የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነው!

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 1724

የር.ሊ.ጳ. የሰንበት መልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ

ውድ ውንድሞችና እኅቶች

Gesùየዛሬው እሁድ ወንጌል የቅዱስ ማርቆስ ምዕራፍ 9 ከቍ 38-41 ሆኖ ክርስቶስ ካከናወናቸው አንዱን አጋጣሚ የሚገልጥ እንደነገሩ አለፍ ሲል የተፈጸመ ቢሆንም ጥልቅ ምሥጢር የያዘ ክፍል ነው፣ ታሪኩ እንዲህ ነው፣ ወጣትና ቀናተኛ የነበረው ዮሐንስ ሐዋርያ የኢየሱስ ተከታይ ያልሆነ አንድ ሰው በኢየሱስ ስም አጋንንትን ሲያወጣ ባዩት ጊዜ ሐዋርያት ከልክለውት እንደነበር ለኢየሱስ ይነግረዋል፣ ኢየሱስ ግን እንዳይከለክሉት ይነግራቸዋል ከዚህ አጋጣሚ በመነሳትም ሐዋርያቱን ማስተማር ይጀምራል፣ እግዚአብሔር የማኅበራቸው አባላት ባልሆኑትም መልካም ነገሮች እንዲሁም ተአምራትም ሊፈጽም እንደሚችል ይነግራቸዋል፣ አያይዞም ለእግዚአብሔር መንግሥት መተባበር የሚችል ሁሉ ለመልእክተኛየ አንድ ብርጭቆ ውሃ የመስጠት ቀለል ያለ የመልካም ተግባር ሳይቀር የመተባበር ምልክት መሆኑን እወቁ ይላቸዋል።

ቅዱስ ጎስጢኖስ ይህንን ጥቅስ ሲገልጥ "በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ቢሆን ካቶሊክ ያልሆነ ሰው ሊገኝ ይችላል እንዲሁም ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውጭ ደግሞ ካቶሊካዊ የሆነ ሊገኝ ይችላል" ይላል፣ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አባላት በሌሎች መልካም ሥራ መቅናት የለባቸውም ነገር ግን ከማኅበሩ ውጭ የሆነ ሌላ ሰው በክርስቶስ ስም መልካም ሥራ ሲያደርግ ባዩ ቍጥር ተግባሩ በቅን ኅሊናና በአክብሮት እስከተፈጸመ ድረሰ መደሰት አለባቸው።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥም አንዳንዳንዴ ይህን መሰል ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደገረጉ የተለያዩ መልካም ሥራዎችን ለመቀበልና ዋጋ ለመስጠት የሚያስቸግራቸውም ሰዎች ይኖራሉ፣ ሆኖም ግን ሁላችንም ዘወትር በእነኚህ በጎ ተግባሮች ጌታ በቤተ ክርስቲያኑና በዓለም በሚያደርጋቸው ቍጥር ስፍር የሌላቸው አስደናቂ ነገሮች አንዱ ሌላውን ማድነቅና ዋጋ መስጠት መቻል አለብን።

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ንባባት የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ ከቍ.1-6 ዋስትናቸውን ባከማቹት ሃብትና በኃይላቸው ዓመጽ የሚተማመኑት ሃብታሞችንና ቅኑ ያልሆኑትን ሐዋርያዊ ዘዴ በተሞላበት መንገድ ሲገስጻቸው እንመለከታለን፣ ቸዛርዮ ዘአርለስ ይህንን በተመለከተ በሚያቀርበው ሐተታ "ሃብት ለመልካም ሰው በግብረ ሠናይ ለሌሎች ካካፍለው ምንም ሊጐዳው አይችልም፣ እንዲሁም በተፈጥሮው ክፉ የሆነን ሰው በስግብግብነት የሚያጠራቅመውን ወይንም ለማይሆን ነገር በትኖ የሚያጠፋውን ሰው ሊረዳው አይችልም" ይላል፣ የያዕቆብ ሐዋርያ ቃላት ያለንን ንብረት በስግብግብነት ከማከማቸት ይልቅ ሁሌ በሁሉም ደረጃ በእኩልነትና በግብረገብነት ለመተባበርና ለጋራ በጎ አገልግሎት እንድናውለው ከፍ ያለ ጥሪ ያቀርብልናል።

ውዶቼ! በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በእያንዳንዱ መልካም ተግባርና ዓላማ መቀናናትን ትተን እንድንደሰትበትና ያሉንን ምድራዊ ሃብቶች ለሰማያዊ ሃብት ፍለጋ በጥበብ ለመጠቀም እንድንችል ዘንድ እንማጠን፣ ካሉ በኋላ ቅዱስ አባታችን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን አሳርገዋል፣ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ምሥራቅ ኮንጎን የሚመለከት ጥሪ አቅርበዋል፣ "በእነዚህ ቀናት ውስጥ በዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቅ ክፍል በሚገኘው ሕዝብ ላይ እየወረደ ያለው በከፍተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር ትኵረት የተሰጠበት ችግርን በብርቱ ስሜትና አሳቢነት እየተከታተልሁት ነው፣ በግጭቱ ምክንያት የሥቃይ የዓመጽና የጭንቀት ሰለባ ከሆኑት በተለይ ደግሞ ከስደተኞች ከሕጻናትና ከሴት ልጆች ጐን መቆሜን እገልጻለሁ፣ የውይይትና የብዙ ንጹሓን መከላከያ ሰላማዊ መንገዶች ተገኝተው በፍትሕ የተመሠረተ ሰላም እንዲሰፍንና በፈተና በሚገኘው እና በመላው አከባቢው በወንድማማችነት የመኖር መንፈስ እንዲታይ እግዚአብሔርን እለምናለሁ" በማለት መልእክታቸውን ደምድመዋል።

ምንጭ፡- ራድዮ ቫቲካን