ኃጢአትን መቋወም ኃጢአተኛን ግን መንከባከብ አለብን

ቫቲካን ሬድዮ - ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ አሑድ ዕለት ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ባቀረቡት ትምህርትነበር "ኃጢአትን መቋወም ኃጢአተኛን ግን መንከባከብ አለብን" ያሉት። ቅዱስነታቸው የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመመርኰስም የሚከተለውን ትምህርት ሰጥተዋል:- "ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ ዛሬ 5ኛ የዘመነ ጾም እሁድ ይዘናል፣ የዛሬው ቃለ ወንጌል ስለ በዝሙት የተገኘችውን ሴት ኢየሱስ ከሞት ቅጣት ሲያድናት እንመለከታለን፣ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8:1-11 የተመለከትን እንደሆነ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ተቀምጦ ሕዝቡን እያስተማረ ጸሐፊዎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ሕግ ተወግራ መሞት የነበረባትን በምንዝርና የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጥዋት። ኢየሱስ እንዲፈርዳት ፈልገው ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት። ይህንን ያሉት ደግሞ የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ነው። ሁኔታው እጅግ ከባድ ነው።...

በመጀመርያ የሴትየዋ ሕይወት በእርሱ ፍርድ ይወሰናል፣ ሊከሱትና ሊገድሉት ምክንያት ይፈልጉ ስለነበረም የእርሱም ሕይወት በሚሰጠው ፍርድ ይወሰናል። ፈሪሳውያኑ ከሳሾች ፍርድን ለእርሱ እንደሰጡ በማስመሰል ዋና ፍላጎቶቻው እሱን ለመክሰስና ለፍርድ ለማቅረብ ነው። ኢየሱስ ግን የሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 1:14 እንደሚለው “በጸጋና በእውነት የተሞላ” ነው። በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ያውቃል፣ ኃጢአትን ለመኰንን ኃጢአተኛን ለማዳን ፈሪሳውነትን ለማጋለጥ ይፈልጋል። ሰዎቹ መላልሰው እየጠየቁት ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ ቅዱስ አጎስጢኖስ ይህንን ነገር ሲፈታ በጽላተ ሙሴ ሕግን የጻፈው የእግዚአብሔር ጣት አሁንም በምድር ላይ የሚጽፈው ጣት ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ሕግን የሚሰጥ መሆኑን ያመለክታል ይላል። ስለዚህ ኢየሱስ ሕግ አውጪና ትክክለኛ ዳኛና ፍትሕ ራሱ መሆኑን ያመለክታል። እንታድያ ፍርዱ ምን ይሆን፣ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። እነኚህ ቃላት እውነትን የመግለጽና የፈሪሳዊነት ግድግዳን የማፍረስ እንዲሁም ኅሊናዎችን የሁሉም ሕግ ምንጭ ወደ ሚገኝበት ትልቁ የፍቅር ፍትሕ ይመራል። ይህ ፍትሕ የጠርሴስ ሳውልን በማዳን ወደ ቅዱስ ጳውሎስ የለወጠ ፍትሕ ነው።

ከሳሾቹ ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ከወጡ ብኋላ ኢየሱስ ሴቲቱን ከኃጢአትዋ ይፈታታል ወደ መልካም መንገድ ያቀና አዲስ ሕይወትም እንደትጀምር ያደርጋል። እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት። ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍሊጵስዩስ በጻፈው መልእክቱ ምዕራፍ 3 ቍ.14 ላይ “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።” ለማለት የገፋፋው ይህ ጸጋ ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ለልጆቹ የሚመኝልን በጎ ነገርና ሕይወትን ነው። የነፍሳችን ጤናን ይከታተላል፣ አንድ እንኳ እንዳይጠፋ ሁላችን የመዳንን የመለወጥ ዕድል እንድናገኝ ይህንን የሚያደርገው በመልእክተኞቹ በሆኑ ካህናት በምሥጢረ ንስሐ ኃጢኣታችን ይቅር በማለት ነው። በዚሁ የካህን ዓመት ለዓመተ ካህን ባስተላለፍኩት መልእክት እንደጻፍኩት “በፍላጎቱ እኪምረን ድረስ በፍላጎቱ ኃጢኣታችንን እስከ መርሳት ራሱን በሚገፋ በመሐሪው የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲድኑ ምእመናን የምሥጢረ ንስሓ ትርጉምና ጣዕም እንዲያጣጥሙ፣ ነፍሳትን የሚንከባከቡ ካህናት የአርስ ቅዱስ ቆሞስ ምሳሌ እንዲከተሉ እማጠናለሁ።

ውድ ጓደኞቼ ሌሎች ላይ ያለመፍረድንና ሌሎችን ያለመኰነን ከጌታችን ኢየሱስ እንማር፣ ከገዛ ራሳችን ኃጢኣት ጀምረን ኃጢአትን መቋወም ኃጢአተኛን ግን መንከባከብ እንዳለብን መማር አለብን፣ ይህንን ለማድረግ ከኃጢኣት ሁሉ ነጻ የሆነች ቅድስትዋ የእግዚአብሔር እናትና ለተጸጸተ ኃጢኣተኛ ሁሉ ጸጋ የምታማልድ ማርያም ትርዳን" ብለው ካስተማሩ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል።

ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ እፊታችን እሁድ በዕለተ ሆሳዕና የሚከበረውን የወጣቶች ቀን በማስታወስ “በተወዳጁና በተከበሩ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከታወጀ ጀምሮ ለ25ኛ ጊዜ ለሚከበረው የወጣቶች ቀን ለመዘጋጀት ከፊታችን ሐሙስ የምሽቱ አንድ ሰዓት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አብረን እንድንጸልይ ለመላው የሮማና የላስዮ ወጣቶች ጥሪ አቀርባለሁ።” ብለዋል።

በመጨረሻም ትምህርታቸውን ለመስማትና አብረዋቸው ለመጸለይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ነጋድያንና ምእመናን እንዲሁም በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ለሚከታተልዋቸው ሁሉ በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሐዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።