የር.ሊ.ጳ. የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ

(ሰኔ ፳፮/፳፻፫ ዓ.ም.) - ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር አዲስ በሆነው የወንጌል ቃሉ እንዲህ ይለናል “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” ይላል (ማቴ.11፡28-30)። እንዲሁም “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ የሕዝቡንም ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር፣ ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴ፣9፣35-36) ይላል። ኢየሱስ ያኔ ያሳየው ርኅራኄ አሁን ባለነው ዓለማችንም ሳይቀር እስከ ትውልዳችን ይዘረጋል። ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ በሕይወት ችግር ተጨቁነው በሚገኙ እንዲሁም ኑሮ የመረራቸውንና የሕይወት ትርጉምና ስሜት አጥተው የሚጨነቁትን ወገኖች በርኅራኄ እየተመለከተ ነው። በድሆች አገሮች ብዙ የተራቈቱና የተቸገሩ እንደሚገኙ ሁሉ በበለጸጉና በሃብታም ነን ባይ አገሮች ደግሞ መሠረታዊ የሆነውን  ነገር በማጣት በአእምሮ ጭንቀት እየተቸገሩ ናቸው፣ ከሁሉም በላይ ግን በጦርነት ድህነትና ሰው ሠራሽ ጭቆና ተገደው ሕይወታቸው ለአደጋ በማጋለጥ በየቦታው ስለሚገኙ ስደተኞችና መጠለያ አልባ ድሆችን ያሰብን እንደሆነ ኢየሱስ በርኅራኄ እንደሚመለከታቸው ለእያንዳንዱ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ “እናንተ ሁላችሁ ወደኔ ኑ” በማለት ደጋግሞ እየጠራ ነው።

ኢየሱስ ለሁሉም ዕረፍትን እንደሚሰጥ ቃል ይገባል፣ ከዚህ ጋር ደግሞ
መፈጸም ያለበትን አንድ ውል ያያይዛል፣ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝ” ይለናል። ይህ ከመክበድ የሚቀለው ጫና ከመሆን ነፃነትና ዕረፍት የሚሰጥ ምን ዓይነት ቀንበር ነው? ዮሐንስ በወንጌል 13፣34 እና 15፣12 እንደሚያመልክተን የክርስቶስ ቀንበር የፍቅር ሕግ ነው፣ ይህም ለሐዋርያቱ የተወላቸው ትእዛዝ ነው፣ ይለናል፣ ረሃብና ኢፍትሐዊነት ከመሰሉ የሰው ልጆች ቊሳዊ ቊስሎች እና እውነተኛ ካልሆነ መልካም ኑሮ የመነጩ ሥነ ልቦናዊና ሞራላዊ ቁስሎችን የሚፈውስ በወንድማማችነት ፍቅር የተመሠረተ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚመነጭ የፍቅር ሕግ ነው። ስለዚህ የእብሪት ጐዳናንና የበላይ ሥልጣን ለመቀዳጀት የምንጠቀመው ዓመጽን እንዲሁም ድልን ለመቀዳጀት የተከፈለው ይከፈል የሚለውን አቋም እርግፍ አድርጎ መተው ያስፈልጋል፣ እንዲሁም በአካባቢ ላይ የምንፈጽመው ዓመጽ ማለት ተፈጥሮን አለአግባብ መበዝበዝን ትተን ትሕትና እንልበስ፣ ከሁሉም በላይ ግን ሰው የመሆንን ክብር የሚያሳዩ ግላዊና ኅብረተሰባዊ ግንኙነቶች በሚመለከት ዓመጽና ኃይል መጠቀምን ትተን ለሰው ልጅ የወደፊት ሕይወት ዋስትና የሚሰጥ ግንኙነቶች እንፍጠር።

 

የተከበራችሁ ጓደኞቼ፤ ትናንትና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላዊ ሥርዓተ አምልኮ እግዚአብሔርን እጅግ ተወዳጅ ቅዱስ ልቧን ስለሰጠን አመሰገንነው፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከኢየሱስ ትሕትናን እንድንማርና ቀላል ቀንበሩን ለመሸከም እንድንወስንና ውሳጣዊ ሰላምን በማጣጣም እኛም በበኩላችን በብርቱ ድካምና ትግል በሕይወት ጉዞ እየተቸገሩ ላሉት ሌሎች ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን ለማጽናናት እንድንችል ትርዳን፡፡ አሜን
ምንጭ፡- ቫቲካን ራድዮ

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።