተማረን ውጭ በሆነ መንገድ ከተጓዝን ግን ክርስቶስን ከሁሉም በላይ አላደረግነውም ሕጉን አልፈጸምንም ከሱም ዕጣ ክፍል የለንም።

ክርስቶስን ከመውደድና ሕጉን ከመጠበቅ ከሱ ጋር በሰላም መገኘትን ስለሚያስከትል ክርስቶስ በልባችን እንዲነግሥና የሕይወቱ ተካፋይ እንድንሆን በነጻ የተሰጠንን የክርስትና ሕይወት ጸጋ ሳናባክን እንኑረው። ኃጢአት በሟች ሥጋችን ላይ ከነገሠ ግን ክርስቶስ የሕይወታችን ንጉሥ ሊሆን አይችልም። በዚህ የምንጠየቀው እኛው ነን፤ ምክንያቱም ከክርስቶስ በኩል ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚሆን ሁሉ ስለተሰጠን በሱ በኩል ምንም የጎደለ ነገር የለም። ዛሬ በመንፈሳዊ ዓይናችን እግዚአብርን እያየንና እየታዘዝን ከተጓዝን በጊዜያዊና ሥጋዊ ኑሯችን የጀመርነውን ደስታ ነገ ከሱ ጋር ለዘለዓለም እንቀጥለዋለን።

ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚወደን የምናየው በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ “ይህን ያህል ነው የምወዳችሁ” እያለ ሕይወቱን ስለኛ ያሳለፈበትን የመስቀል መሥዋዕት ላይ ነው።

     ስለዚህ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8፡35-39) ብለን በሱ እንመካ ፈቃዱንም እንፈጽም።

 

አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ 

ወደ ላይ ለመመለስ ይህንን ይጫኑት

በዓለ ጰራቅሊጦስ  

  የቅዳሴ ንባባት   ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው

 

የአንድነትና የፍቅር ቋንቋ - እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ

      ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከትንሣኤ 50 ቀናት እንዲሁም ወደ ሰማይ በክብር ካረገበት ደግሞ 10 ቀናት በኋላ በዓለ ጰራቅሊጦስን፡ እናከብራለን።

በዓለ ጰራቅሊጦስ:-

  • መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት

  • አማንያን በሐዋርያት ስብከትና በምስጢረ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ተዋህደው የአዲስ ኪዳን አዲስ ሕይወት የጀመሩበት

  • በመንፈስ ቅዱስ የምትመራዋ ቅድስት ቤተ ክርስትያን በይፋ የተቆረቆረችበት

  • ሕግዋ ፍቅር፤ እውነትም መሠረትዋ የሆነችው ቤተክርስትያን የአማኞች

ማኅበር ሆና የተመሠረተችበት ፍጻሜ ነው።

    የበዓለ ጰራቅሊጦስ ሁኔታና ክናዋኔዎች ዛሬ ባነበብነው የሐዋርያት ሥራ ሁለተኛ ምእራፍ ላይ የሚከተሉትን ነጥቦች እናገኛለን፦

·         በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥

·         ሐዋርያት በአንድ ቤት ተሰብስበው ለዘጠኝ ቀናት በጸሎት ላይ እንደነበሩ --ከዕርገት- ጰራቅሊጦስ- (በቤተ ክርስትያናችን የዘጠኝ ቀናት ጸሎት (Novena) የምናደርገው ከዚሁ የጀመረና በዚሁ ምሳሌነት ነው።)

·         በድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።

·         እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።

·          በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።

·          ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤

·          ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።

·          ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ። እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

·         እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? (ግሐ 2፡ 1-4)

      ይህ የአዲስ ኪዳን ታላቅ ክንዋኔ የተፈጸመው አይሁድ በዓለ ኀምሳቸውን በሚያከብሩበት ዕለት ነው። አይሁዳውያን በየዓመቱ ከግብፅ ባርነት ነፃ የመውጣታቸውን በዓለ ፍሥሐ ካከበሩበት ከሶስት ቀናት በኋላ ምርታቸውን የሚሰበስቡበት ወቀት በመሆኑ የመጀመርያ ፍሬዎችን ይዘው፡ ዝናሙን፡ ነፋሱንና፡ ጸሐዩን አመጣጥኖ በመስጠት በመሬት ለተዘራውም ዘር ሕይወትን ሰጥቶ፡ አብቅሎ፡ አለምልሞ፡ እንዲያብብ በማድረግ በ 30፡ 60፡ እና መቶ እጥፍ አፍርቶ አትረፍርፎ የሰጣቸውን አምለክ የሚያመሰግኑበት በዓልም ነበራቸው። (ዘፀ 34፡22፤ ዘኁ 16፡10) ይህ በዓል እስከ ኀምሳ ቀናት ከተከበረ በኋላ በእርሾ የተጋገረ ቂጣ እንደ የምስጋና መባ የሚያስያስገቡበት ዕለትም ነበር። (ዘሌዋ 23፡ 17-20፤ ዘኁ 16፡9-10)

     ይህን በጣም የታወቀ በዓል በከፍ ያለ ሁኔታ ለማክበር አይሁዳውያን ከያሉበት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ነበር።

     የጰራቅሊጦስ ተአምር የተፈጸመበት ዕለት ከዚሁ በዓል ጋር የተደራረበም ስለነበር በዚያን ዕለት በኢየሩሳሌም በጣም ብዙ ሕዝብ መገኘት ቻለ። ያ የአውሎ ነፋስ የሚመስል ድምጽ በተሰማ ጊዜ ሕዝቡ ምንድነው? በማለት ሐዋርያቶቹ ወደ ነበሩበት ቦታ አመሩ። ያን ጊዜ ከልዩ ልዩ ቦታዎችና የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆነው ሕዝብ፡ ሐዋርያት በሚያውቁት በገዛ ቋንቋችው ሲናገሩ፤ በሐዋርያት አንደበት ተናጋሪ፡ በሕዝቡ ጆሮ ሰሚ በሆነው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሁሉም በየቋንቋቸው ይረዱት ነበር። (ግሐ 2፡ 7-13)

ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው። ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ። (ግሐ 2፡ 12-13)

      ያን ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት “ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ።” (ግሐ 2፡14…) በማለት በብሉይ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ የነበረውን ትንቢት ጠቅሶ ይሰብክ ጀመረ። ስለ ጌታ ኢየሱስ ስለ ሕማማቱና ትንሣኤው በሰፊው አስተማረ። ሕዝቡም ይህንን ሐቅ በሰሙ ጊዜ በልባቸው ሠረፀና በአምላክ አመኑ። “ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት። ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም። ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።  የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።  በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ” (ግሐ 2፡ 37-41)

የክርስትያን ሕይወት አርአያ መሆን የሚገባውንና መንፈሳዊ ቅናትን በውስጣችን መጫር ያለበትን ሃሳቦች ሲተርክ እንዲህ ይላል... ያመኑት ደግሞ፦

·         ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤

·         ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ።

·         መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥

·         ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር።

·          በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥

·         በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤

·         እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ

·         በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው።

·         ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። (ግሐ 2፡ 45-47)

      የጰራቅሊጦስ ዕለት የተከሰተው ሁኔታ ሁሉ በፊት በባቢሎን ላይ የተለያየውን ቋንቋና ሕዝብ ወደ አንድነት የሚመልስ ፍጻሜ ነው። በባቢሎን ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ስለሸፈተ ቋንቋቸውን በተነባቸው። ሊረዳዱም አልቻሉም። በአንጻሩ በጰራቅሊጦስ ደግሞ  የተበታተነውን ሰብስቦ አንድና አዲስ ሕዝብ አድርጎ ሐዋርያት ባንድ ቋንቋ የተናገሩትን ሁሉም ሊረዱት እንደሚችሉ አደረገ።

      ክርስቶስ በሞቱና በትንሣአው ዓለምን አድሶ የጽድቅ ፍሬ እንድናፈራና ለዘላለም የህይወት ጎተራ በሆነው በመንግሥተ ሰማያት ሊሰበስበን ፈቅዶ አይሁዳውያን የምርት በዓላቸውን በሚያከብሩበት በበዓለ ኀምሳ ሐዋርያቱን ልኮ የመጀመርያ የመዳን ፍሬ የሆኑትን 3000 ምእመናንን አፈሩ።

     ስለዚህ እኛም በጥምቀታችን ምክንያት ራሱ አማላክና የእግዝአብሔር ታላቅ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናልና ከሱ ጋር ሆነን እግዚአብሔር በሚከበርበት እኛም በምንድንበት መንገድ እንጓዝ።    

     የእግዚአብሔር ልጆች የአንድነት ቋንቋ በሆነው በእግዚአብሔር ፍቅርና በእርስ በርሳችን ፍቅር ተዋህደን የአዲስ ኪዳን ሕዝብና መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሕዝብ ሆነን እንጓዝ።

አባ ዓውተ ወልዱ ሲታዊ 

ወደ ላይ ለመመለስ ይህንን ይጫኑት

 ሰንበተ ዕርገት፣  

  የቅዳሴ ንባባት   ጥቅሶቹን በመጫን ያንብቧቸው

በኢየሱስ ስም መጸለይ

<